
ሁለቱ ባልና ሚስቶች በቅርቡ ለገቡበት አዲስ ቤታቸው ገና አዲስ ናቸው። ታዲያ በዚህ አዲስ ቤታቸው የተጋቡበትን 10ኛ ዓመት የጋብቻ በዓል ከቤተሰቦቻቸው እና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን እያከበሩት ይገኛሉ። በሁሉም የእድሜ ክልል እናት አባት ወጣት ጓደኞቻቸው እህቶቻቸውና ሕፃናት ቤቱን ሞልተውታል። ከውጭ ለሚመለከት አልያም ለሚያዳምጥ ሰው ሳቅ ጨዋታ እና ቤተሰባዊነትን የደራበት ሲሆን የጨዋታው አካል መሆንን ያስመኛል።
ወይዘሮ መሠረት እና አቶ ከበደ በ10 ዓመት የትዳር ቆይታቸው ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል። አዲስ የገቡበት ሰፈር ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት ቅርብ እና ራሳቸው ሠርተው የገቡበት ቤት በመሆኑም እፎይታን አግኝተዋል።
አካባቢው በርካታ በመገንባት ላይ ያሉ ቤቶች ያሉበት ሲሆን እንደ አቶ ከበደ እና ባለቤቷ ቤታቸውን አገባደው የገቡ ሰዎች ቁጥር ጥቂት ነው። ታዲያ ጉርብትናውም ቢሆን በናፍቆት እና በፍጹም መፈላለግ የሚመሠረት ነው። በመሆኑም ጠዋት ሲወጡም ሆነ በመንገድ ሲገናኙ ሰላምታ መለዋወጥ እና በአዲስ መልክ እየተነቃቃ ያለ ሰፈር በመሆኑ የጸጥታውን ነገር ለማጠናከር ጎረቤታሞቹ እርስ በእርሳቸው ይወያያሉ። ወደ ሰፈሩ የሚያስገባው አስፓልት ጫፍ ላይም የአካባቢው የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ የሚገኝ በመሆኑም በመጠኑም ቢሆን የጸጥታው ነገር እፎይታን ፈጥሮላቸዋል።
አቶ ከበደ እና ባለቤቱ አዲሱ ቤታቸው ከገቡ በኋላ የጋብቻ በዓል ክብረ በዓላቸውን ባከበሩ ምሽት ወዳጆቻቸውን ሸኝተው በክብረ በዓሉ ምክንያት የተዘበራረቀውን ቤታቸውን እንደነገሩ አስተካክለው ወደ መኝታቸው አመሩ። በነጋታው እናት መሠረት ልጆቿን ወደ ትምህርት ቤት ለመሸኘት እና ወደ ሥራዋ በጊዜ ለመሄድ ቀደም ብላ ከእንቅልፏ ተነስታለች። ሥራውንም በሰዓቱ አጠናቃ ልጆቿን በጊዜ ቀስቅሳ እና አዘጋጅታ ከባለቤቷ ጋር በመሆን ወጣች።
ነገር ግን ባልተለመደ ሁኔታ በዚህ ጠዋት ከመኖሪያ ቤታቸው አለፍ ብሎ ባለ ቤት በሩ ተከፍቷል። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ተሰብስበዋል፤ ወደ ግቢው የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችም በርከት ያሉ ናቸው። ጉዳዩ ግራ ያጋባቸው እና ጥያቄ ያጫረባቸው ባለትዳሮቹም ልጆቻቸውን መኪናቸው ውስጥ አስቀምጠው ጎረቤቶቻቸውን ለመጠየቅ ጠጋ አሉ።
ምሽቱን ባላወቁት ሰው በራቸው ተሰብሮ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ገንዘብ እና በቤታቸው ያለ አንድ ትልቅ ቴሌቭዥን መዘረፉ ሰዎቹ እንዲሰበሰቡ ያደረጋቸው ጉዳይ መሆኑን አወቁ። ያልጠበቁት በመሆኑ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለውን በተለያዩ ጥያቄዎችን ለቤቱ ባለቤቶች በመሰንዘር ለመረዳት ቻሉ። ከዚያም መጨረሻው እንዲታወቅ እና የሰረቀው አካል በቁጥጥር ስር እንዲውል ተመኝተው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለማድረስ መውጣታቸውን አስታውሰው ወደ መኪናቸው ተመለሱ።
ጉዳዩ በባለትዳሮቹ ላይ ስጋትን ፈጥሮባቸዋል፤ በገዛ ቤታቸው ላይ ገብቶ ራሳቸውን ለመከላከል የነቁ የቤቱ አባላትን በማስፈራራት በቤት ውስጥ የሚገኝን ገንዘብና ትልቅ ቴሌቭዥን እንዲሁም ሌሎች ብዙ ገንዘብ ሊያወጡ የሚችሉ ቁሳቁሶችን ወስደው ከቤቱ ሊወጡ ችለዋል። ፖሊስ በቦታው በመገኘት ከቤተሰብ አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ተጠርጣሪውን ለመለየት ጥረት እያደረገ ነው።
ባለትዳሮቹ ጉዳዩ ቢያሳስባቸውም እንዴት መከላከል እንችላለን የሚለውን ለእለቱ በመነጋገር ልጆቻቸውን ወደ ማድረስ እና ወደ ራሳቸው ሥራ የእለት ተግባራቸው አመሩ። አንዳንድ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው አልያም ከሰዎች በመዝረፍ መክበርን ልምዳቸው ያደረጉ ሰዎች ጉዳታቸው የከፋ ነው። የተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎችን በመጠቀም የሰዎችን ንብረት ይነጥቃሉ፣ አስፈራርተው ይወስዳሉ፣ ከሚነጥቁት ቁሳቁስም በላይ የሰዎችን ሕይወትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል አጸያፍ ተግባርን ይፈጽማሉ። ታዲያ ሰዓት እላፊን ጠብቆ ከመንጠቅ አልፎ ሰዎች እረፍት ወደሚያገኙበት እና ደህንነት ወደሚሰማቸው መኖሪያ ቤቶች በድፍረት ገብቶ ማሸበር እና መዝረፍ ማንም ሰው እንዳይደርስበት የሚፈልገው ነው።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ኮተቤ አካባቢ ፖሊስ ጉዳዩን በማጣራት ወንጀሉን የፈጸመውን ተጠርጣሪ ለማግኘት የራሱን ማጣራት ማድረጉን ቀጠለ። በወቅቱ ሰዎች ተነጋግረውበት እና በድጋሚ ሌሎች ላይ እንዳይደርስ ምን ሊደረግ ይገባዋል ቢሉም ሲቆይ ግን ጉዳዩ ሰዎች በቤታቸው የሚያወሩበት ሆኖ እልባት ሳያገኝ ተረሳ።
ታኅሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ነው በእለቱ ወ/ሮ መሠረትም ሆነ ባለቤቷ ከበደ ከሥራ አምሽተው መጥተው እራታቸውን ከበሉ በኋላ እለቱን እንዴት እንዳሳለፉ በመወያየት ላይ ሳሉ አልፎ አልፎ ከውጭ ድምጽ ይሰማሉ፤ ነገር ግን ሰዓቱ በመምሸቱ እነሱን ፈልጎ በራቸውን የሚያንኳኳ ሰው የለምና ትኩረት ሳይሰጡት ወደ ጨዋታው አመሩ። ሰዓቱ ወደ እኩለ ሌሊት እየተጠጋ ነው። በድንገት ግን የሳሎናቸው በር ሲገነጠል ካሉበት ቦታ ደንግጠው ቆመው ቀሩ።
በግምት ከሌሊቱ 7፡15 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ኮተቤ ሰላም ዳቦ ቤት አካባቢ የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ሶስት የሚሆኑ ሰዎች ፌሮ ብረት ይዘው በማስፈራራት ተከሳሹ ደግሞ ሽጉጥ ይዞ ባትሪ እያበራ እንዳትንቀሳቀሱ በማለት የባለቤቷ ግንባር ላይ በመደቀን እንደሚተኩስበት በማስፈራራት፣ ሌላኛው ዘራፊ ደግሞ የጣውላ እንጨት ይዞ በማስፈራራትና ለግል ተበዳይ ርዳታ እንዳይሰጥ በማድረግ በቤት ውስጥ የተቀመጠ ጥሬ ብር፣ የተለያዩ ሞባይሎችንና የጣት የጋብቻ የወርቅ ቀለበት አጠቃላይ ዋጋቸው 150 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ከቤት ውስጥ ይዘው ለመውጣት ሲሉ ያላትን ኃይል በመጠቀም እና ፍርሃቷን በመቆጣጠር ወይዘሮ መሠረት በአቅራቢያዋ ላሉ ሰዎች ባደረገችው የስልክ ጥሪ ከግቢው ወጥተው ለማምለጥ በሚሞክሩበት ጊዜ በሌሎች ሰዎች እገዛ ሲያዙ በቦታው የነበሩ ሌሎች አባሪዎች ግን ሊያዙ አልቻሉም። በአካባቢው ሰዎች ርዳታ የተያዘውን እና በዝርፊያው ወቅት ለግብረ አበሮቹ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ የነበረው ሰውም በቁጥጥር ስር አውለው ወደ አቅራቢያው ባለ ፖሊስ ጣቢያ ይዘዋቸው አመሩ።
የወንጀሉ ዝርዝር
ፖሊስ በአካባቢው የተፈጸመውን ከግል መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚፈጸም ዝርፊያ በሚል ክስ መስርቶ ማጣራቱን ጀመረ። ባደረገው ማጣራትም በሌሎች የአካባቢው ቤቶች ላይ የተፈጸመ የስርቆት ወንጀል ላይ በመሳተፍ በሁለት ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።
ወንድሙ ሞላ የተባለው ተከሳሽ በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ በሁለት ክሶች የተከሰሰ ሲሆን በአንደኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ ታኅሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7፡15 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ኮተቤ ሰላም ዳቦ ቤት አካባቢ የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት የሳሎን በር ገንጥሎ በመግባት ያልተያዘው ግብረአበሩ ፌሮ ብረት ይዞ ሲያስፈራራ፣ ተከሳሹ ደግሞ ሽጉጥ ይዞ ባትሪ እያበራ እንዳትንቀሳቀሱ በማለት የግል ተበዳይን ግንባሩ ላይ በመደቀን እንደሚተኩስበት በማስፈራራት፣ ሌላኛው ግብረአበር ደግሞ የጣውላ እንጨት እንደ መሳሪያ አድርጎ በመያዝ አንድን ግለሰብ እንዳትበላሽ በማለት በማስፈራራት ለግል ተበዳይ ርዳታ እንዳይሰጥ በማድረግ ጥሬ ብር፣ የተለያዩ ሞባይሎችንና የጣት የወርቅ ቀለበት አጠቃላይ ዋጋቸው 150 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት በመውሰድ ተከሷል።
በተመሳሳይ በ2ኛ ክሱ ላይም ተከሳሽ ከላይ በ1ኛ ክስ በተገለፀው ቦታ በኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም በዚሁ አኳኋን መሠረት ከሌላ ተበዳይ መኖሪያ ቤት ገብተው በማስፈራራት የተለያዩ 10 ሺ 200 ብር የሚገመቱ ንብረቶችን የወሰዱ በመሆኑ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው የውንብድና ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።
ውሳኔ
ከግል መኖሪያ ቤቶች በር ገንጥሎ በመግባት ስርቆት የፈፀመው ተከሳሽ በዐቃቤ ሕግ በቀረበበት ክስ ክርክር ሲደርግ ቆይቷል፡፡ በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም