
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን፤ የግብርና ምርቶችን፣ ግብዓቶችንና አገልግሎቶችን እንዲሁም የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ኤክስቴንሽንና ሜካናይዜሽን ቁጥጥር ሥራዎችን በማከናወን የሚታወቅ የግብርና ቁጥጥር ተቋም ነው።
ባለሥልጣኑ በእፅዋት እና በእንስሳት ቁጥጥር ላይም ሥራውን እያጠናከረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋርም አብሮ የሚሠራ ነው። የግብርና ቁጥጥር ሥራዎችን በመተግበር፣ የግብርና ምርቶችን የሀገር ውስጥ እና የዓለም ገበያ ተደራሽነትና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለላቀ ሀገራዊ ጥቅምና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከትና ተልዕኮው አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።
ባለሥልጣኑ፣ በ2017 በጀት ዓመት አከናውናለሁ ብሎ ካቀዳቸው ተግባራት ምን ያህል ስኬታማ እየሆነ ነው? በተለይም የግብርና ምርት የቁጥጥር ሥርዓቱ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ሚናውስ እስከምን ድረስ ነው? በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ጋር ያደረገውን ቆይታ የመጀመሪያውን ክፍል እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ሥራ ምንድን ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡– የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከተቋቋመ ሶስት ዓመት ሞልቶታል። በተቋቋመበት ወቅት የተሰጡት ተልዕኮዎች 35 ያህል ናቸው። እነዚህን ተልዕኮዎቹን በዋናነት ሶስት ቦታ ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው ሁሉንም የግብርና ግብዓት ጥራት እና ደህንነትን መቆጣጠር ሲሆን፣ ቁጥጥሩ የሚካሄደው ደግሞ በላቦራቶሪ እና በኢንስፔክሽን ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ቁጥጥር የምናደርገው የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ ነው። ለምሳሌ ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ፤ ከምርምር የሚወጣ የዘር ቴክኖሎጂ ጥራቱንና ደኅንነቱን ለገዛው ሰው የገንዘቡን ዋጋ የሚመለስ መሆኑን አረጋግጠን ሰርተፊኬት እንሰጣለን። በሶስተኛ ደረጃ የምናደርገው የምርት ጥራት ቁጥጥር ነው። ምርት ሲባል በአብዛኛው ከተጠቃሚው አኳያ ሲታይ ሁለት ቦታ የሚከፈል ነው። በሀገር ውስጥ የምንጠቀመውና ወደ ውጭ ገበያ የምንልክ ስለሆነ ይህ ተቋም በዋናነት ኤክስፖርት የሚደረጉና ከውጭ ኢምፖርት በሚደረጉት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።
ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆነውን በተመለከተ ሥልጣን የተሰጠው ለክልሎች ነው። ነገር ግን ባለሥልጣኑ እገዛ ያደርጋል። በላቦራቶሪ ምርመራ እንደርጋለን። እንዲሁም ኢንስፔክተሮችን እየላክን በክልሎች አማካይነት ለተጠቃሚው የሚቀርበው ምርት በሰዓት መቅረቡንና ጥራት ያለው መሆኑን መረጋገጣቸውን ቁጥጥር እናደርጋለን። በአራተኛ ደረጃ ምርት የሚያመርቱ ኮሜርሻል እርሻዎችን ጣቢያቸው ድረስ ሄደን ኢንስፔክሽን እናደርጋለን። ብቃት አላቸው? ወይስ የላቸውም የሚለውን አረጋግጠን ሰርተፊኬት እንሰጣቸዋለን። ስለዚህ ባለሥልጣኑ እነዚህን ዋና ዋና ሥራዎችን የሚሠራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር በ2017 በጀት ዓመት አከናውናለሁ ብሎ ካቀዳቸው ውስጥ ምን ምን ተግባራዊ አድርጓል?
አምባሳደር ድሪባ፡- ተቋሙ በ2015 ዓ.ም ራሱን በማቋቋም ላይ ነበር፤ በ2016 ዓ.ም ደግሞ ወደ ሥራ ገባ። በተያዘው 2017 ዓ.ም የበለጠ ተደራጅቶ ወደ ሥራ የገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንዲህም ሲባል ይህ በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና ሁሉንም ግብዓት በማሟላት ወደ ሥራ የገባንበት ጊዜ ነው። ይህ በመሆኑም የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወር ግምገማ አካሂደናል። ባለሥልጣኑ፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመሆን ባደረግነው ግምገማ ከያዛቸው አቅዶች መካከል 96 በመቶውን ማሳካት ችሏል።
የምንሠራው በተለያዩ ዘርፎች ነው። ለምሳሌ የእንስሳትም የእፅዋትም ዘርፍ አለ፤ በድምሩ ወደ አስር የሚሆኑ ቴክኒካል ዲፓርትመንቶች አሉ። አንዳንዶቹ ቴክኖሎጂ ላይ ይሠራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የእንስሳት መድኃኒት ላይ ያተኩራሉ። ገሚሱ ደግሞ የመኖ ጥራት ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩ የእርሻ ምርቶች እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬን ጨምሮ ጥራትን ያረጋግጣሉ። ሌላው የአበባ እና ሆርቲካልቸር በተለይ የፍራፍሬና እንዲሁም የአትክልት ምርቶች የዘር ጥራት እናረጋግጣለን። እነዚህን ሁሉ በማድረግ የሚሠራ ነው፤ የሁሉም አፈጻጸም አንድ ዓይነት ሳይሆን የተለያየ ነው። የሁለቱ ዘርፎች የስድስት ወራት በአማካይ ሲመዘን ወደ 96 በመቶ የሚጠጋ ነው።
ከዚህ ውስጥ ትልቁን ሥራ የሠራነው ተቋሙን ወረቀት አልባ ማድረግ ነው። ይህ ማለት ዲጂታል የሆነ ሁሉ ነገር በቴክኖሎጂ የሚሠራ ለማድረግ ጥረት አድርገናል። የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ባለፈው በጠቅላይ ሚኒስትራችን ይፋ ተደርጓል። ከዚያ በኋላ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር አንድም የመንግሥት በጀት ሳንጠቀም ከምንሰጣቸው 64 የአገልግሎት ዓይነቶች ውስጥ 48ቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል አድርገናል። የቀሩን ወደ 26 ያህል አገልግሎቶችን ደግሞ እስከ ሰኔ ድረስ ሙሉ በሙሉ ኦንላይን እናደርጋለን።
ተገልጋይ በአካል እዚህ መምጣት አያስፈልገውም። ቤቱ ሆኖ መስፈርቱን አሟልቶ ይልካል። እኛ ደግሞ እዚህ በሲስተም እንቆጣጠራለን። የተቀመጠ የጊዜ ስታንዳርድ አለ፤ በዚያ ጊዜ ውስጥ ከባለሙያ ጀምሮ እስከ ኃላፊ ድረስ ውሳኔ ይሰጣል። ማታ ማታ ኦንላይን እየገባን ስንት ሰው አመለከተ? ስንት ሰው አገልግሎት አገኘ? በሚል እናረጋግጣለን። ስለዚህ ከዘንድሮ እቅዳችን ውስጥ አንዱ ተቋማችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ተቋም እንዲሆን ማስቻል ነው። በአሁኑ ጊዜ ወደ 80 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት ችለናል። የቀረውን 20 በመቶ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ እናጠናቅቃለን።
በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውንና ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸውን ምርቶች በሙሉ እስካሁን ትሰጥ የነበረው የወረቀት ሰርተፊኬት ነበር። ይህን ዘንድሮ የአውሮፓ ኅብረት ፈንድን ጠይቀን ትሬድ ማርክ አፍሪካ በሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ሙሉ በሙሉ ወደ ኢፋይቶ (ePhyto) ገብተናል፤ ይህ ማለት ሥራችንን ወደ ወረቀት አልባ የሆነ የዲጂታል አገልግሎት ቀይረናል ማለት ነው። ይህ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትሬድ ማርክ አፍሪካ ከአውሮፓ ኅብረት በተደረገው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ሲስተም ገንብቶልን አሁን በአፍሪካ ውስጥ ኢፋይቶ (ePhyto) የሚሰጥ ሀገር መሆን ችለናል።
እንዲህም ሲባል በወረቀት ፋይቶ የማይሰጡ ሀገሮች 17 ነበሩ፤ እኛ 18ኛ ሆነን ገብተናል ማለት ነው። ኢትዮጵያ እስከ ጥቅምት ድረስ ስትሰጥ የነበረችው በወረቀት ላይ በመመስረት ነበር። በሰነድ ተደግፎ ወደ ውጭ ሀገር ምርት መላክ ከጀመርን ግን 108 ዓመታችን ነው። በዚህ ጊዜ ቴክኖሎጂ አንጠቀምም ነበር። አሁን ሙሉ በሙሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀይረናል።
ይህን ያደረግነው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተሠራው መሠረተ ልማት ነው። ከዚህም የተነሳ ባለፈው መጋቢት ወር ጣሊያን ሀገር በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ እና ማሊዤያ ከዓለም ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው በሚል እንድናቀርብ ተጠይቀናል። ስለዚህ ይህ ትልቅ ነገር ነው፤ እስካሁን ያልተሠራ፤ ነገር ግን የአውሮፓ ኅብረት አግዞን ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች ከእነርሱም ከእኛ ሀገር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ኢንሳም ጭምር ያዩት እና ጥሩ ሥራ የሠራንበት ነው።
ሌላው ወደ ውጭ የሚላክ የአበባ እና ሆርቲካልቸር እርሻ የተባይ (ፔስት) ቁጥጥር ሲስተም ወደ ሲስተም አፕሮች ቀይረናል። አንዳንድ ጊዜ ተባይ ይገኝበታል። በመሆኑም የአውሮፓ ድንበር ላይ ደግሞ እንዳይገባ ይደረግና የሚመለስ ይሆናል፡፡
ይህን ለማስተካከል ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ኅብረት ምክረ ሃሳብ ሰጥቶናል። በወቅቱም መከተል የሚገባን ‹የሲስተም አፕሮች› ቁጥጥርን እንደሆነ አሳውቆናል። ስለዚህ ከኔዘርላንድ ወደ ሶስት ባለሙያዎች አስመጥተን እንዲሁም ከእኛ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከተቋማችንና ከግብርና ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የአበባ እርሻ የተባይ ቁጥጥር ሥርዓቱ ወደ የ‹ሲስተም አፕሮች› አድርገን መተግበር ችለናል። ከአፍሪካ ይህን ተግባራዊ ያደረግነው እኛ እና ኬንያውያን ነን። የዚህን ሥራ ሪፖርቱንና ሲስተሙን ለአውሮፓ ኅብረት ልከን ስለጉዳዩ በአግባቡ ካብራራን በኋላ ደስተኞች በመሆናቸው ምርታችንን ወደ ውጭ ገበያ እንዲቀጥል ማድረግ ችለናል።
ሌላው የሥጋ ምርታችን ወደ ቻይና ሀገር እንዲገባ ከሥጋ ምርት ጋር በተያያዘ የቻይና ኤክስፐርቶች ወደ ሀገራችን መጥተው አይተዋል። ኤክስፐርቶቹም ማስተካከል ስለሚገባን ነገር፤ ምክረ ሃሳብ ሰጥተውናል። ስለሆነም ቻይና የምትፈልገውን የሥጋ ንግድ ሥርዓት በመረዳት በዚያ መሠረት ሥርዓቱን መቃኘት ችለናል፤ ይህ በመሆኑም ቻይናውያን አሠራራችንን ተቀብለውታል። በቀጣይም ሥጋን ወደ ቻይና ለመላክ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ እንገኛለን።
ሌላው በዚህ በስድስት ወር ውስጥ ትልቁ ሥራ መሥራት የተቻለውና ከዚህ በፊት ያልሠራነው የቁም እንስሳት ንግድን በተመለከተ ነው። ሚሌ ላይ ኳራንታይን ከፍተን ነበር። ይህ ኳራንታይን ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ 400 ሺህ እንስሳት ወደ ውጭ ሀገር ልኳል። ከዚህ በፊት የቁም እንስሳት በኮንትሮባንድ ከሀገር ይወጡ ነበር። አሁን ግን የሚሌ ኳራንታይን ትልቅ ሥራ እየተሠራበት ይገኛል።
400 ሺህ የቁም እንስሳት መዳረሻቸው አብዛኞቹ ዓረብ ሀገራት ነው። ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚሄዱ ናቸው። የቁም እንስሳቱን ወደ ጂቡቲም ጭምር ኤክስፖርት እናደርጋለን። በአብዛኛው እስከ ሳዑዲና ኦማን ድረስ ይሄዳሉ። በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በሕጋዊ መንገድ እንዲወጡና ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ያደረግናቸው ከ400 ሺህ በላይ ከብቶች ናቸው። እንዲህ ሲባል በሕገ ወጥ መንገድ የመጓጓዙ ነገር ቀርቷል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ የሚታወቅ ነው፤ ፈተናው አሁንም አለ። በርግጥ የእኛ ሥራ የሕገ ወጥ ንግዱ ላይ ሳይሆን የጥራት ቁጥጥር ላይ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሊ ኳራንታይን ሥራ የጀመርንበት ጊዜ ነው። አምና 300 ሺህ ያህል ከሚደርሱ ከብቶች በዓመቱ መጨረሻ የተገኘው 18 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን ገና በግማሽ ዓመቱ ከ400 ሺህ ከብቶች ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል። ይህ የሆነው የፋይናንስ ሴክተሩ ላይ በተደረገው ማሻሻያ ሲሆን፣ በተለይ በውጭ ምንዛሬው ላይ የተደረገው ማሻሻያው በብዙ ጠቅሞናል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚሌ ኳራናታይን መከፈቱ እንስሳቱ ታክመውና ጤንነታቸው ተረጋግጦ በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ሰርተፍኬት ድንበር አቋርጠው እንዲወጡ ተደርጓል። የእንስሳት ንግዱ አሁን ሥርዓት እየያዘ መጥቷል። ይሁንና አሁንም ክፍተት መኖሩ የሚታበል አይደለም። ምክንያቱም በሕገ ወጥ መንገድ በኬንያም በሱማሌም የሚወጡ አሉ። በአሁኑ ጊዜ ኳራንታይኖች እያስገነባን እንገኛለን። ዙሪያውን አስገንብተን ከዚህ በኋላ በሙሉ በኳራንታይን እንዲወጡ እናደርጋለን።
ከተገነቡ ኳራንታይን ውስጥ አንዱ የሚሌው ሲሆን፣ ጅግጅጋ ሲያስገነባ የነበረው ግብርና ሚኒስቴር ዘንድሮ ወደ እኛ ካስተላለፈ ተቀብለን አገልግሎት እንጀምራለን። በሞያሌ በኩልም የኳራንታይን ግንባታ እናስጀምራለን።
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ በስድስት ወራት ውስጥ 96 በመቶ ስኬታማ ሆኗል፤ በእነዚህ ጊዜያት በሥራችሁ በተግዳሮትነት የሚነሳ ነገር ይኖር ይሆን?
አምባሳደር ድሪባ፡– እንደ ተግዳሮት ከተወሰደ ተቋሙ አዲስ ነው። የግብርና ቁጥጥር የሚሠራው በተበታተነ ሁኔታ ነበር። አንዱ የነበረበት ችግር ደግሞ የሰው ኃይል ብቃት ነበር። ብዙ ተቆጣጣሪዎች (ኢንስፔክተሮች) ማፍራት ያስፈልግ ነበር። ይህን ለማሟላት በተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ስናካሂድ ነበር፡፡
ሁለተኛው ትልቁ ፈተና ደግሞ በተለይ አውሮፓ ኅብረት የቁጥጥር ሕጉን ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀያየርና ማሻሻል ስለጀመረ ከዚህ ጋር የሚሄድ ፈጣን የሆነ መልስ መስጠት ላይ ገና ብዙ ነገር ይቀረናል። ይህንን እንደ ፈተና የምናየው ነው። ሌላው በተለይ የላቦራቶሪ የምርመራ ተቋም አሁን በከፊል የምንጠቀመው የጥራት መንደር ነው።
አንዳንድ ምርቶች ላይ ምግብ የሚመርዝ ሕዋስ (salmonella) ዓይነት በተለይ ሰሊጥ ምርት ላይ አጋጥሞን ነበር። አፍላ ቶክሲንም በተወሰነ ደረጃ ነበር። እኛም ትልቅ የምርመራ ተቋም ቃሊቲ አለን። ነገር ግን የአፍላ ቶክሲን ችግር አልፎ አልፎ በወተት ምርት ላይ የሚታይበት ጊዜ ነበር። ይህን ዓይነቱን ችግር ለማስተካከል መሥራት ያለብን ከአምራቹ ጋር ነው። በመሆኑም ከአምራቹ ጋር ሰፊ ሥራ ሠርተናል። በሁለተኛ ደረጃ ላቦራቶሪያችን አቃቂ ያለውን የሶስተኛ ወገን እውቅና እንዲያገኝ አድርገናል፡፡
ሬጉላቶሪ የሚሠራው በሕግ ነው። ሕግ ከሌለ ጥርስ የሌለው አንበሳ እንደ ማለት ነው። ስለዚህ የተወሰኑ ሕጎች ገና በሂደት ላይ መሆናቸው ሬጉላቶሪው በሙሉ አቅሙ እንዳይራመድ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሮብናል። በራሳችን የምናሸንፋቸውን ችግሮች በራሳችን እያሸነፍን፤ የሌሎቹን ድጋፍ የሚሻውን ችግር ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን እቅዳችንን ማሳካት ችለናል። ትልቁ ነገር ከክፍተቱ እየተማርን ነው። ቁጥጥር ለብቻ የማይሠራ እንደመሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በተለይ የጥራት ቁጥጥር ላይ ከሚሠሩ ለምሳሌ ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ ከጥራት መንደር ላቦራቶሪ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ጋር ተባብረን ስለሠራን አብዛኛውን ችግር በተለይ የግብርና ሚኒስቴር የቅርብ እገዛ ስለሚያደርግ ሥራችንን በተገቢው ለማሸነፍ ጥሩ አቅም ሆኖልናል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ሰፊ ሀገር ናት፤ 80 በመቶ የሚሆነው የሕዝቡ ኑሮ የተመሠረተው ደግሞ በግብርናው ላይ ነው። ግብርና ደግሞ ከጤና ጋር ይያያዛል። የሰው ልጅን የሚያጠቃው በሽታ 65 በመቶው ወይ ከእንስሳት ምርት ነው፤ አሊያም ከግብዓት ምርት ነው። በመሆኑም የምግብ ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ ትልቅ ሥራ መሆን አለበት። ከዚህ አኳያ ክልሎች ዘንድ ክፍተት አለ። ተቀናጅቶ መሥራትና ከእኛም ጋር ተሳስቦ ከመሥራት አንጻር እኛ ዓለም አቀፉ ላይ ወይም ከክልል ክልል በሚዘዋወሩ ምርቶች ላይ ስለምናተኩር እዚያ ያለውን የአቅም ችግር ያለማሟላት ችግር አለብን። የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግርንና የሰው ኃይል ብቃት የመገንባት ችግርን እስካሁን ያላለፍናቸውና ገና መሥራት የሚጠበቅብን የቤት ሥራችን ነው ማለት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ባለሥልጣኑ ሚናው እስከ ምን ድረስ ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡– የእኛ ድርሻ የምግብ ደኅንነትን መቆጣጠር ነው። በተለይ በዋናነት ምርት እንዲጨምር ድርሻ አለን። ለምሳሌ በየዓመቱ አዳዲስ ዘሮች ከምርምር ሲወጡ ለአርሶ አደሩ የሚሠራጨው በብሔራዊ የዘር አጽዳቂ ኮሚቴ ታይቶ፤ ከዚያ በኋላ በእኛ ተቋም ተረጋግጦ ነው። ዘንድሮ ለምሳሌ ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ወደ 40 ዓይነት አዳዲስ ዝርያዎች እንዲወጡ አድርገናል። ዘር አጽዳቂው ኮሚቴ አይቶ ወደ እኛ ተቋም ያስተላለፈ ሲሆን፣ እኛ አረጋግጠን ለአርሶ አደሩ እንዲሠራጭ አድርገናል።
ሌላው የምንሠራው ሥራ ከምግብ ራስን መቻል ጋር በተለይም የኤክስቴንሽን ሥርዓቱን መቆጣጠር ነው። ለምሳሌ የእንስሳት ግብዓት የሆነው የመኖ ጥራት እንዲረጋገጥ እንሠራለን። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት በስፋት እያደገ ይገኛል። በዚህ ላይ ባለሀብቶችም ሆነ አርሶ አደሮች ተበረታትተው መኖ እንዲያመርቱ፤ የወተት፣ የሥጋና የእንቁላልም ምርት እንዲስፋፋ ብዙ ጫጩቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ቁጥጥር የምናደርገው እኛ ነን። ደግሞም ብዙ ጫጩቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል። በዓመቱ ውስጥ ወደ ውጭ ሀገርም የተወሰኑ እንቁላሎች ኤክስፖርት ተደርገዋል። የእነዚህን ሁሉ ጥራት የምናረጋግጠው እኛ ነን፡፡
በሌላ በኩል 24 ሺህ ኩንታል የሆርቲካልቸርና የፍራፍሬ ዘር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርገናል። ይህ ጥቅሙ ምንድን ነው ከተባለ ምርት እንዲጨምር የሚያደርግ ነው። በጣም ከፍተኛ የምርታማነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ዝርያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ለኮሜርሻል እርሻም፤ ለአነስተኛ አርሶ አደርም እንዲሠራጭ በማድረግ የምርት እድገት እንዲጨምር እንሠራለን። ይህ ማለት ደግሞ ሀገሪቷ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት የመደገፍ ሥራ ነው፡፡
ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ የስንዴ ምርት በስፋት በመመረት ላይ ይገኛል፤ እኛ የእነዚህን ምርት ጥራት እናረጋግጣለን። ይህም ማለት ውስጣዊ ይዘታቸው እንደ ፕሮቲን፣ ፋት እና የካርቦሃይድሬት ይዘታቸው ምን ያህል ነው የሚለውን እናጤናለን። ለበጋ ስንዴም ሆነ ለክረምት ስንዴ እንዲሁም ለሩዝም የሚወጡ ዘሮች ጥራታቸው ተረጋግጦ ነው። ዘር ላይ የምናረጋግጠው ሶስት ነገሮችን ነው። አንደኛው የብቅለት ደረጃው፣ ሁለተኛው እርጥበት የመያዝ አቅሙ ሲሆን፣ ሶስተኛው ደግሞ ከበሽታ ነፃ መሆኑን ነው። ለአርሶ አደሩ የምንሰጠው እነዚህን ሶስቱን አረጋግጠን ነው፡፡
በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ዘር ጥራት አረጋግጠን እናሠራጫለን። ለዚህኛው በጋ ለስንዴ እርሻ እንዲደርስ ብለን ፈጥነን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ጥራቱን አረጋግጠን ብዙ ዘር ለአርሶ አደሩ አሠራጭተናል። ስለዚህ በሁሉም መስክ ራስን በምግብ ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ አለንበት ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ማዳበሪያ በዓመት ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ይገባል። ማዳበሪያው ምን ያህል ጥራት አለው? የግራሙ መጠን ምን ያህል ነው? ዩሪያ፣ ዳፑ በሀገር ደረጃ ባለው ደረጃዎች የተቀመጠውን ስታንዳርድ ያሟላሉ ወይስ አያሟሉም፤ በሀገር ውስጥ ደግሞ የሚመረቱ ማዳበሪያዎች አሉ። በኮምፖስት (compost)፣ ቨርሚኮምፖስት (Vermicompost) እና የተለያዩ ኬሚካሎችንም ከውጭ ሀገር በማስመጣት የሚያመርቱ አሉና የእነዚህንም የጥራት ደረጃ እናረጋግጣለን። ስለዚህ ምርትን ብቻ ሳይሆን ምርትን የሚያሳድጉ ግብዓትንም ጭምር ጥራታቸውንና ጤንነታቸውን እናረጋግጣለን፤ ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱም በማድረግ ቀጥታ በማምረት ውስጥ ባንሳተፍም ለማምረት የሚያገለግሉና ከተመረቱ በኋላ ደግሞ ተገቢው ጥራትና ደኅንነት ያለው ምርት መሆኑን ስለምናረጋግጥ ሚናችን የጎላ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ምርት የቁጥጥር ሥርዓት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አምባሳደር ድሪባ፡– የጥራት ቁጥጥርን አራት ቦታ ከፍለን ማየት እንችላለን። አንደኛው የግብዓት ቁጥጥር፤ ሁለተኛው የምርት ሂደት ቁጥጥር ሲሆን፣ ሶስተኛው የምርት ሂደትን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና ምርት ላይ የሚሠማሩ ተቋማትን መቆጣጠር ነው። አራተኛው ደግሞ ምርቱ ከተመረተ በኋላ ምርቱን እራሱ መቆጣጠር ነው። ስለዚህ የግብዓት ቁጥጥር በምንልበት ጊዜ በዋናነት አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የምናረጋግጠው በላቦራቶሪ ነው። ለምሳሌ መኖን ብንወስድ አቃቂ ባለው ላቦራቶሪ ጥራት ያለውና የሌለው መሆኑን እንቆጣጠራለን። ጥራት ሲባል ለምሳሌ መኖው ተገቢውን የምግብ ይዘት ይዟል አልያዘም የሚለውን መቆጣጠር ማለት ነው። መኖው ተፈላጊውን ግብዓት ይዞ ከተገኘ አርሶ አደሩ እንዲጠቀምበት እናደርገዋለን። የማያሟላ ከሆነ ደግሞ ውድቅ እንዲሆን እናደርጋለን።
ሁለተኛው ደግሞ ቁጥጥር የምናደርገው ዘር ላይ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዘርን ቁጥጥር የምናደርግበት 20 ላቦራቶሪ አለን። አብዛኛዎቹ ላቦራቶሪዎች ያሉት ክልል ላይ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ እንደ ሪፈራል የሚያገለግል ላቦራቶሪ አለን። ክልሎች ማጤን ያልቻሉት ካለ ወደ እኛ ዘንድ ይመጣል። ከእኛ አቅም በላይ የሆነውን ደግሞ ወደ ሪሰርች ማዕከል ልከን እናያለን። ስለዚህ እነዚህ ላቦራቶሪዎች በሽታን ሁሉ የሚቆጣጠሩ ናቸው።
ሌላው የምንቆጣጠረው የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ነው። ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ማለት የተለያየ ዓይነት የግብርና መሳሪያ ሲሆን፣ እነዚህን የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ጥራት ከውጭ ሲመጡ መቆጣጠር የሚያስችል ማዕከል በአሁኑ ጊዜ በመመረቁ ሥራ ይጀምራል። ስለዚህ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን እንቆጣጠራለን። ከግብዓት አኳያ ደግሞ ከምርምር የሚወጡ ዘሮችን እናጸድቃለን። አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በዚህ ዓመት በምርምር የወጡ ዘሮች ከመቶ በላይ ናቸው፤ ዘንድሮ በምርምር ከወጡ ከመቶ በላይ ዘሮች ውስጥ የጸደቁት 4 ናቸው። ሌሎቹን ዘሮች የተሟሉ ሆነው ስላላገኘናቸው ውድቅ አድርገናቸዋል። ምክንያቱም ያልተሟላ ነገር ስላላቸው እንደገና እንዲታዩ አድርገናል። ስለዚህ የመጀመሪያ የግብዓት ቁጥጥር ነው ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ሂደቱንም እንቆጣጠራለን። ይህንን የሚቆጣጠር የኤክስቴንሽን ዲፓርትመንት አለ። ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲከተሉ፣ የዘር እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው እንዲሁም የእርሻ አስተራረሳቸው ላይ ድርሻችን የጎላ ነው። ይህንን የበለጠ ተቋማዊ ለማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የተለያየ ሕግ አውጥተናል። በቅርቡም የሚጸድቅ ይሆናል፤ እስካሁን ያለው አሠራር አንድ አርሶ አደር ዝም ብሎ ከመንግሥት ኤክስቴንሽን የሚገዛ ነው። ነገር ግን አርሶ አደሩ እራሱ ከሌላ ከባለሙያው እውቀቱን ገዝቶ የሚጠቀምበትን ሥርዓት በአሁኑ ጊዜ እየዘረጋን እንገኛለን።
በአሁኑ ጊዜ ግን አገልግሎቱን የሚሰጠው መንግሥት በመሆኑ ቁጥጥራችን የጠበቀ አይደለም። ሥርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ ግን አገልግሎቱ የሚገዛው ከባለሙያው በመሆኑ የዚያን ባለሙያ ብቃት እንቆጣጠራለን፤ የኤክስቴንሽን አገልግሎት የመሸጥ ችሎታውንም እንመዝናለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ እንሰጣለን የሚሉ ተቋሞችም ሊቋቋሙ ይችላሉ። እነርሱም ተገቢ እውቀት ያላቸው ስለመሆናቸው እና ስላለመሆናቸው፣ ተገቢ አሠራርና ቴክኖሎጂ ስለመከተላቸውና ስላለመከተላቸው እንዲሁም የሚያስተላልፉት እውቀት ምን ያህል ነው የሚለው ይጤናል። ስለዚህ ሂደቱ ውስጥም አለንበት ማለት ነው።
ኦዲትም ኢንስፔክሽንም እናደርጋለን። ለምሳሌ ኢንስፔክተሮቹ ኮሜርሻል እርሻ ዘንድ ይሄዳሉ። መድኃኒት አስመጪዎች ዘንድም ሆነ ቄራ ይሄዳሉ። ለምሳሌ ቄራ እንስሳው ከመታረዱ በፊት ጥራቱና ጤንነቱ ይረጋገጣል። ከታረደ በኋላ ደግሞ የሥጋው ጥራት እንደገና ይረጋገጣል። ስለዚህ ይህ ሂደት ነው፡፡
የእርሻ ኬሚካል (ጸረ ተባይ) የሚያመጡ ድርጅቶች የሚያከማቹበትን ስፍራ እናያለን። ያላቸውን ባለሙያ እንቆጣጠራለን፡። አርሶ አደሩን እንዴት እንደሚያስተምሩ እናጤናለን። በጥቅሉ የምርት ሂደቱ ላይ በጣም ትኩረት እድርገን እንሠራለን። ይህን የሚሠራ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት አለ።
በተለይ ከኮሜርሻል እርሻዎች ለምሳሌ የአበባን እርሻ ብንወስድ የማሳ (የፋርም) ላይ ኦዲት አለ። ፍራፍሬና አትክልት የሚያመርቱ ኮሜርሻል እርሻዎች ዘንድ ኤንስፔክተራችን ይሄድና እያንዳንዷን ነገር ይቆጣጠራል። ሪፖርቱንም ይዞልን ይመጣል፤ በዚያ መሠረት ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን።
ከዚህ ቀጥሎ በመጨረሻ የምንቆጣጠረው የተመረተውን ምርት ነው። እኛ የምግብ ደኅንነት ላቦራቶሪ (food safety laboratory) ጉርድ ሾላ ላይ እያቋቋምን ነው። እሱ ሲያልቅ እያንዳንዱ ምርት ይዘቱን እናይበታለን፤ በምርቱ ላይ የኬሚካል ቅሪት መኖር አለመኖሩን እናጤናለን። አሁን ግን ለጊዜው የምንጠቀመው የጥራት ማዕከልን ነው።
የቅባት እህሎችን አጠቃላይ እዚያ ምርመራ ይደረጉና ካርድ ይላካል፤ የምርመራ ውጤት መሠረት ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ወይም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንዲውል የኢፋይቶ ሰርተፊኬት እንሰጣለን። ስለዚህ የምንቆጣጠረው በጠቀስኳቸው ሂደቶች ውስጥ ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም ቦታ ደርሰናል ማለት አይደለም። ምክንያቱም በአንድ በኩል አዲስ መሆናችን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ክልሎች ላይ የሚመረቱ ምርቶች ክልሎች ራሳቸው እንዲቆጣጠሩ ሥልጣን ስላላቸው ነው። ነገር ግን ክልሎች ላይ ያሉ የቁጥጥር ተቋማት ያልተጠናከሩ ናቸው። ኅብረተሰቡ በተለይ ስለምርት ደኅንነት እና ጤንነት ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ይህ እንደ ችግር የሚታይ ነው።
የፍራፍሬ እና የአትክልት ምርቶች አንዳንዴ የሚመረቱባቸው ቦታዎች ለጤና ስጋት የሚሆኑ ናቸው። በመሆኑም ምርቱን በመመርመር የሚገኘው ውጤት የማኅበረሰብ ጤና ላይ ችግር የሚያመጣ ከሆነ አምራቹ የምርት ሥርዓቱን እንዲያስተካክል ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን። ለአምራቹ ለራሱ አሊያም በግብርና ሚኒስቴሩ በኩል ኤክስቴንሽን እንዴት እንደሚጠቀም እንዲማር ይደረጋል። የማኅበረሰብ ጤና ላይ ችግር ትኩረት የሚደርግባቸው አካባቢዎች አሉ፤ ለምሳሌ የሪፍት ቫሊ፣ ከከተሞች ጎን እና ከፋብሪካ ጎን የሚመረቱ ምርቶች ካሉ እነዚያ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ምክንያቱም ከፋብሪካ የሚወጣ ዝቃጭ እንዳይነካው ሰፊ የሆነ የአመራረት ሥርዓቱና በመጨረሻም ምርቱ ተመርቶ ከወጣ በኋላ ለጤና ብቁ ነው አይደለም የሚለው ላይ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ለመቆጣጠር እንሞክራለን። ይህ ግን ሰፍቶ መሔድ አለበት። በሕዝብም በመገናኛ ብዙሃንም መታገዝ አለበት።
ምክንያቱም መጨረሻው የማኅበረሰብ መብትና ጥቅም በጥቅሉ የሀገር ጥቅም ማስከበር ነውና። በአጠቃላይ ግን እንደ ጅምር ሲታይ ሰፋ ያለ ሥራ እየሠራን ነው። የችግሩንም ጥልቀት እና ጉዳት እንዲሁም መፍትሔዎችን አሁን ከምንሠራቸው ሥራዎች እየተነሳን እየተገነዘብን መጥተናል፡፡
ክፍል ሁለትና የመጨረሻው ሳምንት ይቀርባል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም