‹‹ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ሥርዓት የማስያዝ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ የሚላላ አይሆንም›› -አቶ ያብባል አዲስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ ደህንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ እና ተስማሚ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል የተቋቋመ ነው::

አዲስ አበባ የሀገሪቱ ከዛም አልፎ የአፍሪካ ርዕሰ መዲና፣ ሶስተኛዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከተማ ነች። በየጊዜው እየሰፋች ያለች፣ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ መኖሪያ ነች። ይህንን ተከትሎም ከፍ ያለ እና እያደገ የሚሄድ የትራንስፖርት አገልግሎት የምትፈልግ ከተማ ናት። ይህም የከተማዋን ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ አማራጮች ተግባራዊ ተደርገዋል፣ ከችግሩ ስፋት እና ውስብስብነት አኳያ ግን ችግሩ አሁንም ከተማዋን እየተፈታተነ ይገኛል።

በመዲናዋ ከትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ሕግ እና ሥርዓትን በአግባቡ ካለመተግበር ጋር በተያያዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተፈተነች ነው። ችግሩን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችም የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም።

እኛም ከተማዋ በትራንስፖርት ዙሪያ እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮች፣ ችግሮቹን ለመሻገር እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች እና እያስገኙ ስላለው ውጤት የአስተዳደሩን የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስን አነጋግረን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል::

አዲስ ዘመን፡- የከተማዋን የትራንስፖርት ችግሮች ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ያብባል፡- የትራንስፖርት ቢሮው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አቅዶ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሥራ ክንውን ወቅት ያጋጠሙ መሠረታዊ ችግሮችን በጥናት በመለየት፣ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ዕቅድ አውጥቶ ተግብሯል::

በጥናቱም የከተማ አስተዳደሩ ያለውን የብዙሃን ትራንስፖርት በብቃት የመጠቀም ችግር እንዳለበት፤ የብዙሃን ትራንስፖርት የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም መኖሩን፤ የትራፊክ መጨናነቅ ከፍተኛ መሆኑ በአጠቃላይ ለትራንስፖርት አገልግሎቱ እንቅፋት መሆኑ በዝርዝር ተቀምጧል:: ከዚህ በተጨማሪ ዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉበት ተመልክቷል። ችግሮቹን በ2017 በጀት ዓመት በመሠረታዊነት ማቃለል እንደሚገባ በመገንዘብ ችግሮቹን ሊፈታ የሚችል ዕቅድ አዘጋጅተን ወደ ሥራ ገብተናል::

ያለውን የብዙሃን ትራንስፖርት አቅም በተሟላ ሁኔታ ከመጠቀም አኳያ፣ ለከተማችን አገልግሎት የሚያቀርበው የከተማ አውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትን ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ተቋሙን በአደረጃጀት፤ በአሠራር፤ በመመሪያ፤ በሰው ኃይል፤ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ራሱን እንዲያሻሽል የሪፎርም ሥራ እየተሠራ ነው::

ከማሻሻያ ሥራው ጎን ለጎን ያሉትን አውቶብሶች ወደ ስምሪት በማስገባት አገልግሎቱን እንዲያሻሽል የሚያደርግ ሥራ ተሠርቷል:: በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ድርጅቱ ካሉት አውቶብሶች በተጨማሪ 149 አውቶብሶችን ወደ ስምሪት እንዲገቡ አድርጓል:: በቀን 900 ሺ በላይ ሕዝብ እንዲያጓጉዝ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል ተደርጓል::

የከተማ አስተዳደሩ የትራስፖርት ዘርፉን ለማሻሻል 80 አውቶብሶቹ ያሉት አደይ አበባ የሚባል የግል ትራንስፖርት ድርጅት ወደ አገልግሎት እንዲገባ ተደርጓል:: በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የነበረበትን የመለዋወጫ እቃ እጥረት ችግር በመፍታት ባለፈው ዓመት በየቀኑ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ባቡሮች ቁጥር ከ13 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ 16 ማሳደግ ተችሏል:: ይህም ለዘርፉ አገልግሎት መሻሻል ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል::

አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች በተለይ ወደ ሥራ መግቢያና ከሥራ መውጫ ሰዓት ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ይስተዋላል፤ ቢሮው ችግሩን ለምን መፍታት አልቻለም?

አቶ ያብባል፡- ከብዙሃን ትራንስፖርት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በጊዚያዊነት ለማቃለል ከፌዴራል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጊዜያዊነት መናኸሪያ ላይ የሚገኙ ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች ማታ ማታ ከፍተኛ የሆነውን ሰልፍ እንዲያነሱ እየተደረገ ነው:: በዚህም በየቀኑ ከ120 እስከ 150 የሚደርሱ ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች በተመረጡ አካባቢዎች የሚታየውን ሰልፍ እንዲያነሱ ተደርጓል::

በሌላ በኩል የሕዝብ ትራንስፖርት የሚባሉት ኮድ አንድና ኮድ ሶስት ታክሲዎች ከታሪፍ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቅሬታ ነበረባቸው:: የነዳጅ ድጎማ መነሳቱ፤ ቀድሞ ከተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በኋላ አምስት ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ለውጥ መደረጉ እና ይህን ተከትሎ ታሪፉ ያልተሻሻለ መሆኑ ለቅሬታው ምንጭ ሆኗል:: ከዚህ የተነሳም ጠዋትና ማታ ከስምሪት ሲደበቁ ነበር:: የከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን በዝርዝር ገምግሞ የሕዝብ ትራስፖርትን ከማሻሻል እና አቅርቦቱን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ በመሆኑ ታሪፋቸው እንዲሻሻል አድርጓል::

በሩብ ዓመቱ እነዚህንና መሰል ርምጃዎችን በመውሰዳችን በየቀኑ ለማጓጓዝ ያቀድነው 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕዝብ ሲሆን በተደረገው የማሻሻያ ሥራ 3 ነጥብ 46 ሚሊዮን ሕዝብ በየቀኑ ትራንስፖርት እንዲያገኝ ተደርጓል:: በዚህም የመጀመሪያውን ችግር ከመፍታት አኳያ በጣም መሠረታዊ ለውጥ አምጥተናል::

ሌላው በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል የነበረውን ልዩነት የማጥበብ ሥራ መሥራት ነው። የከተማ አስተዳደሩ ቀደም ብሎ ግዥ የፈጸመባቸው መቶ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ወደብ ላይ ደርሰዋል:: ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሶስት አራት ወር ውስጥ ተገጣጥመው ወደ አገልግሎት የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል::

መንግሥት በነደፈው የኮሪደር ልማት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ለትራንስፖርት ዘርፉ ነው:: በዚህም ቅድሚያ የሚሰጠው የእግረኛ እና የብስክሌት ትራንስፖርት ነው:: ይህ ለከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት መቀላጠፍ ከፍተኛ ሚና አለው:: ምቹ የእግረኛ መንገድ ሲኖር ቅርብ ሰፈር የሚጓዙ ሰዎች በእግራቸው ወደ ቤታቸው ይጓዛሉ:: ብስክሌት ያላቸውም በተመሳሳይ በተሠራላቸው የብስክሌት መንገድ ይጠቀማሉ::

የታክሲና የአውቶብስ ተርሚናሎች፤ የመኪና ፓርኪግ መሠረታቸው የትራፊክ መጨናነቁ ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንዲመጣ አድርጓል:: እንደ አደይ አበባ የመሳሰሉ አደባባዮች እየፈረሱ ወደ ትራፊክ ምልክት እንዲቀየሩ ተደርጓል:: ዲያስፖራ፤ ቀበና፤ ጀርመን አደባባይ፤ ሳሊህተ ምህረትና መሰል አደባባዮች ተጠቃሽ ናቸው::

እነዚህ መሠረተ ልማቶች በመሠራታቸው አገልግሎቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል:: ከዚህ በተጨማሪም የትራስፖርት ቢሮ ተቆጣጣሪዎች፤ የትራፊክ ማኔጅመንት፤ በትራፊክ ፖሊስ ተቆጣጣሪዎች የአዲስ አበባ ከተማን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ሰፊ ሥራ እየሠሩ ነው:: በአንዳንድ መንገዶች ጠዋትና ማታ መኪና ማቆም ተከልክሏል:: ይህንና መሰል ርምጃዎች በመወሰዳቸው በሩብ ዓመቱ የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነስ ረገድ የሚታይ ሥራ ተሠርቷል::

አዲስ ዘመን፡- በትራንስፖርት ታሪፍ በሚታዩ ጭማሪዎች ተገልጋዩ ቅሬታ እያነሳ ነው፣ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ያብባል፡- ታሪፍ በዝቷል የሚል ሃሳብ ይነሳል:: ነገር ግን ታሪፍ የሚጨምረው አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ተከትሎ ነው:: የነዳጅ ድጎማ ሲነሳ እና ዋጋ ማሻሻያ ሲደረግ ታሪፉ አብሮ ይሻሻላል:: ትልቁ የትራንስፖርት ወጪ ነዳጅ በመሆኑ የሳንቲም ጭማሪ በተደረገ ቁጥር የታሪፍ ጭማሪ መደረጉ የማይቀር ነው:: ታሪፉ የበዛ መስሎ የታየው በተከታታይ አምስት ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ታሪፍ አለመሻሻሉ ነው።

በየጊዜው ታሪፉ እየተሻሻለ ቢመጣ ኖሮ ጭማሪው ዝቅተኛ ይሆን ነበር:: ተከማችቶ አንድ ጊዜ ስለተተገበረ የበዛ ይመስላል:: ነገር ግን የታሪፍ አጨማመር የራሱ የሆነ ቀመር አለው:: አስተዳደራዊ እና የመለዋወጫ እቃዎች ወጪዎች እና ሌሎች ጉዳዮች ታይተው ዓለም አቀፋዊ የጭማሪ ስታንዳርድን ተከትሎ የተደረገ ነው:: የትራንስፖርት ታሪፉ በኪሎ ሜትር ሲሆን አጭር፤ መካከለኛ እና ረጅም ኪሎ ሜትሮችን ታሳቢ ተደርጎ ነው:: ጭማሪው በመገናኛ ብዙሃን በዌብሳይት እንዲጫንና እንዲደርስ እንዲሁም አገልግሎት በሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ በሚታይ ቦታ እንዲለጠፍ ተደርጓል::

እያንዳንዱ የታክሲ ተጠቃሚ የታሪፉን ዋጋ እንዲያውቅ መነሻ እና መድረሻው መሠረት ተደርጎ ታሪፍ በየታክሲው ተቀምጧል:: የቢሮው ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ትራፊክ ፖሊስ እና የትራፊክ ማኔጅመንት ተቆጣጣሪዎች ከታሪፍ ውጭ እንዳይጭኑ የቁጥጥር ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል::

በየቀኑም የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ነው:: ነገር ግን በተግባር ስናየው ሁሉም አካባቢ ጉዳዩን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ጉድለቶች አሉ:: አሁንም ቢሆን ከታሪፍ በላይ ተገልጋዩን የሚያስከፍሉ ታክሲዎች፤ ከታሪፍ በላይ እንዲከፈል ግፊት የሚያደርጉ የተራ አስከባሪዎች እንዳሉ ገምግመናል:: ችግሩን የምንፈታው በየጊዜው የተገልጋዩን ግንዛቤ በማሳደግ ከታሪፍ በላይ አልከፍልም ብሎ ራሱ መብቱን እንዲያስከብር የማድረግ ሥራ በመሥራት ነው::

አዲስ ዘመን፡- ዘርፉ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት ነው፤ ችግሩን ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ያብባል፡– በዘርፉ ላይ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከፍተኛ ነው:: ከሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ጋር፤ ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ አገልግሎት ተያይዞ፤ ከተራ አስከባሪዎች፤ ከትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ጋር በዘርፉ የሚነሱ ከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ:: ቢሮው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጀንዳው በዘርፉ ያሉ ተቋማት በጋራ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እቅድ አቅደው እንዲሠሩ ተደርጓል::

በሩብ ዓመቱ መሠረታዊ የሚባሉ መሻሻሎች እንዳሉ ታይቷል:: የተቋሙ ዋናው የመልካም አስተዳደር ችግር ጠዋትና ማታ ሕዝባችን በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት አለማግኘት ነው:: ችግሩን በመፍታት በኩል በመሠረታዊነት ለውጥ አምጥተናል:: ነገር ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ በየጊዜው እየጨመረ ስለሚሄድ መሻሻሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግም ገና ብዙ መሥራት እንዳለብን አይተናል::

አዲስ ዘመን፡- አውቶብሶችም ሆኑ ታክሲዎች በተገቢው መንገድ አገልግሎት ሲሰጡ አይታይም:: ለዚህም የቁጥጥር ማነስን እንደ ምክንያት የሚያነሱ አሉ፤ በእናንተ በኩል የችግሩ ምንጭ ምንድነው ትላላችሁ?

አቶ ያብባል፡- ከሕዝብ ትራንስፖርት ጋር ተያይዞ የእኛ ተቆጣጣሪዎች ምሽት ላይ እና በበዓል ቀን ቅዳሜና እሁድ የማይገቡበት ሁኔታ ነበር:: እነሱ በማይኖሩበት ጊዜ ቁጥጥሩ ስለሚላላ እንደ ታክሲ፤ ሀይገር፤ ቅጥቅጥ የሚባሉ የትራስፖርት ዓይነቶች ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉበት፤ ከመስመር ውጭ የሚሠሩበት እና ሥራ የሚያቆሙበት ሁኔታ ነበር:: ቢሮው ይህን ለማስተካከል በሁሉም መስመሮች ባይሆንም ማታ ማታ እና ቅዳሜ እና እሁድ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እንዲኖሩ አድርገናል::

ጠዋትና ማታ ላይ የትራፊክ ፍሰቱ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ አንዳንድ ታክሲዎች ወደ ስምሪት የማይገቡበት ሁኔታ ነበር:: ችግሩን ለመፍታት ቁጥጥሩን ለማጥበቅ የቁጥጥር ሥራውን በማጥበቅ እንዲሁም በመግባባት ችግሩን ለመፍታት እየተሞከረ ነው:: ከታክሲ ማህበራትና ባለንብረቶች ጋር ተግባብቶ ለመሥራት ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በዚህም የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ተደርጓል::

እነሱ በሚፈጥሩት ውስን ችግር ሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግር ከፍተኛ ነው:: በመግባባትና በመነጋገር ችግሩን ለማሻሻል ጥረት የተደረገ ቢሆንም ሁሉም ችግር በመግባባት ስለማይፈታ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችን ቁጥጥር የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል::

በዚህም በየቀኑ ከ400 በላይ ታክሲዎች በተለያየ መንገድ ይቀጣሉ:: የታክሲ ባለንብረቶች አደረጃጀት ችግር አለበት:: በቀጣይ አደረጃጀቱን በማሻሻል አገልግሎቱ በካምፓኒ የሚሰጥ እንዲሆን ይሠራል:: አሁን ባለው ሁኔታ ግን ክትትልና ቁጥጥሩን አጠናክረን ለማሻሻል ጥረት እያደረግን ነው::

አዲስ ዘመን፡- የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ምቾት እና ንጽህና የጎደለው ስለመሆኑ ተገልጋዮች ቅሬታ ያነሱበታል፣ ቢሮው ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ያብባል፡– የከተማ አውቶብስ ድርጅት በአሠራር፤ በአደረጃጀት፤ በሰው ኃይል፤ በቴክኖሎጂ እና በንጽህና ሪፎርም እየተደረገ ነው:: የከተማዋን ትልቁን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው የከተማ አውቶብስ ድርጅት ነው:: በዚህ በጀት ዓመት በሁሉም መንገድ መሠረታዊ ለውጥ የምናመጣበት ነው::

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመተግበር ሥራ የተጀመረ ሲሆን ሲጠናቀቅ ድርጅቱ የሚሰጠውን አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳድገዋል የሚል እምነት አለን::

እንደሚታወቀው በብዙሃን ትራንስፖርት ላይ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው:: ይህን ለማሳደግ እየሠራን ነው:: አሁን ላይ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ኦፕሬተሮች ናቸው:: ይህም ሆኖ ብዛት ያላቸው የግል ዘርፉ ኦፕሬተሮች መፈጠር አለባቸው:: ከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶችንም እያነጋገረ ነው፤ ከተሳካለት 100 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ አውቶበሶች ይዞ የሚሠራ የግል ባለሀብት ወደ ሥራ እንዲገባ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው:: በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የማበረታቻ ሥርዓት እየተጠናም ነው::

አዲስ ዘመን፡- የቢሮው ተራ ተቆጣጣሪዎች ባሉበት በተራ አስከባሪ ስም የተደራጁ ግለሰቦች የተራ በሚል የሚያስከፍሉትን ገንዘብ ቢሮው ያውቃቸዋል? ከአሽከርካሪዎች የሚቀበሉት የብር መጠን ከፍ ለማድረግ ታክሲዎች ትርፍ እንዲጭኑ፤ ከታሪፍ በላይ እንዲያስከፍሉ ሲገፋፏቸው ይስተዋላል፤ እነዚህንና መሰል ችግሮች ለማስቆም ቢሮው ምን እየሠራ ነው?

አቶ ያብባል፡- ልክ ነው:: አንዳንድ ሕገ ወጥ ተራ አስከባሪዎች አሉ:: ከሕገ ወጥ አሽከርካሪዎች ጋር ሆነው ተጨማሪ ክፍያ የሚያስከፍሉ፤ መስመር የሚያስቀይሩ እና ከአቅም በላይ እንዲጫን የሚያደርጉ አሉ:: በተለይ የቢሮው ስምሪት ተቆጣጣሪዎች በሌሉበት ጊዜ ይህ ልምምድ ሰፋ ይላል:: ተራ አስከባሪ ያስፈለገው ሰልፍ ላይ የመንገደኛውን ደህንነት እንዲጠበቅ እና ታክሲዎች ሥርዓት እንዲይዙ ነው:: አሁን ላይ የእርምት ርምጃዎችን በመውሰድ መሻሻሎች አሉ:: በሁሉም አካባቢ ተራው እስከሚደርሰው ድረስ የሚፈጠር ትርምስ የለም፤ ሥርዓት ይዞ፤ ተሰልፎ ትራንስፖርት እየተገለገለ ነው:: አሽከርካሪዎችም ሥርዓት ይዘው በተራቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው::

አገልግሎት ሰጭዎች የመነሻውን ታሪፍ መሠረት አድርገው ከመነሻ እስከ መድረሻ የታሪፉን መሠረት ያደረገ ሕጋዊ ክፍያ እያገኙ ነው:: ነገር ግን ከዚህ ሕጋዊ አሠራር ውጭ ከታሪፍ በላይ እንዲከፈል፤ ከመቀመጫው በላይ ትርፍ እንዲጫንና መስመር እንዲቆራረጥ የሚያደርጉ ተራ አስከባሪዎች አሉ:: በዚህ ላይ ጥብቅ የሆነ ርምጃ እየወሰድን ነው:: በቀጣይ የተራ አስከባሪዎችን የአሠራርና የአደረጃጀት ከመሠረቱ ለማሻሻል እና ከንክኪ ነፃ ለማድረግ አሠራር እያዘጋጀን ነው:: አሠራሩ በሚመለከተው አካል ሲጸድቅ ተግባራዊ ይሆናል::

አጠቃላይ የትራንስፖርቱን ዘርፍ ምቹ ከማድረግ አኳያ ብዙ ጉድለት አለ:: በተለይ ኮድ አንድ የሚባሉ ታክሲዎች በጣም ለተሳፋሪ ምቹ ያልሆኑ አሮጌ ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪ በተደጋጋሚ አገልግሎት ላይ እያሉ የሚቆሙ፤ ጋራዥ የሚገቡ፤ መንገድ ላይ የሚገፉ፤ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀታቸው ከፍተኛ ነው:: መቀመጫቸው የማይመች ሲሆን ቴክኖሎጂ ለመቀበል አስቸጋሪ ናቸው::

የከተማ አስተዳደሩ የትራስፖርት ዘርፉ አቅርቦት ችግር ስላለበት እንጂ ተሽከርካሪዎቹ ከአገልግሎት ውጭ መሆን ነበረባቸው:: ባለቤቶችም ታክሲዎቻቸውን ወደ አዲስ የመቀየር ሥራ መሥራት አለባቸው:: ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሥራዎች ተጀምረዋል:: የታክሲ ማህበራትና ባለንብረቶች አሮጌ ታክሲዎችን ከመንግሥት ብድር እና የታክስ ቀረጥ ነጻ ድጋፍ ካገኙ ወደ አዲስ መቀየር አለባቸው የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል:: ስለዚህ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግላቸው ከሆነ በአጭር ጊዜ ዘመናዊ ታክሲ ይዘው አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ይኖራል::

አዲስ ዘመን፡- የቢሮው የስምሪት ተቆጣጣሪዎች በተለይም እሁድና ቅዳሜ ባለመሥራታቸው በአንድ በኩል ሰዎችን የሚጠራ ታክሲ ፤ በሌላ በኩል ታክሲ የሚጠባበቅ ረጃጅም የተሳፋሪ ሰልፍ ይታያል:: ይህን ዓይነት ችግር የምትፈቱት መቼ ነው?

አቶ ያብባል፡- የሕዝብ የትራንስፖርት ፍሰቱ በየጊዜው የሚቀያየር ስለሆነ ስምሪቱ በየጊዜው ይከለሳል:: ለምሳሌ ፒያሳ አካባቢ የነበረው ነዋሪ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውሯል:: ስለዚህ በሄደበት አካባቢ የትራንስፖርት ፍላጎት ይጨምራል:: ቀድሞ ከተነሳበት አካባቢ ላይ ደግሞ የትራስፖርት ፍላጎቱ ይቀንሳል:: በዚህ ሳቢያ በየሩብ ዓመቱ የታክሲዎችና የአውቶብሶች የስምሪት ክለሳ ይደረጋል:: የተሽከርካሪ የአቅርቦት መጠን የተጠቃሚውን ብዛት መሠረት ተደርጎ ለማጣጣም ጥረት ይደረጋል::

አንዳንድ ጊዜ የሳሳ አንዳንድ ጊዜ የበዛ ይመስላል፤ ነገር ግን ስምሪቱ በጥናት ተመስርቶ የሚከናወን ነው:: የሕዝብ ክምችት የሚታይባቸው ላይ ችግሩን ለመፍታት በአውቶብስ አማካኝነት ጥረት እየተደረገ ነው:: አሁን ላይ የታክሲ አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የብዙሃን ትራንስፖርት የምንለው አገልግሎት ባለመስፋፋቱ ነው:: ችግሩን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ዋና ትኩረት የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ማስፋፋት ነው:: የሌሎች ሀገራት ተሞክሮም የሚያሳየው የታክሲ ትራንስፖርት ሳይሆን የሕዝብ ትራንስፖርት ነው:: በእኛ ሀገር ግን የአውቶብስ ትራንስፖርት፤ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት፤ የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት ገና ስላልተስፋፋ ታክሲ ላይ ጥገኛ ነን::

ከተማ አስተዳደሩ እየሠራ ያለው የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማሳደግ ነው። ብዙሃን ትራንስፖርት የታሪፍ፤ የስምሪት ጉዳይ አይነሳም:: የታክሲ አገልግሎትን ስንመለከት ግን ባለንብረቱ ቁርስ ሲባላ፤ ቤተእምነት ሲሄድ፤ ሲታመም እና መሰል ጉዳዮች ሲገጥመው ይቆማል:: ይህ ሁኔታ ባለበት ተቆጣጥሮ ለማሠራት ከፍተኛ የሆነ ፈተና ነው::

የቢሮው የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ባሉበት አካባቢ ቁጥጥር አለ:: ነገር ግን ሁሉም ቦታ ላይ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ማድረግ አይቻልም:: ቁጥጥር በሌለበት ቦታ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ ይታያል:: ችግሩን ለመቅረፍ በምንችለው ልክ የሰው ኃይል አሰማርተን እየተቆጣጠርን ነው::

የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ገና በሁሉም ቦታ ሳይሆን የማታ ሰልፍ ባለባቸው የተመረጡ ቦታዎች ላይ ብቻ እየሠሩ ነው:: በተመደቡበት ቦታ ላይ እስከ ምሽቱ ሁለት ሶስት ሰዓት ድረስ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ:: ሥራው የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም ተቆጣጣሪዎች ማታም ትርፍ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ቁጥጥሩን እንዲያጠናክሩ ተደርጓል::

አዲስ ዘመን፡- የታክሲና የራይድ ሹፌሮች ጥፋት ሳንሠራ እየተቀጣን ነው እያሉ ቅሬታ ያቀርባሉና ከትራፊክ ማኔጅመንት ጋር ያላችሁ ቅንጅታዊ አሠራር እስከምን ድረስ ነው?

አቶ ያብባል፡– በእኛ ሀገር ሁለት የተለያየ ሃሳብ አሉ:: ቁጥጥር ሲጠበቅ በዛ፤ ሲላላ ደግሞ ቁጥጥር የለም ይባላል:: ከዚህ የተነሳ “እንቀጣለን” የሚለው ሃሳብ በሚዛኑ ማየት ያስፈልጋል:: እንደ አዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ከሆነ ቁጥጥሩ ዝቅተኛ ነው:: ምክንያቱም አገልግሎቱን ለመከታተል የምንጠቀመው ቴክኖሎጂ የለም:: ቴክኖሎጂ በሚጠቀሙ ሀገሮች የትኛውም ተሽከርካሪ ከተፈቀደለት ቦታ ውጭ መቆም አይችልም::

እኛ ሀገር ግን ሁሉም አሽከርካሪ መንገድ ላይ ሰው ይጭናል፤ ያወርዳል፤ መኪና ያቆማል:: ይህ ልምምድ ትክክል አይደለም። በኮሪደር ልማቱ ችግሩን ለመፍታት ሥፍራዎች ተለይተው ተገንብተዋል፤ ከተፈቀደው ቦታ ውጭ መጫንና ማውረድ፤ መኪና ማቆም አይቻልም:: ለዚህም አሠራርና ሕግን በተከተለ መንገድ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል:: ስለሆነም እንደ ከዚህ ቀደሙ የትም ቦታ ላይ ማውረድና መጫን አይቻልም:: ሕግን በተከተለ አግባብ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው::

ለመጫኛና ማውረጃ ከተዘጋጀው ቦታዎች ውጭ መኪና አቁሞ ማውረድና መጫን ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ክልከላውን ተላልፎ የተገኘ አሽከርካሪ ይቀጣል፤ ቅጣቱም ጨምሯል:: በቀጣይም የትራንስፖርት አገልግሎቱን ሥርዓት የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ የሚላላ አይሆንም::

ታክሲዎችም ይህንን ማወቅ እና ሕጉን መጠበቅ አለባቸው:: የትራፊክ ማኔጅመንት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል:: ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር መሻሻሎች አሉት:: ቢሮውና የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን፤ የትራፊክ ማኔጅመንትና የትራፊክ ፖሊስ በቅንጅት እየሠሩ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ከተማዋን በማዘመን ሂደት ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ አብሮ እንዲዘምን ከማድረግ አኳያ በቀጣይ ምን አስባችኋል?

አቶ ያብባል፡- የከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ነው:: ዓላማው አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከተማ ማድረግ ነው:: ከዚህ አኳያ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የትራንስፖርት ዘርፉ ነው:: ከትራንስፖርት አገልግሎት አኳያ ቅድሚያ የሚሰጠው የእግረኛ ትራንስፖርት ነው:: በሌሎች ሀገራት ያለው ተሞክሮ የሚያሳየው ይህን ነው::

ሞተር አልባ ትራንስፖርት የሚበረታታ ነው:: ከዚህ አንጻር አዲስ አበባ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት መቶ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የእግረኛ መንገድ፤ ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ የብስክሌት መንገድ ገንብታለች:: ግንባታው የሞተር አልባ ትራንስፖርት በማበረታታት በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል:: እስካሁን ባለው ሁኔታ እግረኞች እየተበረታቱ ነው::

የብስክሌት ትራንስፖርትን ስንመለከት በግለሰቦች ደረጃ እንጂ በአማራጭ ትራንስፖርትነት ወደ ሥራ የተገባበት አይደለም። አሁን ላይ እንደ ከተማ የብስክሌት ኦፕሬተር አልተፈጠረም:: ለዚህም ቢሮው የብስክሌት ኦፕሬተሮችን መፍጠር የሚያስችል የአደረጃጀትና የአሠራር መመሪያ አዘጋጅቷል:: በቅርብ ጊዜ ውስጥ የአደረጃጀትና የአሠራር መመሪያ ተግባራዊ ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የብስክሌት መጋራት የትራንስፖርት ሥርዓት ተግባራዊ ይሆናል::

ይህ ሲሆን ከፍተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ኦፕሬተር ይኖራል:: ለምሳሌ ከሃያት ወደ ሲኤምሲ፤ ከሜክሲኮ ወደ ሳር ቤት፤ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ስንሄድ የምናየው የእግረኛ መንገድ ከፍተኛ መኪና ተጠቃሚ ነበር:: አሁን ላይ ግን ማህበረሰቡ መንገዱ በመሠራቱ አጫጭር መንገዶችን የሚጓዘው በእግሩ ነው:: ይህ ሲሆን የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ያሻሽላል::

በኮሪደር ልማቱ መንገዶች የመጫኛና የማውረጃ ቦታ እንዲኖራቸው ተደርጓል:: ይህም ትናንት ያልነበረ ዛሬ ላይ የሚታይ ነው:: ይህ የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ዘመናዊነትና ተወዳዳሪነት የሚያመጣ ነው:: ስለዚህ ከተፈቀደው ቦታ ውጭ መጫንና ማውረድ ስለማይቻል የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ሰላማዊና የተቀላጠፈ ይሆናል::

ከ185 በላይ የታክሲና የአውቶብስ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች በመጀመሪያው የኮሪደር ምዕራፍ ተሰርተዋል:: በተጨማሪም ከተማዋ ካሁን በፊት ደረጃቸውን የጠበቁ ተርሚናሎችና ፓርኪንጎች አልነበሩም:: በለውጡ መንግሥት የመስቀል አደባባይ፤ አንድነት ፓርክ፤ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የመሳሰሉ ፓርኪንጎች ተገንብተዋል::

በሁለተኛውም ምዕራፍ ኮሪደር ልማት በርካታ ፓርኪንጎች እየተገነቡ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: መውጫ መግቢያ ላይ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም፤ መኪና የሚያቆም ሰው ደግሞ ከገንዘብ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ በሞባይል ባንኪንግ እና በስማርት ስልክ አማካኝነት የሚከፈልበትን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራን ነው::

በመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ብቻ 32 ፓርኪንጎች ለምተዋል:: በህንጻ መልክ ጭምር በሁለተኛ መሠረት እና ከዚያ በላይ መሠረት ያላቸው ፓርኪንጎች እየተሠሩ ነው:: በሁለተኛው ኮሪደር ልማት ከ58 በላይ ፓርኪንጎች ይሠራሉ:: ይህ ለከተማችን ዘመናዊነትና ተወዳዳሪነት ብሎም ለተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት እና የትራፊክ ፍሰት መሻሻል ትልቅ ሚና ይኖረዋል::

በአንድ ጊዜ ከ600 በላይ አውቶብሶችና ታክሲዎች ማስተናገድ የሚችሉ ተርሚናሎች ተሠርተዋል:: በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮግራም ሰፋፊ የተርሚናል ግንባታ እቅዶች አሉ:: ዘመኑ የትራንስፖርት ዘመን ነው:: አዲስ አበባ የብስክሌት፤ የእግረኛ መንገድ፤ ተርሚናሎችን እያሰፋች በሄደች ቁጥር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት አገልግሎት ይሻሻላል::

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን ዘርፉን በቴክኖሎጂ መምራትን ይጠይቃል፤ ከዚህ አንጻር ቢሮው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግ አኳያ ምን ሠርቷል?

አቶ ያብባል፡– አጠቃላይ የትራንስፖርት ዘርፉ በቴክኖሎጂ መመራት አለበት:: በኮሪደር ልማቱ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ‹‹ITS›› የተባለ የኢተለጀንስ ትራንስፖርት ሥርዓት እንዲኖር የሚያግዝ ቴክኖሎጂ አልምቶ ወደ ሥራ ማስገባት ነው:: ቴክኖሎጂው በኮሪደር ልማቱ በቀኝና በግራ ልክ እንደ ቴሌ እንደ ውሃ መስመር አብሮ እየተዘረጋ ነው:: በተጨማሪም መገናኛ ላይ የትራፊክ ማኔጅመት ሲስተም የሚመራበት ህንጻ ተገንብቷል::

በአጠቃላይ የከተማዋን ትራንስፖርት ማኔጅመንት የምንቆጣጠርበት ማዕከል በህንጻ ደረጃ ተገንብቶ ተጠናቋል:: ከዚህ በኋላ የሚቀረው ቴክኖሎጂ ሲሆን ግዥ እየተካሄደ ነው:: ሲጠናቀቅ በየኮሪደር ከተዘረጋው አይቲኤስ ጋር እንዲገናኝ በማድረግ የትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ መቆጣጠር የሚቻልበት ሥርዓት ይፈጠራል:: ከቅርብ ጊዜ በኋላ የትራፊክ ማኔጅመንቱን በቴክኖሎጂ የምንቆጣጠርበት ሥርዓት ይኖራል::

አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ በኋላ ሲባል መቼ ማለት ነው?

አቶ ያብባል፤– ይህ የሚሆነው በሂደት ነው:: ለምሳሌ ሞዴል የሚሆን ሥራ ከእንግሊዝ ኢምባሲ ወደ ጎላጎል እየተሠራ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅ ከማዕከሉ ጋር በማገናኘት ኮሪደሩን በቴክኖሎጂ መቆጣጠር እንጀምራለን:: ይህ ምናልባትም በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ ይደረጋል:: ሥራው በዚህ መልኩ እየሰፋ አጠቃላይ የአዲስ አበባን ትራንስፖርት በቴክኖሎጂ የምንቆጣጠርበት ሥርዓት ይፈጠራል::

የባቡር፤ የአውቶብስ ትራንስፖርት በቴክኖሎጂ በመደገፍ የትኛው አውቶብስ በየትኛው መስመር ገብቷል፤ በስንት ኪሎ ሜትር እየሄደ ነው፤ በስንት ሰዓት እየተነሳ እንደሆነ እና ምን ያህል አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ ቢሮ ላይ ሆኖ በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው:: አሽከርካሪና ተሽከርካሪም የሚሰጡት አገልግሎት በመንጃ ፈቃድ እና መሰል ሥራዎች በቴክኖሎጂ በመደገፍ እየተሠራ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የቢሮው የስምሪት ተቆጣጣሪዎች በብር የስምሪት አቴንዳንስ ይሞላሉ የሚል ቅሬታ ይነሳልና ዘርፉን እንደሚመራ ተቋም ሠራተኞችን የምትከታተሉበት አግባብ ምን ይመስላል?

አቶ ያብባል፡- እውነት ለመናገር የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች በጣም እየደከሙ ነው:: 12 ሰዓት ወደ ሥራ ገብተው የሚሠሩት አምሽተው ነው:: የሚሠሩት ጸሐይ ላይ ብርድ፤ አቧራ ላይ እና ጭስ ላይ ነው:: የእኛ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ብቻ ሳይሆን የትራፊክ ማኔጅመንት ተቆጣጣሪዎች፤ የትራፊክ ፖሊስ ተቆጣጣሪዎች ለትራንስፖርት ዘርፉ ዋጋ እየከፈሉ ነው::

በአጠቃላይ በዘርፉ ለተሰማሩ አገልግሎት ሰጭዎች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል:: ነገር ግን ጉድለቶችም አሉ:: ጉድለቶችን እንዲያርሙ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ይሠራል:: ከዚህ አልፎ ብልሹ አሠራር ውስጥ የሚገባ የቢሮው ሠራተኛ ከማባበር ጀምሮ ጥብቅ ርምጃ ይወሰድበታል::

በከተማ አውቶብስ የሚባረረው ሠራተኛ ከትኬት ቆራጭ እስከ ሹፌር ቀላል አይደለም:: ይህም ከአገልግሎት አሰጣጥና ከብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ ማንንም አንታገስም:: ያም ሆኖ ግን ያልተደረሰባቸው አሉ:: በቀጣይ ከተጠቃሚ በሚመጣው ጥቆማና መረጃ መሠረት እያስተካከልን እንሄዳለን:: ለሥራው ውጤታማነት የተገልጋዩ ህብረተሰብ ጥቆማ በመስጠት መተባበር አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ምላሽ እና ማብራሪያ እናመሰግናለን::

አቶ ያብባል፡- እኔም አመሰግናለሁ::

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You