የክብር ዶክተር የሆኑት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ የተወለዱት ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም በቀድሞው አጠራር በሸዋ ክፍለ አገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ነው። አባታቸውም ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ናቸው።
ስንዱ እድሜዋ ለትምህርት በደረሰበት ወቅት ከቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህርት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተምረዋል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስ ምንተኛ ክፍል ተምረዋል።
አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ስንዱን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷቸው እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጋር እንዳስተዋወቋቸው ስለ ስንዱ የተጻፉ ሰነዶች ያሳያሉ። አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልህነትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ወይዘሮ ስንዱ በ1921 ዓ.ም ወደ ስዊስ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮው ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በመጨረሻም በስዊስ እና በፈረንሳይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማ ተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነ ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት እዚያው ተምረው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
የጣሊያን ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ወይዘሮ ስንዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ። ወደ ነቀምት በመሄድም ሕዝብን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ
አማክረው በተሰጣቸው 500 ብር አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በጣልያን ሠራዊት እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ አምጥተዋቸው የቁም እስረኛ ሆነዋል።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ ወይዘሮ ስንዱ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምን ጭምር) ሆነው በመርከብ ‹‹አዚናራ›› ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ።
ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥምና ወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።
ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት፤ ‹‹ኮከብ ያለው ያበራል ገና››፣ ‹‹የየካቲት ቀኖች››፣ ‹‹የኑሮ ስህተት›› የሚሉ ትያትሮችን ሠርተው አቅርበዋል።
ወይዘሮ ስንዱ ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና ‹‹የወንድ ዓለም›› በገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ።
ስንዱ ገብሩ ከተሳተፉባቸው ጥቂቶችን እንጥቀስ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ ሆነው አገልግለዋል።
ከመጽሐፎቻቸው ደግሞ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
ኮከብህ ያውና ያበራል ገና፣ በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች (1947 ዓ.ም)፣ የታደለች ህልም (1948 ዓ.ም)፣ ርእስ የሌለው ትዳር (1948 ዓ.ም)፣ የኔሮ ስህተት (1948 ዓ.ም)፣ ከማይጨው መልስ (1949 ዓ.ም)፣ ፊታውራሪ ረታ አዳሙ (1949 ዓ.ም) እና የመሳሰሉት ሌሎች ጽሑፎቻቸው ይጠቀሳሉ።
የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግና እና ፀረ ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ (የክቡር ዶክተር) ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም በተወለዱ በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2015