የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ 7ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ 7 የፕሬዚዲየም አባላቱን መረጠ።
ጉባዔው፦ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር- ሰብሳቢ
ኢንጂነር አይሻ መሃመድን- ምክትል ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል።
በተጨማሪም፦አሊ ሁሴን ወኢሳ፣ አወል አርባህ፣ ዘሃራ ሁመት፣ አባሂና ኮባ እና አህመድ ሱልጣንን የፕሬዝዲየሙ አባላት በማድረግ ሰይሟል።
እስከ ነገ የሚቆየው የአብዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ ላለፉት 3 አመታት በተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ በተዘጋጀው ሪፖርት ላይ ጉባኤተኞቹ የቡድን ውይይት እንዲያካሄዱበት መርቷል።
የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያ ፓርቲ /አብዴፓ/ 7ኛ መደበኛ ጉባዔ በትናንትናው እለዐት ነው በሰመራ ከተማ መካሄድ የጀመረው።
በጉባዔው መክፈቻ የአብዴፓ ሊቀመንበር ሃጂ ስዩም አወል፤ ድርጅቱ ከምስረታው ማግስት ጀምሮ የአፋርን ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የአርብቶ አደሩን ህዝብ ኑሮ ለመለወጥ ባደረጋቸው ጥረቶች ድሎች ቢመዘገቡም የክልሉን ህዝብ ኑሮ በሚፈለገው ደረጃ ለውጧል ማለት ግን አይቻልም ብለዋል።
ስትራቴጂክ አመራር፣ የውስጠ ድርጅታዊ ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት፣ የተደራጀ ሌብነት እንዲሁም የግልና የቡድን የስልጣን ሽኩቻዎች ድርጅቱን በተለያዩ ጊዜያት የተፈታተኑት ነገሮች እንደነበሩም አንስተዋል።
ለዚህም አብዴፓ በቅርቡ ባካሄደው ኮንፈረንስ ከመግባባት ላይ የደረሰ መሆኑና በ7ኛው ድርጅታዊ ጉባዔም የሪፎርም ስራዎች እንደሚኖሩ የተወሰነ መሆኑን ገልፀዋል።
በጉባዔው መክፈቻ ኢህአዴግን ጨምሮ የኦዴፓ፣ ህወሃትና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ተወካዮች የድጋፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ይሆናል ነው የተባለው።
በቆይታውም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በመገምገም፥ ነባር የድርጅቱን አባላት በክብር ይሸኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በሚሸኙ አባላት ምትክም ሴቶችን ያሳተፈ፣ ወጣትና የተማረ ኃይልን ወደ አመራርነት በማምጣት የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲጠናከር ይደረጋል ተብሏል።
አብዴፓ ከዚህ ጉባዔ አስቀድሞ ሰመራ ላይ ባካሄደው ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ፥ የታችኛው፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሩ በክልሉ ለማስመዝገብ አቅዶት የነበረውን ልማት አለማሳካቱን መገምገሙ ይታወሳል።
ጉባኤ የሚደረገው መተካካትም ግምገማውን ተከትሎ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።
አብዴፓ እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ በአፋር ክልልም ለማስቀጠል ቁርጠኛ አቋም ላይ መድረሱንም ተጠቅሷል።
ከፍተኛ የድርጅቱ አመራር የአገልግሎት ዘመንም ከ10 አመት በላይ እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችል የገደብ ሰነድ ቀርቦ በአባላቱ ውይይት ይደረግበታል።
በድርጅታዊ ጉባዔ 700 አባላት የሚታደሙ ሲሆን 594ቱ በድምፅ የሚሳተፉ ናቸው ሲል የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።