ባለፈው ሰሞን ለአንድ ጉዳይ በአቅራቢያዬ የሚገኝ ወረዳ ሄጄ ነበር።እንደተለመደው የወረዳው ግቢ በትርምስ ተሞልቶ ማን ለምን ጉዳይ እንደመጣ በማይታወቅበት መልኩ የቅዳሜ ገበያ መስሏል።እኔ የሄድኩት ደግሞ ወሳኝ ኩነት የሚባለው ከገበያም በላይ የሚደምቅ ቦታ ነው።በጊዜ የደረስኩ ቢመስለኝም ሰልፉ ግን ተጠማዞ የትና የት ሄዷል።እንደማንኛውም ሰው ተሰለፍኩ።ሠራተኞቹ አሠራራቸው ዲጂታላይዝድ ነው ቢባልም መንቀራፈፋቸው ግን ጥልፍ እንደሚሠራ ሰው ነው።አስተሳሰብ ዲጂታላይዝ ካልሆነ ሥርዓት ዲጂታላይዝ ቢሆን ጥቅም እንደሌለው ሁነኛ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
ከብዙ መቆየት በኋላ ደረሰኝ።መሣሪያ ተደግኖበት የሚሠራ የሚመስል አንድ ስልቹ ሰው ቆጣ ቆጣ እያለ ወደ መዝገብ ቤት መራኝ።መዝገብ ቤት ያለችው ደልዳላ ሴትዮ ከሰውየው በበለጠ በሥራውም ብቻ ሳይሆን በሕይወቷም የተበሳጨች ትመስላለች።ማነው የላከህ አለችኝ።ወደላከኝ ሰውዬ ጠቆምኳት።እኔ የማንንም ፋይል በመጎተት ክንዴ ተገነጠለ ፤ ለምን እነሱ ኮምፒዩተር ላይ አያዩላችሁም ብላ ተፈናጥራ ተነሳች።ፋይሉን ካለበት ጎትታ አምጥታ አገላብጣ ማየት ጀመረች።እርግጥ የኛም ቤት ፋይል ከመወፈርም በላይ በጣም አርጅቶ ለዓይንም ይከብዳል።የሆነ ነገር ጽፋ ወረቀቱን ሰጠችኝ ፤ ወደ ሰውየው ተመለስኩ።ወረቀቱን አየና በል ወደ ወረፋህ ተመለስና ተራህን ጠብቀህ ትስተናገዳለህ አለኝ።ተመልሼ ተቀመጥኩ፡፡
ተራዬ ሲደርስ ኮምፒውተር ላይ ወደተቀመጠ ወጣት ልጅ ሄድኩ።ለምን ቀስ ብለው እንደሚሠሩ አሁን ገባኝ።ልጁና ሲስተሙ ብዙም አይተዋወቁም።ስለዚህም ቀስ እያለ ነው የሚሠራው።የሲስተሙን አንዳንድ ክፍል እንደማይረዳው ከአሠራሩ ማየት ችያለሁ።መረጃዎችን እየጠየቀኝ ሞላ።ከዚያ ግን መሞላት ግዴታ ያልሆነበት ክፍል ላይ ደረሰ።መረጃ ሲጠይቀኝ ይህ ክፍል ግዴታ እንዳልሆነ ነገርኩት።ግዴታ ነው አለኝ።ግዴታ እንዳልሆነ ኮምፒውተሩ ላይ እንደሚያሳይ ባመላክተውም ሊሰማኝ ፈቃደኛ አልሆነም።ሞላው።መረጃው ተጠናቆ ሲወጣ እኔ ከምፈልገው በተቃራኒው ሆነ።ሁሉንም በተራ አናገርኳቸው።አንዳቸውም ስህተታቸውን ለማመን አልፈለጉም።ሲስተሙ ግድ ይለናል አሉ።ሲስተሙ የግድ እንደማይል ባሳያቸውም ሊቀበሉ አልፈቀዱም።ሽንፈት መሰላቸው።በኋላ አናግረው ተብዬ ወደ ቡድን መሪው ጋር ደረስኩ።ወጣት ነው።ጉዳዬን ከሰማኝ በኋላ ትንሽ እንድጠብቅ ነግሮኝ ሄደና ሌላ ጉዳይ ፈጽሞ ሲመጣ አወራን።መምሪያው ይፈቅዳል አለ።ሌሎቹ አይፈቅድም አሉ።እርስ በርስ ክርክር ተጀመረ።ክፍለ ከተማ እና ሌላ ወረዳ ደወሉ።በመጨረሻ መመሪያው እንደሚፈቅድ ተረጋገጠና በድጋሚ ተስተካክሎ ተሠራልኝ፡፡
ከአንድ ቢሮ ጠቅላላ ሠራተኛ መመሪያ በትክክል የሚያውቀው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ አስገረመኝ።ብዙዎቹ መመሪያውን አያውቁትም ወይም የሚያውቁት በአንድ ወቅት የነበረውን ብቻ ነው።ሲለወጥ አልሰሙም ወይም አላስተዋሉም።ይሄ አንደኛው ችግር ነው።መመሪያ ተለዋዋጭ ነው።ያን ግን የሚረዳው ሰው ጥቂት ነው።ብዙው ሰው እንደ መንፈሳዊ ሕግ አንዴ ከሰፈረ የሚቀየር አይመስለውም፡፡
ዋነኛው ችግር ግን የመመሪያ እውቀት አለመኖር አይደለም።ስንፍና ነው።እንዳስተዋልኩት ብዙዎቹ አለማወቃቸውን ወይም ስህተታቸውን የሚሸፍኑት መመሪያው አይፈቅድም ወይም ሲስተሙ አይፈቅድም በሚል ሽፋን ነው።የትኛው መመሪያ መቼ የወጣው መመሪያ ቁጥር ስንት ቢባሉ ማስረዳት አይችሉም።እንዲሁ በደፈናው መመሪያው ይሉሃል።ሕዝብም መንግሥት ያወጣው መመሪያ ከሆነ መቼስ ምን አደርጋለሁ ብሎ እሺ ይላል።በዚህ የተነሳ መንግሥት ባላወጣው መመሪያ ሕዝብ ይጉላላል።ብዙው ሕዝባችን በተለይ እናቶችን እና አባቶች ዛሬም ቢሆን መንግሥትን የሚያምኑ ናቸው።የመንግሥት መመሪያ ነው ከተባሉ እሺ ብለው ነው የሚሄዱት።በዚህም የተነሳ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ሳያገኙ ነው የሚሄዱት ማለት ነው።ይህ መንግሥት ገቢ ፤ ሕዝብን አገልግሎት ያሳጣል።ምሬትን ይወልዳል።ምሬት ደግሞ ሲጠራቀም አመጽን ይወልዳል።እንዲህ አይነቱ አመጽን የሚፈጥሩት እንዝላል ሠራተኞች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ሲስተምም ላይ እንደዚያው።በጣም ያስገረመኝ ራሱ የጻፈው ጽሑፍ ላይ ያለን የፊደል ግድፈት ሲስተሙ ነው ሲለኝ ነው።ሲስተሙ በባለሙያዎች የተዘጋጀ ነው።ምን ተብሎ እንደሚጻፍ በግልጽ ተቀምጧል።status የሚልን ቃል states ብሎ ሲጽፍ ስህተት እንደሆነ ብነግረው ሲስተም ነው ብሎኝ ድርቅ አለ።በሁለቱ ቃላት መሐከል ያለው የፍቺ ልዩነት በጣም ሰፊ ነው።ይህ ዶክመንት በዓለም ዙሪያ የሚሠራ ዶክመንት ነው።ስለዚህ ይህ ዶክመንት የኢትዮጵያን መንግሥት አቅም የሚያሳይ ነው።ታዲያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ የሚመራ መንግሥት እንዲህ አይነት ስህተት ተሳሳተ ቢባል ማን ያምናል።መንግሥት ተሳስቶ አይደለም ፤ ሲሰተሙ አስገደዶም አይደለም ፤ ሲስተሙ ላይ ያለው ሰው ንዝላልነት ግን ይህን አላስፈላጊ ስህተት ፈጥሯል፡፡
በጥቅሉ ብዙዎች መምሪያ እና ሲስተምን እነሱ ላለባቸው ንዝላልነት ፤ የቀናነት ችግር አና የሙስና ዝንባሌ እንደመጠቀሚያ እያደረጉት ነው።ይሄ በእርግጥ የእነሱ ችግር ብቻ ሳይሆን የብዙው ሕዝባችን ችግር ነው።እሱ የማያውቀውን እውቀት እንደ እውቀት የማይቆጥር ፤ እሱ ያልሰማውን መረጃ እንደ ፈጠራ ወሬ የሚያናንቅ ፤ ለአዲስ ነገር ክፍት ያልሆነ ሕዝብ ብዙ ነው።ጓዶች እውቀት ማለት እኛ የሰማነው እና የምናውቀው ብቻ አይደለም።እንዲያውም እኛ የማናውቀው ብዙ ነገር እንዳለ ማወቅ የእውቀት ጅማሮ ነው።ብዙ ሰዎች ዛሬ ላይ ስለ ዓለም ፤ ስለ ሀገር ፤ ስለ መንግሥት ፤ ስለ ሀይማኖት፤ ስለ ሌላውም እነሱ ጋር ያለው እውቀት የመጨረሻው እውቀት እንደሆነ በማመን በእርግጥኝነት ይናገራሉ።ይህ ስህተት ነው።እውቀት ተለዋዋጭ ነው።ነባራዊው ሁኔታም ተለዋዋጭ ነው።ሲስተምም መመሪያም ሕግም ተለዋዋጭ ነው።ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ማወቅ እና መዘጋጀት እንጂ እኔ የማውቀው ብቻ ነው የመጨረሻው እውቀት ከዚያ ወዲህ አዲስ እውቀት አልመጣም ብሎ መታገል ስህተት ነው፡፡
ሲጠቃለል ፤ በመንግሥት ተቋማት የምትሠሩ ሰዎች እባካችሁ ስንፍናችሁን በመመሪያ ፤ በደንብ ፤ በሕግ ፤ በሲስተም አንሸፍነው።ይልቁንም ወቅታዊውን መረጃ በትከክል ማወቃችንን እርግጠኛ እንሁን ፤ ለማወቅም እንጣር።እንደ ሕዝብ ደግሞ ለአዲስ እውቀት በራችንን እንክፈት ፤ ያላወቅነው ነገር ሊኖር እንደሚችል በጥቂቱም ቢሆን እንጠርጥር፡፡
ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም