ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ እየተስፋፋ ቢሆንም ሁሉንም ማህበረሰብ አካታች በማድረግ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ግን ይነገራል። በዚህ ዘመን ለሰው ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው በይነመረብ (ኢንተርኔት) በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈለገው መጠን ተደራሽ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአዲስ አበባ በተካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ጉባኤ ላይ እንደተጠቆመው፤ በዓለም 2ነጥብ 7 ቢሊዮን፤ በአፍሪካ ደግሞ 871 ሚሊዮን ሕዝብ ከኢንተርኔት ግንኙነት ውጭ ነው።
በኢትዮጵያም የበይነ መረብ ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን ነው በዚሁ ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ያለው የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት 19 ሚሊዮን በአሁኑ ወቅት ከ30 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ተናግረዋል። የዓለማችን ግማሽ ያህሉ ሕዝብ ከኢንተርኔት ውጪ እንደሆነም ይገለጻል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ደግሞ የታዳጊ አገሮች ሴቶች መሆናቸው እየተጠቆመ ይገኛል።
የዲጂታል ዘርፉ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በማቅለል ረገድ ትልቅ ሚና አለው። በተለይም ጫና የሚበዛበትን የሴቶች ኑሮ ቀላል በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሎ ይታሰባል። በዛሬው የ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ›› አምድ ዳሰሳችን በዲጅታሉ ዘርፍ በፆታ እኩልነት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማጥበብ እየተሰሩ ስላሉ ሥራዎች ያዘጋጀነውን ጥንቅር ይዘን ቀርበናል።
በቅርቡ ‹‹ዲጂታል ለሁሉም›› (Digital for All) በሚል ርዕስ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን/ኢሲኤ/ አዳራሽ በተከበረበት ወቅት፤ አካታች የዲጂታል ምጣኔ ሀብትን እውን ለማድረግ እውቀትና ክህሎት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራት እንዳለበት ተገልጿል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንዳሉት፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሕይወትን ቀልጣፋ፣ ቀላልና ምቹ እንዲሆን አድርጓል። በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ዘርፎች ላይ ሕይወት ቀላልና ምቹ እንዲሆን የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየፈጠረ ነው።
በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በመሆን በኩል ግን በጾታ ልዩነት እንዳለ ነው የተጠቆመው፤ የሴቶች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚነት ከወንዶች ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ትምህርት ወይም ክህሎት አስፈላጊ በመሆኑ ነው። እንደ አገር በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው ልዩነት ሴቶች በዲጂታሉ ዓለም ላይ የሚመጡትን ቴክኖሎጂዎች በተፈለገው መጠን እንዳይጠቀሙ እያደረገ ነው። ለዚህም ትልቁ ማነቆ የዲጂታል ክህሎትና እውቀት ማነስ ነው ይላሉ።
‹‹በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ከተለዩ አንኳር ችግሮች ውስጥ የዲጂታል ክህሎትና እውቀት ማሳደግ አንዱ ነው›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሴቶች የዲጂታል ክህሎትና እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው ያስታወቁት። እሳቸው እንደሚሉት፤ ሴቶችን የዲጂታል ክህሎትና እውቀት እንዲኖራቸው ማስተማር ይገባል። ከዚያ በኋላ የሚመጡትን ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ ሴቶች ለኢኖቬሽን፣ ለቴክኖሎጂና ለዲጅታላይዜሽን የቀረቡ እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥናቶች ጠቅሰው እንደተናገሩት፤ ሴቶች ለኢኖቬሽን፣ ለቴክኖሎጂና ለዲጂታላይዜሽን የቀረቡ ናቸው። ይህንን እድል እንዲጠቀሙ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ‹‹ሴቶች ለአዳዲስ ፈጠራዎች ቅርብ ስለሆኑ እውቀት ቢጨመርላቸው ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙና እንዲፈጥሩ ያግዛቸዋል፤ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ይሆናሉ›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አሁን ላይ ሴቶች በዲጂታሉ ዘርፋ እየተሳተፉ ትላልቅ ቴክኖሎጂዎችን እየፈጠሩ እንደሆነም ይናገራሉ። አገራችንም የዚህ ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ እንድትሆን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል በዲጂታል ልዩነት ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የዲጂታል እውቀት ልዩነቱ በወንድ እና በሴት፣ በከተማ እና በገጠር እንዲሁም በወጣቶችና በአረጋውያን መካከል ያለ መሆኑን ጠቁመው፤ መጠኑ የሚሰፋው ግን በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለው ልዩነት እንደሆነ ይናገራሉ። ልዩነቱን ለማጥበብ እንደ አገር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በጥናቱ ግኝት መሰረት ስትራቴጂ በመቅረጽ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ በአገር ደረጃ በዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ረገድ ከተሰሩ ሥራዎች አንዱ የቴሌኮም ዘርፉን ለገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ነው። ይህም በሴቶች እኩልነት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። የዲጂታል ተደራሽነትን በማስፋት ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።
በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂና በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የጾታ እኩልነት እንዲኖር አካታች የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ለዚህም የጾታ እኩልነትን የተመለከተ ፖሊሲ በመቅረጽና ስትራቴጂ በመንደፍ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመላክተዋል። እሳቸው አንደተናገሩት፤ እ.ኤ.አ በ2017 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የባንክ አካውንት ካላቸው ከአምስት ሰዎች መካከል አንዷ ብቻ ሴት ናት። ለዚህም የመታወቂያ አለመኖር በምክንያት ይጠቀሳል። አነስተኛ ገቢ ካላቸው አገራት 45 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆነ ሴቶች ሕጋዊ መታወቂያ የላቸውም ይላሉ።
ዲጂታል መታወቂያ የጾታ እኩልነትን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም አካታች ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት በመዘርጋቱ ሴቶች ሕጋዊ የመታወቂያ አገልግሎት እንዲያገኙ ሰፊ እድል ይፈጥርላቸዋል ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የሴቶች የዲጂታል እውቀት ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው። በቴክኖሎጂና በዲጂታላይዜሽን ዘርፍም ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ሆኖ ይታያል። ተሳትፏቸው አነስተኛ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ የዲጂታል እውቀትና ክህሎት ማነስ ይጠቀሳሉ።
እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ በሴቶችና በወንዶች መካከል እኩል የሆነ ሶሾዮ ኢኮኖሚ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የሴቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሻሻል ለማድረግ የሴቶችን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የዲጂታል ዘርፉን ለማሻሻል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው፣ በተጨማሪም አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት በሩ ክፋት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ ያመለክታሉ፤ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች መስጠት ለመጀመራቸው ቴሌ ብር አንዱ ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ጥናቱ የዲጂታል ፋይናንሺያል ክህሎት ክፍተትን በመለየት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል። ‹‹ዲጂታል ኢኮኖሚን ከዲጂታል እውቀትና ክህሎት ውጪ ማሰብ የማይቻል ›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለዚህም ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ።
‹‹ዲጂታል ዘርፉን መንግሥት ብቻውን ስለሰራ በዘርፉ የሚፈልገውን እውን ማድረግ እንደማይቻል ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል፤ ስራው የሁሉንም ተቋማት ርብርብ እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ። በአገራችን ያሉ በዲጂታል ላይ ፍላጎት ካላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይ ሴቶች በዲጂታል ዘርፉ ላይ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ‹‹ከተቋማት ጋር አብረን ከሰራን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በአጭር ጊዜ እውን በማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን። ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ደግሞ አዳዲስ የሥራ እድሎችን መፍጠር ይቻላል፤ የውጭ ምንዛሬን መጨመር ይቻላል። አካታች የሆነ ዲጂታል ኢኮኖሚን እንደአገር መገንባት ይቻላል›› ሲሉ አስረድተዋል።
የሴቶች የዲጂታል ተሳትፎ በጣም አነስተኛ ነው የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያው አቶ ሀብታሙ ዳምጤ በበኩላቸው፤ ‹‹የሴቶች ዲጂታል ተሳትፎ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ዓለምን እየመሩ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች አሃዝ ብንመለከት እንኳን የሴት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑን መመልከት ይቻላል›› ይላሉ።
‹‹በተመሳሳይ የቴሌብር፣ የሞባይል ባንኪንግን ተጠቃሚ ሴቶችን ብንመለከት አሃዙ ስለሌለ እንጂ ከዚህ የተለየ ነው ማለት አያስደፍርም›› ሲሉ ገልጸው፣ ሴቶች በዲጂታል ዘርፉ ጎልተው እንዳይወጡ ካደረጉ ችግሮች መካከል ትምህርት ቤት ያለመግባት፣ ሥራ ላይ አለመሳተፍ፣ ወጥቶ መሥራት አለመቻል፣ የተደራሽነትና የግንዛቤ እጥረትን በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ‹‹ለምንም ነገር መሠረት የሚጣለው ከታች ነው›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ ለአብነት ሴቶች መስሪያ ቤት የሚሰሩበት ሁኔታ ቢፈጠር ለዲጂታሉ ዘርፍ ቅርበት ይኖራታል፤ ከቴክኖሎጂ ጋር ግንኙነት ሊኖራት የሚችልበት አጋጣሚም ይፈጥራል ይላሉ።
አቶ ሀብታሙም በዲጂታል ዘርፉ የሴቶች የእውቀትና የክህሎት ክፍተት መኖሩን ይገልጻሉ። በተመሳሳይ በኢንተርኔት አጠቃቀምና ቴክኖሎጂ ላይ ሴቶች የአመለካከት ክፍተቶች እንዳሉባቸው ይናገራሉ። ማህበራዊ ሚዲያን ሀሰተኛ መረጃ የሚወራበትና ስህተት እንደሆነ ብቻ አድርጎ የመመልከት አመለካከት እንዳላቸውም ነው አቶ ሀብታሙ የሚጠቁሙት። በመሆኑም ብዙ ሴቶች ዘመናዊ ስልክ ይዘውና ኢንተርኔት መጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ሆነው አንጠቀምም የሚሉበት ሁኔታ እንዳለ ይጠቅሳሉ።
‹‹ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ለሴቶች ብቻ ተብለው የሚለቀቁት ማስታወቂያዎች እንኳን ብንመለከት በጣም ውድ ናቸው›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ ለዚህም እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆን ነው። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሳይንሱ እንደሚለው ሴቶች በቴክኖሎጂ እድገት ላይ በጣም ወሳኝና ቅርብ ናቸው። ወንዶች በሀርድ ዌር ማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም ሴቶች ደግሞ ለሶፍት ዌር ኮዲንግና ለዌብ ሳይት ዲዛይን ተመራጭ ናቸው።
በዌብ ሳይት ዲዛይን የከለሪንግ እና ፈጠራ የሚጨመርባቸው ሥራዎችን ለመሥራት ሴቶች እንደሚመረጡ ተናግረዋል። አንድ መተግበሪያ ወይም ዌብ ሳይት ለማበልጸግ ኮድ መደረግ ስላለበት ኮድ ማድረግ ደግሞ ረጅም ሰዓት መቀመጥን ስለሚጠይቅ የሴቶች ባሕሪ ለዚህ የተመቸ ነው የሚሉት አቶ ሀብታሙ፣ ቴክኖሎጂን በማላመድ ረገድም ሴቶች በባንክ ሲስተሞች ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ዘርፎች ላይ ተመራጭ እንደሆኑም ይጠቁማሉ።
አቶ ሀብታሙ እ.ኤ.አ በ2023 የተካሄደ ጥናት ያመለከተውን ጠቅሰው ሲያብራሩም፤ ኮዲንግ (ኮምፒዮተር ፕሮግራሞች ላይ የሚሰሩ) ተሳታፊ ሴቶች 27 በመቶ ያህል መሆናቸውን ይናገራሉ፤ በኢትዮጵያ ደረጃ የሴቶች የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሴቶች የኮምፒዩተር ሳይንስ የትምህርት ክፍል ምርጫቸው እንዲያደርጉ ምክረ ሀሳብ ቢለገሱ ውጤታማ መሆን ይቻላል ሲሉም ይጠቁማሉ።
አቶ ሀብታሙ ‹‹የሴቶችን ዲጂታል ተጠቃሚነት የማጎልበቱ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን ይጠይቃል። በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ሌሎች ተፅዕኖዎችን ማስቀረት የሚያስችሉ የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰሩ ሁሉ በዲጂታሉም ረገድ የሴቶችን ግንዛቤ በማሳደግ ውጤታማ ሥራ መስራት ይቻላል›› ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ጎግል፣ ፌስቡክ የመሳሳሉት ተቋማት ለሴቶች ብቻ እያሉ የሚያዘጋጇቸው ስልጠናና ሌሎች እድሎች እንዳሉም ገልፀው፤ ይህንን ወደ አገራችን በማምጣት ማስፋፋት ሴቶች ከቢዝነስና ቴክኖሎጂው ዘርፎች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። ቀደም ሲል የኔትወርክ ፍጥነት፣ የዘመናዊ የስልኮች ተደራሽነት አለመስፋት እና ብዙ አይነት የገንዘብ ዋሌቶችና የመሳሰሉ ፕላትፎርሞች አለመኖር ወደኋላ ሲጎትቱን ቆይተዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ እነዚያ ወደኋላ ሲጎትቱ የነበሩት ችግሮች መቀረፋቸውን ተናግረዋል፤ አሁን ላይ ያለው የግንዛቤ እጥረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰዎች ላይ መሠራት አለበት። ግንዛቤ ላይ ከተሰራ ደግሞ ለውጥ በማምጣት ውጤታማ መሆን ይቻላል›› ይላሉ።
‹‹ኢንተርኔት ሁሉም ነገር መማሪያ ነው፤ ያለንን እውቀት ማሳደግ የሚቻልበት ነው›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የዕለት ከዕለት ሕይወት ቀላል የሚያደርግ በመሆኑ ሴቶች ለቴክኖሎጂ ቅርብ ከመሆናቸው አንጻር ቢጠቀሙ ራሳቸውን ተጠቅመው ለአገርም ይጠቅማሉ ብለዋል። ሴቶች የራሳቸውን ቢዝነስ ለመስራት፣ ያለባቸውን የሥራ ጫና ለማቅለል፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሳር ቀላል ለማድረግ ቢችሉ መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2015