
ኢትዮጵያውያን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓሎችን እያከበሩ ይገኛሉ። ህዝበ ክርስቲያኑ ባለፈው እሁድ ትልቁን የትንሳኤ በአል አክብሯል፤ በዚህኛው እሁድ ደግሞ ዳግማ ትንሳኤን ያከብራል። በሙስሊሙም ዘንድ ታላቁ የረመዳን ፆም ተጠናቆ ትናንት የኢድ አልፈጥር በዓል በድምቀት ተከብሯል። እነዚህ ሁለት ታላላቅ ሃይማኖታዊ በአላት ሲከበሩ አንድ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ አለ። ይህም የእርድ በዓል መሆናቸው ነው።
በበዓላት ወቅት ከወትሮው የተለዩ የምግብና መጠጥ ዓይነቶችን መመገብ የተለመደ ቢሆንም፣ አንዳንዶች በበዓላት ወቅት በአመጋገብ ሳቢያ ጤናቸውን ያጣሉ። በበዓላት ወቅት አመጋገብ በተለያየ ሁኔታ ጤና የሚነሳ ወይም ላልተጠበቀ አደጋና ሕይወት ማለፍ ሊዳርግ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ደጋግመው ይናገራሉ።
ብዙዎቻችን ግን የመጣው ይምጣ ብለን በአብዛኛው የበዓላት ሰሞን ቀዩን ከሻኛው ካልቆረጥን፣ ጮማው በጉሮራችን ካልወረደ በዓል በዓል መስሎ አይታየንም። ይህም የአመጋገብ ባህል ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርገን ማየት አዲስ አይደለም። ለዚህ ምክንያቶቹ ደግሞ ከመጠን በላይ መመገብ፣ ስጋና የእንስሳት ተዋጽዖን ማዘውተርና ብዛት ያላቸው የአልኮል መጠጦች መውሰድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
አጿማትን ተከትለው በሚመጡ በዓላት አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ የሥነ ምግብ ባለሙያዎችም ይመክራሉ። በተለይም የትንሣኤ በዓል በመጣ ቁጥር አንዳንድ ሰዎች ቅባት የበዛበት ምግብ ተመግበው ለሕመም የሚጋለጡበት አጋጣሚ ብዙ
እንደመሆኑ በዚህ ወቅት ጥንቃቄ ማድረጉ የግድ ነው። የትንሣኤ በዓል ከረጅም ጊዜ ጾም በኋላ የሚመጣ በዓል በመሆኑ ቅባት የበዛበት ምግብ እና አልኮል መጠቀም ተገቢ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በብዙዎች ዘንድ ግን በዚህ ወቅት የአመጋገብ ባህሉ ከሳይንሱ የተጣላና ተቃራኒ ነው።
የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የበዓል አመጋገብ ተመሳሳይ ነው። ጾም ሲፈታ የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ማለትም ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦችን መመገብ የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየው ጨጓራ በአንድ ጊዜ ለመቀበል ይቸገርና ለሕመም ይዳርጋል። ለበዓል ቅባት የበዛበት ምግብ ማዘጋጀት የተለመደ ቢሆንም፣ መጥኖ መሥራት ተገቢ ነው። ጤናን ለመጠበቅ ሰውነትን ቀስ በቀስ አለማምዶ መመገብ ይገባል።
በበዓል ወቅት ማኅበረሰቡ የሚመገባቸው የእንስሳት ተዋጽዖዎች በተፈጥሯቸው ከፍተኛ ቅባት አላቸው። በጾም ወቅት የሚዘወተሩ ምግቦች ቅባት ያልበዛባቸው በመሆናቸው ጨጓራ ለሥርዓተ ልመት ይጠቀምባቸው የነበሩ ንጥረ ነገሮች (ኢንዛይሞች) መጠናቸው ይቀንሳል። በዚህም ጨጓራ ከለመደው ሥርዓት የወጣ አመጋገብ ማለትም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ስንጀምር ሆድ መንፋት፣ ማቃጠል፣ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና መሰል ሕመሞች ያስከትላል። አንዳንድ ጊዜ ከበዓል አመጋገብ ጋር በተያየዘ ከሚከሰቱ የተለመዱ ሕመሞች በተጨማሪ በተለይ ከስጋ አመጋገብ ጋር በተያየዘ በድንገት ለሞት የሚያጋልጡ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል በስጋ ውስጥ የሚገኙ አጥንቶች ለድንገተኛ ሞትና አደጋ ሊዳርጉ ይችላሉ።
ስጋ በተፈጥሮው በቫይታሚን ኤ፣ ቢ እና ዲ የበለጸገ ሲሆን፣ በእነዚህ ቫይታሚኖች የበለጸገ መሆኑ ደግሞ ለዐይን መስተካከል፣ ለጥርስ ጥንካሬና ለአዕምሮ ጤንነት ትልቅ አስተጽዖ አለው። በዚህ ወቅት ግን ቀይ ስጋና ጮማን አዘውትሮ መመገብ አይመከርም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀይ ስጋን አዘውትሮ መመገብ ለልብ ሕመምና ለስኳር ሕመም መንስኤ ሊሆን ይችላል።
አስገራሚው ነገር በነዚህ በአላት ወቅት ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ የሆድ ህመም ሲገጥመን የምንወስደው እርምጃ ነው። ወደ ህክምና በመሄድ ተገቢውን መድኃኒት ከመውሰድ ይልቅ አልኮልን መጠቀም የሚቀናቸው ብዙዎች ናቸው።
በበዓል ወቅት ሰዎች አልኮልን በብዛት ይጠቀማሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የምግብ መፍጨትን ያፈጥናል በሚልና በበዓል ወቅት እንደ መዝናኛ ስለሚቆጠር ነው። ነገር ግን፣ አልኮል አብዝቶ መውሰድ ጉበት በመጉዳት ቅድሚያውን ቦታ ይወስዳል። በበዓል ሰሞን ስጋን እና አልኮልን በአንድ ላይ መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ጥናቶች ያሳያሉ።
ብዙዎች በበዓላት ወቅት ሳይንሱ ከሚለው በተቃራኒ ሲመገቡ ያታያል። የሚገርመው ግን ሳይንሱን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ጭምር የመጣው ይምጣ ብለው የተለመደውን ባህላዊ አመጋገብ ከመምረጥ ወደ ኋላ አለማለታቸው ነው።
የጤናና ስነ ምግብ ባለሙያዎች ከረጅም ፆም በኋላ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሁሉም የምግብ ክፍሎች ማለትም ከጥራጥሬ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተሰባጠረ ጤናማ አመጋገብን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው በማለት ይመክራሉ። በባሕላዊ መንገድ የሚዘጋጁ እንደተልባና ሱፍ ምግቦችን ቀድሞ በመመገብ ከአፍ ጀምሮ እስከ ጨጓራ ያለውን የሥርዓተ ልመት አካሎች ወደ መደበኛው ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ሌላኛው ተገቢ መፍትሔ ነው። የምግብ መጠንን በመቀነስና የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ ባለመጠቀም በበዓል ወቅት የሚከሰቱ ሕመሞችን ማስወገድ እንደሚቻልም ይመክራሉና እናስተውል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015