ግልፍተኝነት – ቂመኛነት = ጥፋት

በሀገራችን ጉርብትና ብዙ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን እርስ በእርስ ተቀራርቦ መኖርና በእለት ተእለት ኑሯችን አብረው ከሚኖሩት ሰው ጋር ያለን ቅርበት ትልቅ ቦታ ያላቸው ናቸው:: በዚህም ‹‹በሩቅ ካለ ዘመድ ይልቅ በቅርብ ያለ ጎረቤት ይበልጣል›› የሚል የቆየ አባባል አለ:: ታዲያ ጉርብትናው ሀዘንን ለመካፈል በክፉ ቀን ፈጥኖ ለመድረስ ብቻም ሳይሆን ደስታንም በጋራ ለማክበር ነው::

አቶ ኃይለማርያም ተክሉ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ኮንጎ ሰፈር ነዋሪ ናቸው:: በሚኖሩበት የእትዬ መንበረ ግቢ ውስጥ ከቤተሰቡ ጋር ተከራይቶ መኖር ከጀመረ ሶስት ዓመት ያህል ጊዜን አስቆጥሯል:: የእትዬ መንበረ ግቢ ብዙ ቁጥር ያላቸው ተከራዮች በጋራ የሚኖሩበት ሲሆን አብዛኛዎቹ ረጅም ዓመት የኖሩ ናቸው:: በዚህም ቤተሰባዊነትን አፍርተዋል፤ እርስ በእርሳቸውም ደስ የሚል የጉርብትና ጊዜን አሳልፈዋል:: አቶ ኃይለማርያም ባለትዳር እና አንድ ልጅ አባት ሲሆን ነገር ግን በትዳሩ ላይ ይህ ነው የሚባል ሰላምም ሆነ መስማማት የማይታበት ነው:: የአቶ ኃይለማርያም እና የባለቤቱ ሰናይት ቤት አንድ ቀን ሰላም ከዋለ በሌላኛው ቀን ደግሞ ንትርክ እና ጭቅጭቅ ከቤታቸው ያለፈ የኃይለ ቃል ምልልስን ያስተናግዳሉ:: በዚህ መሀል ጎረቤቶቻቸውም ሆኑ አከራያቸው እትዬ መንበረ ማስታረቅ እለት ተእለት ተግባራቸው ሆኗል:: በሁለቱ እጅግ የሚያዝኑትና የሚበሳጩት እትዬ መንበረ በሰላሙም ቀን ቤታቸው ጠርተው እርስ በእርስ እንዲስማሙ እና የእነርሱ አለመስማማት ለልጃቸው መልካም እንደሆነ መምከራቸውም አልቀረም::

በግቢው ውስጥ ተከራይተው ከሚኖሩት ውስጥ በባሕሪዋ ተናጋሪ እና ተጫዋች የምትባል ናት ወይዘሮ ሰላም:: ሰላም ከሩቅ ለሚያያት ሰው በንግግሯ ሰውን የምታስቀይም ብትመስልም በቅርቧ ላሉ ሰዎች ግን ከልብ በመቅረቧ የምታደርገው መሆኑን ይረዳሉ:: ሰላም በዚሁ በእትዬ መንበረ ግቢ ተከራይታ በመኖር ረጅም ዓመትን ያስቆጠረች ናት:: ታዲያ ሰላም ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላም ስትሆን በግቢው ውስጥ ግን ልክ ሳይሆን የታያትን ነገር ከመናገር ወደኋላ የማትል ናት:: በዚህም ጎረቤቶቿ የሆኑት ኃይለማርያም እና ባለቤቱ ሰናይት በሚኖራቸው ግጭት ቀድማ የምትደርስ እና የምትገላግለው ሰላም ናት:: ታዲያ በዚህ ወቅት አቶ ኃይለማርያም ከባለቤቱ ጋር በሚጣላበት ወቅት ዱላ በማንሳት የሚደበድባት በመሆኑ ይህ ጉዳይ ሰላምን በእጅጉ የሚያስቆጣት ነው:: በዚህም ከባለቤቱ ሰናይት ጋር ይበልጥ ቅርበት ያላት ሲሆን፤ አቶ ኃይለማርያምን መክራና ዘክራ ያልሆነላት ሰላም ባለቤቱ የሆነችውን ሰናይት በየቀኑ የሚኖራቸው አለመስማማት ለልጃቸው መልካም አለመሆኑን ትነግራት ነበር:: በዚህም ምክንያት ኃይለማርያም የባለቤቱን ከወይዘሮ ሰላም ጋር ወዳጅነት መፍጠር አልወደዱትም:: ይህም አልፎ አልፎ የጸባቸው መንስኤ ይሆናል::

ግልፍተኝነትና እልህ

ከእለታት በአንዱ ቀን ወደ 10 ሰዓት አካባቢ እንደተለመደው ኃይለማርያም ከውጭ ወደቤቱ ሲገባ ከባለቤቱ ጋር በጥቂት ጉዳይ እርስ በርሳቸው መነጋገር ጀመሩ:: የጸባቸው መንስኤ ባይታወቅም እየቆየ ግን ድምጻቸው እየጨመረ እና በግቢው ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዲያስተውሉት ሆኗል:: በወቅቱ በቅርባቸው የምትገኘው ሰላም የመኖሪያ በሯ ላይ በክስል ማንደጃ ላይ ምግብ ለማብሰል እየተንጎዳጎደች ትገኛለች:: ጭቅጭቁ ትንሽ ረገብ ካለ በኋላ ኃይለማርያም ከቤቱ ሲወጣ በር ላይ የገዛ ልጁን እየተጫወተች ያገኛታል:: የአራት ዓመት ሕፃን የሆነችው ልጅም ከአባቷ ጋር ለማውራትና ለመጫወት ስትሞክር ንዴቱ ያልበረደለት አባትም ልጁን የያዘችውን እግሩን ለማስለቀቅ ወደ ጎን ገፍተር አድርጓት ለመሄድ ሲሞክር ሕፃኗ መሬት ላይ ወድቃ ይበልጡኑ ማልቀስ ጀመረች:: በዚህ ጊዜ አይታ ማለፍ የማይሆንላት ሰላም ንግግሩን ማረም ጀመረች:: በዚህ ወቅት ኃይለማርያም የአንቺ ጉዳይ አይደለም በሚል በቤት ውስጥ የጀመረውን ጸብ በአይነ ቁራኛ ከሚያያት እና ቀልቡ ከማይወዳት ጎረቤቱ ጋር አደረገ:: እርስ በርስ የሚያደርጉት ንግግርም ኃይለ ቃል የተሞላበት እና ጩኸት የተቀላቀለበት እየሆነ ሲሄድ በቤት ውስጥ ያሉ ሰዎችም ወደ ውጭ መውጣት ጀመሩ:: ባልታሰበ ሁኔታ ግን አቶ ኃይለማርያም በድንገት እሳቱ ላይ የሚገኘውን እየተፍለቀለቀ የሚገኝ ውሃ ብድግ አድርጎ በጎረቤቱ ሰላም ሰውነት ላይ አፈሰሰው::

ጉዳይ በአደባባይ

እለት ተእለት አለመግባባት በእርቅ እየታየ እና በቤተሰባዊነት ችግሩን ለመፍታት ሙከራ ሲደረግ ግልፍተኝነት እና እልህ የፈጠረው አለመግባባት ግን ጉዳዩን ከቤት ወደ አደባባይ አልፎም ወደ ሕግ ሊወስደው ግድ ብሏል:: የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስም በደረሰው መረጃ መሠረትም ጉዳዩን ማጣራት ጀመረ::

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ተጠርጣሪውን አቶ ኃይለማርያም ተክሉ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ጉዳት የደረሰባትን ተበዳይ የሕክምና ውጤት እስኪጣራም ተጨማሪ መረጃዎችን ማሰባሰብ ፣ የምስክር መረጃን ማጠናከር እና በቦታው የነበሩ ሰዎችን ቃል መቀበል ሂደቱን ቀጠለ::

የወንጀሉ ዝርዝር

የግል ተበዳይ ወይዘሮ ሰላም እና ተከሳሽ አቶ ኃይለማርያም ተክሉ በአንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን በሁለቱ ግለሰቦች መካከል በተደጋጋሚ በተፈጠረ የንግግር የተፈጠረን አለመግባባት ቂም በመያዝ በየካቲት 1 2016 ዓ.ም የግል ተበዳይ ግቢ ውስጥ ቁጭ ብላ ሥራዋን እየከወነች ባለችበት ወቅት ተከሳሽ በጀርባዋ በኩል በመሄድ የፈላ ውሃ ደፍቶባት ከባድ የአካል ጉዳት በማድረሱ መረጃው የደረሰው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮልፌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር አውሎታል::

ፖሊስ የተፈፀመውን ወንጀል መነሻ በማድረግ ተገቢውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በማደራጀት በዐ/ህግ በኩል ክስ እንዲመሠረትም አድርጓል::

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስም በተከሳሽ ላይ ክስ ከመሠረተ በኋላ ጉዳዩን የያዘው ዐቃቤ ሕግም በወንጀሉ ዝርዝር ላይ ተከሳሽ አቶ ኃለማርያም ተክሉ ወንጀሉን የፈፀመው በክፍለ ከተማው ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ኮንጎ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከጎረቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የፈላ ውሃ ሰውነቷ ላይ በመድፋት ከባድ የአካል ጉዳት አድርሷል ሲሉ ለፍርድ ቤት አሉኝ ካላቸው የሰው ምስክር እና የተበዳይን ጉዳት የሚያስረዳ የሐኪም የሰነድ ማስረጃዎች በማጠናከር ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል::

ግጭትም ሆነ እርስ በርስ አለመግባባት በሰው ዘንድ ያለ ነገር ነው:: ነገር ግን ግጭቶች በንግግር መፍታት እና አለመግባባቶች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱባቸው መንገዶች በሽማግሌዎች ፣ በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች መካከል እርቅ በማድረግ እና ጉዳዩ ላይ በመምከር አለመግባባቶች እንዲፈቱ ይደረጋል:: አንዳንዶች በባሕሪያቸው ቁጡ በቶሎ ተናዳጅ እና ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሲሆኑ ሳይታሰብ መመለስ የማይቻል ጉዳት አብሮ በሚኖረው ሰው ላይም በራሱ ይህንን የግልፍተኝነት ባሕሪ ማረቅ ባልቻለው አካል ላይ ያደርሳል:: ይህም በተጎጂው ላይ እና በባለቤቱ ላይ ከባድ የሕይወት ጠባሳን ሊጥል ይችላል::

ውሳኔ

የወንጀል ምርመራ መዝገቡን ሲከታተል የቆየው በፌዴራል የመጀ መሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ ፈጣን ችሎት የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ኃይለማርያም ተክሉ ከግል ተበዳይ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የፈላ ውሃ ሰውነቷ ላይ በመድፋት ባደረሰው ከባድ የአካል ጉዳት አድር ሷል በሚል ክስ መስርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚ ፈፀሙ ማናቸውንም ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከልም ሆነ ተፈ ፅሞ ሲገኝ አስፈላጊውን የሕግ እርምት እንዲወሰድ እና ለሌሎች ማስተማሪያ ይሆናል በሚል በመ ሠረተው ክስ መሠረት ባካሄደው ችሎች ተከሳሽ በ7 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You