ከሰሞኑ የክልል ልዩ ኃይልን አስመልክተው የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የክልል ልዩ ኃይል እንደገና ሪፎርም ተደርጎ እንደሚደራጅ መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል። ይህ መልዕክት ከተላለፈ በኋላ ግን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት እየተስተዋለ ያለው ተቀባይነት አዎንታዊም አሉታዊም እየሆነ እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው።
እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም በብዙዎች ዘንድ የአገር መከላከያ ሰራዊት እያለ የክልል ልዩ ኃይል ማዋቀሩ ለምን አስፈለገ? በሚል ይቀርቡ የነበሩ ተቃውሞዎችና ትችቶች እንደነበሩ አይዘነጋም። ይሁንና ዛሬ ወደተግባራዊነቱ ሲመጣ ግን ምላሹም ተቀባይነቱም ቀድሞ ከነበረው በተቃራኒው ሆኖ ተስተውሏል። ለዚህ አሉታዊ ምላሽ ምክንያቶች ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች የተለያዩ እንደሆኑ አስባለሁ።
እንደ እኔ አረዳድ የመጀመሪያው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ከልዩ ኃይሉ ጋር በተያያዘ ያለውን የአደረጃጀትና ሕግ ክፍተት፤ ይህም ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፤ ሌላው ደግሞ ያልተገቡ ወቅታዊ ስጋቶችን ታሳቢ በማድረግ በየዋህነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው።
ይህ በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር የተያያዘ፤ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ወደሰላም መምጣት ቢቻልም፤ ከፈጠረው ስጋት ጋር ተያይዞ አካባቢያዊ ትንኮሳዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ከሚል ስጋት የሚነሳ ነው ። ይህ የመከላከያ ሰራዊቱ አሁናዊ ቁመናን በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ብዬ እገ ምታለሁ።
ዋነኛው ጉዳይ ግን የአገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ ግጭት ፈጣሪዎች እና አራጋቢዎች ሥራዬ ብለው፤ የልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ አጣምመው በማቅረብ ላይ በስፋት መሰማራታቸው ነው፤ ይህ አገሪቱን የሁከት እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ካላቸው መሻት የሚመነጭ።
በርግጥ የክልሎች ልዩ ኃይል የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ በወደቀበት ወቅት ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል፤ አገርን በመታደግ ሂደት የጎላ ታሪክ ባለቤት መሆን የቻለ ነው። በዚህም በመንግሥት እና በመላው ሕዝብ እውቅና የተቸረው፤ ዛሬም የሚቸረው ነው። ይህንን ኃይል በአዲስ መልክ ለማደራጀት የተፈለገውም ለበለጠ ዓላማ እና ለትልቅ ተልእኮ እንዲሰለፍ ነው።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የመንግሥት ውሳኔ፣ ስለአገር የተዋደቀውን እና ትልቅ ዋጋ የከፈለውን ኃይል ‹‹አሁን በቃህ ! አታስፈልገኝም›› የሚል አይደለም። ወይም ደግሞ ‹‹ ከዚህ በኋላ ዕጣ ፈንታህ ትጥቅህን መፍታት እና መበተን ነው ›› የሚል አይደለም ።
ከዚህ ይልቅ በመንግሥት የተነገረውም ሆነ እንዲሆን የተፈለገው ጉዳይ መከላከያን መቀላቀል የሚፈልግ መከላከያን፣ ፌዴራል ፖሊስ መግባት የሚፈልግ ወደ ፌዴራል ፖሊስ እንዲገባ፤ መደበኛ ፖሊስ መሆን የሚፈልገው ደግሞ መደበኛ ፖሊስ እንዲሆን ነው። ከዚህ ባለፈም እስከዛሬ ያለው ይበቃኛል የሚል ካለም በክብር የሚሰናበትበት አሠራር ተግባራዊ የሚያደርግ ነው። ይህ መልሶ ማደራጀቱ የተዋቀረበት የአስተሳሰብ መሠረት ነው።
እንደ እኔ ግንዛቤ፤ የልዩ ኃይል አባላቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልን መቀላቀል ተልዕኳቸውን የበለጠ ከፍ የሚያደርግ፤ የክልላቸውንም ሆነ የአገር አለኝታነትን ከምን ጊዜም በላይ የሚያሳድግ ነው። የአገር ኩራት የመሆንን ዕድል የሚያጎናጽፍም ጭምር ነው።
በተለይ ደግሞ በአህጉር ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠላም ማስከበር ተልዕኮን ተቀብሎ የሚሰማራ የታላቅ አገር የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆን ትርጉሙ የቱን ያህል ሰፊና ጥልቅ መሆኑን መገንዘብ የሚከብድ አይደለም።
ይህ እውነታ በእርግጥ አገሩን ለሚወድድ ዜጋ የሚያስደስት እንጂ የሚያስከፋ አይሆንም። ሁሌም ስለአገሩ መሞትን ክብር የሚያደርግ የሰላም ተምሳሌት አርማ የሆነውን የአገር መከላከያን መቀላቀል እንደትልቅ እና መልካም አጋጣሚ ሊታይ የሚገባ ነው።
ከሕግ አንጻርም ቢሆን፤ ክልሎች ከመደበኛ ፖሊስ ውጪ ማደራጀት አይችሉም። የክልል መንግሥት ስልጣንና ተግባርን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 52 ስር ባለው ንዑስ አንቀጽ 2(ሰ) ላይ እንደተደነገገው፤ የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃል የሚል ነው።
በዚህ መልኩ የየራሳቸውን የፖሊስ ኃይል እንደሚያደራጁ እና የክልሉንም ሰላም እና ጸጥታ እንደሚያስጠብቁ በግልጽ አስቀምጦ እያለ ያልተደነገገ ሕግ ውስጥ ገብተው እስካሁኗ ሰዓት የየራሳቸውን ልዩ ኃይል አዋቅረው ቆይተዋል።
እንዲያም ሆኖ ግን ይህ ልዩ ኃይል የክልሉን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር በፌዴራል ደረጃ በሚደርሰው ጥሪ መሠረት አገር የጣለችበትን አደራ ሲወጣ እንደቆየም የሚካድ አይደለም። በዚህም ደማቅ ታሪክ ማስመዝገቡ የትናንት ትዝታ ነው።
ይህ ኃይል በአዲሱ አደረጃጀት በተለያዩ የመከላከያና የጸጥታ መዋቅሮች ውስጥ መካተቱ መከላከያ ሆነ ፖሊሰ ብሔር የሌለው ከመሆኑ አንጻር ክልልንም አገርንም መጠበቅ የሚያስችል ነው። በክልል ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ አለኝታ የሚኮነው ያው ለሕዝብና ለአገር ነውና ልዩነት አይኖረውም።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 87 የመከላከያ መርሆች ተብሎ በተቀመጠው ንዑስ ርዕስ ስር ቁጥር 1 ላይ የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ እንደሚሆን በግልጽ የደነገገ ከመሆኑም በተጨማሪ በተግባር መሬት ላይ ያለውም እውነታ ይኸው ነው።
በአገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ መካተት ወይም ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ መሆን አሊያም ደግሞ በመደበኛ ፖሊስ ውስጥ መደራጀት ያው ሕዝብንና አገርን መጠበቅ ተቀዳሚ ተልዕኮው ለሆነ አካል የመንግሥት ውሳኔ የሚፈጥረው አዲስ ነገር አይኖርም። የአገርንም ዳር ድንበር፤ የሕዝብንም ሰላም ለመጠበቅ የበለጠ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተደረገ ውሳኔ ነውና በሪፎርሙና በአደረጃጀቱ መካተት መልካም ነው እላለሁ።
ወጋሶ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም