ጉስቁል ካለችው ቤት ውስጥ ዘልቄያለሁ። ጣሪያው እጅግ ዝቅ ከማለቷ የተነሳ ከወለሉ ጋር ሊገናኝ ምንም አልቀረውም:: ከዚህች ጣሪያ ሥር ሰው ይኖራል ብሎ ለመገመትም አዳጋች ነው:: ጭራሮ ለማስቀመጥ እንኳን አይመችም:: አካባቢው ንፅህና የናፈቀው ነው:: ይህች ቤት ደግሞ ከሁሉም ለየት ትላለች:: እጅግ ወደ ውስጥ ገባ ያለች ስትሆን፤ እኚህን ሰው ለመጠየቅና ሊያግዛቸው ለሚፈልግ ሰው አመቺ አይደለችም::
ከዕይታም የተጋረደች ናት:: ከዚህች ጣሪያና መሬቱ ሊነካካ ከሚዳዳት ቤት ውስጥ ሁለት ነፍሶች አሉ:: አንደኛው ሰው አቅም ቢያንሳቸውም ወጣ ገባ እያሉ በአካባቢው እየሆነ ያለውን ነገር ይመለከታሉ። የጊዜን ዑደት በትዝብት ይቀበሉታል፤ ይሸኙታል:: ሲመሽና ሲነጋ ለእርሳቸውና ለባለቤታቸው አዲስ ነገር ይዞ ባይመጣም የተፈጥሮ ቀመር ነውና የሚሆነውን በትዝብት ይመለከቱታል:: ከንፈራቸውን እየመጠጡ እየተዋወቅን ተላለፍን እያሉ ከጊዜ ጋር በሾርኒ የሚነጋሩ፣ መሸ ደግሞ ነጋ እያሉ ቀናትን የሚቆጥሩ እንጂ ለእነርሱ ጊዜ ይዞላቸው የመጣው በረከት ያለ አይመስልም:: ሰውየው አልጋ ላይ ከቀሩ ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥረዋል::
ቤት ውስጥ ጋደም ብለዋል:: ጣሪያው በጣም ለመሬት ከመቅረቡ የተነሳ ግለቱ ከባድ ነው:: በጭስ፣ በዝናብ፣ ቁርና ፀሐይ መፈራረቅ ብስክስክ ያለው ጣሪያም የፀሐይ ጨረር እያስገባ በ‹‹እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኖባቸዋል:: በጋ በደመና ተሸንፎ ክረምት ሲገባም ይህች ጣሪያ ሥራ ይበዛባታል:: ክረምቱም በጣሪያው ቀዳዳ ዶፉን ይለቀዋል:: ታዲያ እኝህ ለ18 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ የሆኑት ሰው በዓመት 365 ቀናት ቤት ውስጥም ሆነው ጃንጥላ ይዘረጋሉ:: የኑሮ ጉስቁልና እና ህመማቸው እንዳለ ሆኖ ተፈጥሮም የለበጣ የምትስቅባቸው፣ በአሽሙር ንግግር የምታደብናቸው፣ በጭካኔ አርጩሜ የምትገርፋቸው፣ በጎሪጥ የምታያቸው ትመስላለች:: እኚህ የ88 ዓመት አዛውንት አቶ አይገፉ መታፈሪያ ይባላሉ።
የሕይወትን ውጣ ውረድ አብረው የሚገፉት ደግሞ የ70 ዓመቷ የዕድሜ ባለፀጋ እማማ ብዙነሽ ደምሴ ናቸው:: ደብረብረሃን ከተማ ቀበሌ 02 ይኖራሉ:: አባባ አይገፉ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረው ነበር:: ዛሬ ላይ ግን ይቆጫቸዋል:: ያኔ በትምህርት ገፍተው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ኑሮ እንዲህ ባልደቆሰችኝ ይላሉ:: «ያኔ በትምህርቴ እንደ መስጅድ ሚናራ ቀጥ ብዬ ብቆም፤ ሲበድሉኝ እንደ ቤተክርስቲያን ፅናፅል ድምፅ ባሰማ እንዲህ ባልሆንኩ» ሲሉ ይቆጫሉ:: በእርግጥ በወቅቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል መማርም አበጀህ! የሚያስብል ዘመን ነበርና መንግሥት ፈልጎ ቀጥሯቸው ነበር::
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር በተለያዩ ተቋማት ሠርተዋል:: ሰሜን ሽዋ ዞን መሃል ሜዳ ከተማ ነበር ሥራ የጀመሩት:: ግን ለስምንት ዓመታት ካገለገሉበት መሃል ሜዳ ሌላ ሰው በዝምድና በቦታው በደረጃ ዕድገት ለማስቀመጥ ሲባል አባረሯቸው:: ከዚያም ወደ ደብረብርሃን ሆስፒታል መጥተው 28 ዓመታት አገልግለዋል:: የመዝገብ ቤት ረዳት ሆነው አምስት ዓመት፣ የካርድ ክፍል ኃላፊ ሆነው 10 ዓመት፣ ሌሊት አዳሪ ገንዘብ ያዥ ሆነው አምስት ዓመት ሠርተዋል:: ባሶና ወራና ወረዳ ጤና ጣቢያ ገንዘብ ያዥ ሆነው አምስት ዓመት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል::
እኚህ ሰው ባላቸው ዕውቀት፤ ልምድና ችሎታ አገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል:: ከደጎች ጋር ተመራርቀው፤ ከክፉዎችም ጋር ታርቀው ዘመናት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሁሉ በብቃት ተወጥተዋል:: እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ ራሳቸውን ደግፈው ባለቤታቸውንም አግዘው የሰው እጅ ሳያዩ ኑሯቸውን መርተዋል:: 1992 ዓ.ም ጥቅምት ወር በሽታ ቀድሞ ታሪካቸውና ጥረታቸው በሌላኛው ጥቁር ታሪክ መቀየር ጀምሯል:: በሽታ ፀንቶባቸው፤ ከአልጋ ላይ ውለዋል:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንቀሳቀስ አልቻሉም:: ግራ ሲገባቸው ጡረታቸውን አስከብረው ሥራ አቁመዋል:: ኃይለኛ የደም ግፊት ስላለባቸው ዕይታቸውተጋርዷል:: ‹‹ከአንገቴ በላይ የሚሠራው ምላሴ ብቻ ነው›› ይላሉ:: በአሁኑ ወቅት በወር 156 ብር ጡረታቸውን እየተቀበሉ ይኖራሉ:: ይህች ብር የቤቱን ቀዳዳ በሙሉ ለመድፈን ትገደዳለች:: ከልጅነታቸው ጀምሮ ክኒን ውጠው፤ መርፌ ተወግተው አያውቁም:: አሁንም ቢሆን አቋማቸው ይኸው ነው::
ግን ደግሞ ለዘመናት የአልጋ ቁራኛ ያደረጋቸውን በሽታ በህክምና ቢገላገሉት ደስታቸው የትዬሌሌ ነው:: ነገር ግን በአገር ውስጥ ታክሞ የመዳን ተስፋቸው ከባድ እንደሆነ በሃኪሞች ተነግሯቸዋል። እርሳቸውም የውጭ አገር ህክምና ቀርቶ የዕለት ጉርስ አሮባቸዋል:: መታከሙንም እርግፍ አድርገው ትተው ታል:: ዕድሜና ጉልበት ሳይገድባቸው አልጋ ላይ መቅረታቸው የዘላለም ቁጭት ፈጥሮባቸዋል:: ባለቤታቸውንም በትካዜ ባህር ውስጥ ከቷቸዋል:: ለመፍረስ አንዲት ሐሙስ የቀራት ጎጆ ብዙ ውጥንቅጦችን ተሸክማለች::
እርሳቸውም እርጅና መላቅጥ ካሳጣው አልጋ ላይ ሆነው በይሆናል ተስፋ ጊዜያቸውን ይገፋሉ:: እንዲህም እያሉ በስንኝ ቋጠሮ ብሶታቸውን ይገልጻሉ:: «የሌሊቱ ዝናብ ምንም አላለኝ፤ ቀን ጥሎ ነው እንጂ የደበደበኝ» ቀን ባይጥለኝ እንኳንስ ለራሴ ለሰውም መትረፍ በቻልኩ ነበር ይላሉ:: እኚህ ሰው በመጀመሪያ ትዳራቸውም ብዙም ደስተኛ አልነበሩም:: አጠገባቸው ያሉት ባለቤታቸውም በመጀመሪያ ትዳራቸው ደስተኛ አልነበሩም:: ልጆቻቸው ከራሳቸው ተርፈው እናታቸውን የሚያግዙ አልሆኑም እንጅ ሦስት ልጆችን ወልደዋል። የእህል ውሃ ነገር ሆኖ 1973 ዓ.ም ድንገት ደብረብረሃን ተገናኙና ተደጋግፈን እንኑር በሚል አብረው መኖር ጀመሩ::
አቶ አይገፉም ከቀድሞ የትዳር አጋራ ቸው በርከት ያሉ ልጆችን ወልደዋል:: ግን የልጆቻቸውን ቁጥር ለመናገር ደስተኛ አልሆነበሩም:: ለረጅም ደቂቃዎች እእእ…….. ምምምም አሉ:: ትንሽ አስበውበት ‹‹ 11 ልጆች ወልጃለሁ:: ሁለቱ ሞተዋል፤ ሌሎቹ ግን በሕወይት አሉ:: የሚያሳዝነው አንዳቸውም ከእኔ ጋር ያለመሆናቸው ነው›› አሉ:: አቶ አይገፉ በብሶትና በችግር ውስጥ ሆነው 18 ዓመታት ከህመም ጋር ታግለዋል። ለሞት እጅ ላለመስጠት ያገኙትን ከባለቤታቸው ጋር እየተቃመሱ ከሞት ጋር ተፋጠዋል::
ከቤት ውጪ ያለው መንፈስ ውል ይልባቸዋል፤ የዘመድ ናፍቆት አንጀት አንጀታቸውን ይበላቸዋል:: ግን ከማሰብ ውጪ ለምስቅልቅል ሕይወታቸው አንድም መፍትሔ ሊያበጁ የሚያስችላቸውን አቅም አላገኙም:: ባለቤታቸውም ከአቶ አይገፉ መታፈሪያ ጋር እህል ውሃዬ ብለው ዘመናትን በችግር ውስጥ ማሳለፉን ወደውና ፈቅደው ያደረጉትበመሆኑ ብዙም አይቆጩበትም:: እማማ ብዙነሽ በደከመ ጉልበታቸው ትንሽ ትንሽ እንጀራ ይጋግራሉ:: በእርግጥ በቀን ቢበዛ ምግብ የሚመገቡት ሁለት ጊዜ በመሆኑ ብዙም አይደንቃቸውም:: በየወሩ ለምግብ ማብሰያነት ማገዶ ለመግዛት ብቻ 80 ብር አይበቃቸውም::
ይህ ደግሞ ከሚያገኟት የጡረታ ገንዘብ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሚያወጡት ለማገዶ መሆኑ ነው። ማዕልቱ ለሌሊቱ ተራውን ሲለቅ አባባን እንቅልፍ ቢያምራቸውም ቅዝቃዜው እንደ ክፉ ጎረቤት አያስተኛቸውም ይጠዘጥዛቸዋል:: ሳይፈልጉ ከእንቅልፍ ይቀሰቅሳቸዋል:: ያረጀውና ለዘመናት ሳይቀየር የቆየው የተበሳሳ ጣሪያ ዝናብና ፀሐይ፤ የተሸነቋቆረው ግርግዳ ደግሞ በተራው አቧራና ንፋስ በሰፊው ያስገባል::
በወሬ ደረጃ አካባቢው በአዲስ መልክ ስለሚለማ ይፈርሳል ተብለውም ሌላ ተለዋጭ ቤት እንደሚሰጣቸው ይጠብቃሉ:: ግን እስከአሁን ይህ አልሆነም:: ታዲያ ‹‹ትወልዳለች ብዬ ባገባት ከነደሟም ከለከላት›› የሚለውን ብሂል ይተርታሉ:: እኝህ የ88 ዓመት አዛውንት የደብረ ብርሃን ሆስፒታል ለዘመናት ሠርተው 156 ብር ጡረታቸውን ይውሰዱ እንጂ ደብረብረሃን ሆስፒታል ካለፉት 18 ዓመታት ወዲህ እንዴት ተለውጦ ይሆን? የሚለውን ለማየት አልታደሉም:: በዚህ ሆስፒታል ለመታከም ሞክረዋል:: ግን በሆስፒታሉ አቅም በሽታቸውን ማከም አልተቻለም:: የረባ ድጋፍም ሊያደርግላቸው አልቻለም::
ሙሉ ለሙሉ ታክሞ ለመዳንም ወደ ውጭ መሄድ አለባቸው:: ሆስፒታሉ ግን ይህን ወጪ ሊሸፍንላቸው አልቻለም:: እርሳቸውም ደጋግመው እርዱኝ ብለው መጠየቁን አልፈለጉም:: የደም ግፊቱ ዓይናቸውን ከዕይታ ከልሎ ከቤት አስቀርቷቸዋል:: ቀና ብለው እንዳይቀመጡም ወገባቸው አይችልላቸውም:: ከኑሮ ጋር የገጠሙትን ፈተና በአልሸነፍ ባይነት እየኖሩት ነው:: አንዳንድ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው፤ ባለቤታቸው ደግሞ በደከመ አቅማቸው ባለቤታቸውን ቀና እያደረጉ ይንከባከባሉ::
አልፎ አልፎ የሚያግዟቸው ቅን ሰዎች ቢኖሩም አሁንም የሚደግፋቸው ሰው ይፈልጋሉ:: እኝህን በችግር አለንጋ እየተገረፉ ያሉ ዜጎችን ማገዝ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። በተለይም በአካባቢው ያሉ የቀበሌ አመራሮች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። እንዲሁም በጉብዝናቸው ዘመናት ያገለገሉት የደብረብርሃን ሆስፒታል እኝህን አዛውንት ማገዝ ይኖርበታል። በአካቢው ያላችሁ ወጣቶችም የአረጋውያኑን ምርቃት ታገኙ ዘንድ ጎብኟቸው። ደግነት መልሶ ይከፍላችኋልና አለሁ በሏቸው። እነዚህን አዛውንቶች ለመርዳት የሚፈልግ አድራሻቸውን ከዝግጅት ክፍላችን ማግኘት ይችላል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር