የትንሳኤ በዓል በመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ነገ ይከበራል። ኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህል አለን፣ የተቸገረን መደገፍና የታመመን የመጎብኘትም ልምድ አለን፣ ለበጎ ሥራ ደግሞ በቀዳሚነት የሚያስፈልገው መልካም ልብ ብቻ ሲሆን በጎነት ለራስ ጤንነት የሚሰጥ፤ በፈጣሪ ዘንድም ውድ ዋጋ ያለው ክቡር ተግባር ነው። የትንሳኤ በዓልም ይህ አኩሪ ባሕላችን ጎልቶ ከሚወጣባቸው አጋጣሚዎች አንዱና ትልቁ ነው።
በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ይህን በዓል በማስመልከትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ቀናት ለአቅመ ደካሞች፣ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አካሂደዋል። የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤም የፋሲካ እና የዒድ አልፈጥር በዓላትን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርተዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ አቅም የሌላችውን በመርዳት፣ያለው ለሌለው በማካፈል መንፈስ በዓሉን ሊያከብረው እንደሚገባም በማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሩ ወቅት ተናግረዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችን በማሰብና ድጋፍ በማድርግ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። ከአጠገቡ ያሉ አቅም ያነሳቸውና ኑሮ የከበዳቸው ጎረቤቶቹን እንዲጠይቅና እንዲያግዝም ጥሪ ቀርቧል።
እውነት ነው ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው እንደሚባለው ሁሉም የአቅሙን ያህል የተቸገረን ቢጎዳ የብዙዎች ችግር ይቃለላል፤ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትም ያብባል።በተለይም ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለተቸገሩ ማዕድ በማጋራትና በመሳሰሉት በጎ ተግባራት በዓሉን ሊያከብሩ ይገባል። በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረው የሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግር ውስጥ እንደመሆናቸው፣ እነዚህን ወገኖችን በዚህ ታላቅ በዓል በመመገብ፣ በማጠጣት እና በማልበስ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል። ይህንንም በማድረግ የትንሳዔን ዓላማ ማሳካትና በሰማይም በምድርም መልካም ዋጋ ማግኘት ይቻላል።
በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም ሰው ክፋትን ከልቡ በማስወገድ በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ክርስቶስን መምሰል አለበት። ከተበላሸ ሕይወት በመጽዳት የክርስቶስን አብነት መከተልና የሰላም አባት መሆን ያስፈልጋል።
እንደ ክርስትና ተከታዮች እምነት ትንሳዔ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ታዛዥነትን ንጽሕናን ለሰዎች መስዋዕት መሆንን በተግባር የገለጠበት ትልቅ በዓል ነው።ስለሆነም ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን በመተሳሰብና በፍቅር ሊያከብርና የተቸገሩና አስታዋሽ ያጡትን ማሰብና መርዳት ይጠበቅበታል። ወንጌልን ከቃል ባለፈ በተግባር በማሳየትም እርስ በርስ ተከባብሮና ተረዳድቶ በፍቅርና በሰላም መኖር ይገባል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ስቃይ ለሁሉም በመሆኑ የትንሳኤ በዓል ደጋፊ የሚያሻቸውን በማሰብና በመርዳት ሊከበር ይገባል። ኢየሱስ ክርስቶስ በኑሮው ገልጦ ለሐዋርያት ካስተማረው ትምህርት አንደኛው ለራስ ሳይሆን ለሌሎች መኖርን ነው። በመሆኑም በዓሉ ሲከብር እርስ በእርስ መረዳዳትና በመተሳሰብ ማሳለፍ ይገባል!
ትንሳኤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሠው ልጆች ሲል ብዙ መከራ ተቀብሎ ይቅርታ እና ፍቅርን ያስተማረበት በዓል በመሆኑ ምዕመናን በዚህ ተምሳሌት መተሳሰብ እና በጎ ተግባርን ማጠናከር ይገባቸዋል። ትንሳኤ ለሰው ልጆች ሁሉ ከመከራ የመነሳት የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ እኛም አሁን የገጠሙንን የውስጥና የውጭ ችግሮች ተቋቁመን ፈተናዎችን በፅናት ለመሻገር መነሳት ይኖርብናል። እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች ለማለፍ ትለቅ አቅምና ምሳሌ ይሆነናል ።
ትንሳዔ አሁን ላይ እንደሃገር የገጠሙንን ፈተናዎች አልፈን የምንሻገር እንድንሆን ተስፋን የምንሰንቅበት በዓል ነው። በሀገራችን አልፎ አልፎ እያየን ያለነው ጥላቻ እና መገፋፋት የኢትዮጵያውን መለያ አይደለምና በትንሣዔ በዓል ፍቅርን እና አንድነትን በመስበክ ጥላቻንና መከፋፈልን ልናስወግድ ይገባናል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም