
የአዲስ ዘመን፤ ዘመን አይሽሬ የመረጃና መዝናኛ ገጸ በረከቶች ዛሬም እንደ ጥንቱ ሳያራጁና ሳይደበዝዙ ጊዜ ዘመኑን፣ ክስተት አጋጣሚውን ይነግሩናል። ሰዎች ነብሳቸው ከስጋቸው ልትለይ በተቃረበች ሰዓት ብዙውን ጊዜ የመጨረሻው ንግግራቸው የኑዛዜ ቃላቸው ነው። ወይዘሮ ሙላቷም “…ከሰልስቴም በኋላ ጥቁር ልብስ የለበሰ፣ ጥቁር ከረባት ያሰረ የተረገመ ይሁን” ብለው ተናዘዋል። 32ቱ ሰካራሞች እና 32ቱ ጠንቋይና አስጠንቋዮች፤ ሁለቱም በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ነበሩ። ከወዲያ ማዶ ደግሞ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች የቦብም ድብደባን አስመልክቶ የወጣ መረጃም ይገኝበታል።
ወይዘሮ ሙላቷ ፉንቄቦ እንዳይለቀስላቸው ተናዘው ሞቱ
የሀገራችን የለቅሶ ልማድ የተለያየ ቢሆንም፤ አንዱ ክፍል ሙሾ ገጣሚ በገንዘብ ገዝቶ ከብዙ ዓመታት በፊት የሞቱትን የሟቹን ዘመዶች ስምና ሙያ እየጠቀሱ፣ ግጥም እየገጠሙ የተሰበሰበውን ሕዝብ እንባ በእንባ ማራጨት፣ ደረት መድቃትና ፊት መንጨት በጠቅላላው እዚህ ግባ የማይባል ስቃይ የሚታይበት መሆኑ አይካድም። የኢትዮጵያ ተዋህዶ ሃይማኖት መሪዎች ከማስተማር አልፈው እስከ መገዘትም የደረሱበት ጊዜ ጥቂት አይደለም።
ወይዘሮ ሙላቷ ፉንቄቦ ስለዚህ ጉዳይ ከማረፋቸው አስቀድመው ሙሾ ገጣሚ ገዝተው እንዳያለቅሱና እንዳያስለቅሱ በማለት ከኑዛዜያቸው ጋር አያይዘው “ልጆቼና ዘመዶቼ የሆናችሁ ሁሉ ጥቁር ልብስ የለበሰ፣ ጥቁር ከረባት ያሰረ የተረገመ ይሁን” ሲሉ ተናዘው በተወለዱ በ87 ዓመታቸው ሐምሌ 4 ቀን 1962ዓ.ም አረፉ።
በኑዛዜው መሠረት የቀበሩ ስነ ስርዓት ያለ አንዳች ዋይታ እንባ በማፍሰስ ብቻ ተፈጽሟል። በስነ ስርዓቱም ላይ ብጹእ አቡነ ፊሊጶስ ተገኝተው የሟቿን ኑዛዜ በመደገፍ ጠቃሚ ምክር ለሀዘንተኞች አሰምተዋል። ከብጹእነታቸው ቀጥለው ከቤተ ዘመድ አንደኛው “ወይዘሮ ሙላቷ ልጆቼን መርቄያቸዋለሁ፤ እናንተም መርቁልኝ ከሰልስቴም በኋላ ጥቁር ልብስ የለበሰ፣ ጥቁር ከረባት ያሰረ የተረገመ ይሁን” ብለው መናዘዛቸውን ለለቀስተኛው ገልጸዋል።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 1962ዓ.ም) 32 ሰካራሞች እያንዳንዳቸው 50 ብር ተቀጡ
አዲስ አበባ፤(ኢዜአ) በአዲስ አበባ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያለ ሰዓት በሚዘዋወሩና ከመጠን በላይ በመጠጣት አቅማቸውን ባልመጠኑ ጠጪዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር 32 ሰዎች በሰዓት እላፊ ተይዘው 6ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ እያንዳንዳቸው ከማስጠንቀቂያ ጋር 50 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው መሆኑን የጣቢያው አዛዥ ገለጹ።
ከዚህ በቀር በህዝብ መተላለፊያ መንገዶች፣ በዋና አደባባይ ዙሪያ፣ በመኖሪያ ሠፈሮች አካባቢ ያለ አንድ ምክንያት በሥራ ፈትነት “ይቺን ያገኘ ይጪኝ ይብላ” እያሉ በማወናበድ ሕዝብን የሚያስቸግሩ 48 የካርታ ቁማርተኞች ተከሰው እያንዳንዳቸው ከብርቱ ማስጠንቀቂያ ጋር 50 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ፣ መቀጫውን ባይከፍሉ በ2 ወር እሥራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው መሆኑን የ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሻምበል ደጀኔ መሸሻ በተጨማሪ አረጋግጠዋል።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 1962ዓ.ም) ጠንቋይና 32 አስጠንቋዮች በቀበሌ ማኅበር ተያዙ
በቦሌ ወረዳ በ03-በ04-31 ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆነች ወ/ሮ ዘሐራ ፋንታ የተባለች ሴት ሕዝቡን ሥራ በማስፈታት ሕገ ወጥ የሆነ የጥንቆላ ተግባር ስትፈጽም ተገኝታ ለማስጠንቆል ከሔዱት ሠላሳ ሁለት ሰዎች ጋር ተይዛ ፖሊስ ጣቢያ ትገኛች።
…
በአንደኛዋ ተከሳሽ ቤት ይህንኑ አስነዋሪ የሆነ የማስጠንቆል ተግባር ሲፈጽሙ ከተገኙት 32 ሰዎች መካከል 22 ሴቶችና 10 ወንዶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ወታደሮች እንደሚገኙ ምርመራውን የያዘው ወታደር ኪሮስ ሞልቶት አስረድቷል።
(አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 1975ዓ.ም)
በእሥራኤል ጦር አውሮፕላኖች የቦምብ ድብደባ ስምንት ሰዎች ተገደሉ
የእሥራኤል ጦር አውሮፕላኖች በአንድ ሳምንት ውስጥ በደቡብ ሊባኖስ ውስጥ ከትናንት በስቲያ ባካሄዱት የቦንብ ድብደባ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ ሃያ ስምንት ደግሞ መቁሰላቸውን ከሥፍራው የደረሰ ዜና ገለጠ።
……..
የእሥራኤል ጦር አውሮፕላኖች ባለፈው ዓርብ በሚይህ ሜይህ አቅራቢያ በሚገኙ የስደተኞች ሰፈሮች ድብደባ በመፈጸም አሥራ አራት ሰዎች ከተገደሉና ሰላሳ ሰባት ከቆሰሉ ወዲህ ስደተኞች ከአካባቢ እንዲወጡ መደረጉን ዜናው በተጨማሪ ያመለክታል።
……
በሌላ በኩል የአረብ ሊግ በእሥራኤል የጦር አውሮፕላኖች በደቡባዊ የሊባኖስ ውስጥ የፈጸሙት የቦንብ ድብደባ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚካሄድ ሽብር መሆኑን በማስመልከት ድርጊቱን በጥብቅ አወገዙ። አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 ቀን 1979 ዓ.ምየተባበሩት መንግስታት ስለሰው ልጅ ማሰብ አለበት
-ኡታንት
ኒውዮርክ/ሮይተር/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአይዶሎጂ ልዩነትና በሀገሮች አለመግባባት በንትርክ ጊዜውን ስለሚጨርስ ስለጠቅላላው የሰው ልጅ ደህንነት እንደተፈለገው ለመሥራት አለመቻሉን የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ኡታንት አስገነዘቡ።
ዋና ጸፊው አስተያየታቸውን የሰጡት በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ የአለም ወጣቶች ጉባኤን ከትናንት በስቲያ በከፈቱበት ወቅት ነው።
በዓለም ውስጥ በየጊዜው በሚፈጠሩት የሀገሮች አለመግባባትና በሚነሱት ጦርነቶች ምክንያት አብዛኛውን የዓለም ሕዝብ ገና ከችግር ያልወጣና የኑሮ ደረጃው ያልተስተካከለ መሆኑን ኡታንት ገልጸዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቢሆን እስከዚህ ድረስ የሰው ልጅ በቀጥታ ድምጽ የሌለው መሆኑን አስረድተዋል። ይሄውም አባል ሀገሮች ቃል ኪዳናቸውን ባለማክበራቸው ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመበትን 25ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በድርጅቱ አማካይነት በተዘጋጀው የዓለም ወጣቶች ጉባኤ ላይ ከ101 ሀገሮች የተውጣጡ ስድስት መቶ ወጣቶች ተገኝተዋል።
የወጣቶች ጉባኤ ገና ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሲሆን በልዩ ልዩ የኢንተርናሽናል ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል። ጉባኤው ሥራውን ከመቀጠሉ በፊት 18 አባሎች ያሉበት የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ መርጧል። አብዛኞቹ ከ18 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 1962ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም