የዚህ ሰው ነገር ይገርማል! ከውልደቱ ይጀምራል። የተወለደው በዕለተ መስቀል መስከረም 17 ቀን ነው። ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ደግሞ የፋሲካ በዓል ዕለት ሚያዚያ 11 ቀን ነው። የዚያን ዓመት የፋሲካ በዓል በሀዘን ድባብ የተዋጠ እንዲሆን አድርጎታል። በዘፈኑ ደግሞ በዓላትን ሲያደምቅ ኖሯል። በሕያው ሥራው የወደፊት በዓላትንም ያደምቃል። ይህ ሰው የሙዚቃው ንጉሥ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ነው።
ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ከ14 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በፋሲካ በዓል ነው። የፋሲካ በዓል ቀኑ ስለሚቀያየር በዓመቱ ሚያዚያ 11 አይሆንም። የ2001 ዓ.ም የፋሲካ በዓል የተከበረው በጥላሁን ገሠሠ ሞት ሀዘን ነው። ያም ሆኖ ግን የጀግና ሞት ሀዘን አይደለምና መገናኛ ብዙኃንን ለአንድ ሳምንት ያህል በአንድ ጉዳይ ብቻ አድምቆ ይዞ ቆይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም የተፈጸመው ለሳምንት ያህል ሰፊ ሽፋን ከተሰጠው በኋላ ነው።
የ14ኛ ዓመት የጥላሁን ገሠሠን የሙት ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ከሕይወትና ሥራዎቹ ጥቂቶችን እናስታውስ።
ጥላሁን ገሠሠ ከእናቱ ከወይዘሮ ጌጤ ጉርሙ እና ከአባቱ ከአቶ ገሠሠ ንጉሤ በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጠመንጃ ያዥ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የመስቀል ዕለት ተወለደ። ዕድሜው 14 ዓመት እንደሆነ ከአያቱ ጋር እንዲኖር ወደ ወሊሶ ተወሰደ፤ ራስ ጎበና በሚባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ጀመረ።
በትምህርት ቤት ሳለ፤ ጥላሁን ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ፍቅር እያሳየ መጣ። አያቱ ግን ትኩረቱን በሙሉ በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ይመክሩት ነበር። የራስ ጎበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ የነበሩት ሱዳናዊው አቶ ሼዳድ ደግሞ የጥላሁንን የሙዚቃ ፍቅር በማየት ወደ ሱዳን እንዲሄድና በዚያም ሙዚቃ እንዲያጠና ይመክሩት ነበር። ጥላሁን ወደ ሱዳን ባይሄድም ምክራቸውን ግን ትልቅ ቦታ ስጥቶት ነበር።
ከአገር ፍቅር ቲያትር ንጋትዋ ከልካይ እና ኢዮኤል ዮሐንስ ሌሎችም የአገር ፍቅር ተዋንያን በትምህርት ቤታቸው ትርኢት ሊያሳዩ በመጡ ጊዜ፤ ይህን እድል በመጠቀም ጥላሁን ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር ኢዮኤል ጋር ባደረገው ውይይት በሙዚቃ መግፋት ከፈለገ ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳለበት መከሩት። ጥላሁን ትምህርቱን አቋርጦ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አቀና። ኩብለላውን በእግር የጀመረው ለአያቱ ሳይነግር ስለነበር ከቤት ሲጠፋ አያቱ ለአጎቱ ሁኔታውን በመንገር ጥላሁንን ይጠብቁ ጀመር። ጥላሁንም የአሥራ አምስት ኪሎ ሜትር መንገዱን ጨርሶ ቱሉ ቦሎ ደረሰ፤ ከዚያም ከአክስቱ ከወይዘሮ ተመኔ ባንቱ ቤት አድሮ ወደመጣበት ወደ ወሊሶ አያቱ ዘንድ ተይዞ ተመለሰ ።
በሙዚቃ ፍቅር በጣም የተቃጠለው ጥላሁን አያቱ ቤት አንድ ቀን ብቻ በማደር ጉዞውን እንደገና ወደ አዲስ አበባ አቀና፤ በዚህ ጊዜ ግን በጭነት መኪና ላይ በመንጠልጠል ነበር። ጥላሁን አዲስ አበባ እንደገባ በአገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተቀጠረ። በዚያም ጥቂት ዓመታት ከሰራ በኋላ ወደ ክብር ዘበኛ ባንድ በመቀላቀል እነሆ ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን በቃ።
በ1953 ዓ.ም የታሕሣስ ግርግር ትልቅ ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር። ለጥቂት ጊዜም ታስሮ ተፈቷል። ከዚያም ወደ ቀድሞው አገር ፍቅር በመመለስ ተወዳጅና ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አገር ፍቅር ቲያትር ቤትን በጎበኙበት ጊዜ ሦስት ጊዜ ወጥቶ ዘፍኗል፤ ንጉሠ ነገሥቱም ‹‹ጥሩ ድምጽ አለህ፤ እንዳታበላሸው›› የሚል አስተያየትም እንደሰጡት ይነገራል።
ከጥላሁን ዘፈኖች አብዛኞቹ የአማርኛ ሲሆኑ፤ የተወሰኑ ዘፈኖችን ደግሞ በኦሮምኛ እና በሱዳንኛ ዘፍኗል። ጥላሁን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ላደረገው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጥቶታል። ከኢትዮጵያ ኪነጥበብና የብዙህን መገናኛ ሽልማት ድርጅት የሙሉ ዘመን ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል።
ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ
ይህ ነው የሞትኩለት የኔ ማስታወሻ
ውበቷን ሳሞግስ የለምለም አገሬን
ማንም አይዘነጋም በጩኸት መኖሬን!
ዜማ እንጉርጉሮዬም የግሌ ቅላጼ
ተቀርጾ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምጼ
ያስቀየምኩት ቢኖር የጠላኝ በቁሜ
ድምጼን ሰምቶ ያዝናል ለረገፈው አጽሜ
እኔን ለበደሉኝ ሰርዣለሁ ቂሜን
በኔም የከፋችሁ ይቅር በሉት አጽሜን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም