
ኤለን መስክ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የግብር እና የወጪ ሕግ “አሳፋሪ እና አስጸያፊ” ሲል ኮነነው። የባለብዙ ትሪሊዮን ዶላር የታክስ እፎይታ እና ተጨማሪ የመከላከያ ወጪዎችን ጨምሮ የአሜሪካ መንግሥት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲበደር የሚፈቅደው ይህ ሕግ በግንቦት ወር በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጹ ላይ በለጠፈው ጽሑፍ ላይ “ይህንን ሕግ ለማጽደቅ ድምጻቸውን የሰጡ ያሳፍራሉ” ብሏል። ቢሊየነሩ መስክ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ዶጅ ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለ129 ቀናት ወጪን ለመቀነስ ከሠራ በኋላ በድንገት አስተዳደሩን መልቀቁ ይታወሳል። ኤለን መስክ ቀደም ሲል እቅዱን “አሳዛኝ” ብሎ የጠራው ቢሆንም፣ አሁን የሰጠው አስተየየት ግን የመንግሥትን ኃላፊነት ከለቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያለውን አለመግባባቱን ያመለክታል።
ደቡብ አፍሪካ የተወለደው ቢሊየነሩ መስክ ምንም እንኳን ትራምፕ “ሁልጊዜም ከእኛ ጋር በመሆን በሁሉም መንገድ ይረዳናል” ቢሉም፣ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ያለው ሥልጣን ከቀናት በፊት ግንቦት 23/2017 ዓ.ም. አብቅቷል። ትራምፕ “ግዙፍ ቆንጆ ሕግ “ ብለው የሚጠሩት ይህ አዋጅ መንግሥታቸው ያለበትን የበጀት ጉድለት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚያደርገው ተገምቷል ።
ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገፁ ላይ በተከታታይ ባጋራቸው ልጥፎች ላይ መስክ “አስፈሪ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ወጪን ለመሸፈን” የወጣ ሕግ “ቀደም ሲል ያለውን ግዙፍ የበጀት ጉድለት ወደ 2.5 ትሪሊዮን ዶላር (!!!) በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል” እንዲሁም “ የአሜሪካ ዜጎችን በሚያስደነግጥ አስተማማኝ ባልሆነ እዳ ይጫናቸዋል” ሲል ተችቶታል።
ከዚህ ቀደም የትራምፕን አጀንዳ በሚቃወሙ ሪፐብሊካን የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ቃል ገብቶ የነበረው መስክ በሌላ ልጥፍ ላይ ከዚህ በተቃራኒ የቆመ የፖለቲካ ማስጠንቀቂያ አክሎ ተናግሯል። “በሚቀጥለው ዓመት ሕዳር ወር ላይ የአሜሪካን ሕዝብ የከዱ ፖለቲከኞችን በሙሉ እናባርራለን” ሲል ጽፏል። ከመጀመሪያው ጽሑፍ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ስለ መስክ አስተያየት የተጠየቁት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሌቪት “ፕሬዚዳንቱ ኤለን መስክ በዚህ ሕግ ላይ ያለውን አቋም ያውቃሉ” ማለቷን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም