በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል – የኢንቨስትመንት ቅኝት

በኢንቨስትመንት ዕምቅ አቅም ካላቸው መካከል አንዱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው። ክልሉ በግብርና እና በማዕድን እንዲሁም በሌሎችም በተለያዩ የልማት መስኮች ለሀገር የሚተርፍ ሀብት ያለው ቢሆንም፤ በሚጠበቀው ደረጃ ኢንቨስትመንት በክልሉ እንዳልተስፋፋ ሲነገር ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ በክልሉ እየተካሄዱ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የባለሀብቶችን ቀልብ ለመሳብ የበቁ እየሆኑ መጥተዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ስንል የክልሉን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በክልሉ አስራ ሁለት የኢንቨስትመንት ዘርፎች አሉ:: ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚ ተደርገው የሚወሰዱት ግብርና እና ማዕድን ናቸው። ለግብርናው ዘርፍ በክልሉ ያለው መሬት ለቅባት እህሎችና እንደ በቆሎ ማሽላ ላሉ ጥራጥሬዎች እንዲሁም ለፍራፍሬና ለጥጥ ምርት ምቹ ነው።

የአየር ሁኔታውም ለግብርና ምቹ ሲሆን፤ ታላቁን የዓባይ ወንዝ ጨምሮ ለመስኖ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ዓመት ከዓመት የሚፈሱ አስራ ሁለት ትልልቅ ወንዞች በክልሉ ይገኛሉ። በተጨማሪ ከሚያዚያ እስከ ህዳር ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭትም አለ። እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች ክልሉ በግብርና ዘርፍ ለኢንቨስትመንት ያለውን ተመራጭነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

ይህም ሆኖ በክልሉ ከ64 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለእርሻ ምቹ የሆነ መሬት ያለ ቢሆንም፤ ይሁንና እስካሁን ልማት ላይ እየዋለ የሚገኘው ከሃምሳ በመቶ ብዙም አልዘለለም። በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከለውጡ በፊት በርካታ ችግሮች ነበሩ። እነዚህን ተግዳሮቶች ክልላዊና ከክልሉ ውጪ ያሉ ሲሆን፤ እንደ ክልል የለውጡ መጀመሪያ ማለትም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም አጋማሽ በነበረው ችግር በርካታ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች ተቀዛቅዘዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሰላም ለማስፈን በተሠሩ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሰፍኗል። ይህም ሆኖ እንደ ኢንቨስትመንት ላሉ እንቅስቃሴዎች በሰው አዕምሮ ውስጥ ያለው ጉዳይ በአጭር ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል ለማለት አይቻልም። በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ የነበረው ችግር መልሶ ሊያገረሽ ይችላል የሚልም ስጋት ያለ ሲሆን፤ ወድመው የነበሩት የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ አልተመለሱም።

በሌላ በኩል ባልተገባ መንገድ ከልማትና ንግድ ባንኮች የተወሰዱ ብድሮችን፤ ይዘው የተሰወሩ ግለሰቦች በርካታ ስለነበሩ ብዙ የተበላሹ ነገሮች ነበሩ። ከለውጡ በኋላ ግን ይህንን ለማስተካከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተሠርቷል:: በከተማም በገጠርም መሬት ከመንጠቅ ጀምሮ በርካታ ውሳኔዎች ተወስደዋል:: በተለያዩ መንገዶች ያለፉ ችግሮችን ለማጽዳት እየተሠራ ይገኛል። በእነዚህ ምክንያቶች በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሚጠበቀው ደረጃ ነው ለማለት አያስደፍርም።

ከግብርና ቀጥሎ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደ ትልቅ ሀብት የሚታየው የማዕድን ዘርፍ ነው:: ከዚህ ውስጥ ወርቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 34 ኩንታል የሚጠጋ ወርቅ ለማምረት ተችሏል። ከዚህ ቀደም ይህን መጠን የሚቀራረብ የወርቅ መጠን ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ አያውቅም። በዚህ ዓመትም ይህንን ያህል ለማስገባት የተቻለው እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ በተሠሩ መሠረታዊ የማሻሻያ ርምጃዎች ነው። ይህም ሆኖ ክልሉ ካለው እምቅ አቅም እና ሊደረግ ከሚገባው ቁጥጥር አኳያ ከዚህም በላይ ማምረት ይቻል እንደነበር አንስተዋል።

ዛሬም ድረስ በዘመናዊ መንገድ አለመመረቱ እና ይህን ተከትሎ የሚፈጠር የምርት ብክነትና ኮንትሮባንድ እንደ ተግዳሮት የሚነሳ ነው። በተጨማሪ በማዕድን ዘርፍ በካማሺ ዞን ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ክምችት አለ። በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በሙሉ አቅም ለማምረት ባይቻልም፤ በጅምር ደረጃ ቢሆንም በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከውጪ እየገባ ያለውን ለመተካት ተችሏል። በክልሉ ሁሉም ዞንና ወረዳዎች እምነ በረድ እና ግራናይት የሚገኙ ሲሆ፤ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ዘርፎች በርካታ ባለሀብቶች ጥያቄ በማቅረብ ወደ ኢንቨስትመንት እየገቡ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

ሌላው ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሚጠበቀው ደረጃ አለማደግ ከክልሉ ውጪ ካሉ ምክንያቶች መካከል አንዱ የመንገድ ጉዳይ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአዲስ አበባ እና ከቀሪው አካባቢ ጋር የሚገናኘው በአንድ በኩል በመተከል ዞን በጎጃም ነው:: በሌላ በኩል በወለጋ ይገናኛል። በእነዚህ አካባቢዎች ብልጭ ድርግም የሚሉ ችግሮች ዛሬም ድረስ በመኖራቸው፤ ኢንቨስተሮች በነጻነት እቃዎችንና ምርቶቻቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እንቅፋት ተፈጥሯል። በዚህ ውስጥም ቢሆን ግን ነገ ሰላም ይሆናል በሚል እሳቤ ዛሬም ድረስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።

ቢሮው የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በግብዓት፤ በቴክኖሎጂና በሰው ሀብት ረገድ ክፍተት ያለበት መሆኑን አስታውሰው፤ ባለው አቅም ልክ እየሠራ ይገኛል ብለዋል:: ከለውጡ በኋላ በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችንም እንደሚከተለው ገልጸዋቸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ በክልሉ ከለውጡ በፊት የኢንቨስትመንት ዘርፍ በሚጠበቀው ደረጃ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም። ለምሳሌ አንድ ፈቃድ የወሰደ ባለሀብት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በየወቅቱ ባስቀመጠው እቅድ መሠረት በሚጠበቀው ደረጃ ክትትልና ቁጥጥር ሲደረግበት አልነበረም። ለዚህ ደግሞ ዘርፉን የሚቆጣጠረው ክፍል ራሱን ችሎ አለመደራጀቱ አንደኛው ምክንያት ነበር።

በአዲሱ አደረጃጀት ማዕድን እና መሬት ራሳቸውን ችለው በቢሮ ደረጃ በከተማና በገጠር እንዲደራጁ ተደርጓል። የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮም የተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች ተመስርተውለት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በአዲሱ አደረጃጀት የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ በዘርፉ ፍቃድ ከመስጠት ጀምሮ የድጋፍ ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ያከናውናል።

በዚህ አይነት ክትትል የሚደረግለት ተቋም ከብድር አገልግሎት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎለት ውጤታማ ሳይሆን ከቀረ ፈቃዱን እንዲመልስ ይደረጋል። በዚህ አካሄድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አበረታች ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል። ለምሳሌ በቀርከሃ ምርት ረገድ ሥራ አቁሞ የነበረውን የባንቡ ስታር ፋብሪካን ከፌዴራል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል። በተመሳሳይ ሥራ አቁሞ የነበረ አንድ የእምነበረድ ፋብሪካንም ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል። ይህም ሆኖ ትልልቅ ፋብሪካዎች እንዲቋቋሙ ለማድረግ እንዲሁም ድጋፍና ክትትል ከማድረግ አኳያ እንደ ክልል ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ።

እንደአጠቃላይ በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው:: ይሁንና ከሚጠበቀው አኳያ ሲመዘን በርካታ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ። ምክንያቱም ዘርፉ መመዘን ያለበት እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ሊያበረክት ከሚችለው አኳያ ነው። በዚህ ረገድ በሌሎች ክልሎች እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ያህል በክልሉ አለ ለማለት አያስደፍርም። ለቀጣይም እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር የተቀመጡ እቅዶችን መነሻ በማድረግ ዘርፉን በፈጣን ለውጥ ለመምራት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ400 ሺህ ብር በክልሉ ለኢንቨስትመንት ያለውን ሁኔታ እየተጠና ይገኛል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኢንቨስትመንት ሥራ በባህሪው በቢሮው በኩል ብቻ ሊከናወን አይችልም። የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎም ወሳኝ ነው:: ከእነዚህም መካከል እንደ መብራት ሃይል ፣ መንገድ፣ውሃ፣ ቴሌ ኮም ያሉት የአቅርቦት ተቋማት ተብለው በአንደኛ ደረጃ የተለዩ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የፋይናንስ ምንጭ የሆኑት ባንኮች ፤ እንዲሁም መሬት አስተዳደር፣ ማዕድን ቢሮ ፤ የባለሀብቶች ማህበራትን ጨምሮ አሉ። እነዚህ ለኢንቨስትመንት ወሳኝ ባለድርሻ አካላት ናቸው።

ከእነዚህ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት የተፈጠረ ሲሆን፤ የመግባቢያ ሰነድ ፈርመው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉም አሉ። ከእነዚህ ተቋማት ጋር እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ሲሆን፤ በየሩብ ዓመቱ መድረክ በማዘጋጀት ግምገማም የሚካሄድ ይሆናል። እንደ ተቋም ውጤታማ ያደርጋሉ ተብለው ከተለዩት ሥራዎች መካከል አንዱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ የመሥራት እንቅስቃሴ ነው።

በዚህም ከተገኙ ውጤቶች መካከል እንደ ክልል ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ፤ ነገር ግን በመንገድ ችግር ምክንያት ለልማት ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች በተመለከተ እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ ከባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ገንዘብ በማሰባሰብ የመንገድ ጠረጋ ሥራዎች ማከናወን ተችሏል። በኢትዮ ቴሌኮም በኩልም ተደራሽ ያልሆነባቸውን የጠረፍ አካባቢዎች ለማዳረስ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።

በሌላ በኩል ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት ባለሀብቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማግኘት ይጠበቅበታል። በዚህ ሂደት ከሥነ ምግባር መጓደል ጀምሮ ሙስና እና በተደጋጋሚ እንዲመላለሱ ማድረግ እንደነበር ካለፉ አፈጻጸሞች ለመገምገም ተችሏል። ይህ ለዘርፉ ትልቅ ማነቆ በመሆኑ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልፀው፤ ከጅምሩ አበረታች ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን ያመላክታሉ።

ሌላው በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማፋጠን እንደ አቅጣጫ እየተሠራባቸው ካሉ ነገሮች አንዱ ማህበረሰቡን ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ነው። በክልሉ ከ2011 ዓ.ም በፊት ለኢንቨሰትመንት አለማደግ አንዱ ማነቆ ዘርፉ ከማህበረሰቡ ጋር የነበረው ተቃርኖ ነው። አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ ሲሰጥ የነበረው የሳተላይት ፎቶ መነሻ ማድረግ በመሆኑ፤ ባለሀብቱ ሊረከብ ሲመጣ ቦታውን በአርሶ አደሩ ተይዞ ያገኝ ነበር። አጠቃላይ የነበረው እንቅስቃሴ ማህበረሰቡን የማያሳትፍም ነበር። እነዚህን ተግዳሮቶች መሻገር ያስፈልግ ስለነበር ከለውጡ በኋላ በርካታ ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ ተደርጓል።

ከእነዚህም መካከል ደንብ በማውጣት ማዕድን በሚገኝባቸው እና በሚሠራባቸው አካባቢዎች ከሚገኘው ጥቅም 30 በመቶ ለአካባቢው ነዋሪ ይተዋል:: ለባለሀብቱ የሚደርሰው ሰባ በመቶ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል። በአንዳንድ የኢንቨስትመንት መስኮች ሃያ በ80 የሚደረግም አለ። በአሁኑ ወቅት በማዕድን ዘርፍ ማህበረሰቡ በባለቤትነት የማይሳተፍበት ኢንቨስትመንት የለም። ማንኛውም ኢንቨስትመንት ሲካሄድ የአካባቢው ማህበረሰብ ስለሚያካሂደው ነገር አጠቃላይ ገለጻ ተደርጎለት መስማማቱን በቃለ ጉባዔ ሳያረጋግጥ የሚጀመር ኢንቨስትመንት የለም።

በግብርና ዘርፍም የማህበረሰብ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋጋጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም፤ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር የተከሰቱ ችግሮች ግን ዛሬም ያልተፈቱ አሉ ያሉት ኃላፊው፤ ሰፋፊ ቦታዎችን የወሰዱ ኢንቨስተሮች አሉ፤ የአርሶ አደሩ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የድንበር መገፋፋት ፤ የእርሻ ቦታዎች ለእንስሳት ግጦሽ መጠቀም ይታያል። እነዚህንም ከመሬት አስተዳደር ጋር በመሆን እዛው በማህበረሰቡ እንዲፈታ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለቀጣይ ከሰላም ማስፈን ምቹ አሠራር ከመዘርጋት ባለፈ ዘርፉን የማስተዋወቅ ሥራ የትኩረት አቅጣጫ ነው ያሉት አቶ አመንቴ፤ በዚህ ረገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን እንደሚከተለው አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉ የመንግሥትና የግል የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎችን እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በክልሉ ለኢንቨስትመንት ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን እያስተዋወቅን እንገኛለን።

ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በየወቅቱ የሚዘጋጁ ሀገር አቀፍ መድረኮችና ኢግዚቢሽኖችም እየተካሄዱ ይገኛል። ይህ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጪ የሚመጡት ባለሀብትንም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል። ይህም ሆኖ ክልሉ ካለው ሀብትና ሊመጣ ከሚችለው ኢንቨስትመንት ተሳታፊ አኳያ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ በግምገማ አረጋግጠናል። ይህም በቀጣይ ዓመት በቀዳሚነት ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራበት ይሆናል።

በራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You