ተወልደው ያደጉት ‹‹ዶሮ ማነቂያ›› ከተባለ ሰፈር ነው። ዛሬም ኑሯቸው በዚሁ መንደር ቀጥሏል። የ73 ዓመት አዛውንት ቢሆኑም ለእርጅና እጅ አልሠጡም።ቤት መቀመጥ፣ ከቤተክርስቲያን ደጃፍ እየለመኑ መኖርን አልሞከሩም።አቅም ጉልበት ሲደክም አማራጭ መፈለግ ያለ ነው።እሳቸው ግን እንዲህ መሆኑን አይፈቅዱም፡፡
እማማ ፀሐይ ኃይሉ መቼም ቢሆን በሰው እጅ ወድቀው ተጧሪ መሆንን አይሹም። ራስን ችሎ መንቀሳቀስን በነፃነት ያዩታል። ወዲያ ወዲህ ብሎ አየር ማግኘቱ ለእሳቸው እንደ ስፖርት ነው።ጤናን እንደ መንከባከብ ይቆጥሩታል።እየተዘዋወሩ በስተእርጅና ሎተሪ ሸጦ ማደር እንጀራቸው ሆኗል።ሎተሪን ራሳቸውን በመደጎም ሕይወታቸውን ይመሩበታል።ቀልጣፋነታቸውን የወረሱት ተወልደው ካደጉበት አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ።ቀጭን ሰውነታቸው ደግሞ ሮጦ ለማደር አግዟቸዋል፡፡
ለየዕለት ሥራቸው ሥፍራን ይመርጣሉ።መገናኛ አካባቢ ግርግርና ኪስ ዳበሳ በመኖሩ ምርጫቸው አይደለም። አራት ኪሎ ፤ፒያሳ፤ ስድስት ኪሎ፤ቴዎድሮስ አደባባይ ፤ብሔራዊ ቲያትር ፤መርካቶና ተክለ ሃይማኖት ከሎተሪያቸው ጋር አይታጡም።
የሎተሪ ሽያጭ ጊዜ አይሰጥም።በእጅ ያለን ሸጠው ካልጨረሱ ለኪሳራ ይጥላል።አንዳንዴ እማማ ፀሐይ በዚህ ገጠመኝ ያልፋሉ።ሎተሪ በመጨረሻው ምሽት ሊወጣ ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው በእጃቸው ካሉ የሎተሪ ቅጠሎች ጋር ይፋጠጣሉ።ይህኔ ቀሪውን ለመሸጥ መላ አያጡም፡፡
‹‹ከማለዳ ጀምሬ ቀኑን ሙሉ ያዞርኳቸው ሎተሪዎች ሊያከስሩኝ ነው›› እያሉ በልመና መንገደኞችን ይማጸናሉ።ብዙዎች አይጨክኑባቸውም።የቀሩትን ሰብስበው ይገዟቸዋል።እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ሥራቸውን መልካም አድርጎላቸው እስከዛሬ ያለ ኪሳራ ዘልቀዋል።
እናት ፀሐይ በዶሮ ማነቂያ ተወልደው ይደጉ እንጂ እናታቸው ገና በ10 ዓመት ዕድሜያቸው በመመንኮሳቸው ወደሚኖሩበት ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሊሄዱ ግድ ነበር።እስከ አሥር ዓመታቸው በአባታቸው እጅ ያደጉት ልጅ እናታቸው ከአባታቸው ተለያይተው ለመመንኮስ የበቁበትን ምስጢር ዛሬም ድረስ አያውቁትም።
ፀሐይ ለአንድ ዓመት በደብረሊባኖስ በኖሩ ጊዜ በ11ዓመት ዕድሜያቸው በአንድ ሰው ተጠልፈው ይወሰዳሉ።የዛኔ አስራ አንድ ዓመታቸው ነበር።ጠላፊው ያለ ፍላጎትና ፍቃዳቸው በር ቆልፎ ሚስት አድርጎ ያስቀምጣቸዋል።ይህን የሰሙ ቤተሰቦቻቸው በድርጊቱ በመበሳጨት ከሰውዬው እጅ ሊያላቅቋቸው ብዙ ጥረዋል።ቢሆንም ሰውዬው ባለጊዜና ባለ ገንዘብ ነበርና ሳይሳካላቸው ቀርቶ ሴት ልጅ ያረግዛሉ፡፡
በወቅቱ ሰውነታቸውም ሆነ ዕድሜያቸው ለአቅመ መውለድ ባለመድረሱ በሰላም መገላገል አልቻሉም።ልጃቸው ሆዳቸው ውስጥ ይሞታል።እሳቸውም ብዙ ደም ይፈሳቸውና ለወራት ካልጋ ይውላሉ።በሕመም ተሰቃይተውም ከሞት ይተርፋሉ።
እንዲያውም ሆኖ ሰውዬው በቀላሉ የሚለቃቸው አልነበረም።መልሶ ቤቱ ወሰዳቸው ያለፍቃዳቸውም ሚስት እንዲሆኑ አስገደዳቸው።ቤተሰቦቻቸው ተሰባስበው በሃይማኖት አባቶችና ተሰሚነት ባላቸው የአገር ሽማገሌዎች አስለመኑት።‹‹በጄ›› አላለም።ረግመው እንዳስረገሙት አወቀ።ምርጫ አልነበረውም ሚስት ያደረጋቸውን ፀሐይን ለቀቃቸው።
ከዚህ በኋላ ቀድሞውኑም ብቻቸውን ያሳደጓቸው አባታቸው ቀድሞ ይኖሩበት ወደነበረና ወደ ተወለዱበት ዶሮ ማነቂያ አመጧቸው። ከሳቸው ጋር ብዙ ከቆዩ በኋላ እንደፊቱ ተገደው ሳይሆን ወድደውና ፈቅደው ባል በማግባት ወደ መርካቶ አቀኑ።መርካቶ ከባለቤታቸው ጋር አንዲት ልጅ በማፍራት ለረጅም ጊዜ በትዳር ቆዩ።ልጃቸው በተራዋ ሴት ልጅ ወልዳ ወግ አሳየቻቸው።ይህ ደስታቸው ግን ብዙ አልዘለቀም፡ አንድዬ ልጃቸውን በሞት ተነጠቁ።
‹‹ሳይደግስ አይጣላም ›› እንዲሉ እሷ ስታርፍ የሦስት ዓመት ሕጻን የነበረችውን የልጅ ልጃቸውን አሳደጉ።ዛሬ ደግሞ ዘራቸውን አብዝታ ቅድመ አያት ሆነዋል።ዛሬም ግን ፀሐይ ከብቸኝነት ጋር ናቸው።የልጅ ልጃቸው ከአባቷ ወገኖች ጋር በማደጓ ልጆቿ ጭምር አጠገባቸው የሉም፡፡
‹‹ብቻዬን ነው የምኖረው ጧሪም ቀባሪኝ የለኝም››የሚሉት እናት ባለቤታቸውም ሆነ አባታቸው ከሞቱ በኋላ ወደ ተወለዱበት ዶሮ ማነቂያ ተመልሰው አባታቸው ይኖሩበት በነበረ የቀበሌ ቤት እየኖሩ ይገኛሉ።በየወሩም 10 ብር የወር ኪራይ ይከፍላሉ።
አኗኗራቸው ከመንደሩ ነዋሪዎች በእጅጉ የተለየ እና የተገላቢጦሽ ነው።እሳቸው ጿሚ ቆራቢ፣ ከብዙ ዓለማዊ ድርጊቶች የተቆጠቡ ናቸው።ዶሮ ማነቂያ ደግሞ የበግም፤ የፍየሉ፣ የበሬ ሥጋ ታጥቶ አያውቅም።ቀን ከሌት ሥጋ ይቆረጥበታል።ከካቲካላ ጀምሮ እስከተፈለገው መጠጥ ማወራረጃ አይጠፋም። ብዙዎቹ የዶሮ ማነቂያ ነዋሪዎች ዛሬ የሥራ መስካቸውን ለውጠዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ትልቅ ካፒታል ከሚጠይቀው ሥጋ ቤት ውጪ በመጠጦች ሽያጭና በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡
የ73 ዓመቷ እናት ፀሐይ የተወለዱበትና የሚኖሩበት ዶሮ ማነቂያ ዛሬም እንደ ድሮው ከበርቻቻ አልተለየውም።እንደ ፊቱ አይብዛ እንጂ አሁንም በቀደመው ሕይወት የሚተዳደሩ አይጠፉም።መንደሩ ሌብነቱ፤ ማጭበርበሩ፣ዝሙቱ፤ ስድቡ እንደበፊቱ ሳይለየው አብሮት እየኖረ መሆኑን እማማ ፀሐይ ይናገራሉ፡፡
እማማ ፀሐይ በሌቦች ሁለት ሶስቴ ተጎድተዋል። ቢሆንም በመጨረሻ እንደተሰረቁት ዓይነት ስርቆት የከፋ አልነበረም።ሰርክ ቤተክርስቲያን የሚሄዱት ገና ጨለማው ሳይገፍ ማልደው ነው።ይህን ደግሞ ድፍን የዶሮ ማነቂያ ነዋሪ ያውቀዋል።እናም አንድ ማለዳ እነዚህ ውስጥ አዋቂዎች እማማ ፀሐይን ጉድ ሰሯቸው።“ከቤተክርስቲያን ስመለስ በሬ ወለል ብሎ ተከፍቷል ትልቁ የልብስ ሣጥኔና ሌሎች ዕቃዎቼ በመወሰዳቸው ኦናውን ነበር ያገኘሁት” ሲሉ ያስታውሱታል።ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ የበር ቁልፋቸው ተጠምዝዞ መዘረፋቸውን ቢናገሩም ሌቦቹ ሊያዝኑላቸው አልቻሉም።ከዚህ በኋላ ኑሮ ከበዳቸው።አቅማቸው ተፈተነ። በቀበሌ ምሳ እንዲፈቀድላቸው ምክንያት ከሆነው አንዱም ይሄው ችግር ነበር፡፡
በመንደሩ በሚስተዋሉ እኩይ ሥራዎች ፍፁም ተሳትፈው የማያውቁት እማማ ፀሐይ ተወልጄ አደኩበት ብለው አያማርሩትም።የእዛ መንደር ሕይወት ከእርሳቸውና ከባሕርያቸው ጋር የማይሄድ ቢሆንም እንደማይጠሉት ግን ይናገራሉ።በብዙዎቹ፤ በተለይም ከገጠር እየመጡ በሴት አዳሪነት በሚሰማሩበት ታዳጊዎች ሕይወት ሁሌም ያዝናሉ፣ እንባ አውጥተውም ያለቅሳሉ።
ወደ ደጀ ሰላም ሲሄዱ ፈጣሪ የተሻለ ኑሮ እንዲሰጣቸው እንደሚፀልዩላቸውም ይናገራሉ።ፀሐይ ዛሬ ወደሚሠሩት የሎተሪ ማዞር ሥራ ከመግባታቸው በፊት ይሠሩት የነበረም ሥራ በዚሁ ሁሌ በሚማፀኑት ደጀ ሰላም ዙሪያ ላይ የተመሠረተ ነበር። ለብዙ ዓመታት በጧፍ ሽያጭ ተሰማርተው ቆይተዋል።ከዓመት በፊት ግን በቤተክርስቲያን ደጃፍ ጧፍ በመሸጥ የሚተዳደረው ሰው ቁጥር ተበራከተ።ድሆችን መርዳት ዓላማዋ ያደረገችው ቤተክርስቲያን ከኑሮ ውድነቱ በተያያዘ በሚያገኙት ጥቂት ትርፍ ይቋቋሙታል በሚል ነፍሰ ጡርና ሕፃናት ልጆች ያሏቸው ሴቶች ለስለት የገባውን ጧፍ እየወሰዱ እንዲሸጡና ትርፉን እንዲወስዱ ፈቀደች፡፡
ልጅ በጀርባቸው ያዘሉና ሁለት ሦስት ልጆች የሚጎትቱ ሴቶች በሙሉ ግር ብለው መጥተው በጧፍ ንግድ ተሰማሩ።ቦታ ጠፋ።አስፋልት መሐል ሲገቡ ፖሊስና ደንብ አስከባሪ ማስነሳት ጀመረ።በዚህ ላይ ጧፍ ተወደደ።ፀሐይ 75 ሳንቲም ገዝተው አንድ ብር በመሸጥ ያገኝዋት የነበረችውን የ25 ሳንቲም ትርፍ መጠኑ ሳይጨምር ዋጋው አምስት ብር ገባ፡፡
በተወደደው ጧፍ ምክንያት ገበያ በመጥፋቱ ዕድሉን ጠበበ።እንዲህ የሆነው ጧፏ ከቤተክርስቲያን በሦስት ከሀምሳ በመውጣቷ ምክንያት ነበር።ይሄን ቢችሉትና የእሳቸው ትርፍ ከፍ ቢልም ተቀምጠው ጧፍ የሚሸጡበትን ቦታ በቀላሉ ማግኘት አልቻሉም።ሻጮቹ በመበራከታቸው ቦታቸው እየተያዘባቸው በብርቱ ሲቸገሩ ቆዩ።‹‹በስተመጨረሻ ለምን አልተውላቸውም ብዬ ጧፍ ሽያጩን ተውኩት›› የሚሉት እናት እንዳወጉን ታዲያ ከእጅ ወደ አፍ የሆነችው ጥቂት ሳንቲም በመቋረጧና ከተፈፀመባቸው ዘረፋ ጋር ተዳምሮ ብርቱ ችግር ሲፈትናቸው ቆየ።የሚኖሩበት ቀበሌ በደሀ ደሀ መልምሎ ምሳ ባያስፈቅድላቸው ኖሮ ዛሬን በሕይወት የመቆየታቸው ነገር ያጠራጥራል፡፡
‹‹ጧፍ ንግዱን ከተውኩ በኋላ ብቻዬን ቁጭ ብዬ ምን ሠርቼ በመኖር ቀሪ ሕይወቴን ልገፋ እንደምችል አሰብኩ።ፈጣሪዬንም በፀሎት ጠየቅኩ›› ይላሉ።በዚህ መሐል ሰው ሎተሪ ሲሸጥ ያያሉ።ሥራው የወንድና የሴት ነው፤ የአረጋውያን ነው የወጣቶች አይልም።
‹‹እኔስ ታዲያ ለምን ሎተሪ አላዞርም›› በማለት ፈጣሪያቸውን ጠየቁ።ፀሎታቸው ተሰማ።ሎተሪ የማዞር ሥራውን ጀመሩት።ፀሐይ ወደ ሎተሪ ሥራው የገቡት የዛሬ ዓመት መሆኑን ይናገራሉ።ከዛ በፊት ግን በቤተክርስቲያን ደጃፍ ተቀምጠው ጧፍ በመሸጥ እየተዳደሩ ረጅም ጊዜ ሕይወታቸውን ሲገፉ ቆይተዋል፡፡
‹‹ሰው ኑሮውን የሚገፋው በብዙ መልኩ ነው።እኔ ደግሞ ቀሪ ሕይወቴን ሎተሪ በማዞር እንድገፋ አማኑኤል ፈቅዶልኛል።ስለዚህ ሥራውን በፀጋ ተቀብየዋለሁ።ደስ ብሎኝ ነው የምሠራው›› ይላሉ።እሳቸው እንዳወጉን ሥራውን ለመጀመር ግር አላላቸውም።ብሔራዊ ሎተሪ እሳቸው የሚኖሩበት ዶሮ ማነቂያ ፒያሳ ውስጥ እንደሚገኝ አሳምረው ያውቁ ነበር። ከፈጣሪያቸው ፈቃዱን እንዳገኙ ፈጥነው ወደዚያው አመሩ።
‹‹ሠራተኞቹ በጣም ጥሩዎች ናቸው።ሎተሪ ከነሱ እየወሰድኩ ለመሸጥ ማሰቤን ስነግራቸው በጥሩ ሁኔታ አስተናገዱኝ›› ይላሉ።እንደውም እንዲጠነክሩና ጎብዘው ሥራቸውን እንዲሠሩ ‹‹አይዞሽ›› እያሉ አበረታቷቸው።ሎተሪ እንዴት እንደሚታይ፤መቼ እንደሚወጣና እስከመቼ እንደሚቆይ ማወቅ የሚያስችላቸውን ግንዛቤም በስልጠና አስጨብጠዋቸዋል፡፡
ወደ ሥራው ከገቡ በኋላም ከሰዎች የሚታዘቧቸውን ለሥራው እንቅፋት የሆኑ አንዳንድ ትዝብቶችን ሲነግሯቸው ዝም ብለው ሥራቸውን እንዲሠሩ፤ ቦታ እንዳይሰጧቸውና በሥራው እንዲገፉበት መክረዋቸዋል።ሎተሪው በወጣ ማግስት ማውጫ ይሰጧቸዋል።በዕድሜ ጫና ዓይናቸው የደከመው እናት ሳይማሩ ቁጥሮችን እንዲለዩ የገለፀላቸውን አምላክ ያመሰግናሉ።
ከብሔራዊ ሎተሪ ያገኙትን ግንዛቤ መሠረት እያደረጉ የተወሰኑትን ደንበኞች የወጣ ሎተሪ ዕጣ እያመሳሰሉ ያያሉ።ብዙዎች ግን ማውጫውን ተቀብለዋቸው ራሳቸው የሚያስተያዩበት አጋጣሚ ስላለ እንደማይቸገሩ ይናገራሉ። ብሔራዊ ሎተሪ ብቻ ሳይሆን ደንበኞቻቸውም ጭምር ያበረታቷቸዋል።
ሰው በዚህ ዕድሜ ቀርቶ ገና ጉልበቱ ሳይደክም በወጣትነቱ ጭምር ከሥራ ራሱን አግሎ ሲለምን በሚስተዋልበት ከተማ እርሶ ሎተሪ መሸጥዎት የሚበረታታና ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው እያለ ያበረታታቸዋል።‹‹የ10 ብር ሎተሪ ገዝቶ 100 ብር ቲፕ(ጉርሻ) የሚሰጠኝ ሁሉ አለ›› ሲሉም አውግተውናል።አንድ ሊገዛ የነበረው አምስት ወይም አራት የሚይዘውን በሙሉ የሚገዛቸውም አይጠፋም።እሳቸው ሎተሪ ሳይሸጥላቸው ቀርቶ፣ የሚወጣበት ቀን ደርሶባቸው በፍፁም ከስረው አያውቁም። ማንነታቸውን በማየት ብቻ ሎተሪ የመግዛት ፍላጎት የሚያድርበትና የሚያበረታታቸው ደንበኛ ብዙ ነው።
ሁሌም ለእማማ ፀሐይ ጉርሻ (ቲፕ) የሚሰጣቸው ሞልቷል። ብዙ ሎተሪ የሚገዙ ደንበኞችም አሏቸው። ‹‹ያያቸው ሁሉ ያወደስና ያጀግናቸዋል። በዚህ ሎተሪ በማዞር ሕይወታቸውን መግፋት ከጀመሩ በመጋቢት ላይ ድፍን ዓመታቸውን አስቆጥረዋል ።ክንደ ብርቱዋ ፣ አይበገሬ እማማ ፀሐይ ኃይሉ።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2015