ከየካቲት እስከ ግንቦት፣በበጋው ደግሞ ጥቅምትና ኅዳር ወራት ያሉት ወቅቶች መደበኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ሶማሌ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል ቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ቆላማ አካባቢዎች ወሳኝ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በእነዚህ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት በነዚህ ወቅቶች ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ባለመጣሉ አካባቢዎቹ ለከፋ ድርቅ ተጋልጠው እንደነበር ይታወቃል፤በድርቁም የሰው ሕይወት ባያልፍም ከፍተኛ ጉዳት ግን ደርሷል፤ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና በሶማሌ ክልል የተለያዩ ዞኖች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶች ማለቃቸውን መረጃዎች አመልክተዋል። በቅርቡም በድርቁ ከ6 ሚሊዮን በላይ ከብቶች መሞታቸውን መረጃዎች አመላክተዋል።
ድርቁ አንዳንድ የበልግ አብቃይ አካባቢዎችንም በእጅጉ ማጥቃቱ ይታወቃል። በእነዚህ አካባቢዎች ወይ ዝናቡ ባለመጣሉ አልያም ዘግይቶ በመጣሉ የተነሳ በግብርና ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተያዘው የበልግ ወቅት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ መጣሉን የኢትዮጵያ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል። የጣለው ዝናብ ለእርሻ ሥራም ለከብቶች መኖ ለማግኘትም በአረንጓዴ አሻራ ለተተከሉ ችግኞችና ለአጠቃላይ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው የሚትዎሮሎጂ ባለሙያዎች የሚናገሩት።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትም የአየር ጠባይን በመተንተን አስቀድሞ መረጃ ሲሰጥ ቆይቷል። የበልግ ዝናብ ሊዘገይ እንደሚችል፣ሲመጣም ሊኖረው የሚችለውን አዎንታዊ ተጽዕኖ በየጊዜው ያሳውቅም ነበር፤ በዚህ ላይ በመመሥረትም ነው የበልግ የግብርና ሥራ በተለያየ መንገድ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ የተገባው።
በሁሉም የበልግ አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጥሩ የሚባል የዝናብ ስርጭት እንደተገኘ ከየአካባቢው የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። የግብርና ሥራውም በቅድመ እቅዱ መሠረት እየተከናወነ እንደሆነም እየተጠቆመ ይገኛል።
የበልግ የግብርና ሥራ ሦስተኛ ወሩን ጀምሯል። ስለ ቅድመ እቅዱና አሁን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣በግብርና ሥራው ለሚያጋጥሙ ያልተጠበቁ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ስላለው ዝግጁነት እንዲሁም ስለሚጠበቀው ውጤት የበልግ አብቃይ ከሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ የሆነውን የኦሮሚያ ክልል እንቅስቃሴ በዛሬው የግብርና ዓምዳችን እንቃኛለን።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ እንዳሉት፤ ወደ 10 የሚሆኑት የክልሉ ዞኖች በልግ አብቃይ ናቸው። በዞኖቹም ወደ አንድ ነጥብ አንድ ሚለዮን ሄክታር መሬት በተለያየ ዘር በመሸፈን ምርት ለመሰብሰብ ነው በቅድመ እቅድ የተያዘው። በቅድመ እቅድ ሥራውም ለአርሶ አደሩና ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጡ የግብርና ባለሙያዎችን በሥልጠና የማዘጋጀት ሥራ በማከናወን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተካሂዷል፤ የግብዓት አቅርቦትም አስቀድሞ ነው የተከናወነው። ክልሉ የግብዓት አቅርቦት ሥራውን ያከናወነው የመኸር የግብርና ሥራን ታሳቢ በማድረግም ጭምር ነው።
በዚሁ መሠረትም ወደ ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማስገባት አቅዶ በማስገባት ላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም ወደ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ገብቶ ለበልጉ ሥራ እንዲውል እየተደረገ ነው። የፀረተባይና ተያያዥ የሆኑ የግብርና ግብአቶችም በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ ይገኛሉ። ግብአቶቹም በገበሬዎች መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች አማካኝነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል።
እሳቸው አንዳሉት፤ በዚህ በኩል በእስካሁኑ የበልግ ግብርና ሥራ ያጋጠመ ክፍተት የለም። በምርጥ ዘር አቅርቦት ረገድም ቢሆን የበቆሎ ምርጥ ዘር ወደ 47ሺ ኩንታል፣ የስንዴ ምርጥ ዘርም ከ20ሺ ኩንታል በላይ ተሰራጭቷል። የማሰራጨቱ ሥራ በአግባቡ እንዲከናወንም በዞንና በወረዳ ግብረ ኃይል ወይም ታስክ ፎርስ ተቋቁሞ ነው እየተሠራ ያለው።
ግብረ ኃይሉ መረጃዎችን በመሰብሰብ ችግሮች በሚያጋጥሟቸው አካባቢዎች በመገኘት የሚፈታ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ ያለው ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ በመሆኑ የበልግ የግብርና ሥራ ውጤታማ እንደሚሆን ከሥራው ሂደት መገምገም ተችሏል ይላሉ።
በዚህ የበልግ ወቅት በስፋት የሚከናወነው የሰብል ልማት በቆሎና ስንዴ እንደሆነ ይታወቃል።ባለፉት የግብርና ወቅቶች ደግሞ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳለ በስፋት ይነሳ ነበር። ይነሳ የነበረው ክፍተትም የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደመሆኑ ክልሉ በፀጥታ ስጋት ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይታወሳል።
እዚህ ላይ አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ለአቶ በሪሶ አንስተንላቸው በሰጡት ማብራሪያ ፤ ከበቆሎ ምርጥ ዘር አንዱ የሆነው ‹ኦነር› የሚባለው የበቆሎ ምርጥ ዘር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ፣ ጅማ ላይ ነው የሚገኘው ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህ ዘር በስፋት በአርሶ አደሩ የሚፈለግ በመሆኑ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር የተጣጣመ አለመሆኑ እንጂ ዘሩን መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል። የሚፈለገውን ያህል ግን አይደለም ሲሉም ጠቁመዋል።
አቶ በሪሶ ይህን ዘር ሊተኩ የሚችሉ ምርጥ ዘሮች ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ዘሮቹ በምርታማነታቸው፣በውስጣቸው በያዙት ንጥረ ነገር፣የምግብ ፍላጎትን በማሟላትና በገበያ ላይ ባላቸው ተፈላጊነት የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህ ረገድም ባለሙያውም ሆነ አርሶ አደሩ በቂ ግንዛቤ ይዞ ዘሮቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው። ከአንድ መቶ ሺ ኩንታል በላይ እንዲዘጋጅ ተደርጎ ከዚህ ውስጥም ወደ 47ሺ ኩንታል ተሰራጭቷል። ከምርጥ ዘር ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዚህ መንገድ አማራጮችን በመፈለግ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ የግብርና ሥራ ቅድመ ዝግጅቱ በዚህ መልኩ ነው እየተከናወነ የሚገኘው።
በክልሉ የበልግ የግብርና ሥራው በቅድመ እቅዱ መሠረት እየተከናወነ እንደሆነ የጠቆሙት የክልሉ ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በሪሶ፣ በእስካሁኑ ሥራም በእቅድ የተያዘው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት የማረስ ሥራ ተጠናቅቋል ማለት ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል። እስከ አለፈው ሳምንት መጀመሪያ ድረስም 700ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር መሸፈኑን አስረድተዋል።
እንደ ክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገለጻ፤ ከቅድመ እቅድ እስከ ክንውን ያለው ሥራ ግምገማ የአርሶ አደሩ ዝግጁነት፣የባለሙያው ድጋፍና አመራሩም እየሰጠ ያለው አቅጣጫ በድምሩ ውጤታማነቱን ያመላክታል። ከቀደሙት ተመሳሳይ ወቅቶች ጋር የተከናወነው ሥራ በንጽጽር ሲቀርብ በሁለንተናዊ እንቅስቃሴም ሆነ ባለው የዝናብ ስርጭት የተሻለ ነገር መኖሩን በግምገማ ተለይቷል።
በኦሮሚያ ክልል በልግ አብቃይ ከሚባሉ አካባቢዎች አርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር የሚኖርበት ጉጂ ዞን አንዱ ነው። በአካባቢው በተከታታይ ለአራት ዓመታት ባጋጠመ የዝናብ እጥረት ለድርቅ በመጋለጡ እንስሳት መኖ ማጣታቸው፣ አርሶአደሩም ባለማምረቱ በእጅጉ መጎዳቱ ይታወቃል። በዚህ የበልግ ወቅት አካባቢው ላይ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ አቶ በሪሶ ላቀርብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በምሥራቅ ጉጂም ሆነ በምዕራብ ጉጂ ላይ የዝናብ ስርጭቱ ጥሩ ነው መሆኑን ነው የገለጹልን። ምዕራብ ጉጂ በዚህ ወቅት የበቆሎና ስንዴ ልማቱ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ከአካባቢው ከፍተኛ የሚባል ምርት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። የዘር አቅርቦቱም በአርሶ አደሩ ጭምር እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል። በከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢም ለእንስሳቱ የሚሆን የሳር ግጦሽ በዝናቡ አማካኝነት እየተገኘ ነው ያሉት ኃላፊው ፣ በአካባቢው የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ በኃላፊነት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በግብርና ሥራ ውስጥ ያልተጠበቁ የተፈጥሮ ክስተቶች መኖራቸው ተፈጥሮዓዊ ነው። ሰው ሠራሽ ችግርም ቢሆን በሥጋትነት ይጠቀሳል። ግን ዝግጁ መሆን ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ስላለው ዝግጁነትም አቶ በሪሶ ሲያብራሩ ፡- በተፈጥሮ ከሚጠበቁት ወይንም እንደስጋት ከሚነሱት የዝናብ ማነስና መብዛት አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ።
በዚሁ መሠረትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በአንዳንድ ቦታ የዝናብ መብዛት፣ በአብዛኛው ግን መደበኛ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ትንበያ መስጠቱን አቶ በሪሶ አስታውሰዋል። ቢሮው የትንበያ መረጃውን መሠረት በማድረግ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ውሃ ከማሳ ውስጥ የማስወጣትና በተለያየ ዘዴ የሰብል ልማት ሥራው እንዲከናወን እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል። የልማት ሠራተኛው ከአርሶ አደሩ እንዳይርቅ፣ አርሶ አደሩም ተግቶ እንዲሠራ በማድረግ በዝናብ መብዛት በኩል ያለውን ስጋት ለመቀነስ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
እንደ አቶ በሪሶ ማብራሪያ፤ የዝናብ እጥረት ያጋጥማቸዋል ተብለው በተለዩት አካባቢዎችም የሚደረገው ጥረት ተመሳሳይ ነው። አርሶ አደሩ የውሃ ጠብታን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውል ግንዛቤ በመፈጠሩ በተለያየ አጋጣሚ የተገኘውን የዝናብ ጠብታ ወደ ማሣ በማስገባት ጥቅም ላይ እንዲያውል በክትትልና ድጋፍ እየታገዘ እንዲከናወን አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው።
በዚህ ወቅት ሰው ሠራሽ ችግር ተብሎ እንደስጋት የሚነሳው ከአለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንደሆነም ኃላፊው ጠቁመው፣ ይህንንም ባለው የመንግሥት መዋቅርና በተደራጀ አሠራር እንዲሁም የግንዛቤ ሥራዎችን በመሥራት ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ይሆናል ብለዋል።
እሳቸው አንዳሉት፤ እስካሁን ባለው ግን የበልግ የግብርና ሥራን የሚያስተጓጉል የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች አላጋጠሙም። አሁን እየተደረገ ባለው የበልግ የግብርና ሥራም በሁሉም ሰብል 22ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ነው በቅድመ እቅድ የተያዘው። በክልሉ በተፈጠረው ምቹ የአየር ፀባይና ከላይ እስከታች በንቅናቄ እየተከናወነ ባለው ሥራ እቅዱ ይሳካል የሚል እምነት ተጥሏል።
ስለግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም በስፋት የሚነሳው በመኸሩ እና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ቁርጠኝነት በተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የግብርና ወቅቶች ነው። በበልጉ ላይ ያለው ተሞክሮ ፣ምን እንደሚመስል አቶ በሪሶ እንደገለጹት፤ በክልሉ በየትኛውም የግብርና ሥራ ወቅቶች የግብርና ሜካናይዜሽንን መጠቀም የተለመደ ነው። በልግ አብቃይ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች አርሲና ባሌ፣ምሥራቅና ምዕራብ ሐርጌና ጉጂ ዞኖች፣ ምሥራቅ ሸዋ በከፊል የግብርና ሜካናይዜሽን በስፋት ይጠቀማሉ። ለበልጉ የእስካሁን የግብርና እንቅስቃሴ ጥሩ የሆነ ውጤት መታየት የግብርና ሜካናይዜሽን ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።
አቶ በሪሶ አያይዘውም ከዚህ የበልግ ግብርና ሥራ ጎን ለጎን የሚጠበቀው ሥራ የደረሰውን የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት አዝመራ ከሥር ከሥር መሰብሰብ ነው፤ ይህም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ወደ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ነው ለበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ተዘጋጅቶ በዘር የተሸፈነው የሚሉት አቶ በሪሶ፣ ከዚህ ውስጥ ከሦስት መቶ ሺ ሄክታር መሬት በላይ የሚሆነው ሰብል ለመሰብሰብ መድረሱን አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥም ከግማሽ ሄክታር መሬት በላይ ከሚሆነው ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው፣ እንቅስቃሴውም ጥሩ የሚባል ነው ይላሉ።
ክልሉ የሁለቱን የግብርና ሥራ ወቅቶች ብቻ ሳይሆን ለዋናው የመኸር የግብርና ሥራም ከወዲሁ እየተዘጋጀ መሆኑንም አቶ በሪሶ ጠቅሰዋል። በመኸሩ ወደ አንድ መቶ ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። ክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሀገራዊ የምርት መጠንን ከፍ ለማድረግ በግብርና ሥራው ከባለሙያ ጀምሮ እስከ በላይ አመራር ትኩረት መሥጠቱን ጠቅሰው፣ አርሶአደሩም ቁርጠኛነቱን የሚያሳዩ ትግበራዎች እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህ የጋራ ርብርብም ለስኬት የሚያበቃ እንደሆነም አስረድተዋል።
ተከታታይ የሆነው የግብርና ሥራ ያልተቆራረጠ ክትትልና ድጋፍ፣የግብዓት አቅርቦት ይፈልጋል። በዚህ የተነሳም ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ይገመታል። ጫናው በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በሚጠበቀው ውጤት ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ተጽዕኖ ይኖር እንደሆንም አቶ በሪሶ ተጠይቀው፤ ‹‹ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚባክን ጊዜ መኖር የለበትም፤ በጫና ውስጥም ሆኖ ውጤታማ መሆን ይጠበቃል።›› ሲሉ መልሰዋል። በዚህ እሳቤ ነው ከላይ እስከ ታች በጋራ ሆነን እየሠራን ያለነው ሲሉም ነው ያረጋገጡት። አርሶ አደሩም እንዲሟላለት ለሚፈልጋቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው ሠርቶ ውጤት ማምጣት ሲቻል ነው ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹በሥራ እየታየ ያለው ውጤትም ሞራል የሚገነባና በዚህ መንፈስ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው ›› ብለዋል።
በበልግ የግብርና ሥራ እንደሀገር የተያዘው እቅድ ሁለት ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት በማረስ በዘር ለመሸፈን እንደሆነ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚህ የበልግ የግብርና ሥራ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ አነስተኛ ይዞታ ባላቸው የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚከናወነው ሥራ ነው። የበልጉ ምርት አምስት በመቶው ለሀገራዊ ምርት ፍጆታ እንደሚውል ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። በምርትም ወደ 24 ሚሊዮን ኩንታል ለመሰብሰብ በእቅድ ተይዟል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም