የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቋማትን ሪፎርም ተከትሎ ከቀድሞው ሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር እና ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በማዋሀድ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተብሎ የተደራጀ ተቋም ነው። በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነትም የእነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች መብት፤ ደህንነት እና ጥቅም ማስከበርን መሠረት ያደረገ ነው።
ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ እየሠራ ስላለው ሥራ፤ የሴቶችን መብት እና ደህንነት በመጠበቅ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ምን እያከናወነ ነው ? የህጻናትን እና የአካል ጉዳተኞችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት ምን ሠራ? ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከመደገፍ አኳያ መሥሪያ ቤቱ እየሠራቸው ስላሉ ሥራዎች የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡– ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሴቶችን መብት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ እየሠራ ያለው ሥራ እንዴት ይገለጻል?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡– ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች አንዱ የሴቶች መብትን እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። ይህንንም ከመተግበር አኳያ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ከነዚህ ውስጥም የሴፍቲኔት ፕሮግራም አንዱ ነው። በዚህ ፕሮግራም ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን በገጠርና በከተማ ሥራዎችን እንሠራለን።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዋነኛነት የቀጥተኛ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን፤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን እና አቅመ ደካማ የሆኑ ሴቶችና ህጻናትን የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይከታተላል፤ ይደግፋል፤ ይቆጣጠራል። በዚህም ከ1 ሚሊየን 251 ሺ በላይ ዜጎችንም በገጠር እና በከተማ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር በዘንድሮ ዓመት ከ27ሺ በላይ ሴቶች የቁጠባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል። 129ሺ566 የሚሆኑ ሴቶችን የብድር ተጠቃሚ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። ይህም ሴቶቹን ተጠቃሚ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በሴቶቹ ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለው ሚና የጎላ ነው።
ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ጋር በተያያዘም፤ ዜጎች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡ የተለያዩ ሥራዎችን እንሠራለን። ከስደት ሲመለሱ ከሚሠራው ሥራ ይልቅ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረግን ፍልሰት መከላከል ጥቅሙ የላቀ ነው። በዚህም ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ሥራዎችን እንሠራለን።
የኢትዮጵያ መንግሥት አንዱ እየሠራ ያለው ሥራ የውጭ ስደተኞችን መብት እና ጥቅም ማስከበር ነው። በእስር ቤት ያሉ ዜጎች መብቶቻቸው እንዲጠበቅ እና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራም ይሠራል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጊዚያዊ መጠለያዎች ላይ ‹‹የሳይኮ ሶሻል›› ድጋፍ ይሰጣል። የተመላሾችን መረጃ በመሰብሰብ ይተነትናል። ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉም የማድረግ ሥራም ይሠራል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን የያዘ እንደመሆኑ የአካቶ ትግበራ ሥራዎችንም እንሠራለን። ከዚህ በፊት በነበረው አካሄድ ተቋሙ በአካቶ ትግበራ ሥራዎች ውስጥ የማስተባበር ኃላፊነት ብቻ የነበረው ሲሆን አሁን ግን የመቆጣጠር ኃላፊነት ጭምር አለው።
ይህም ማለት ተቋማትን ተጠያቂ ማድረግም ይችላል። በምንሠራቸው ሥራዎች ውስጥ ምን ያህል ሴቶች፤ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ ሆነዋል የሚለውን እናረጋግጣለን። ተጠያቂ የማድረግም ሥራ እንሠራለን። በዚህም የተለያዩ ሴቶች፤ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችን የመከታተል ሥራ እንሠራለን።
የሴቶች ፖሊሲያችን ከ30 ዓመት በላይ የሆነው ስለሆነ ክለሳ የማድረግ ሥራ ሠርተናል። የሴቶች ተጠቃሚነትና የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ፖሊሲን እንዲጸድቅ ለሚመለከተው መሥሪያ ቤት ሰጥተናል። የወጣቶች ፖሊሲን፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታን ያገኘው የወጣቶች የብሔራዊ አገልግሎት ፖሊሲ እና የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ፖሊሲን ጨርሰን ለሚመለከተው መሥሪያ ቤት አስረክበናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ከ20 በላይ የሚሆኑ ኮንቬንሽኖችን እንዲተገበሩ እናስተባብራለን።
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንሠራለን። ከ71ሺ 4መቶ በላይ ሴቶችም የታዳሽ ኃይል አማራጮችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ተችሏል። የሴቶች የልማት ህብረትን የማጠናከር ሥራም እየሠራን ነው። በዚሁ የልማት ህብረትም ሴቶች በግብርና ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው። በዚህ ሩብ ዓመትም ከ36ሺ በላይ የልማት ህብረቶችን ማደራጀት ተችሏል። በአንድ የልማት ህብረት ውስጥ 10 ሴቶች ይገኛሉ፤ በዚህ ዙሪያ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።
በበጎ ፈቃድ ሴቶችን የማሳተፍ ሥራም ተሰርቷል። ሴቶች በእለት ተዕለት ሥራቸው ቤተሰባቸውን የመንከባከብ ሚና በዋነኝነት ይጫወታሉ። ከቤተሰባቸው ወጥተውም ማህበረሰቡን በበጎ ፈቃድ ሥራ እንዲያገለግሉ ለማድረግ ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን። በዚህም አምስት ሚሊየን ሴቶችን ተሳታፊ ማድረግ ተችሏል። በእነዚህና መሰል ፕሮግራሞች የሴቶችን ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋሙ እየሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግጭት እና የተፈጥሮ አደጋ በደረሰባቸው ሥፍራዎች ሴቶችን ከማገዝ እና ከጥቃት ከመጠበቅ አኳያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች እንዲሁም በሌሎች ሥፍራዎች ሴቶች ላይ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ጥቃቶች እንዳይደርሱ ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንሠራለን። ሥጋት ያለባቸው ሴቶች ካሉ ደግሞ ‹‹የሆት ላይን ሰርቪስ›› ወይም የነፃ መስመር ስልክ ተጠቅመው መረጃ እንዲሰጡ በሁሉም ክልሎች መስመሮችን ዘርግተናል። በዚህም ዘንድሮ 1ሺ584 የሚሆኑ ሴቶች የጥቃት ሥጋት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ጥቃቱ ሳይፈጸም ቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት ተችሏል።
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እንዲያገግሙ እና ህክምና እንዲያገኙ እናደርጋለን። የሕግ ድጋፍም ያገኛሉ። ከጤና ሚኒስቴር፤ ከፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች የሕግ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ሥራዎችን እንሠራለን። ከዚህ በተጨማሪም የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የአንድ ማዕከል አገልግሎታችንን ለማስፋት ሥራዎችን እየሠራን ነው። ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው 32 የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቁጥሩን ወደ 87 ማሳደግ ተችሏል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት አላማው ግጭት እና የተፈጥሮ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁለንተናዊ አገልግሎት ለሴቶች መስጠትን መሠረት ያደረገ ነው። ከዚህ አንጻር በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ350 በላይ ሴቶች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ በማህበረሰብ መገለል የደረሰባቸውን ሴቶች በተሃድሶ ማዕከሎቻችን ድጋፍ የምናደርግበት ሁኔታ አለ። ሥልጠና በመስጠት እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲቋቋሙ የማድረግ ሥራዎችንም እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች የምትሰጡት የባለሙያ ሆነ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ምን ይመስላል?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- የፍትህ ሚኒስቴር ጠበቃ ማቆም ላልቻሉ ዜጎች ጠበቃ የማቆም ሥራ ይሠራል። በኛም በኩል በአንድ ማዕከል አገልግሎታችን ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ነፃ የሕግ አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን። በተጨማሪም ጥቃት ደርሶባቸው ለጠበቃ አገልግሎት የመክፈል አቅም የሌላቸውን ሴቶች ለመደገፍ ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጋር በጋራ እንሠራለን።
የፍርድ ቤቶች ያላቸውን ነፃ ውሳኔዎች መከበር ስላለበት በፍትህ አሠራር ሂደት ላይ የፍትህ መዛባት ወይም በቂ ያልሆነ ውሳኔ ቢተላለፍ፤ ፍርዱ ይቀየር አንልም። ነገር ግን የተወሰነው ውሳኔ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ይግባኝ በመጠየቅ የፍርድ ሂደቱን የመከታተል ሥራዎችን እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተመለከተ በሕጉ የተቀመጠው የቅጣት መጠን ሊሻሻል ይገባል የሚሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች እና ሌሎች ባለሙያዎች ጥያቄ ያነሳሉ። በዚህ ጉዳይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አቋም ምንድነው?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ጥቃትን የምንከላከልበት አንደኛው መንገድ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ሲኖር ነው። እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሕጉ ይሻሻል የሚለውን ጥያቄ እኛም እናነሳለን። ይህን የምንለው ግን ሰዎች እንዲቀጡ ከመፈለግ አይደለም። በተደጋጋሚ ጥቃት ሲከሰት አይተናል። ይህ ሕጉ ጋር ያለውን ክፍተት ያሳያል። አንድን ሕግ ለማሻሻል ነባሩ ሕግ ላይ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ከዚህ አንጻር ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሕጎችን የመፈተሽ ሥራ እየሠራን እንገኛለን።
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየረቀቁ መጥተዋል። ጥቃቶቹ ምስክር ሊቀርብባቸው የሚችሉም አይደሉም። በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች የሚይዙ የሕግ አካላት በምን መልኩ ጉዳዮቹን ሊይዟቸው ይገባል የሚል ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ጥቃትን ለመከላከል የጥቃት አድራሾች ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን እየገነባን ነው። አንድ ጥቃት አድራሽ የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ እንዳለ ሆኖ በጥቃት አድራሽነት በዚህ ዲጂታል ሲስተም ትመዘገባለች/ይመዘገባል።
ይህ ምዝገባ ከዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጽምን አካል ለማህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲደረግ ይፋ ይደረጋል፤ ከማህበራዊ አገልግሎቶች ይገለላል። ይህ ዲጂታል ሲስተም ማንኛውም ጥቃት አድራሽ ጥቃቱን አድርሶ በሰላም መኖር እንደማይቻል አስቀድሞ ማሳሰብ የሚችል። የዲጂታል ሲስተሙን የማልማት ሥራ እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ዓመት የሚጠናቀቅም ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለችግር የተጋለጡ ሴቶችን በመደገፍ ያለው ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ለችግር የተጋለጡ ሴቶች ወደ ማዕከላችን መጥተው የሥነ-ልቦና ሥልጠና እና ድጋፍ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናዎች ከወሰዱ በኋላ የመቋቋሚያ ገንዘብ አግኝተው ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ይደረጋል። በዚህ መንገድ የተለወጡ በርካታ ሴቶች አሉ። ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የተቋቋመውን የነገዋ ማዕከል ማንሳት ይቻላል። አዲስ አበባ ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በመሆን በማዕከሉ የሚገኙ ሴቶች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎችን እየሠራን ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ከኮታ ባሻገር በችሎታቸው በአመራርነት ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን እየሠራ ነው?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ለሴቶች የአመራርነት ክህሎት ሥልጠና በሰፊው እንሰጣለን። በሚቀጥለው ሩብ ዓመት ላይ ካስቀመጥናቸው እቅዶች መካከል ይህ ዓመት እስከሚጠናቀቅ ድረስ አራት ሺህ ለሚሆኑ ሴቶች የአመራርነት ክህሎት ሥልጠና እንዲሰጥ እናደርጋለን። ሥልጠናውን ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የምንሠራው ሲሆን ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና በመመዝገብ የአመራር ቋት እንዲኖረን አድርገናል። ብዙውን ጊዜ ሴቶች ለአመራርነት ሲፈለጉ የሉም፤ ካሉም ደግሞ አልበቁም ይባላል። ቋቱ የሰለጠኑ ሴቶችን መዝግቦ በመያዝ ወደ አመራርነት እንዲመጡ የሚያደርግ ነው።
ሴቶች የሚሰጠን የአመራርነት ቦታ የለም፤ መውሰድ ነው ያለብን። ለዚህ ደግሞ በሥራ ብቁ መሆን ያስፈልጋል። ሴቶች የተለያየ የአመራርነት ቦታ ሲሰጣቸው የተሻለ ውጤቶችን በማስመዝገብ ችሎታቸውን በተግባር እየገለጡ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ 50 በመቶ ካቢኔያቸውን ሴቶች ሲያደርጉ ብዙ ጥያቄ አስነስቷል። ነገር ግን እነዚያ ሴቶች በአመራርነት ላይ ከመጡ በኋላ ብቃት ያለው ሥራ በመሥራታቸው አሁንም 50 በመቶ ካቢኔው ሴቶች ናቸው።
ከላይ ጀምሮ ያለውን ብቻ ሳይሆን ከታችኛው እርከን ከክልሎች ጀምሮ መወከል አለባቸው የሚል ቁርጠኝነት በመንግሥት በኩል አለ። የማሰልጠን የማብቃት ሥራውን ደግሞ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በመገናኛ ብዙሃን የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎችና ፊልሞች ላይ የሴቶች ውክልና የቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ ብቻ እንዳይሆን ምን ሥራዎች እየተሠራ ነው?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- የጾታ ውክልና አልያም ሚና በአስተሳሰባችን ውስጥ ያለ ከአስተዳደግ ጀምሮ የምንመለከተው እና በቤተሰብ ውስጥ የሚሰጥ ነው። ይህ ባሕል በሌሎች ሀገራትም ላይ አለ። በሀገራችን በይበልጥ ከባሕል ጋር ያለን ትስስር ትልቅ በመሆኑ በጉልህ ይታያል። በሚዲያዎች በኩል ያለውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን የሚዲያ ፎረሞችን ለግንዛቤ ማስጨበጫነት በአግባቡ ይጠቀምበታል።
በተለይም ከሴቶች ውክልና አንጻር በሂደት የሰውን አመለካከት የመቀየር ሥራ እንሠራለን። ይህ ማለት ግን ባሕልን መስበር አይደለም፤ ሴቶች ተንከባካቢ ሆነው መሳላቸው ብዙ ጊዜ መጥፎ አይደለም። ነገር ግን ሴቶች የተንከባካቢነት ባህሪ ስላላቸው ብቻ ወደ አመራርነት መምጣት የለባቸውም የሚለው እሳቤ ግን መቀረፍ አለበት። ተንከባካቢ መሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ሊኖር የሚገባ ስብዕና ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጾታዊ ትንኮሳ እና የህጻናትን ጥቃት በመከላከል ረገድ ምን ዓይነት ተጨባጭ ሥራዎችን ሰርቷል?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- የህጻናትን ጥቃት ለመከላከል በዚህ ዓመት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የህጻናት የመረጃ አያያዝ ዲጂታል ሲስተምን ይፋ አድርገናል። በስድስት ክልሎች ላይ እስከ ወረዳ ድረስ ኬዞችን በመመዝገብ ኦንላይን ላይ መመልከት የሚቻልባቸው ናቸው። ሲስተሙ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የህጻናትን ቁጥር፣ ኬዛቸው ምን እንደሆነ እና ከየት አካባቢ እንደሆኑ እና ምን ዓይነት መፍትሔ እንደተሰጣቸው ማየት የሚቻልበት ነው። በተዋረድ ባሉን ቢሮዎች መፍትሔ ያልተሰጣቸው ከሆኑ ደግሞ አካባቢውን፣ ምክንያቱን እንዲሁም ስጋቶችን ማየት የሚቻልበት የዲጂታል ሲስተም ነው። በዚህም በቀላሉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለመቆጣጠር ያስችለናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማህበራት /ኤን.ጂ.ኦ / የሚሠሩት ህጻናት ላይ ነው። ህጻናትን በተለያየ መልኩ እንደግፋለን በሚል የተቋቋሙ ተቋማትን እንፈትሻለን። በእነዚህ ማህበራት የሚገኙ ህጻናት ለሚያስፈልጋቸው የማህበራዊ ድጋፍ ምን ዓይነት እገዛ እንደተደረገላቸው እና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ፤ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በዚህ የዲጂታል ሥርዓት እንዲመዘገቡ ይደረጋል። ከዚህ ውጪ ከሆነ እና የመረጃ ሥርዓቱን የማይጠቀሙ ከሆነ ህጻናቱን እንዳልደገፉ እንደሚቆጠር በአጽንኦት አስታውቀናቸዋል።
አሁን ላይ የአጠቃቀም ሁኔታውን በተመለከተ ግንዛቤ የመስጠት ሥራ በየወረዳው ያሉ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ልክ እንደሌላው ሴክተር በማሰማራት መረጃ የመሰብሰብ ሥራ እንዲሠሩ እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- መሥሪያ ቤቱ የህጻናትን መብት ከማረጋገጥ እና ህጻናቱ ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ከማድረግ አኳያ ምን እየሠራ ነው?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ከህጻናት መብት ጋር ተያይዞ በዘንድሮ ዓመት ከ66ሺ በላይ ህጻናት አባትነትን በማረጋገጥ የልደት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። 6 ሕፃናት በሕግ አባታቸውን እንዲያውቁ በማድረግ አባታቸውን የማወቅ መብታቸው ተረጋግጧል፡፡ 732 የሚሆኑ ህጻናት ለጉልበት ሥራ ሲዘዋወሩ አግኝተን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ ችለናል። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የተሠረቁ ወዴት እንደሚሄዱና ቤተሰቦቻቸውም የት እንዳሉ የማያውቁ ህጻናት ናቸው።
”የህጻናት ድምጽ ሊሰማ ይገባል” የሚልም አቋም እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አለን። ህጻናት እኛ ያልነው ብቻ የሚደረግላቸው እና የኛ ሃሳብ ማስፈጸሚያ ሊሆኑ አይገባም። ከዚህ አንጻር ዲሞክራሲ እና የጥላቻ ንግግርን መጸየፍ እንዲማሩ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጸናል። ለዚህም የህጻናት ፓርላማ አቋቁመናል። የሁለት ዓመት የማብቂያ ጊዜው ስለደረሰ የሀገር አቀፍ ምርጫ ቦርድ በተገኘበት የምርጫ ሥራውን አከናውነናል። ባለፉት ሁለት ዓመት ሲሰሩ የነበሩ ህጻናትም አዲስ ለተመረጡ ህጻናት ሥራውን አስረክበዋል። የህጻናት ፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ለዋናው ፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ በየጊዜው እየተገናኙ የሠሩትን ያሳውቋቸዋል።
የበጎ ፈቃድ ሥራንም በልጅነታቸው እንዲለማመዱ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። ደሃና ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን የመደገፍ ሥራም ሠርተናል። ህጻናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ እና ቀድመን ከጥቃት የመከላከል ሥራም እየሠራን ነው። ከዚህ አንጻር የማህበረሰብ የመደጋገፍ ጥምረት ፕሮግራምን በሰፊው በማንቀሳቀስ በዚህ ዓመት ከ3ሺ9መቶ በላይ ህጻናትን ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ ተችሏል። በተቋማት የአንድ በመቶ ድጋፍ ሁሉም መንግሥታዊ የሆኑ ተቋማት 5ሺ580 የሚሆኑ የሚያሳድጓቸው ህጻናት አሏቸው። በዚህም ህጻናቱን በትምህርታቸው እና በኑሯቸው መደገፍ ተችሏል። በተጨማሪም ድጋፉ ህጻናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል።
በአደራ ቤተሰብ ፕሮግራምም ወደ386 የሚሆኑ ህጻናት ድጋፍ አግኝተዋል። በቀጥተኛ ጉዲፈቻ እንዲሁ 294 የሚሆኑ ህጻናት አሳዳጊ እንዲያገኙ ተደርጓል። በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ አማራጮች ብቻ ከ10ሺ አንድ መቶ በላይ ህጻናት በዘንድሮው ሩብ ዓመት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- የወጣቶችን ሁለንተናዊ ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ተቋሙ ምን ዓይነት ሥራዎችን እየሠራ ነው?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ወጣቶች የመደራጀት መብታቸው እንዲጎለብት የማድረግ፤ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት እና በኢኮኖሚ ራሳቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉባቸውን ሥራዎችን እየሠራን ነው። በዚህም ከ165ሺ አምስት መቶ በላይ ወጣቶች እንዲደራጁ እና ኢኮኖሚው ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማድረግ ተችሏል።
ወጣቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣትም ሥራዎችን እንሠራለን። ወደ977 የሚሆኑ ወጣቶችንም በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በተለያዩ እርከኖች አመራር እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህም ወጣቶች የነገ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ የዛሬም መሪዎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በባለፈው የክረምት ወራትም 22 ሚሊየን 493 ሺ የሚሆኑ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሥራ ተሳታፊ ማድረግ ተችሏል። በዚህም በ13 ዘርፍ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ ማትረፍ ተችሏል። ይህ የዋጋ ግምት የተሰላው ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በነበረው ዋጋ ነው። በአሁኑ ዋጋ ቢሠራ ተመኑ ከዚህ በላይ ይሆናል።
ከ540 ሺ በላይ ለሆኑ ወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። ከዚህ ውስጥም ወደ 254ሺ የሚሆኑ ወጣቶች የብድር አገልግሎት እንዲገኙ ተደርጓል። ይሄ ሰፊ ቁጥር ቢሆንም ከዚህ በላይ ለመሥራት አቅደናል።
ወጣቶችም ወደ ሱስ እንዲገቡ እና ብልሹ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው የሚያደርጉ የቁማር ቤቶችን (ቤቲንግ) ለመከላከል ሁሉንም የጸጥታ አካላት እና የሚመለከታቸውን ሴክተር መሥሪያ ቤቶች (ትምህርት ሚኒስቴር፤ ጤና ሚኒስቴር) አካተን ግብረ ኃይል አቋቁመናል። ግብረ ኃይሉ ከሚያዝያ እስከ ሚያዝያ የሚባል የድርጊት መርሃ-ግብር አለው። በዛም ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚገኙ አዋኪ ነገሮችን ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የማስወገድ ሥራ ይሠራል። በየክልሉ ያሉ አመራሮችም የቤቲንግ ስፖርት ማዝወተሪያ ቦታዎችን የማስወገድ ሥራ ይሠራሉ። በሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ደግሞ በሱስ የተጠቁ ወጣቶችን እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ያለው የሱስ ማገገሚያ ተቋማት ቁጥሩ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ያንን ከማሳደግ አኳያ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ምን እየተሠራ ነው?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- በሀገራችን ያለው አንድ የሱስ ማገገሚያ ተቋም ብቻ ነው። የሱስ ማገገሚያ መገንባት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። አንዳንዶቹ መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ አይገኙም። በግለሰብ ደረጃ ራሱ ጥቂት ማገገሚያ ብቻ ነው ያለው። በሌላው ሀገር ያለው አካሄድ መንግሥት በግለሰቦች የሚገነቡ የማገገሚያ ማዕከላት እንዲኖሩ እገዛ ያደርጋል። እኛ እንደ ሀገር የምንሠራው ቅድመ የመከላከል ሥራ ነው። ለዚህም 3ሺ የሚሆኑ የስብዕና ግንባታ ማዕከላት አሉን።
አዲስ ዘመን፡- በጠለፋ ፣ አስገድዶ መድፈር እና ግርዛት ዙሪያ ማህበረሰቡ አሁን ላይ ያለው ግንዛቤ ምን ላይ ነው ብለው ያምናሉ?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- አሁን ከበፊቱ የተሻሻለ ነው ማለት እንችላለን። ዓለም አቀፍ ተቋማት የራሳቸውን ጥናት አካሂደው በ2024 ኢትዮጵያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሠራችው ሥራ ከሌሎች ሀገራት የተሻለ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የሥነ-ሕዝብ የእውቅና ሽልማት እንድታገኝ ተደርጓል። ይህ ማለት ችግሩ ተቀርፏል ማለት ግን አይደለም። አሁንም የሴት ልጅ ግርዛትን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የሚያደርጉ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ።
በእያንዳንዱ ቀበሌ ከሴት ልጅ ግርዛት ነፃ ሲሆን አረንጓዴ ባንዲራ እንዲውለበለብ እናደርጋለን። በዚህም ባንዲራው የተውለበለበባቸው ከተሞች ቁጥራቸው በርካታ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደ አዲስ የመጀመር አዝማሚያ አለ። ይህንን ለመከላከል የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የሃይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች እንዲያውቁት እና በዚህ ተግባር ይሳተፉ የነበሩት ሴቶች የልማት ሕብረት ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየሠራን ነው። የሴቶች ልማት ህብረት አንዱና ትልቁ ሥራው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሲከሰቱ ማሳወቅ እና እንዳይከሰት የማስተማር ሥራ ከመዋቅራችን ጋር በመሆን የምንሠራበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- ትልቁ ለሀገር ልማት የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው። የተከሰቱ ግጭቶች መቆም እንዲችሉ የሁላችንም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል። ሰላም ከሌለ ብዙ ማህበራዊ ችግሮች ይፈጠራሉ። ሰላም ሲኖር ግን ሁሉም ወደ ሥራ ያተኩራል ፤ ማህበራዊ ችግሮችም ይቀረፋሉ።
የሴቶች ጥቃት እና ለችግር የተጋለጡ ሴቶች ችግርን መፍታት የሚጀምረው አዕምሯችን ውስጥ ነው። እኔ እየበላሁ ሌላው ወገኔ መቸገር የለበትም የሚል አስተሳሰብ ሊኖረን የሚችለው ሰላማዊ የሆነ ጤናማ አዕምሮ ሲኖረን ነው። መንግሥት ምን አደረገ ሳይሆን እኔ ለራሴ እና ጎኔ ላለው ሰው ሰላም ምን አስተዋጽኦ አደረግሁ? ብለን የምንሠራ እንዲሆን እመኛለሁ። በኛ በኩል ሴቶች ለሰላም ፣ ወጣቶች ለሰላም የሚሉ እንቅስቃሴዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን።
ሌላኛው የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት መቻል አለብን። ሁልጊዜ ከውጭ ርዳታ የምንጠብቅ መሆን የለብንም፤ ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገር ይኖርብናል። ይህንንም ማድረግ የምንችለው የሥራ ባሕላችንን ማሻሻል ስንችል ነው። በመሆኑም ዛሬ ላይ የሚሰጠን ጥቂት ነገር እጃችንን የሚሸብብ መሆን የለበትም። ያንን እንደመሰላል ተጠቅመን ነገ ለሌላ መትረፍ የምንችልበት መሆን ይገባል።
በተለይም ለወጣቶች የሥራ ባሕልን ማዳበር፣ ሥራን አለመናቅ እና ከትንሽ ተነስቶ በራስ ላብ የሚገኝ ውጤትን ማድነቅ ይገባቸዋል። በአቋራጭ መክበርን ትተው ራሳቸውን ከአልባሌ ሁኔታዎች በመጠበቅ ወጣትነታቸውን መጠቀሚያ ሳይሆን ራሳቸው የሚጠቀሙበት፤ የሚያከብሩት እንዲሆን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። መንግሥት ብቻ ሁሉንም ሥራ ይሥራ ከተባለ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ይሆናል። የግል ሴክተሮች እና የልማት ድርጅቶች አብሮ በጋራ በቅንጅት ለአንድ አላማ መሥራት አለባቸው ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
ኤርጎጌ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም