የቡናና ሻይ ባለስልጣን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ሰፋፊ ተግባሮችን ሲያከናውን ቆይቷል:: በተለይም በቡና ልማት እና ግብይት ያለውን ችግር መፍታት እንዲቻል ትኩረቱን ሪፎርም ላይ በማድረግና ሪፎርሙን ሊደግፉ የሚችሉ አዋጆች፣ ደንቦችና አሠራሮችን በማሻሻል የቡና ግብይቱ እንዲፋጠንና የቡና ምርታማነት እንዲያድግ በማድረግ የአገርና የሕዝቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል::
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ዘርፉን ለማሳደግና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከተሠሩ ሪፎርሞች መካከል የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚረዱ ዘመናዊ ማዕከላትን ማቋቋም አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ::
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ማዕከላቱን ዘመናዊ ማድረግ በተለይም በውጭ ገዢዎችና በአገር ውስጥ ገዢዎች እንዲሁም በአገሪቱ ምርቶችና በውጭ አገር ምርቶች መካከል የሚኖረውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ያስችላል:: ከዚህ ቀደም ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ የሚያስችለው ማዕከል በአዲስ አበባ ብቻ ነበር የሚገኘው:: በአሁኑ ወቅት ግን በሪፎርሙ በተቀመጠው መሠረት ማእከላቱን ወደ ክልሎችም ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው::
በመሆኑም አዲስ አበባ ብቻ የነበረውን ማእከል በጅማና ሀዋሳ ላይ በመክፈት የአገሪቱንና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም አቶ ሻፊ ጠቁመዋል:: የእነዚህ ማዕከላት አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሻፊ፤ አንደኛ የቡና ጥራትን ከማስጠበቅ አንጻር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አመልክተዋል::
እንደ አቶ ሻፊ ማብራሪያ፤ የቡና ጥራትን ማስጠበቅ ሲባል ደግሞ እያንዳንዱ ቡና ወደ ማዕከላቱ በሚመጣበት ጊዜ ደረጃ ወጥቶለት ጥራቱ ታውቆ በተለይም ዱካውን የጠበቀ ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የተሻለ ገቢ ለማስገኘት አንዱና ትልቁ ሥራ ሲሆን፣ እነዚህን ቡናዎች በመመርመር፣ ደረጃ በመስጠት ወደ ውጭ ገበያ እንዲላኩ ማድረግ ነው:: ይህም በቡና ጥራት ላይ የሚኖረው አበርክቶ እጅግ ከፍተኛ ነው::
ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ከ2013 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና በቀጥታ ግብይት ትስስር (ቨርቲካል ኢንቲግሬሽን) በላኪና አቅራቢ መካከል ግብይት መካሄድ መጀመሩን ያስታወሱት አቶ ሻፊ፤ ይህም አምስት ጥቅሞችን ማስገኘት እንደቻለ ነው የገለጹት:: ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንደኛው በቡና ግብይት ወቅት የነበረውን ረጅም የእሴት ሰንሰለት እንዲያጥር ማድረግ የሚለው ነው:: በላኪና በአቅራቢው መካከል የእሴት ሰንሰለት የማይጨምሩ አካላትን በማስወገድ ቡና ላኪው በቀጥታ ከአቅራቢው ቡና እንዲገዛ አስችሎታል፤ በዋጋው ላይም ከፍተኛ ልዩነት ያመጣ በመሆኑ አርሶ አደሩም በዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል:: ይህም አርሶ አደሩን የሚያተጋና የበለጠ የሚያነሳሳ በመሆኑ ምርትና ምርታማነቱን ለማስፋትና ለማሳደግ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል::
ሁለተኛው ጠቀሜታ የምርት ጥራት እንዲጨምር ማድረግ ማስቻሉ ሲሆን፤ የምርት ጥራት በሚጨምርበት ወቅት ቡና በተሻለ ዋጋ ስለሚሸጥ አገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች:: ምርትና ምርታማነቱን ከማሳደግ ባለፈም የቡናውን ጥራት በማስጠበቅ ጭምር ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አገሪቷ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ማግኘት ያስችላታል:: ቡናን በጥሩ ዋጋ በመሸጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ በማስመዝገብ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ከማምጣት ባለፈ፣ አርሶ አደሩም ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እየፈጠረለት ይገኛል::
ሦስተኛው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ማስቻሉ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ይህም ማለት አርሶ አደሩ ባመረተው ልክ መጠቀም እንዲችል በቡና ውስጥ ያሉ ትክክለኛ ተዋናዮች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል::
ሦስተኛው ተዋናይ ላኪ መሆኑን ጠቅሰው.፣ ላኪውም የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንዲችል በተለይም የውጭ ገዢ ትክክለኛና ዱካውን የጠበቀ ምርት፣ ጥራቱን የጠበቀና በጊዜውና በወቅቱ ተደራሽ መሆን የሚችል ምርት የሚፈልግ በመሆኑ ላኪው ይህን ቡና አግኝቶ ለደንበኛው ስለሚሸጥ ተጠቃሚ መሆን ይችላል ይላሉ:: በመሆኑም ይህ ቨርቲካል ኢንቲግሬሽን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግብይቱ እንዲሳለጥ እንደሚያደርግ ተናግረዋል::
አራተኛው ጠቀሜታ በአቅራቢና በላኪው መካከል የመተሳሰብና የመጠባበቅ ሁኔታን መፍጠር ማስቻሉ መሆኑን አቶ ሻፊ ጠቅሰዋል:: በመጋዘን ውስጥ ያለውን ቡና ከመሸጥ ባለፈ በመነጋገርና በመግባባት የሚፈጸም የግብይት ሂደት መሆኑንም ገልጸው፣ ይህም ማህበራዊ ግንኙነታቸው እንዲጠብቅ ያደርጋል ይላሉ:: ቡና በቨርቲካል ኢንቲግሬሽን በሚመጣበት ጊዜ በላኪና በአቅራቢ መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ እና ቤተሰባዊ የሆነ ቁርኝት መፍጠር የሚያስችል የመገበያያ መንገድን እንደሚፈጥር ተናግረዋል:: ላኪው ቡናውን የሚያገኘው በቨርቲካል ኢንቲግሬሽን መሆኑ ዱካውን የጠበቀና ተዓማኒነትን ያተረፈ ምርት እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል::
እንደ አቶ ሻፊ ማብራሪያ፤ ቨርቲካል ኢንቲግሬሽን የሚጠናከረው በአነዚህ ማዕከላት ነው፤ ማዕከላቱ ቡና በቨርቲካል ኢንቲግሬሽን በሚመጣበት ጊዜ በላኪና በአቅራቢ መካከል የቡናውን ጥራት ደረጃ ለማስጠበቅ የምርት ርክክብ በማድረግ ክፍያ ይከናወናል:: ክፍያውም በተገባው ውል መሠረት የሚፈጸም ይሆናል::ማዕከሉ እነዚህና መሰል ተግባራት የሚከናወኑበት በመሆኑ እጅግ በጣም ያስፈልጋል::
ማዕከሉ በአንድ በኩል የጥራት ደረጃውን፣ የርክክብ ቦታውንና ተአማኒነቱን በማስጠበቅ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኘ መሆኑንም አመልክተው፣ በሌላ በኩልም ተደራሽነትን የሚያሰፋ እንደሆነም አስረድተዋል:: ቡና የሚገኘው ከቡናው ባለቤት ከአርሶ አደሩ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ ቡና አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ታጥሮ መቅረት እንደሌለበት ይናገራሉ:: የአገልግሎት ተደራሽነቱም አርሶ አደሩ ባለበት ክልሎች ድረስ ሊሆን እንደሚገባ ነው ያመላከቱት::
እሳቸው እንዳሉት፤ አገልግሎት አሰጣጡ እንዲፋጠን ለማድረግ በተለይም የቡና አቅራቢዎችና አጠቃላይ ተዋንያኖቹ ሳይጉላሉና ሳይንገላቱ ማንኛውንም አገልግሎት በአቅራቢያቸው ማግኘት እንዲችሉ መሥራት የግድ ነው:: በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ማዕከላቱን በጅማና በሀዋሳ ማቋቋም ያስፈለገውም ለዚሁ ነው:: በጅማ አቅራቢያ ያሉ ቡና አምራች አርሶ አደሮችና የቡና ተዋንያኖች ጅማ ላይ በማቅረብ በሀዋሳ አካባቢ ያሉትም በተመሳሳይ ቡናቸውን ሀዋሳ ላይ በማቅረብ የቡና ደረጃውን በማስወጣት፣ በማስመዘንና በመነጋገር በመካከላቸው ተአማኒነትን የማጠናከር ትልቅ ድርሻ ያለው ማዕከሉ ነው::
ማዕከሉ በአንድ በኩል የቡና ቀጥታ ግብይት ትስስሩ (የቨርቲካል ኢንቲግሬሽኑ) እንዲፋጠን የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምርቱ በሚገኝበት ቦታ ላይ ታች ላለው አርሶ አደር የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ያደርጋል:: ከዚህ በበለጠ የማዕከሉ ሌላው ትልቁ ጠቀሜታ ቡና ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ የክልል ከተሞች በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ መላክ የሚያስችል ነው::
ቡና ከአዲስ አበባ ማዕከል ብቻ ወደ ውጭ ገበያ መላክ የለበትም ያሉት አቶ ሻፊ፤ ቡና ከጅማ፣ ከሀዋሳና ከሌሎች የክልል ከተሞችም በቀጥታ ኤክስፖርት መደረግ እንዳለበት አስታውቀዋል:: ለአብነትም ቡና ከድሬዳዋ በቀጥታ ኤክስፖርት መደረግ መጀመሩን ተናግረዋል:: በቀጣይም ማዕከላቱን በማስፋት ጊምቢና ነቀምት ላይ በቀጣይ ዓመት ማዕከሉ አንደሚከፈት አመላክተዋል::
ማዕከላቱን በክልል ከተሞች መገንባት ለዘርፉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቨርቲካል ኢንቲግሬሽን ግብይት የእሴት ሰንሰለቱን ማሳጠር አንዱና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት የግብይት ሪፎርም ሲሆን፤ ይህም አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጥና በላኪና በአቅራቢ መካከል ተአማኒነት አንዲፈጠር ማድረግ ማዕከሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው እንደሆነ አስረድተዋል::
ቡና በየአካባቢው ከሚቋቋሙ ማዕከላት በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ የሚላክበትን መንገድ ለማሳለጥ ማዕከላቱ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ሲያስረዱም፤ ለአብነትም የታጠበ ቡና ወደ ማዕከል ተጭኖ ሲመጣ የትራንስፖርት ወጪን ይቀንሳል:: ወደ ውጭ ገበያ የሚላክ ቡና ወደ አዲስ አበባ ማዕከል ከነሸሚዙ መጥቶ ለኤክስፖርት የሚዘጋጀ ነው:: ስለዚህ ይህ ቡና በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው በተቋቋሙ ማዕከላት ውስጥ ለኤክስፖርት ተዘጋጅቶ ወደ ጅቡቲ የሚላክበት ሁኔታ ተፈጥሯል::
ይህም የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ያልተፈለገ ወጪን በመቀነስ የአርሶ አደሩን እና የዘርፉን ተዋናዮች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አስችሏል:: ከዚህ በተጨማሪም ቡናው ከተመረተበት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ማዕከል በሚያደርገው የመጓጓዝ ሂደት የሚያጋጥሙ የጥራት ችግሮችን ማቃለል ተችሏል፤ ይህም አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ከፍ እንዲል ያስቻለ ነው:: ስለዚህ የማዕከላቱ መቋቋም አንድና ሁለት ተብሎ የሚቀመጥ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ነው::
የቡናና ሻይ ባለስልጣን በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ በተለይም የቡናን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ከግብይቱ ጋር አብሮ መሄድ እንዲቻል ለማድረግ አገልግሎቱን ማሳለጥ የሚችሉ ተግባራትን መፍጠር ይገባል:: ለዚህም ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል እነዚህን ማዕከላት በየክልሉ ተደራሽ ማድረግ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::
አንድ አርሶ አደር ያመረተውን ቡና ባመረተበት አካባቢ አስበጥሮና አዘጋጅቶ በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ ማስላክ ይችላል:: ይህም አላስፈላጊ ወጪን በመቀነስ፣ የቡና ጥራትን እያስጠበቀ የሚሄድ፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና አገሪቷም ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መሆኑን አቶ ሻፊ አመልክተዋል:: የቡናና ሻይ ባለስልጣን በልማቱም ሆነ በግብይቱ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም ገልጸው፣ አያይዘውም ይህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ማዕከል ጅማ ላይ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም፤ ሀዋሳ ላይ ደግሞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል::
እሳቸው አንዳሉት፤ የማዕከላቱን ወደ ሥራ መግባት አስመልክቶም ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሲሠራ ቆይቷል:: ማዕከሉን ለመገንባት የቢሮ፣ የቁሳቁስ፣ የሰው ኃይል ቅጥር ማሟላትና የተለያዩ ሥራዎች በቡናና ሻይ ባለስልጣን አማካኝነት ተሠርቷል:: ክልሎችና ዞኖችም እንዲሁ ሰፋፊ ሥራዎችን በመሥራት እገዛ አድርገዋል::
ቡናን ኤክስፖርት ለማድረግ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የኤክስፖርት ማከማቻና ማዘጋጃ አንዱ ነው:: የኤክስፖርት ማዘጋጃና ማከማቻ ሲሠራ የነበረው በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ ነበረ:: አሁን ግን ማዕከላቱ በክልሎች መገንባታቸው ቡና ለኤክስፖርት እንዲዘጋጅና እንዲከማች በማድረግ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲፈጠር አስችሏል::
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባስቀመጠው የልማት፣ የገበያና የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም መሠረት ቡናን በጥረትና በመጠን እያሳደገ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ያመላከቱት አቶ ሻፊ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ብቻ 787 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል:: ባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት 746 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት መቻሉን አስታውሰዋል:: የዘንድሮው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የአምስት በመቶ ብልጫ ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑን ነው ያስረዱት::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2015