የችሎቱ ድባብ
ሰኔ 18 ቀን 2004 ዓ.ም የሰነድ መለያ ቁጥር 72189 መዝገብ በችሎቱ ፊት ቀርቦ የመጨረሻ የተባለው የዳኞች ቃል ያርፍበታል። ሰበር በውሳኔው አንዳች የመጨረሻ ቃል ይናገራል። በዚህች ዕለት የመጨረሻ የተባለችውን ቃል ተመካክረው ለመስጠት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በሰዓቱ ተገኝተዋል። በወቅቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ተገኔ ጌታነህን ጨምሮ አምስት ዳኞች ከመንበሩ ተሰይመዋል። ጉዳዩም ከረር ያለ ነው።
አመልካች አቶ ካሳዬ ያደቴ ከጠበቃ ኮሎኔል መላኩ ካሣዬ ጋር ቀርበዋል። ተጠሪ ደግሞ የውጭ ዜጋ ናቸው። ሲኞር ፌራንችስኮ ቬንሲያን ይሰኛሉ። በተጠሪ በኩል ግን ችሎቱ ዘንድ የቀረበ የለም። ሆኖም መዝገቡን መርምሮ ውሳኔውን ከመስጠት ችሎቱን ያገደ አልነበረም። መዝገቡ ተመረመረ፤ የመጨረሻ ብይንም ተሰጠ። ከእንግዲህ ፍርድም የጸና ይሆናል። ምንም እንኳ ሲኞር ፌራንችስኮ ቬንሲያን ከችሎቱ ቀርበው ምን ተባለ ብለው አስተርጓሚያቸውን ባይጠይቁም። ዳሩ ግን ውሳኔው ይደርሳቸዋልና ዛሬ የቁርጥ ቀን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰማሉ-ሲኞር ፌራንችስኮ ቬንሲያን። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች በሚል ዋና ርዕስ የጥናትና የሕግ ድጋፍ መምሪያው ኅዳር 2005 ዓ.ም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች በሚለው ቅፅ ለታሪክና መመሪያ ይሆን ዘንድም ይህንን የችሎት ውሎ ቅፅ 13 ብሎ ሰንዶታል።
ጉዳዩ ምን ነበር?
መሠረታዊ የመከራከሪያ ጉዳይ የመሬት መቆፈሪያ ማሽን ነው። ታዲያ የዚህ ማሽን ጉዳይ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ የደረሰው እንዲሁ በዋዛ አይደለም። በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር አንቀፅ ምዕራፍ ተጠቅሶ፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታይቶ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤትም ብይን ቢሰጥም ከሁለቱም ወገን ማለትም ከአመልካችም ሆነ ተጠሪ በኩል በፍርድ ሂደቱ የረካ አልነበረም። ጉዳዩም አመልካች ከፍርድ አፈፃፀም መምሪያ በአደራ የተረከባቸውን የተጠሪ ንብረቶች አልመለሰም በሚል ተጠሪ የንብረቶቹን ዝርዝር እና ግምት በመጥቀስ ባቀረበው ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጀመረ ሆኖ አሁን የሚያከራክረው መቆፈሪያ ማሽን በተመለከተ ሲሆን ይሄው ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው ፍርድ ቤት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማሽኑ ተገምቶ ፍርድ እንዲሰጥበት በወሰነው መሠረት አመልካች ማሽኑ ያለበትን ቦታ ማሳየት ባለመቻሉ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ውሣኔ መሠረት አሁንም ብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍሉ በመወሰኑ እና ይሄው ውሣኔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመጽናቱ የተፈጸመው መሠረታዊ የህግ ስህተት እንዲታረምልኝ በማለት አመልካች በማመልከቱ የቀረበ ነው።
አመልካች ምን አሉ?
አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች በማንሳት ያቀረቡ ሲሆን ፍሬ ሃሣቡ፤ በዚህ ጉዳይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማሽኑ ተገምቶ ውሣኔ እንዲሰጥበት በማለት ወደ ታች ፍርድ ቤት መልሶ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች ይሄንን ሳያከብሩ አሁንም በድጋሚ በብር ውሣኔ መስጠታቸው ተቀባይነት ያለው አካሄድ አይደለም የሚል ነው።
አመልካች በበታች ፍርድ ቤትም ሆነ በተለያዩ አካላት ባቀረበው አቤቱታ ሌሎች ዕቃዎችን እንጂ የመቆፈሪያ ማሽን ያልተረከበ ስለመሆኑ ተከራክሮ እያለ እና ሌሎቹን የተረከባቸውን ደግሞ በብር 8,000 (ስምንት ሺህ ብር) መሸጣቸውን የተከራከሩ በመሆኑ፣ በበታች ፍርድ ቤቶች ያቀረብናቸውም ሰዎች ብረታ ብረት መግዛታቸውን እና መቆፈሪያ ማሽን ያልገዙ ስለመሆኑ እና ይሄንንም የገዙትን እቃ ብር 400(አራት መቶ ብር) በማትረፍ የሸጡ ስለመሆኑ ይናገራሉ። በመሆኑም ተጠሪ የክስ ምክንያት የለውም ተብሎ ክሱ ውድቅ መሆን ሲገባው የተሰጠው ውሣኔ አግባብነት የሌለውና መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው በማለት እንዲታረምላቸው ተከራክረዋል።
ጉዳዩ ያስቀርባል በመባል ተጠሪ መልስ እንዲሰጥበት ታዞ በሰጠው መልስ በእርግጥ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሌሎቹ እቃዎች ላይ በበታች ፍርድ የተላለፈው ፍርድ አግባብ ስለመሆኑ በማመልከት ያጸናው ሆኖ የዚህ አከራካሪ ማሽን ግን ዓይነቱ ሊታወቅ እና በባለሙያ ያልተገመተ መሆኑ እየታወቀ ይህ ሳይደረግ መታለፉ እና በብር መወሰኑ አግባብነት የሌለው ነው ተብሎ ወደ ታች መመለሱ ግልጽ ቢሆንም አመልካች ማሽኑን የገዛውን ሰው ማቅረብም ሆነ ማሽኑ ያለበትን ቦታ ማሳየት ባለመቻላቸው፣ ያቀረቡትም ሰው ስለማሽኑ ሲጠየቁ ማሽን እንዳልገዙ ሆኖም ግን ብረታ ብረት ስለመግዛታቸው ብቻ በመግለጻቸው ታልፎ የተሰጠ ውሣኔ በመሆኑ እና ንብረቶቹን ስለመረከቡ ደግሞ ፈርሞ የተረከበበት ሰነድ ስለሌለ አመልካች ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም። በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም በማለት ተከራክሯል። አመልካችም የመልስ መልስ በማቅረብ ቅሬታቸውን በማጠናከር በራሱ መንገድ ክርክሩን ማቀጣጠሉን ተያያዘው።
ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ሲመለከት
ግራ ቀኙ መካከል የተደረገው ክርክር ሂደት ከላይ የተመለከተው ሲሆን ችሎቱም የተነሱትን ክርክሮች፣ ከተያዘው ጭብጥ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምሯል። እንደመረመረውም የበታች ፍርድ ቤቶች አከራካሪውን የመቆፈሪያ ማሽን ግምት በተመለከተ ወደ ድምዳሜ የደረሱት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ በመመልከት የተያዘው ጉዳይ እልባት መስጠት ተገቢ ሆኖ ተገኘ።
በዚህ መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ የመቆፈሪያ ማሽኖቹን በተመለከተ አመልካች አልተረከብኩም የሚል ክርክር በዚህ ደረጃ እያነሳ ስለመሆኑ መመልከት ይቻላል። ሆኖም ግን ኃላፊነትን በተመለከተ ከዚህ በፊት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት በተደረገ ክርክር እልባት ያገኘ እና የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 50776 ግንቦት 19 ቀን 2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲመለስ አሁን የሚያከራክረውን ማሽን ግምት በብር በመወሰን በባለሙያ በማስገመት ውሣኔ ሊሰጥበት የሚቻል በመሆኑ ይሄው ሥርዓት ሊፈጸም ይገባል በሚል ስለመሆኑ መመልከት ይቻላል።
በመሆኑም አመልካች የመቆፈሪያ ማሽኑን አልተረከብኩም በማለት ያነሳው ክርክር ቀደም ሲል በውሣኔ በተቋጨ ጉዳይ ላይ በመሆኑ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 5/1/ መሠረት ተቀባይነት ያለው አይሆንም። ሆኖም ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት አከራካሪውን ማሽን ለማስገመት ተገቢውን ትጋት አድርጓል ወይ? የሚለውን ነጥብ መመልከት ተገቢነት ይኖረዋል ይላል ፍርድ ቤቱ በምርመራው።
ጉዳዩ ወደታች ፍርድ ቤት ከተመለሰ በኋላ ፍርድ ቤቱ ማሽኑ ያለበትን ቦታ ወይም የገዛውን ሰው እንዲያቀርብ የተጠየቀ ሲሆን አመልካችም ማሽኑን እንደቀድሞ ሁሉ እንዳልተረከበ የተከራከረ ሲሆን የገዛውንም ሰው እንዲያቀርብ ታዞ አመልካች ያቀረበው ሰው ማሽን እንዳልገዛ እና ብረታ ብረት እንደገዛ የገዛውንም ብረታ ብረት ብር 400 (አራት መቶ ብር) በማትረፍ እንደሸጠ ገልጿል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤቱም ይሄንኑ ምክንያት በማድረግ ቀድሞ በጥሬ ብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ተብሎ የተወሰነውን ውሣኔ በድጋሚ በመቀበል ወስኗል። ሆኖም ግን አንድ ጉዳይ በበላይ ፍርድ ቤት በነጥብ ሲመለስ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በመጣራት ድምዳሜ ላይ በመድረስ ተገቢውን ትጋት ማድረግ ያለበት ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 343/1/ ድንጋጌ ይዘት እና ዓላማ መገንዘብ ይቻላል ይላል። ይህ አከራካሪው የመሬት መቆፈሪያ ማሽን ያገለገለ ስለመሆኑ እስከታወቀ ድረስ ፍርድ ቤቱ ዓይነቱን በተመለከተ ከግራ ቀኙ ወይም በመዝገቡ ውስጥ ካሉት ሰነዶች በመመልከት እና በመግለጽ አግባብነት ባለው ባለሙያ እንዲገመት በማድረግ ቢያንስ በብር ለሚሰጠውም ውሣኔ መነሻ ነገር ማስቀረብ እየተቻለ እንደዚህ ዓይነት እና ተመሳሳይ ጥረት ሳይደረግ በደፈናው በብር ቀድሞ የተሰጠውን ውሣኔ በድጋሚ በመቀበሉ ውሣኔ መስጠቱ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የተሰጠውን ጉዳዩ የሚጣራበትን አግባብ ያልተከተለ በመሆኑ አግባብነት ያለው የክርክር አመራር በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ነው የበየነው።
በአጠቃላይ የበታች ፍርድ ቤቶች ቀደም ሲል ከዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠውን መመሪያ ሳይከተል እና ተገቢውን ማጣራት ሳያደርጉ የደረሱበት ድምዳሜ አግባብነት የሌለውና መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ይላል። በመሆኑም ቀጣዩ ውሣኔ መስጠቱን ችሎቱ ያስገነዝባል።
ውሳኔ
1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 67129 ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 65277 በቀን 24/5/2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጡት ውሣኔ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽሯል።
2. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አከራካሪውን የመሬት መቆፈሪያ ማሽን ያገለገለ ስለመሆኑ እና ሌሎች ስለማሽኑ ከመዝገቡ እና ከክርክሩ የተገኙትን ነጥቦች የሚመለከተው ባለሙያ በመግለጽ በወቅቱ የነበረው ዋጋ ሙያዊ ግምት እንዲቀርብ በማድረግ እና በማስገመት ቀደም ሲል በዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት በተሰጠው ውሣኔ መሠረት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ውሣኔ እንዲሰጥበት በማለት በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 343/1/ መሠረት መልሰን ልከንለታል ብሎ ከበየነ በኋላ መዝገቡን ዘግቷል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር