ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? መቼም «ቆንጆ ነው!!!» እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ምክንያቱም በሚገባ እያነበባችሁና እየተፈተናችሁ በጥሩ ውጤት ላይ ስለምትገኙ። ይህ ደግሞ የአንድ ጎበዝ ተማሪ ባህሪ ነው። ለማንኛውም ልጆች ዛሬ ቀኑ በዓል ነውና ስለዚህ በዓል ምንነትና በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንዴት እንደሚከበር እነግራችኋለሁ።
‹‹ትንሳኤ›› የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተገኘ ነው። መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል። ስለሆነም ትንሳኤ ማለት መነሣት፣ አነሣሥ፣ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል። ልጆች የትንሣኤ በዓል በቃሉ ምስጢርም ሆነ በይዘቱ ስለሚመሳሰል በሌላ አጠራር «ፋሲካ» ይባላል። «ደግሞ ፋሲካ ማለትስ?» የሚል ጥያቄ እንደምታነሱ አስባለሁ። ስለዚህም ፋሲካ ማለት በእብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ፤ በግሪክኛው ደግሞ «ስኻ» ይባላል።
ወደ ግዕዝና አማርኛ ቋንቋችን ስንመልሰው ደግሞ ማዕዶት፣ የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ፣ መሥዋዕት መሻገር፣ መሸጋገር ማለት ነው። ፈረንጆቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል። ታሪካዊ መልዕክቱም በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደስታ የተሸጋገረበት በዓል ነበር። በዚህም ኦሪታዊ ምሳሌ የነበረው በዓል አሁን ወደ አማናዊው በዓል ተቀይሮ «ትንሳኤ» ወይም «ፋሲካ» ተብሎ ይከበራል። ልጆች ስለ ምንነቱ ይህንን ያህል ካልኳችሁ «እኛ ኢትዮጵያውያን በዓሉን እንዴት እያከበርነው እንገኛለን?» ወደ’ሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ልግባ።
ልጆች፣ ትንሳኤን ብዙዎቻችሁ ደስ ብሏችሁ እንደምታከብሩት ይሰማኛል። ምክንያቱም ይህ በዓል ሃይማኖታዊም ባህላዊም ሥርዓት ስለሆነ ማለት ነው። ሃይማኖታዊ በዓሉ የክርስቶስን ለሰው ልጅ ሲል መሰቀሉን እናይበታለን። የሰው ልጅ ፍቅር ስቦት ለሞት፣ አብቅቶት፣ በሞቱ ሞትን ድል ነስቶ ትንሳኤን እንዳሳየንም እናስብበታለን። እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ፤ ለሰው እስከሞት ድረስ የታመንን እንድንሆንም የተማርንበት ስለሆነ በደስታ እናከብረዋለን።
ወደ ባህላዊ ክዋኔው ስንገባ ደግሞ ብዙ ነገሮችን የምናስተውልበት በዓል ነው። አንዱ ልጆች ከትምህርት ቤት ጥቂት ቀናትን አርፈው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ዘመድ አዝማድን እንዲጠይቁ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል። ይህ ቀን የደስታና የፍስሀ ጊዜ ነውና ሰዎች ተሰባስበው ፍቅርን የሚቀባበሉበት ዕለትም ነው፤ ከቤተሰብ ጋር ሰፊ ጊዜ የምናሳልፈበት ቀን።
መብላት፣ መጠጣቱ፤ መታረቅና በፍቅር መገናኘቱ የሚጠብቅበት ዕለትም ነው። ልጆች ከተማ ያለው ገጠር የሚሄድበት አጋጣሚም የሚያገኘው በዚሁ በፋሲካ ጊዜ ነው። ምክንያቱም በባህሉ ዘንድ ‹‹አክፋይ›› የሚባል ነገር አለና ያንን ይዞ ዘመድ አዝማድን መጠየቅ ግድ ነው።
አክፋይ ማለት ከትንሣኤ ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ ሰው በየቤተዘመዱ የሚያበረክተው ስጦታ ነው። ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ደስታውን ለመግለጽ አንዱ ወደ አንዱ ወዳጁ የተለየ ስጦታ ይዞ ይሄዳል። ለምሳሌ ዳቦ፤ ሙክት በዋናነት ከሚወሰዱ ገጸበረከቶች መካከል ናቸው። አንድ ሰው ይህንን ካደረገ አጸፋውንም ይጠብቃል።
ልጆች በአክፋይ ወዳጅ ዘመድ ጋር የሚደረግ ስጦታ ብቻ አይደለም የሚከናወነው። ድሆችም ይጠየቃሉ። በጣም አስደሳችና ተስማሚ የሚሆነውም ይህ ሲደረግ ነው ተብሎ ይታመናል። ስለዚህም የማህበራዊ ኑሮም ስሜትም መገለጫ ነውና በአክፋይ ስጦታ የማይደሰት አካል አይኖርም። ምክንያቱም ተግባሩ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን መተሳሰብ፤ መረዳዳት ያሳያል። የፍቅሩን ዋጋም ያስረዳል። ስለዚህም በክርስትና አማኖች ዘንድ አክፋይ ይዞ «እንኳን አደረሳችሁ»፣ «እንኳን አደረሰን» የሚባባልበት ቀን ሆኖ ያልፋል።
ልጆች፣ ሌላው የፋሲካ ገጸበረከት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በኢትዮጵያ ሠርግ እጅግ ከሚዘወተርባቸው ወሮች መካከል አንዱ (ሚያዝያ) ስለሆነ ብዙ ሰዎች ትዳር ይመሰርቱበታል፤ ጎጆ ይቀልሱበታል። ምክንያቱ ደግሞ በክርስትናው ዘንድ ሃምሳ ቀን ሙሉ የሚበላበት ወቅት መሆኑ ነው። አርብ፣ ረቡዕ ጭምር አይጾምም። ስለዚህም ሁሉም ደስታውን ለማራዘም ሲል ጊዜውን ይጠቀምበታል። እናም ልጆች ይህንን ጊዜ ተጠቅመው በስፋት ለሚጨፍሩበትና ለሚጫወቱበት የመዝናኛ ጊዜያቸው ይሆንላቸዋል።
ልጆች «ለመሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትስ እንዴት ይህንን ጊዜ ያሳልፉታል?» ካላችሁ እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ነው። የእነርሱ የአከባበር ሥርዓትና የቀናት ልዩነት ይኖረዋል እንጂ በስፋት በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ልዩ ትኩረትን ሰጥቶት ነው ሁሉም የሚያከብረው ነው። ክርስቲያኖች በጣም አስፈላጊ ወቅትና ጊዜ አድርገው ይወስዱታልም። ምክንያቱም ለልጆች አስደሳች እና አዝናኝ ነገርን የሚያሳውቁበት ዕለት ቢኖር ትንሳኤ ነውና።
ልጆች ከትንሳኤ በኋላ ባሉት ጊዜያት ሰዎች በተለይም በዓሉን የሚያከብሩት አካላት ምን ዓይነት ሰላምታ እንደሚለዋወጡ ታውቃላችሁ? መቼም ብዙዎቻችሁ «እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ!!!» ነዋ እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ይህም ይባላል፤ ልክ ናችሁ። ከዚህ ይልቅ ግን በዓሉን የሚገልጽ አንድ ሰላምታ አለ። ይህም በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ ምልልስ ያለበት ሰላምታ ነው።
‹‹ክርስቶስ ተንሥኣ እሙታን›› ሲል አንዱ ሌላኛው ተቀባይ ደግሞ ‹‹በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን›› ይላል። ይቀጥልና ሌላኛው ‹‹አሰርዎ ለሰይጣን›› ሲል መላሹ ደግሞ ‹‹አግዓዝዎ ለአዳም›› የሚል ምላሽ ይሰጣል። ‹‹ሰላም›› ሲል መላሹ ‹‹ሰላም›› ይላል። ‹‹እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም›› በማለት ሰላምታው ይጠናቀቃል።
ትርጉሙ ምን መሰላችሁ «ክርስቶስ ከሙታን በታላቅ ኃይልና ስልጣን ተነሳ፤ ሰይጣንን አስሮ አዳምን ነጻ አወጣው። በምድር ላይ ሰላምም ሆነ» ማለት ነው። ስለዚህም፣ ለዛሬ በዚህ ሰላምታ እንሰነባበት። መልካም በዓል!!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2015