ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ በአገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች የተጀመሩና በአሁኑ ወቅትም በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጓት መሆኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም በጅምር ያሉትን 320 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ብቻ ለማጠናቀቅ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልጋት አስገንዝበዋል።ከዚህም በተጨማሪ ሀገሪቱ ከፍተኛ ዕዳ ያለባት በመሆኑ በልማት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንና መንግሥትም ዶላር ማመንጨት ላይ እየተፈተነ ስለመሆኑ አስረድተዋል።ለመሆኑ ፕሮጀክቶች ለምን ይዘገያሉ? ሲዘገዩስ በአንድ አገር አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉት ጉዳት ምን ያህል ነው? በሚለው ላይ ምሑራን ምልከታቸውን ያጋራሉ።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አረጋ ሹመቴ፣ በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ማጠናቀቅ ማለት በአገሪቱም ላይ ያንዣበቡ ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ፈጣን እልባት እንደመስጠት ይቆጠራል ይላሉ።ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተጠናቀቁ ነው ማለት የአንድ ሀገር የኢንቨስትመንትና የማድረግ ብቃት የሚለካበት መስፈርት መሆኑንን ይናገራሉ።ይሁንና በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ከዚሁ ተቃራኒ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።ፕሮጀክቶች ሲዘገዩ በራሱ የአንድን ፕሮጀክት እይታ ብቻ ሳይሆን ሌላውን የሚነካ ይሆናል።ሜጋ ፕሮጀክቶች በዘገዩ ቁጥር የሚፈጥሩት ጫና ዘርፈ ብዙ መሆኑን ያብራራሉ።
የፕሮጀክቶች መዘግየት የዋጋ ግሽበትን በማባባስ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው የሚሉት ዶክተር አረጋ፣ መሰል ፕሮጀክቶች በፍጥነት የማይጠናቀቁ ከሆነ ከፍተኛ ገንዘብ የሚወስዱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በየጊዜው አዳዲስ በጀት የሚያዝላቸው በመሆኑ ለሌላ ፕሮጀክት መዋል የነበረበት ገንዘብ ለአንድ ፕሮጀክት ይውላል፤ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን በማስከተል የራሱን ሚና ይጫወታል ይላሉ።የመንግሥትን የበጀት ጉድለት ከማባባስ አኳያም ድርሻ እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር አረጋ፣ ለሚዘገዩ ፕሮጀክቶች ተብሎ በጀት ሲበጀት መንግሥትን ላልተፈለገ ወጪ እንደሚዳርግና ይህ ደግሞ የበጀት ጉድለት ከሚያስከትሉ አንኳር ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ሜጋ ፕሮጀክቶች በዘገዩ ቁጥር ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመፍጠር የምጣኔ ሀብትን ከሚያመሳቅሉት ምክንያቶች መካከል በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ የሚናገሩት ዶክተሩ፣ በኢትዮጵያ በየጊዜው አዳዲስ ፕሮጀክቶች እየተጀመሩ መሆናቸውን እንጂ በፍጥነት ስለመጠናቀቃቸው ጥርጣሬ እንዳላቸው ያመለክታሉ።እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ በአብዛኛው የሚጠቀሙት ግብዓት የሚመጣው ከሀገር ውጭ ሲሆን፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚፈልጉ ያብራራሉ።
በዓለም ላይ በፍጥነት ሁኔታዎች ተለዋዋጭ በሆኑበት አጋጣሚ ሁሉ የዶላር ምንዛሪም በተመሳሳይ ሁኔታ እየተቀያየረ የዓለም ምጣኔ ሃብትም በዚያው ልክ እየተለዋወጠ ነው።ታዲያ ኢትዮጵያን የመሰሉ ወደብ አልባ ሀገራት ደግሞ በመሰል ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ቀዳሚዎቹ ተጠቂ ናቸው ይላሉ።ይህም ብቻ ሳይሆን ግብዓቶቹም ተጓጉዘው በፕሮጀክቶቹ ቦታ እስከሚደርሱ ድረስ ያለው አገራዊ የሰላምና መረጋጋት ሁኔታም አስተማማኝ ባለመሆኑ ነገሮች የበለጠ የተወሳሰቡ ያደርጋቸዋል፤ በዚህ ደግሞ አገር ዋጋ እየከፈለች ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ለአብነትም ለስኳር ፕሮጀክቶች ተብሎ 72 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎ በታሰበው ልክ ውጤታማ ባለመሆናቸው ሀገሪቱን ለከፍተኛ እዳ ዳርጓታል።የባቡር ፕሮጀክቶችም ከአዋጭነታቸው ይልቅ አክሳሪነታቸው በጣም የጎላ ስለመሆኑ መንግሥት በራሱ ያመነው ጉዳይ ነው።በርካታ ቢሊዮን ብር ፈሰስ የተደረገባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶችም በታሰበው ልክ አገልግሎት ለመስጠት አልታደሉም፤ ለዚህም በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃሉ ተብለው የተወጠኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዓመታትን የዘለቀ ወቀሳ ማስከተላቸውን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጭር እና በረጅም ጊዜ አገሪቱ ወደማትወጣው ምስቅልቅል ውስጥ ከሚያስገቡ የፕሮጀክት አመራርና አሠራር አንዱ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ ምሑሩ ገለፃ፤ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስተቀር የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችም በትክክል ያሉበትን ደረጃ የሚገልፅ ሪፖርት አይሰማም፤ ጠያቂም የለም።በእነዚህ ላይም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ተደርጓል።መንግሥት ከእነዚህ ፈተናዎች ለመውጣት አማራጮች ላይ ማማተር አለበት።በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የግሉ ዘርፍ በብዛት እንዲገባበትና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ብሎም የአገሪቱን የምጣኔ ሃብት እንዲያድግ መሥራት ያስፈልጋል።የዘገዩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ይረዳ ዘንድም ቁርጥ ያለ ፖለቲካዊ አመራር እና ውሳኔ ሰጪነት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ ጎኑ ደግሞ በርካታ ፕሮጀክቶችን በአንድ ጊዜ ከመጀመር ይልቅ ስልታዊና አዋጭ ተብለው የተለዩ አካሄዶችን መከተል እንደሚገባ ይጠቁማሉ።ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፕሮጀክቶች በመለየትና የአሠራር ሥርዓታቸውንም ሳይንሳዊ ብሎም ከፖለቲካ ጫና የፀዳ በማድረግ፤ ጠንካራ አመራር በመስጠት ችግሮችን ማቃለል ይቻላል፡፡
በሌላ ጎኑ ደግሞ በብዛት እየዘገዩ የሚገኙት ፕሮጀክቶች በመንግሥት የልማት ድርጅት ስር የሚከወኑ ወይንም የሚተዳደሩ አሊያም ደግሞ በመንግሥታዊ ተቋማት የሚመሩ ናቸው።በመሆኑም እነዚህን ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አንዱ ሌላውን መደገፍ አለበት ይላሉ።ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በመደገፍ ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚቻልበትን መላ መምታትም ሌላኛው መንገድ ስለመሆኑን ያብራራሉ።
ቀደም ሲል በባንክ ዘርፍ ውስጥ ያሳለፉትና በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክት በመምራት ላይ ያሉት አቶ ታምራት ዓለሙ በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቶች መዘግየት በሀገሪቱ ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ያደርስባታል የሚለውን የዶክተር አረጋን ሐሳብ ይጋራሉ። ፕሮጀክቶች ሲዘገዩ ምጣኔ ሃብታዊ አንድምታው ጎልቶ ይውጣ እንጂ ጉዳቱ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስን ጭምር የሚያስከትል መሆኑንም ያብራራሉ።
ፕሮጀክቶች በዘገዩ ቁጥር ሥራ ዕድል ፈጠራ በማዘግየትና በርካታ ሥራ አጦችን እንዲፈጠሩ በማድረግ የበኩሉን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።ይህ ደግሞ ሥራ አጦች በበዙ ቁጥር ሀገሪቷን ወደአልተፈለገ አቅጣጫ የመውሰድ ዕድል እንዲኖረው ያደርጋል።ራስን በመቻል እና በዓለም የዕድገት የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ የሀገራትን ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ በመሆኑም እንደ ሀገር የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም።ሀገራት በብዛት የዲፕሎማሲ አቅማቸውን ለማሳየት ከሚጠቀሙት ዋንኛው ምጣኔ ሀብት በመሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት ማለት ምንም እንኳን ሌሎች የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ መፍጠሪያ አማራጮች ቢኖሩም፤ ዲፕሎማሲን በፈለጉት መንገድ ለማሳለጥ ሰፊ እድል ይሰጣል፡፡
ይሁንና አቶ ታምራት፣ በአንዳንድ መልኩ የዶክተር አረጋን ሃሳብ ይቃወሙታል።ምንም እንኳ እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገር ምጣኔ ሃብት ላይ የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የሚገመት ባይሆንም፤ አንዱ እስኪጠናቀቅ ሌላውን ማዘግየት ወይንም ደግሞ አለመጀመር በራሱ ጉዳት አለው ይላሉ።ፕሮጀክቶች ሁሉ በአንድ ላይ እንደማይጀመሩ ሁሉ በአንድ ጊዜም ማጠናቀቅ አይቻልም።
ከዚህ በተጨማሪም የአንድ ፕሮጀክት የገንዘብ ምንጭ በአገሪቱ አቅም ወይንም ከመንግሥት ካዝና የሚመጣ ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ደግሞ የገንዘብ ምንጩ ብድር ወይንም በእርዳታ የሚገኝ ስለሚሆን አዳዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር ወይንም ለመጨረስ እንደቅድመ ሁኔታ መቀመጥ ያለበት ፕሮጀክት መብዛት መሆን የለበትም ባይ ናቸው።ይልቁንም ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ ምን ዓይነት መንገዶችን መከተል ይገባል? የገንዘቡ ምንጭስ ምንድን ነው? የሚለው ላይ በደንብ ማውጠንጠን ይገባል ይላሉ።
ሌላው አንደኛው የመንግሥት የልማት ድርጅት ሌላኛውን መደገፍ አለበት የሚለው ምክረ ሃሳብም ብዙም አያስኬድም ባይ ናቸው።ምክንያት ደግሞ አንዱ ሌላኛውን ሲደጉም ምናልባትም ካለበት ሊንሸራተት እና አፈፃፀሙንም ቀርፋፋ ሊያደርገው ይችላል።ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥመ ገናና እና ተወዳዳሪ ተቋም ነው።
ይሁንና ይህ ተቋም ሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን መደጎም ወይንም ማገዝ ቢጀምር ትኩረቱ ሊበታተን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።ይልቁንም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቀደም ሲል ይተዳደሩበት ከነበረው ዕይታ ወጣ በማለት በሌላ መንገድ ማስተዳደር እና ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ማመንጨት የሚችሉበትን ስልት መንደፍ ተገቢ ይሆናል።ለእዚህም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መቅሰም እና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
ምሑራኑ፣ የፕሮጀክቶች መዘግየት የአንድን አገር የመፈጸም አቅምን በሚገባ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና የተወዳዳሪነት አቅም የሚለካበት ስለመሆኑ ይስማማሉ።በተለይም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምጣኔ ሃብት ተወዳዳሪ የመሆን አንዱ መለኪያ ሜጋ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ ወደሚፈለገው ምርታማ ሂደት መቀየር ነው።
ይህን ያሳኩ ሀገራት በዓለም ላይ ጫና እየፈጠሩ ነው።ከዚህ በዘለለ ፕሮጀክቶችን የማስተዳደር ስልት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የሜጋ ፕሮጀክቶች አጀማመር፣ የግንባታ አካሄድና ውጤታማ የማድረግ ሂደት በብዙ መንገድ ወደኋላ የቀረ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚያሻው ነው።
መንግሥት መሰል ፕሮጀክቶችን ከመጀመሩ በፊት ደጋግሞ ማሰብ እንደሚጠበቅበት የሚናገሩት ምሑራኑ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ሀገር አዲስ ፕሮጀክቶችን ማስተዳደር ባሕል ሊዳብርና ከውጪው ዓለም በቂ የሚባል ልምድ መቅሰም እንደሚገባ ያሳስባሉ።ፕሮጀክቶችንም መጀመር ብቻ ሳይሆን የረጅም እና የአጭር ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ምንድን ነው የሚለው በሚገባ ማጤንና የጥናት ውጤቶችን በጥልቀት መመልከት ተገቢ ነው።የፕሮጀክቶች መዘግየት ዘርፈ ብዙ አንድምታዎች ያሉት በመሆኑም መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ምሑራኑ አበክረው ያሳ ስባሉ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም