ኢትዮጵያ በርካታ የቀንድ ከብት ሀብት ካላቸው አገራት መካከል ትመደባለች። ይህ የቀንድ ከብት ሀብት ባለቤትነቷ በቆዳ ልማት ዘርፍ ትልቅ አቅም እንዲኖራት አስችሏታል። ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉት ከዘርፉ የሚገኙት ብዙዎቹ ምርቶች ከአገር ውስጥ ገበያ ተሻግረው በውጭ አገራት ገበያዎችም ተፈላጊ ናቸው።
በቆዳ ልማት ዘርፍ ባለፉት 20 ዓመታት፣ በተለይም በቆዳ ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስርዓት /የተጨማሪ እሴት አሰራር ስርዓት/ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ፣ በርካታ አወንታዊ ለውጦች ማስመዝገብ እንደተቻለ የዘርፉ አካላት ይገልጻሉ።
እንዲያም ሆኖ ግን በቆዳ ልማት ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይነት አይደለም፤ ይህን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ስራ የሚጠይቅ ሆኖ ይስተዋላል። በእርግጥ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን ማከናወኗ አይካድም፤ ይሁንና በቁጥርም በዓይነትም የበዙት የዘርፉ ችግሮች ተጨማሪ ጥረቶችን የሚጠይቁ ናቸው።
ከአገሪቱ አቅም አንፃር የቆዳ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ የሚችልበት እድል እንዳለው ቢታመንም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች ግን በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው በተደጋጋሚ ይገለፃል። ኋላ ቀር የከብት እርባታ ስልት፣ ጥራት የጎደለው የእርድ ተግባር፣ የቆዳ አያያዝና አመራረት፣ ደካማ የግብይት ቁጥጥር ስርዓት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረት በቆዳ ዘርፍ እድገት ላይ አደጋ ከደቀኑ መሰናክሎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የኢትዮጵያ የቆዳ ልማት ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር አጋጥሞታል። የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና የግብዓት ችግሮች በዘርፉ ህልውናና እድገት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅነዋል። ከአምስት ዓመታት በፊት በዓመት 133 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ የነበረው ይህ ዘርፍ፣ ባለፈው ዓመት ግን ከዘርፉ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ከውጪ ንግድ ገቢው መቀነስ በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፤ አንዳንዶቹ በዝቅተኛ አቅም እያመረቱ ሲሆን ብዙ አምራቾች ደግሞ የምርት ስራቸውን ለማቆም ተገድደዋል።
በቆዳ ማልፋትና ማለስለስ እንዲሁም የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ላይ የተሰማሩ አምራቾች አብዛኛው ስራቸው ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች ላይ የተመሰረተ ነው። ብዙዎቹ ፋብሪካዎች የገበያ ስምምነታቸውን መሰረት በማድረግ ለመስራት የሚያስችላቸው ሁኔታ የለም። የመንግሥትና የአምራቾች የውጭ ምንዛሬ መጋራት የድርሻ አሰራር 50/50 እንዲሆን በተደጋጋሚ ቢጠየቅም 20/80 ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ይህ አሰራር ደግሞ ግብዓቶችና መለዋወጫዎችን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት መሰናክል ሆኗል።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ጌቱ፣ ኢትዮጵያ በቆዳው ዘርፍ ያላት አቅም አገሪቱ ባላት የከብት ሀብት ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ‹‹የኢትዮጵያ የቆዳ ሀብት በብዛት ከመገኘቱ በተጨማሪ በርካታ ልዩ ባህርያት ያሉትም ነው። የቆዳው የተፈጥሮ ጥራት ዋጋው ውድ እንዲሆን በማድረግ ከፍ ያለ ገቢ ለማግኘት ይረዳል። ዘርፉ ከፍተኛ የመልማት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በስራ እድልና በሀብት ፈጠራ ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት ትልቅ አስተዋፅዖ የማበርከት አቅም አለው። የቆዳ ዘርፍ በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚፈጥረው ሀብት ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ቆዳ የሚያስገኘው የተጨማሪ እሴት ጥቅም ሌሎች ዘርፎች ከሚያስገኙት የበለጠ ነው›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ብዙ አገራት በቆዳ ዘርፍ ተጨማሪ እሴት ፈጥረው ራሳቸውን የሚጠቀሙበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው ከአንድ በመቶ አይበልጥም። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ላለፉት ዓመታት ቆዳ ሀብት እንዲፈጥር ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን አከናውነዋል። በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የተጨማሪ እሴት ፖሊሲ/በቆዳ ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስራ/ለውጥ አምጥቷል።
ፖሊሲው የአምራቾች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። አምራቾች የምርት ዓይነትም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ምርቶቹ በውጭ አገራት ገበያዎች ጭምር በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ መሆን ችለዋል።
ይሁን እንጂ ጠንካራ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ትክክለኛ የገበያ ትስስር ተጠቅሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ አገሪቱን ለመጥቀም ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ። የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነትና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች በቆዳ ዘርፍ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እንዳሳደሩ ዋና ፀሐፊው ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው እርድ በቤት ውስጥ መከናወኑ ጥራቱን የጠበቀ ቆዳና ሌጦ የማግኘቱን ስራ አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቁመው፣ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራት ጉድለት፣ በተለይም እየተባባሰ የመጣው የቆዳ መቀደድና የቅርፅ መበላሻት፣ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚፈልግም ያመለክታሉ።
አቶ ሰለሞን ኢንዱስትሪው መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገውም ይጠቁማሉ። ‹‹ቆዳ አምራቾች አዋጭ በሆነ መልኩ በአንድ ቦታ ተሰብስበው እንዲሰሩ ማድረግ (Clustering) ያስፈልጋል። ይህም ተረፈ ምርቶች ወደ ገንዘብ የሚቀየሩበትን እድል እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃና ለተወዳዳሪነትም ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።›› ሲሉ ጠቁመው፣ የትልልቅ ብራንዶች ወደ ገበያው መግባትም በቆዳ ኢንዱስትሪዎች አንድ አካባቢ መሰባሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ይናገራሉ። ሌሎች የአፍሪካ አገራት የሌዘር ፓርኮችን እየገነቡ እንደሚገኙ አመልክተው፣ በዚህም የኢትዮጵያን ገበያ ወደራሳቸው መውሰድ ይፈልጋሉ። ትልልቅ አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ከተበታተነ አሰራር መውጣት ስንችል ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሬድማን በዳዳ በበኩላቸው፣ የቆዳው ዘርፍ ብዙ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ገልፀው፣ ማኅበረሰባዊ የግንዛቤ ለውጥ እና የመንግሥት ቁርጠኝነት ለችግሮቹ መፍትሄዎች እንደሚሆኑ ይናገራሉ። ‹‹ቀደም ባለው ጊዜ የቆዳ ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ትልቁ የኢኮኖሚ ዋልታ ነበር። በቅርብ ጊዜያት ዘርፉ በኮቪድ ወረርሽኝ እና በውስጣዊ ችግሮች ምክንያት ተቀዛቅዟል። መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አለበት።›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
የ20/80 አሰራር ስርዓት ለዘርፉ እድገት ምቹ እንዳልሆነና መሻሻል እንዳለበት ጠቅሰው፣ ተገቢ የውጭ ምንዛሬ ምደባ ሊኖር እንደሚገባ ይገልጻሉ። አምራቾች ከወጪ ንግድ ከሚያገኙት ገቢ ለግብዓትና ለመለዋወጫ ግዢ መጠቀም እንዲችሉ ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የቆዳ ዘርፍ ከፋይናንስ ተቋማት እያገኘ ያለው ገንዘብ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ያላገኘ ዘርፍ እድገት ሊያስመዘግብ እንደማይችልም ተናግረው፣፡ የፋይናንስ ተቋማት ለዘርፉ በቂ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል።
የቆዳውን ዘርፍ ለማነቃቃት ያስችላሉ ተብለው ተስፋ ከሚጣልባቸው ተግባራት መካከል በዘርፉ ተዋንያን መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ መድረኮችን ማዘጋጀት አንዱ ነው። ይህን መሰረት በማድረግም የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) እና ሌሎች አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 13ኛው ‹‹የመላ አፍሪካ የቆዳ ትርኢት›› ከዛሬ፣ ሚያዝያ 12 ቀን እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ፣ ይካሄዳል። ላለፉት 15 ዓመታት በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየው ይህ ትርኢት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራቾችን፣ ሻጮችን፣ ገዥዎችን፣ ባለሀብቶችን፣ የቆዳ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የፋይናንስ ተቋማትንና ሌሎች የቆዳ ዘርፍ ተዋናዮችን የሚያገናኝ ትልቅ አህጉራዊ የንግድ መድረክ ነው።
በዘንድሮው የንግድ ትርኢት ላይ ከ200 በላይ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራቾች፣ ግብዓትና ሎጂስቲክስ አቅራቢዎች፣ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ተቋማት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ከ15ሺ በላይ የአገር ውስጥና ከሁለት ሺ በላይ የውጭ አገራት ጎብኚዎችም ትርኢቱን ይጎበኙታል።
‹‹ትርኢቱ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር የሚያገናኝ ጠቃሚ የንግድ መድረክ ነው›› የሚሉት የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ሰለሞን፣ ‹‹መድረኩ ከኮቪድ-19 ተፅዕኖ እና ከዓለም አቀፍ የገበያ ስርዓት ውድቀት በኋላ የቆዳ ኢንዱስትሪን ለማነቃቃት እና የቆዳውን ዘርፍ ውድቀት ለመቀልበስ ትልቅ ሚና ይጫወታል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የኢትዮጵያን ምርቶች ያስተዋውቃል፤ ሻጪና ገዢን ያገናኛል›› ይላሉ። አቶ ሬድማንም የንግድ ትርኢቱ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለመለወጥ አወንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ይናገራሉ።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል በቅርቡ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የአገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው።
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል። በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለአገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች የገጠሟቸውን ችግሮች በመፍታትና ለምርታማነታቸው ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገራዊ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ ለማሻሻል ታቅዶ መተግበር እንደተጀመረ በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መግለፃቸው የሚታወስ ነው። ንቅናቄው በቀጥታ ከሚመለከታቸውና ችግሮቻቸውን እንደሚያቃልልላቸው ከሚጠበቁት ዘርፎች መካከል አንዱ የቆዳ ዘርፍ ነው። ንቅናቄው በስራ እድል ፈጠራም ሆነ በገበያ ተወዳዳሪነት በተለይ ለቆዳ ልማት ዘርፍ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ ተደርጎበታል።
ከንቅናቄው መጀመር በኋላ በዘርፉ የታዩት ለውጦች ይህን ተስፋ ወደ ተግባር የቀየሩ አወንታዊ እርምጃዎች እንደሆኑ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ። ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ከቆዳው ዘርፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ንቅናቄ ነው። የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትም ለቆዳው ዘርፍ ትልቅ ብስራቶች ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ።
ዘርፉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ለሚገኙ ተማሪዎች በሁለት ዙር ከ600ሺ በላይ ጫማ ማቅረቡን ጠቅሰው፣ ይህም በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በእጅጉ ተቀዛቅዞ የነበረውን ስራ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ አድርጎታል ነው ያሉት። በቀጣይም 800ሺ ጫማዎችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ትንንሽ አምራቾችን በማጣመር አቅም እንዲፈጥሩ በማድረግ ለማምረት ጥረት ተደርጓል ይላሉ። የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላትን ጫማ በአገር ውስጥ ማምረት ተችሏል፤ በዚህም በርካታ የሥራ እድል መፍጠርና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን አስታውቀዋል። ወደፊትም ብዙ አዳዲስ የሥራ እድሎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የቆዳ ዘርፍ እድገት የአመለካከት ለውጥን ይፈልጋል። የአገር ምርትን የመጠቀም ባህልን የማዳበር ጥረት ለዘርፉ እድገት ቀላል የማይባል ሚና አለው። በዚህ ረገድ አቶ ሰለሞን ‹‹ብዙዎቻችን ስለማናውቃቸው እንጂ የሌሎች አገራት ብራንድ ተለጥፎባቸው ከትልልቅ መሸጫዎች የምንገዛቸው ጫማዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱ ናቸው። የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። ሕዝባችን የአገሩን ምርት የመጠቀም ባህል እንዲያዳብር ማድረግ ይገባል። ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት መከናወን አለባቸው›› ይላሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2015