የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ከመሠረቱ ሲቋቋም የአዲስ አበባን አመራሮች አቅም በመገንባት የከተማዋ ነዋሪ መልካም አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል አንዱ አላማ ነው:: ከዚህም ባሻገር ከተማዋ የኢትዮጵያም ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና ብሎም በዓለማችን በርካታ ዲፕሎማቶችን የሚቀመጡባት ሦስተኛዋ ከተማ ናት:: በመሆኑም እነዚህን ታሳቢ በማድረግ ሥልጣንና ተግባራቱም ሰፋ ያሉ ሆነዋል::
በዚህም መሠረት አካዳሚው ከተጣለበት ኃላፊነቶች በጥቂቱ መጥቀስ ተገቢ ነው:: የከተማውና የአገሪቱን የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መሠረት በማድረግ የአካዳሚውን የትምህርትና ስልጠና መርሐ-ግብር መቅረጽ፣ ሞጁሎች ያዘጋጃል፣ በቦርድም ሲፀድቅም በሥራ ላይ ያውላል:: የከተማው አስተዳደር አመራርና ባለሙያ የትምህርትና ስልጠና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ሥልጠናዎችንም ይሰጣል:: የተቋማትን፣ የአመራርንና የባለሙያን የማስፈፀም አቅም ለመገንባት የሚረዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ይሠራል፤ ሲፀድቅም ተግባራዊ ያደርጋል::
ቤተ መጻሕፍትን በማደራጀት የትምህርትና ሥልጠና ሂደቱን ይደግፋል፣ ሌሎች የትምህርት መሣሪያዎችን ያደራጃል፣ ለሥልጠናው አግባብነት ያላቸው የሥልጠና አሰጣጥ፣ የምዘናና ግምገማ ሥርዓቶችን ይነድፋል፣ ሲፀድቅም ተግባራዊ ያደርጋል:: ከመንግሥታዊ መስሪያ ቤቶች ወይም የግል ድርጅቶች በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት ለአመራርና ባለሙያ የሥልጠና፣ የምክርና የማህበረሰብ አገልግሎት ይሰጣል::
ሠልጣኞች ሥልጠናቸውን ሲጨርሱ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፣ የሥልጠና ውጤታማነት ጥናት ያካሂዳል፤ ለሚመለከተው አካልም ያቀርባል፣ ከጥናቱ በመነሳት የተሻሉ የአሠራር ስልቶችን ይቀይሳል:: በቦርዱ ሲፈቀድለት የከተማ አስተዳደሩን ማህበራዊ ችግር የሚፈታ የጥናትና ምርምር ተግባራትን ያከናውናል፣ የተገኙ ውጤቶችንም ያሳትማል፣ ያሰራጫል በሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል:: የአካዳሚውን የትምህርትና ሥልጠና አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ያከናውናል::
ይህ አካዳሚ የተለያዩ ትምህርታዊ ሴሚናሮችን፣ ወርክ ሾፖችን፣ ኮንፈረንሶችንና አውደ ጥናቶችን ያዘጋጃል፣ ያካሂዳል፣ ጥሪ ሲደረግለትም ይካፈላል:: ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች አቻ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው የፌዴራልና ክልል ተቋማት ጋር ግንኙነትና ትብብር ይፈጥራል፣ ምርጥ ተሞክሮም ይለዋወጣል:: ከነዚህ አካላት ጋር በመተባበር ትምህርትና ሥልጠና ይሰጣል ወይም እንዲሰጥ ያደርጋል የሚሉና ሌሎች ሥልጣንና ተግባራትንም ተሸክሟል:: በዛሬ ዕትማችንም ከአካዳሚው ምክትል ፕሬዚዳንትና የምርምር ማማከር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ ኃይሌ ጋር ቆይታ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን አንድ የጥናት ምርምር አካሂዳችኋል:: አውደጥናቱ ምርምሩ ከተማ ተኮር የሆነበት ምክንያት ነው?
አቶ ማንደፍሮ፡- ዓላማው በአገር ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው:: በዚህ ላይ በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት በመሆኑ ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው:: ይህ በዓመታዊ እቅዳችንም የተካተተ ነው:: በዋናነት ከተማ አቀፍ ጥናት ነው የተካሄደው:: ከተለያዩ ተቋማት ምሁራን የተሳተፉበት በመሆኑ ብዙ ተሞክሮ የሚገኝበት ነው:: ከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት የተያያዘው መልካም አስተዳደር የማስፈን፣ ዴሞክራሲን የማስረጽ፣ ልማቱን ለማፋጠን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዕድገት የደረሰበትን ደረጃ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መፍትሄ ማሰባሰብ ነው::
እኛ አገር በብዛት ስለ ችግር ይወራል:: እኛ ደግሞ የምንለው ችግርን ማውራት ብቻ ሳይሆን መፍትሄን እንዴት እናምጣ የሚለው ነው:: በዚህ ላይ ትኩረት አድርገን ነው ጥናትና ምርምሮችን እያካሄድን ያለነው:: በመሆኑም ከሁሉም በቀደመ መልኩ እንዴት የመፍትሄ አካል እንሁን የሚለው ዋነኛ አጀንዳችን ነው:: ለከተማዋ ችግር የመፍትሄ አካል መሆን የሞራል የታሪክም ግዴታ አለብን:: ምሁራንም በዚህ ላይ ግዴታቸውን እንዲወጡ ነው ያሰባሰብነው::
በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኅብረብሔራዊ ወንድማማችነት ከምንም በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው:: ብዙ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን:: ሆኖም ወጣ ገባ የሚሉ ችግሮች አሉ:: በመሆኑም በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ጥናቶች እየቀረቡ ነው፤ በቀጣይም በዚህ ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን:: ብዙሃነትን ባቀፈ መንገድም የመፍትሄ አካል ለመሆን እየሠራን ነው::
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚው ከተመሠረተ ሥምንት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ በርካታ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ አካሂዷል:: በቀጣይም የከተማዋ አሁናዊ እና ቀጣይ ችግሮችን ታሳቢ ያደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል፤ በዚያው ልክ የመፍትሄ አካላትም እልባት መስጠት የሚችሉበት ዕድል ይኖራል:: የተጀመረው ሥራ በየጊዜው እየተጠናከረ ይሄዳል::
አዲስ ዘመን፡- የአካዳሚው ጥናትና ምርምሮች በዋናነት የሚያተኩሩት ችግሮች ላይ ብቻ ነው?
አቶ ማንደፍሮ፡- ችግሮች የመፍትሄዎች መነሻዎች ናቸው:: ችግሮች በከተማ አስተዳደራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የተለያየ ቅርጽ እየያዘና እየተለወጠ ነው:: ዓለማዊ ሁኔታው ደግሞ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሯዊ መንገድ የመለዋወጥ ሁኔታዎች አሉ:: ለምሳሌ ሰው ሰራሽ ከሆኑት የተወሰኑትን ስንመለከት ከፍተኛ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ አለ::
ተደጋጋሚ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እና እሳተ ገሞራ እናያለን:: በሌላ ጎኑ ደግሞ እንደ ኮሮና ቫይረስ የመሳሰሉትና ሌሎች ወረርሽኞችን እናያለን:: ሰው ሠራሽ የምንላቸውን የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ የዩክሬንና ራሺያን ጦርነት ለአብነት ማንሳት እንችላለን:: ይህ ጦርነት በዓለም ገፅታ ላይ የራሱ የሆነ ለውጥ እያመጣ ነው:: በኢትዮጵያም ላይ የራሱን ለውጥ እና ተጽዕኖ እያመጣ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አካዳሚው ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ምልክታ ምንድን ነው?
አቶ ማንደፍሮ፡- ከባቢያዊ ሁኔታዎችን እና ጉዳዮችን መመልከት ይገባል:: እኛ የምንኖረው የአፍሪካ ቀንድ ላይ ነው:: በዚህ ቀጣና ደግሞ ጂኦ-ፖለቲክሱ እየተቀየረ ነው:: በርካታ ኃያላን አገራት በዚህ ቀጣና ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው የጦር ካምፖችን እየገነቡና በምሥራቅ አፍሪካ እየተስፋፉ ነው:: በዚህም አካባቢውን በበላይነት መቆጣጠር ፍላጎት እና ትልቅ ሽኩቻ አለ:: በዚህ ወቅት የእኛ የውስጥ ሠላም በዘላቂነት እንዳይኖር የሚያደርጉ ተጽዕኖዎች ይኖራሉ::
አንደኛው እኛ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው መፍጨርጨር የማይዋጥላቸው አካላት አሉ:: ይህን ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ማያያዝ እንችላለን:: እነዚህን ብቻ ሳይሆን በርካታ የልማት ትልሞቻችንን እንዳናሳካ ምክንያት ይሆናሉ:: ስለዚህ በውስጥ ሰላማችን እየተረጋጋ እንዳይሄድ ከማድረግ ጀምሮ ከውጭ ተጽዕኖ ጋር ተደማምሮ ፈተናዎች እንዲኖሩ ያደርገዋል::
ሌላው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄድና በዚያው ልክ ምርታማነት አለመጨመር ችግር አለ ብለን እንድናስብ ያደርገናል:: ለዚህም የዓለምን እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ሁኔታ በመመልከት እና በመተንተን የመውጫ መንገዱን ማመላከትና የመፍትሄው አካል መሆን እንጂ ችግሮችን ደጋግመን መናገር የለብንም::
ሰዎች በብዛት ስለ ኑሮ ውድነት ያነሳሉ:: ይህ ጊዜያዊ ችግር ነው:: በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚስተዋል ችግር ነው:: ሆኖም የእነዚህ ችግሮች ምንድን ናቸው ብለው ምሁራን ያስባሉ:: ዋነኛ መውጫ መንገዱ እና በዘላቂነት ችግሩ የሚፈታበት መንገድ ልማትን በማሳደግና ተደራሽ በመሆን ነው:: የልማት እጥረት ያመጣው ችግር መፍታት የሚቻለው በልማት ነው:: የሰላም እጦትን መፍታት የሚቻለው ሠላም በማረጋገጥ እና ሰላም በፅኑ መሠረት ላይ በመገንባት ነው የሚፈታው:: ስለዚህ የእነዚህን ችግሮች መፍትሄ ለማመላከት ምሁራን ሚናቸው የጎላ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አሁናዊ እና ቀጣይ የከተማዋን ችግሮች የሚቃልሉ ጥናትና ምርምሮችን ለማካሄድ የተሰጠው ትኩረት በምን ደረጃ ይገለፃል?
አቶ ማንደፍሮ፡– በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ውስብስብ ችግሮችን ለማቃለል ዘርፈ ብዙ ጥናቶችን በማከናወንና ለሚመለከታቸው አካላት በመስጠት ላይ ነን:: በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ ላይ ያንዣበቡ ችግሮች እልባት መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግ ጥናት እየተካሄደ ነው:: የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው::
በከተማ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት ነው የሚሠራው:: እየተደረጉ የሚገኙ የጥናትና ምርምር ሥራዎችም ከተማዋ በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ችግር በጥልቀት የሚመለከት፤ የሚተነትንና መፍትሄ የሚያመላክት ነው:: ጥናቶችና ምርምሮች በቀጣይም ሊገጥሟት የሚችሉትን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄ ማፈላለግ ላይ ያተኮረ ናቸው::
አሁን ያለውን ችግር ብቻ ሳይሆን ቀጣይ የሚመጣውን ችግር በመገመትና በመተንበይ መፍትሄ አስቀምጠው ይሄዳሉ:: እነዚህና በመሳሰሉት ላይ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ አስፈጻሚ አካላት የመፍትሄ አካል የሚሆን አቅጣጫ የሚገኝበት መንገድም ጭምር ነው::
አዲስ ዘመን፡- አካዳሚው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ እንደመገኘቱ መጠን አፍሪካውያንን ያማከለ ሥራ ይሠራል ?
አቶ ማንደፍሮ፡- መልካም ነው:: አዲስ አበባ የበርካታ ዲፕሎማቶች ከተማ ናት:: ምናልባትም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አኳያም መቀመጫነትም ሦስተኛዋ የዲፕሎማት ከተማ ናት:: ይህም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ወክላለች:: ከዚህም በተጨማሪ እኛ የሊግ ኦፍ ኔሽን ብሎም የአፍሪካ ኅብረት መሥራች ነን:: ይህ ማለት ደግሞ የአፍሪካ አገራት መርከቦች መልህቅ ማረፊያ አዲስ አበባ ናት ማለት ነው:: ይሁንና አዲስ አበባን ያለውን ሁኔታ ስናይ በርካታ ችግሮች አሉባት፤ ይህ የሚታበል አይደለም::
ችግሮቹ ምንድን ናቸው ብለን ስንመለከት፤ ከላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነትና ታሪካዊ መሠረቶችን የሚመጥን መሠረተ ልማት፤ ብቃት ያለው አመራርና የሰው ኃይል አለመኖር ነው:: የከተማዋ ዕድገት ላይ ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት አንዱና ዋነኛው የከተማ አስተዳደር ወይንም መሪ ነው:: በዚህ ደረጃ አስበን መሥራት አለብን::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የሚመጥን አመራር አለ ማለት ይቻላል?
አቶ ማንደፍሮ፡- የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ እንደገና ሲዋቀር በዋናነት ማዕከል ያደረገው ይህንን የሚመጥን ወይንም ሊመጥን የሚችል ተተኪ አመራር መፍጠር ነው:: ይህ ደግሞ መጪውን ጊዜ በመተንበይ በዕቅድ የሚሠራ መሆን አለበት:: አሁን ባለው ሁኔታ እና ከአጭር ጊዜ አኳያ የመልካም አስተዳደር እጦትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጎላ ያለ ችግር ይስተዋላል:: በዚህ ላይ ሰፋ ያሉ ክፍተቶች አሉ:: በዚህ ላይ ሊሠሩ የሚችሉና አካዳሚውን የሚመለከቱ ተግባራትን በመንቀስ እንደ ተቋም በትጋት እየሠራን ነው::
አሁን እያወራን ያለነው ችግር አይደለም:: መፍትሄው ምን መሆን አለበት የሚለው ነው:: ኢኮኖሚያችን በሚመጥነው ደረጃ መውሰድ ያለብን ነገር ካለ መውሰድ አለብን:: ሁሉን በአንድ ቀን ማስተካከል አይቻልም:: ኢኮኖሚ የሚፈታውን ኢኮኖሚ ይፈታዋል:: ነገር ግን በአጭር ጊዜ እና ሁኔታ በፈቀደው ልክ ብሎም በሰው ኃይል አደረጃጀትና በማስተካከል የሚታረሙ ችግሮች ካሉ ለማስተካከል ዕድሉ አለን:: ለዚህም የሚመጥንና የከተማዋን ሁኔታ የተገነዘበ አመራር በማፍራት ረገድ ደግሞ እኛ እንደ አካዳሚ የሚጠበቅብን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ነን::
አዲስ ዘመን፡- ከተሞዋን የሚመጥን ተቋምስ ተገንብቷል?
አቶ ማንደፍሮ፡– ተቋማትን ማጠናከር አንዱና ትልቁ የአገራዊ ለውጥ ትኩረት ነው:: እንደከተማም እየተሠራበት ያለ ጉዳይ ነው:: በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገናል:: አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመጣ የሚቀጥል ሌላው ሲመጣ የሚፈርስ ወይንም የሚያጋድል የተቋም ግንባታ መኖር የለበትም በሚል ጠንካራ ተቋም ግንባታ ላይ በሰፊው እየተሠራ ነው::
በመሆኑም ለትውልድ ቀጣይነት ያለው ተቋም ግንባታ ቅድሚያ የተሰጠው ነው:: በዚህ ግንባታ ውስጥ አንዱ ማሳያ ተቋማችን ነው:: ፕሮፌሽናሊዝም እየተገነባ ነው:: ከተማ መመራት ያለባት ስለ ከተማ ክህሎቱም እውቀቱም ባለው ሰው መሆን አለበት ተብሎ ይታመናል:: ይህ ሳይንስ ነው:: ይህ ሳይንስ ደግሞ እየተተገበረ ነው::
እኛ ደግሞ በሁለት ነገሮች ውስጥ ስፔሻላይዝድ እያደረግን ነው:: በአካዳሚክሱ ረገድ ተተኪ አመራሮችን እስከ ዶክትሬት እያሰለጠንና እያፈራን ነው:: በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጥን ትምህርትና ኮርስ መደጋገም ሳይሆን በከተማ አስተዳደር ስፔሻላይዝ ማድረግ ነው::
ሁለተኛው የእኛን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራት ጭምር የልቀት ማዕከል ሆነን እንወጣለን:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብዙዎቻችን ሞዴላችን ነው:: እኛ እንደዚያ ማዕከል እንሆናለን ብለን ነው የተነሳነው:: ሌላኛው የከተማችን ብቁ አመራር ማፍራት ብቻ ሳይሆን በአገራችን ለሚገኙ ከተሞች ሞዴል ሆነን ሌሎች ከተሞች በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የሚሄዱበትን ዕድል መፍጠር ነው::
አሁን በምንሄደው መንገድ ሳይሆን በዚህ ተሞክሮ ካላቸው እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን እና ሌሎች ትልልቅ አገራት መሰል ተቋማት አላቸው:: ቤጂንግም የማዘጋጃ ቤት ኢንስቲትዩት አላት:: ስለዚህ በከተማችን ያለው ነገር አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል ስለሌለበት የበለጠ መዘመንና ዓለም ከደረሰበት ሁኔታና አኳያ መቃኘት አለበት:: እኛ ስለችግር እያወራን መሄድ የለብንም የሚል አቋም ስንይዝ፤ የተፈጠሩ ችግሮችን ወይንም በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት መከላከልና ማስቀረት ይቻላል የሚል ትልቅ ምስል ነው ይዘን የምንሠራው::
መጪው ጊዜ በጣም ውስብስብ ነገሮች ሊኖሩት ይችላሉ:: ቴክኖሎጂው ውስብስብ ነው:: አሁንም እንደምንለው ከተሞች በማንዋል የሚመሩ ሳይሆን ከስማርት ከተማነት አልፈው ወደ ዲጂታል ከተማ እየቀየሩ ነው:: ስለዚህ ይህንን የሚመጥን አመራር እና ባለሙያ መፍጠር ተገቢ ነው:: በመሆኑም እኛ ዘንድ ያለው ኃላፊነት በጣም ትልቅ ነው:: በመሆኑም በሜጋ ፕሮጀክት ደረጃ ትልቅ ኢንስቲትዩት እየገነባን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ ችግር ብለው ከሚነሱት መካከል ከገጠር ወደ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የሕዝብ መብዛትና የኑሮ ውድነት ናቸው:: በዚህ ላይ ለመንግሥት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምን የጠቆማችሁት ነገር አለ?
አቶ ማንደፍሮ፡- የከተማዋ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው:: ከላይ የጠቀስካቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ከከተማ ባህሪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ እና የሚወለዱ ችግሮች አሉ:: ስለዚህም እነዚህን ችግሮች በጥናት እየለዩና መፍትሄ እያበጁ መሄድ ያስፈልጋል:: ነገሮችን በግምት ወይንም በግምገማ ደስ ባለን መንገድ መናገር አይመከረም:: እውነተኛው ነገር ላይ ቆሞ መነጋገር ይጠቅማል:: ሁልጊዜም መነጋገር ያለብን በማስረጃ ላይ ተመስርተን ሳይንሳዊ ዕውቀትን በተላበሰ መንገድ መሆን አለበት::
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞች በተረጋጋ ሠላም ውስጥ መሆን ሲጀምሩ እና ሥራ ዕድል መፍጠር ሲጀምሩ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ሕዝብ ይቀንሳል:: በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ፍልሰት አለ:: በተለይም ሠላምና መረጋጋት በማይሰማቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ የመፍለስ ባህሪ አለ::
ሌላው ደግሞ ሰፊ የሥራ ዕድል ይኖራል በሚል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ዜጎች ቁጥራቸው ከፍ ያለ ነው:: ከተወላጁ በላይ ወደ ከተማዋ የሚመጣው ቀላል አይደለም:: ይህ ለከተማው አስተዳደርም ራስ ምታት ነው:: እንዲያውም ኢ-ተገማች ነው:: የሕዝብ ቁጥር እና በጀቱን አጣጥሞ ለመሄድም አስቸጋሪ ይሆናል:: ስለዚህ እንደ መንግሥት የሚመከረው ዘላቂ የሆነ እና የተረጋጋ ሠላምን በመላ አገሪቱ ማስፈን መቻል ነው:: ይህ ሲመጣ ባለበት ቦታ ተረጋግቶ የመኖር ዕድሉ ይጨምራል:: ይህ ለከተሞች ዕድገትም ትልቅ ፋይዳ አለው::
በየአካባቢው የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባል:: ሥራ ዕድል ከተፈጠረ ከሌሎች ከተሞች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት ይቆማል አሊያም ይቀንሳል:: ምናልባትም የተረጋጋ ሠላም ካለ እና ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ካለም ከአዲስ አበባ ወደ ክልል ከተሞችም የመሄድ ዕድል ይኖራል:: ሌላኛው ምርትና ምርታማነትን መጨመር ነው:: በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት መድፈን ወይንም ደግሞ ማቃለል ተገቢ ነው:: ስለዚህም የአዲስ አበባ ሥራ አመራር አካዳሚ በከተማዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን እያጠና ለሚመለከተው አካል ከነመፍትሄው እየሰጠ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ጥናት ያመጣው ውጤት ምንድን ነው? ለአብነት ፍልሰት አሁን የከተማዋ ችግር ሆኖ ቀጥሏል::
አቶ ማንደፍሮ፡- ከላይ እንደገለጽኩት አመራር አካዳሚው የተለያዩ ጥናቶችን እያጠና ከነመፍትሄው ያቀርባል:: ካለው የአቅም፤ የፋይናንስና የጊዜ እጥረት አኳያ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጀንበር ላይፈቱ ይችላሉ:: ለአብነት ያህል ያነሳኸው የፍልሰት ጉዳይ ተጽዕኖው ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን ሠላም ላይም ጭምር ነው:: ሥራ ያጣ ሰው ለመኖር ሲል የማይጠበቁ ወንጀሎች አሊያም ደግሞ ድርጊቶች ውስጥ ሊሳተፍ ይችላል:: ለተለያዩ ፀረ ሠላም ኃይሎች ወይንም ሱሶችም የመገዛት ዕድል ይኖረዋል:: ለነዋሪዎችም ሥጋት የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው::
ይህ ችግር ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ብቻ የሚፈታ አይደለም:: ዜጎች ስለሆኑም ግቡ አትግቡ ብሎ መከልከል አይቻልም:: በመሆኑም እንደ ፌዴራል ሥርዓቱ በመላው ኢትዮጵያ ሰላም እንዲኖር መሠራት አለበት:: በዚህ ላይ ሁሉም ዜጋ ድርሻ አለው:: ወደ መንግሥት ብቻ መወርወር የለብንም:: እንደ ኢትዮጵያ የችግሮች አልፋ እና ኦሜጋ አድርገን የምናስበው መንግሥትን ነው:: ከዚህም አልፎ መፍትሄ የምንጠብቀው ከመንግሥት ብቻ ነው:: ይህ አካሄዳችን ለዘመናት የመጣንበት ነው:: ነገር ግን መፍትሄ አላስገኘልንም:: በመሆኑም ችግሮችን የምንረዳበትና መፍትሄውን የምንጠብቀው ከአንድ አካል ብቻ መሆን የለበትም::
እንደ አገር እና ሕዝብ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት አለበት:: ለራሱ ሲል እያንዳንዱ ዜጋ ሥራውን መሥራት አለበት:: መንግሥትም የራሱን ሥራና ኃላፊነት መወጣት አለበት:: የመጀመሪያው የውስጥ ሠላምን ማረጋገጥ ነው:: ቀጣይ ደግሞ ምርታማነትን በመጨመር የአቅርቦትና ፍላጎትን አለመጣጣም መሸፈን ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- እንደ ከተማ አስተዳደር እና የከተማዋን ችግር ለማቃለል እንደሚተጋ አካዳሚ የተሻሉ ልምዶችን የመቅሰም ባህላችሁ ምን ይመስላል?
አቶ ማንደፍሮ፡– ከለውጡ በኋላ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች በአፍሪካ ብሎም በዓለም ተጠቃሽ ከተማ ትሆናለች:: አዲስ አበባ ከ40 ዓመት በላይ ስትመራ ከመጣችበት መንገድ በላይ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ያመጣችው ለውጥ ትልቅ ነው:: በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ደግሞ ከዚህ በላቀ ሁኔታ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አለን::
አዲስ ዘመን፡- ተጨማሪ ሃሳብ አልዎት?
አቶ ማንደፍሮ፡- የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የከተማ አስተዳደሩን ችግር ሊቃልል የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማካሄድ አስፈፃሚው አካል እንዲተገብረው የበኩላችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን:: በተለይም ደግሞ የከተማ አስተዳደር በዘመናዊ መንገድ እንዲመራ እና ዓለም ከደረሰችበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የተቃኘች ከተማ እንድትሆን አካዳሚው እየሠራ ነው:: በቀጣይም ይህን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም