
የአስገድዶ መድፈር ጉዳይ በማሕበረሰባችን ዘንድ ሲነሳ ለጉዳዩ መፈጸም ብዙዎች ብዙ ምክንያት ሲያነሱ ይስተዋላል። ከዚ ውስጥ ‹‹እሷ አሳስታው ነው››፤‹‹ አለባበሷ ነው፤ ጠጥቶ ስለነበረ ነው›› እና የመሳሰሉት ምክንያቶች ለማስተባበያነት ይቀርባሉ። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ከእውነት የራቀ ነው።
በሀይማኖታዊ ይሁን በሌላ ምክንያት አለባበሳቸው የተሸፋፈኑ ፍጹም ትኩረትን የማይስቡ ሴቶች በዓለማችን ላይ ይደፈራሉ። የተባበሩት መንግሥታት በ2019 እንዳስታወቀው በሕይወት ዘመናቸው ከሶስቱ አንዷ ትደፈራለች። ሌላው ደግሞ ከላይ የተጠቀሰውን መከራከሪያ ውድቅ የሚያደርገው ነገር ሴት ሕጻናት እና ወንዶችም መደፈራቸው ነው። አንዳንድ ቦታዎች የኛንም ሀገር ጨምሮ ጨቅላዎች ሳይቀሩ ይደፈራሉ።
ሳይንሱ ደግሞ እንደሚለው አስገድዶ መድፈር ከተለያዩ ምክንያቶች የመነጨ ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ወንጀል ነው። ለድርጊቱ መፈጸም ሰበቦቹ ደግሞ የስነ ልቦና ጉዳት አንዱ እና ዋነኛው ሲሆን፣ በማሕበረሰባዊ ግዴለሽነት ወይም ትኩረት ማጣት እና የተጋላጭነት አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የተለያዩ የስነልቦና ባለሙዎች እንደሚናገሩት ለአስገድዶ መድፈር ዋና ምክንያቱ የስነ-ልቦና ችግር ነው። ይህም ማለት አጥቂዎች ባለባቸው የስነልቦና ቀውስ ስልጣን (የበላይ መሆን፤ ኃይልን ማሳየት) እና ነገሮችን በቁጥጥር ስር የማዋል ፍላጎት ይኖራቸዋል። ይህ ፍላጎትም በተለያዩ ምክንያቶች ይምጣ እንጂ አብዛኛውን ግዜ በአይምሮ ጠባሳ ወይም በሙያዊ አጠራሩ ‹‹ቻይልድ ሁድ ትራውማ›› ነው።
ብዙ አስገድዶ ደፋሪዎች በሕይወታቸው ውስጥ በቂ ወይም ለነገሮች ብቁ እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል እና ጾታዊ ጥቃት በተጠቂዎቻቸው ላይ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ እንደ ዘዴ ይጠቀማሉ። ይህ የመቆጣጠር ፍላጎት በተለያዩ መንገዶች ለምሳሌ በንዴት ወይም በሃዘን ሊገለጽ ይችላል። ለምሳሌ ቁጣ የሚደፈሩ ሰዎች በጥቃቱ ወቅት ከልክ ያለፈ ኃይል በመጠቀም ተጎጂዎቻቸውን ለማዋረድ እና መጉዳት ዓላማ ያደርጋሉ።
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ባሕልን መሰረት ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው። ባሕል ለጾታ እና ከፆታዊ ጉዳዮች ጋር ንክኪ ላላቸው ነገሮች መስመር በማበጀት ደረጃ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ይህም ማለት ለአስገድዶ መድፈር መስፋፋት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
የወንዶችን መብትን ያለቅጥ ለጥጠው የሚያዩ እና ለሴቶች ምንም ቦታ የሌላቸው ማሕበረሰባዊ ደንቦች ጾታዊ ጥቃትን ያባብሳሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለምሳሌ ወንዶች ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የፆታ ፍላጎት አላቸው ወይም ሴቶች መደፈርን የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው ብሎ የሚያምን ማሕበረሰብ ጥቃቱን ያባብሳል።
ጥናቶች እንዲሚያመላክቱት ሁኔታዎችም ለመደፈር አደጋ እንደሚያጋልጡ ተረጋግጧል። እንደ መጠጥ ቤቶች ያሉ አካባቢዎች የጾታዊ ጥቃትን አደጋ ሊጨምሩ ይችላሉ። አልኮሆል እና አደንዛዥ እጽ መጠቀም የማስተዋል ችሎታን በመቀነስ አደጋው እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ። ብዙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀለኞች የሚከሰቱት አጥፊው እና ተጎጂዋ በሚተዋወቁበት ሁኔታ ነው።
በዛሬው የተናጋሪው ዶሴ ግን የምናቀርብላችሁ ታሪክ ከላይ ከጠቀስናቸው ከየትኛውም ምክንያቶች ጋር የማይያያዝ እና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ታሪክ ነው። ታሪኩ የሚያጠነጥነውም አንድ የአራት ዓመት ሕጻን ልጅ ላይ ሊፈጸም በነበረ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ሲሆን በዚህ ታሪክ ውስጥ ያሉ ባለታሪኮች ስማቸው የተቀየረ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ሕጻን ሰላም (ስሟ የተቀየረ) የምትኖረው ከወላጅ እናቷ እና ከአክስቷ ጋር ነው። እናት ልጇን እና እህቷን ለማሳደግ ቀኑን መሉ በጉሊት ሥራዋ ላይ ትውላለች። የሰላም አክስት ፍሬህይወትም (ስም የተቀየረ) ገና የ16 ዓመት ለጋ ናት። የእህቷንም ልጅ አብዝታ ስለምትወዳት ቀኑን ሙሉ እሷን በመንከባከብ ተጠምዳ ትውላለች።
ሕጻን ሰላም አይኖቿ ሲንከባለሉ ልብን የሚያርዱ፤ ፍጥነቷ እና ኮልታፋ አንደበቷ ሲያወሯት ቢውሉ እንዳትሰለች የሚያደርጋት መልከ መልካም ልጅ ናት።
ሕጻን ሰላም በአንድ ክፉ ቀን የኬጂ ትምህርት ቤቷ የመምህራን ስብሰባ በመሆኑ ሕጻናት ትምህርት የላቸውም ተብሎ ለአክስቷ ፍሬህይወት ስለተነገራት እንደሌላው ቀን ማልዳ መነሳት አላስፈለጋትም። የሕጻን ሰላም እናትም ለጉሊት ችርቻሮዋ የሚሆናትን እቃ ለማምጣት ማልዳ ወደ ገበያ ስትሄድ እህቷን ፍሬህይወትን ቀስቅሳት ከሰላም ጋር ቁርስ እንዲበሉ እና በሩንም ከውጭ እንድትዘጋ ታስጠነቅቃታለች።
ፍሬህይወትም እህቷን ሸኝታ በሯን ዘግታ ሕጻን ሰላምን አቅፋ ትተኛለች። ሰላምም ከረፋዱ አራት ሰዓት በመንቃቷ ፍሬህይወት አብራት ተነስታ የተኙበትን አልጋ ማነጣጠፍ እና ቁርሳቸውን ማሰናዳት ትጀምራለች።
ሰላምም ቤቱ ተጸድቶ እስኪያልቅ በማለት ከግቢ ወጥታ የእድሜ እኩዮቿን መፈለግ ትጀምራለች። ከአጥራቸው እግሯ ሲወጣ የተመለከቱ አንድ አዛውንትም ሰላምን ይጠሯታል።
አዛውንቱ እድሜያቸው 72 ዓመት ሲሆን ስማቸውም አቶ ከልካይ ማናለህ (ስማቸው የተቀየረ) ይባላሉ። ከነሰላም ቤት ፊት ለፊት ያለውን የአንድ ባለሀብት መጋዘንን የሚጠብቁ ጥበቃ ናቸው። አቶ ከልካይ በዚያ ሥራ ላይ ረጅም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው የአካባቢው ሰው ያውቃቸዋል። የሚጠብቁበት ግቢ ሕጻን ሰላም ጋርም የተዋወቁት ካዝሚሩ በደረሰ ቁጥር ከምትችለው ቁጥር በላይ እያሸከሙ ደስተኛ ስለሚያደርጓት ነው። ለሌላ የሰፈሩ ልጆችም ከሕጻን ሰላም ፈቃድ ውጭ አይሠጡም ነበር። በዚህ በጎ መሳይ ወጥመዳቸውም ምክንያት ፍሬህይወት እና የሰላም እናት አቶ ከልካይን ይወዷቸዋል።
ሕጻን ሰላም ከግቢ ከወጣች አቶ ከልካይ ጋር ካዝሚር ለማምጣት ወይም ከጎረቤት ልጆች ጋር ለመጫወት እንደሆነ ተደርጎም ይታሰባል።
ነገር ግን በዛች የቀን ጨለማ በሆነች ቀን ሕጻን ሰላም እቤቱ እስኪጸዳ ከጓደኞቿ ጋር ልትጫወት ወጣች። አቶ ከልካይም ሰላምን እንዳይዋት በታላቅ ፈገግታ አቅፈው ስመዋት ካዝሚር እንደምትፈልግ ይጠይቋታል።
እሷም በደስታ እየተፍለቀለቀች በአንገቷ ንቅናቄ እና በኮልታፋ አንደበቷ መስማማቷን ገለጸች። አቶ ከልካይም አካባቢው ላይ ማንም አለመኖሩን በትከሻቸው ገልመጥ ገልመጥ አድርገው ቃኙ። የሥራ ቀን ስለነበረ ማንም በአካባቢው የለም።
እሳቸውም ሕጻን ሰላምን ቆዳው በተሸበሸበ ጅማታም በሆነው እጃቸው ሸከም ብለዋት ከተንጣለለው የመጋዘን ግቢ አስገቧት። ሕጻኗም ሁሉም ነገር እንደወትሮው የሚሄድ መስሏት አልተቃወመቻቸውም። ግቢ ውስጥ ካስገቧት በኋላ ግን የተፈጠረው ሌላ ነው።
ሕጻኗን ለጥበቃ ተብላ በተሰራችው ሁለት በሁለት በሆነች ክፍላቸው ውስጥ ይዘዋት ገቡ። በቅጡ ወደ አልተነጠፈችው ወደ ትንሿ ፍራሻቸውም በኃይል ወረወሯት እና በሲባጎ የተቋጠረውን አዳፋ ሱሪያቸውን መፍታት ጀመሩ። ሕጻኗም ጉዳዩ ከዚህ ከደም ያልገጠማት ቢሆንም የልጅነት ደመ ነብሷ የነገራት ይመስል ማልቀስ ጀመረች። ነገር ግን የጥበቃ ቤቱ ከአጥሩ ራቅ ተደርጎ የተሰራ እና ግንብ በመሆኑ ድምጹዋ ሰሚ አላገኘም።
ይህ እየሆነ እያለም ፍሬህይወት አልጋውን አነጣጥፋ እና ቤቱን አስተካክላ በመጨረሷ ከሰላም ጋር ቁርስ እንዲበሉ መጣራት ጀመረች። አጥሩንም አልፋ ወጥታ ሰላምን ያያት ሰው ካለ መጠየቅ ጀመረች። ነገር ግን ሁሉም ጎረቤት መልሱ አላየናትም ነበር፤ ሰላም ወትሮም አቶ ከልካይ ጋር መሄድ ልማዷ ነበርና ፍሬህይወት በዝግታ ወደ እሳቸው መሄድ ጀመረች።
ደጃፉ ላይም እንደደረሰች አቶ ከልካይ ሕጻን ሰላምን አቅፈው ወደ ግቢው ሲገቡ በሩ መዘጋቱን አላረጋገጡም እና ክፍት ሆኖ አገኘችው። አቶ ከልካይንም ውጭ ሆና መጣራት ስትጀምር አንድ በፍርሀት ሲቃ የያዘው ድምጽ ሰምታ ወደ ውስጥ ገባች። ድምጹ ከሚሰማበት ክፍልም ስትደርስ የምታየውን ማመን አቅቷት ነበር።
ሰላም በጀርባዋ ተንጋላ እንባዋ ወደ ጆሮዋ እየፈሰሰ እና በአቶ ከልካይ እጆች አፎቿ ታፍነው የለበሰችው የለሊት ልብስ ተቀዶ አገኘቻት። በድንጋጤም እሪታዋን አሰማች። ባሰማችውም የይድረሱልኝ ጩኸት በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ደርሰው ለፖሊስ በማሳወቅ በቁጥጥር ስር እንዲውል አደረጉ።
በአቶ ከልካይ ላይም ምርመራ ተጣርቶ በፍትህ ሚኒስቴር የቦሌ ቅርንጫፍ ዐቃቢ ሕግ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ለቦሌ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ በ1997 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 627(1) እና 27(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በሕፃን ልጅ ላይ የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል ሙከራ ወንጀል ክስ መስርቶ ክርክር ሲያደርግ ቆየ።
እንደዚህ ያለውን ወንጀል ለመከላከልም አስቀድሞ የግንዛቤ ትምህርቶችን በማዘጋጀት ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳወቅ፣ የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ እና የማሕበረሰብ ተሳትፎን ማጎልበት አስፈላጊ ነው የሚለው የዛሬው መልእክታን ነው። በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ የወንጀል ዶሴ የምንገናኝ ይሆናል እስከዛው ቸር ቆዩ።
ውሳኔ
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቢ ህግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለት ለፍ/ቤቱ የገለፀ ሲሆን ፍ/ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሹ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም