የምግብ ደህንነት – በሁላችን ኃላፊነት

ምግብ በዓለም አቀፍ የንግድ ምህዋር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ነው። ከእርሻ እስከ ጉርሻ የምግብ ደህንነት ጉዳይም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እጅግ ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጠው ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል:: በተባበሩት መንግሥታት የ2023 የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ስድስቱ ከምግብ ደህንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ናቸው::

የምግብ ደህንነት በተለይ የምግብ ዋስትናም ሆነ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ጋር አብሮ ሊታሰበብት የሚገባ ነው:: በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ደህንነት በተለይ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀል፣ ሕገ ወጥ የምግብ ዝውውር፣ ምግብ ላይ የሚሠሩ ወንጀሎች ወይም FOOD CRIME የበርካታ ሀገራት ራስ ምታት ሆኗል::

በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ እንቅስቃሴ ማደግን ተከትሎ ምንጫቸው ያልታወቀ፣ ከባዕድ ነገር ጋር የተደባለቁ እንዲሁም የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ጤናና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የምግብ ምርቶች ስርጭት በዚሁ መጠን ጨምሯል:: የምግብ ምርቶች ደህንነት የሚያሳጡ ፣ የባዕድ ነገር ክለሳ /Food adulteration/ና የክለሳ ዓይነቶችም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሰዋል::

የምግብ ደህንነት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ሲሆን ያልተገባ ጥቅም ለማካበት በማሰብ ወይም በቸልተኝነት ወይም በማምረት፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝ እና ለሽያጭ በማቅረብ ሂደት ውስጥ ተገቢውን የጥረትና ደህንነት ጥንቃቄ ባለማድረግ ሊከሰት ይችላል::

ይሁንና አንዳንዶች ሆን ብለው (Intentionally /Deliberately) ተጨማሪ ትርፍ ለማግኘት ፣ያለአላግባብ ለመበልፀግ ፣ ክብደቱንና ይዘቱን ለመጨመር ፣ ዝቅተኛ ዋጋዎችን በማሳየት የንግድ ገቢን ለማሳደግ ፣ የሕብረተሰቡ የመግዛት አቅም ሲቀንስ /ሲጨምር ፣በዝቅተኛ ዋጋ የገበያውን ውድድር ለማሸነፍና በመሳሰሉት ምክንያቶች ምግብን ደህንነት ሊያሳጡ ይቻላል::

ይህ አይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር ትርፋማነትን ለማሳደግ በአቋራጭ ለመክበር ሲባል አፍቃሬ ነዋይ ያለባቸው፣ ተአማኒነት የጎደላቸው የሚያደርጉት ድርጊት ነው:: ሠብዓዊነትን ወደ ጎን በመተው እና ገንዘብን የሚያስቀድሙ የዘርፉ ተዋናዮች መገለጫ ነው::

የምግብ ደህንነትን ማስጠበቅ ባለመቻል በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታዎች ይጠቃሉ:: ምግብ ወለድ በሽታዎች በተለይ ህጻናትን፣ እርጉዝ ሴቶችን፣ አረጋውያንን እና የበሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመባቸውን ሰዎች ያጠቃሉ:: ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምግብ በተለያዩ መንገዶች ለጤና ችግሮች ከፍ ሲልም ለሞት ይዳርጋሉ::

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ ወለድ በሽታዎች ሲጠቁ፣ 420 የሚሆኑት ደግሞ ይሞታሉ:: ከዚህም ውስጥ ከ125ሺህ የሚበልጡ ህጻናት የምግብ ወለድ በሽታዎች ሰለባ ይሆናሉ:: እነዚህ አኃዞችም የምግብ ደህንነት ችግሮች ዓለም አቀፋዊ የጤና ቀውስ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያሉ::

ዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስምምነቶችና መመሪያዎች ተፈጻሚ ሆነዋል:: እነዚህም የምግብ ምርት፣ ማከማቻ፣ ማጓጓዣ እና ስርጭትን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያካትታሉ:: ለምሳሌ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የምግብ ደህንነት መመሪያዎችን በማውጣት ሀገራት እንዲተገብሯቸው ይመክራል:: የCodex Alimentarius Commission ዓለም አቀፍ የምግብ ደረጃዎችን እና መመሪያዎችን ያዘጋጃል::

እነዚህ ስምምነቶች የምግብ ደህንነት ሥርዓቶችን ለማጠናከር እና ዓለም አቀፍ የምግብ ንግድን ለማመቻቸት መሠረት ይጥላሉ:: ሀገራት እነዚህን ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ተግባራዊ በማድረግ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የምግብ ወለድ አደጋዎችን ለመቀነስ ይጠቀማሉ:: ዓለም አቀፍ ትብብር የምግብ ደህንነትን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥን እና ምርምርን በማበረታታት ለሁሉም ሀገራት ጠቀሜታ አለው::

ኢትዮጵያ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሕጎችን እና መመሪያዎችን አውጥታለች:: የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) የምግብ ደህንነትን የሚቆጣጠር እና የሚያስተባብር ቁልፍ ተቋም ነው:: ባለሥልጣኑ የምግብ ምርቶችን ጥራት እና ደህንነት ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎችን ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ሲሠራ ቆይቷል::

የምግብና የመድኃኒት አዋጅ ቁጥር 1112/2011 የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጠንካራ ድንጋጌዎችን ይዟል:: ይህ አዋጅ በዋናነት ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት በኅብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳት መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ የወጣ ሲሆን በተለይ ምግብን በተገቢው መንገድ በማምረት፣ በመያዝ፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝ ወይም ለተጠቃሚ በማቅረብ ሂደት ምግቡ ለጤና ተስማሚ እንደሆነ የሚረጋገጥበት አሠራር የሆነውን የምግብን ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ መሠራት እንዳለበት ይደነግጋል።

በአዋጁ አንቀፅ 4 ንዑስ አንቀፅ 6 ለአስፈጻሚ አካል በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣንንና የክልል የጤና ግብዓቶች ተቆጣጣሪ አካላት ቁጥጥር የሚደረግበት ምርት በመከለሱ ወይም በሌላ ሕገ ወጥ ድርጊት ምክንያት ሞት፣ ሕመም፣ የአካል ጉዳት፣ የጤና መታወክ ወይም ሌላ የጤና ችግር ያስከተለ ምርትን ወይም ይዘትን ይለያል፣ በናሙናው ላይ ጥናት ያደርጋል፣ ውጤቱን መሠረት በማድረግ አስፈላጊውን ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ በግልፅ ተቀምጧል::

በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እንደተመላከተውም፣ ለሰው ጤናና ደኅንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ ወይም የተመረዘ፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቀ የንግድ ዕቃን ወይም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ በወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ነው::

እነዚህ ሕጎች የምግብ ንግድን ለመቆጣጠር፣ የምግብ ብክለትን ለመከላከል እና ሸማቾችን ለመጠበቅ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው:: የአዋጁ ትግበራ ከፌዴራል እስከ ክልል ባሉ አወቃቀሮች አማካኝነት እየተካሄደ ሲሆን፣ የቁጥጥር ባለሙያዎች አቅም በማጎልበት እና ሕገወጥ የምግብ ምርቶችን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል::

በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ቁጥጥርን ለማጠናከር የምርት ምዝገባ፣ የመልካም አመራር ሥርዓትን በማስተግበርና የምግብ ደረጃዎችን ማስከበር ጨምሮ ውጤታማ የሚባሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል:: የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለአብነት በሀገሪቱ የምግብ ወለድ በሽታዎችን እየቀነሱ ስለመምጣታቸው ጥናቶች አሳይተዋል::

ይሁንና ከምግብ ዘርፉ አድማስ ሰፊነትና ከጊዜ ወደ ጊዜ በአይነትም በረቂቅነቱም እየጨመረ ከመጣው ሕገ ወጥ ተግባር አንጻር የምግብን ደህንነት የማረጋገጥ ተግባር ከተጠቃሚው ጀምሮ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ቅንጅት የግድ የሚል ይሆናል።

‹‹የምግብ ደህንነትን ማረጋገጥ ወቅቱ የሚጠይቀው የሁላችም የቤት ሥራ ሊሆን የግድ ነው›› የሚሉት የዘርፉ ምሁራንም የምግብ ደህንነትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው ሲሉ የሚጠቁሟቸው የተለያዩ የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦችም አላቸው::

የህብረተሰብ ግንዛቤ ማሳደግ፣ ህብረተሰቡ ስለ ምግብ ደህንነት መርሆዎች እና ልማዶች በቂ እውቀት እንዲኖረው ማድረግና የምግብ አያያዝን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃዎችን ማሰራጨትም ከመፍትሄዎቹ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው:: በተለይ ስለ ንጽህና አጠባበቅ፣ ስለምግብ አበሳሰል፣ ምግብን ከአደጋ በሚከላከሉ የሙቀት መጠኖች ማቆየት፣ እና የምግብ ብክለትን ለመከላከል ስለሚረዱ መንገዶች ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ::

የምግብ አያያዝ ልማዶችን ማሻሻል፡ ምግብን በአግባቡ ማብሰል፣ ማከማቸትና ማጓጓዝ የምግብ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል:: ይህ በተለይ የቤት ውስጥ የምግብ አያያዝ ልማዶችን ያካትታል:: ምግብ ከመዘጋጀቱ በፊትና በኋላ እጅን መታጠብ፣ የተበከሉ ምግቦችን ከጥሬ ምግቦች መለየትና ምግቦችን በሚመከረው የሙቀት መጠን ማብሰል ቁልፍ ተግባራት ናቸው::

ሕጎችን እና መመሪያዎችን ማጠናከር፣ የምግብ ደህንነት ሕጎችን በማውጣት እና ተፈጻሚነታቸውን በማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ተጠያቂነት ማሳደግ ከወሳኝ ምክረ ሃሳቦቹ መካከል የተካተተ ነው:: ይህ የመንግሥት አካላት፣ የምግብ ኢንዱስትሪዎች እና የምግብ አገልግሎት ሰጪዎችን ያጠቃልላል:: የሕግ አስከባሪ አካላትም ጠንካራ ቁጥጥር በማድረግ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምግብን ከገበያ ማስወገድ አለባቸው::

የምርመራና ቁጥጥር ሥራዎችን ማጠናከር፣ የምግብ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት የሚቆጣጠሩ ተቋማትን አቅም ማጎልበት የግድ ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ:: ዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎችና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የላቦራቶሪ ምርመራ አቅምን ማሳደግ እና የምግብ ሰንሰለቱን በሙሉ መቆጣጠር የግድ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ::፡

ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ከወሳኝ መፍትሄዎች መካከል የሚካተት ነው:: የምግብ ደህንነት ዓለም አቀፍ ጉዳይ በመሆኑ ሀገራት የምግብ ደህንነት ስጋቶችን ለመቋቋም በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል:: የመረጃ ልውውጥ፣ የጋራ ምርምር እና የድንበር ተሻጋሪ የምግብ ደህንነት ስጋቶችን በጋራ መፍታትም እጅጉን ወሳኝ ነው::

የምግብ ብክነትን መቀነስ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብን በአግባቡ በመጠቀም እና ብክነትን በመቀነስ የምግብ ሀብቶችን ማዳን ይቻላል:: የምግብ ደህንነት ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና የምርምር ውጤቶችን መጠቀም ወሳኝ አቅም የሚፈጥር ነው::

እንደ ሀገር የምግብን ደህንነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት መሰል የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያ ምክር ሃሳቦችን በመተግበር ረገድ ሁሉም ተሳታፊ ሊሆን የግድ ይላል:: ለአብነትም አመጣጡ የማይታወቅ የምግብ ምርትን መጠቀም ሊቆም የግድ ይላል::

ምርት ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ በአግባቡ ማወቅና ይህን በአግባቡ በመረጃ አስደግፎ ማቅረብና መያዝ ተገቢ ነው:: ከሁሉ በላይ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የመልካም አምራችነትን መንገድ መከተል ተገቢ ነው። ግብርናን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ምርት እና ምርታማነት ለማስጨመር ተባይን ለማጥፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የማዳበሪያ ኬሚካሎች አጠቃቃም በየጊዜው በአግባቡ መከታተል ይኖርባቸዋል። ተቆጣጣሪው አካልም አስቀድሞ ሥራዎችን መሥራት አለበት። የምግብ ጥራትና ደህንነት ለመመርመር የሚያስችል ጠንካራ አቅም መገንባት ለእዚህም የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን ማብቃት፣ መሣሪያዎች በአግባቡ ማሟላት ተገቢ ነው::

በሌሎች ሀገራት የመንገድ ዳር የምግብ ንግድ ሳይቀር እውቀትና የሙያ ማረጋገጫን የግድ የሚል ነው። ከፋይናንስ ጀምሮ ሁለንተናዊ አቅምንም ይጠይቃል:: ይሁንና በኢትዮጵያ የምግብ ዘርፉ ማንም እንደፈለገ የሚገባበት ሲሆን፤ ይስተዋላል:: ይህ መታረም አለበት:: ፈቃድን ጨምሮ በሌሎች የሕግ ማሕቀፎች የታጀበ ሊሆን ይገባል::

ይህ ማለት ግን ከምግብ ደህንነት አንፃር ጠንካራ የሕግ ማሕቀፍ የለም ማለትም አይደለም:: ይሁንና የሕግ ማሕቀፎችን በአግባቡ በማስተግበር ረገድ ኃላፊነት የጣለባቸው ባለድርሻ አካላት ሚና መደራረብና የቅንጅታዊ አሠራር ድክመት እንዳለባቸው በግልጽ ይስተዋላል:: ይህም የቁጥጥር ሥራ ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ቅንጅታዊ አሠራሩ ሊፈተሽና ሊስተካከል ይገባል::

በምግብ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት ከአምራቾች እስከ ሸማቾች የምግብ ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ የራሳቸው ድርሻ አለባቸው:: ይህ የተቀናጀ ጥረት የምግብ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል እና የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ ነው::

በዘርፉ የተሰማሩ የምርምር ተቋማት ሳይንስን መሠረት አድርገው የሚያከናውኗቸው ጥናቶች ምግብን ከእርሻ እስከ ተጠቃሚ ድረስ ባለው ሰንሰለት በአግባቡ በማዘጋጀትና በማቅረብ፣ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በመጠቆምና ይህ ባለመሆኑ ሊደርስ የሚችለውንም የጤና ችግር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት ደህንነቱ የተረጋገጠ ምግብ እንዲቀርብና ለሀገራዊ ምርቶች ሳይንስን መሠረት ያደረጉ ሀገራዊ ደረጃዎች እንዲወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል::

መገናኛ ብዙኃን ምግብን ደህንነት ለማስጠበቅ ከእርሻ እስከ ጉርሻ እንዲሁም ከርባታ እስከ ገበታ ያለውን የምግብ ደህንነት ሥራ ኅብረተሰቡ በየደረጃው እንዲያረጋግጥ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡም ይገባል:: ህብረተሰቡን በማስተማር፣ መልእክቶችን በማስተላለፍ፣ እና የምግብ ደህንነት ጉዳዮችን በመዘገብ፣ የምግብ ደህንነት ስጋቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ መረጃዎችን እና ምክሮችን ለህብረተሰቡ ማቅረብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግም ይኖርባቸዋል::

ሸማቾችም፣ ምርቶቹን በሚገዙበት ወቅት ከተለምዶው የተለዩ መጥፎ ባሕሪያትን የሚያሳይ ከሆነ፣ በተለይም ምግቦቹ የጣዕም፣ የይዘት፣ የመጠንና የሽታ ልዩነት ካላቸው፤ የምግብ ክለሳ ችግሮች ሲያጋጥሙ/ ሲከልሱ ወይም እንደዚህ አይነት መሰል ጥርጣሬዎች ሲኖራቸው ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ወይም ለክልል ተቆጣጣሪ አካላት ጥቆማ ማቅረብን መዘንጋት አይኖርባቸውም::

የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን፣ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ የፊታችን ቅዳሜ ይከበራል:: ይህ ቀን ህብረተሰቡ ስለ ምግብ ደህንነት ያለውን ግንዛቤ እንዲያሳድግ እና የምግብ ደህንነትን በተመለከተ ያሉትን ችግሮች እንዲያውቅ ታስቦ ነው:: በዚህ ቀን የሚዲያ ዘመቻዎች፣ የሕዝብ ውይይቶች፣ አውደ ጥናቶች እና ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ::

በዚህ ቀን የሚከናወኑ መርሃ ግብሮችም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ የመንግሥት አካላት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የምግብ ኢንዱስትሪዎችና ህብረተሰቡ የምግብ ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ ያለባቸውን ሃላፊነት በሚወጡበት መንገድ ላይ ትኩረት ይደረጋል:: ዓላማው ሁሉም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተመጣጠነ እና በቂ ምግብ ማግኘት እንዲችል ማስቻል ነው::

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You