ለአገር ሰላምም ሆነ ሕዝባዊ አንድነት መረጋገጥ የእምነት ተቋማት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው እሙን ነው።በእስካሁን የኢትዮጵያ ታሪክም የአገር ግዛታዊ አንድነት እንዲጠበቅ፤ በመቻቻል የተመሠረተ ሕዝባዊ አንድነት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል።በተለይም አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ አማኝ መሆኑ የእምነት አባቶች አስተምህሮ ተቀብሎ የአገሪቱ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክንያት እንደሆነ ይነሳል።አገሪቱ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በፅናት እንድታልፈውና የአንዱ ቤተ- እምነት ተከታይ ከሌላው እምነት ተከታይ ጋር በመደጋገፍ፤ ከውጭ የሚቃጣውን ሴራ ማክሸፍ የተቻለውም ተቋማቱ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታትም ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ አጋጥሟት የነበረውን ብርቱ ፈተና እንደቀድሞው ሁሉ በፅናት ማለፍ የቻለችው በእነዚሁ የእምነት ተቋማት የላቀ ርብርብ እንደሆነ በተጨባጭ ታይቷል።በተለይም አማኙን ሕዝብ ለሰላም በማስተባበር፤ በፆምና በጸሎት ፈጣሪውን እንዲማፀን በማድረግ ረገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሠርተዋል፤ በዚህም አወንታዊ የሆነ ውጤት መታየት ተችሏል።ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታዮች በፆምና በብርቱ ጸሎት ለአገራቸው ዘላቂ ሰላም ፈጣሪያቸውን ሲማፀኑ ቆይተዋል፤ በእነዚህ ጊዜያትም የተቸገሩ ወገኖቻቸውን በመደገፍ ኃላፊነታቸውን እየተወጡም ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም የትንሳኤ በዓል በማስመልከት በበዓሉና በአገራዊ ሰላም እንዲሁም ሕዝባዊ እሴቶች ዙሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በየረር በር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል እና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን መልአከ ምህረት አማረ አበበን አነጋግሯቸዋል።መልአከ ምህረት አማረ አበበ ከሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ በነገረ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ ከአድማስ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ እንዲሁም ከጌጅ ኮሌጅ በማኔጅመንት ተጨማሪ ዲግሪ ማግኘት ችለዋል።በደብረሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን በመምህርነት፤ በመጠል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን፣ ሰሚት ደብረኃይል ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን፣ ደብረ ኢያሪኮ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል።በአሁኑ ወቅትም በየረር በር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል እና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በዋና አስተዳዳሪነት እየሠሩ ይገኛሉ።ከአስተዳዳሪው ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአብይ ፆም ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ከፆም ባሻገር ምን ምን በጎ ምግባራትን ሲያከናውኑ እንደቆዩ ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?
መልዓከ ምህረት አማረ፡- እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከምግብና መጠጥ ፆም ባሻገር ከአንድ ምዕመን ወይም አማኝ የሚጠበቁ በርካታ በጎ ምግባራት አሉ።ከእነዚህም መካከል በእስከዛሬው ሕይወቱ ሲፈፅማቸው ከነበሩ መጥፎ ተግባራት ተቆጥቦና ንስሃ ገብቶ ፈጣሪ የሚወዳቸውን መልካም ነገሮች መከወን ነው።በዚህ የፆም ወቅት አማኙ በተለይ ከራሱና ከፈጣሪ ጋር ታርቆ በጥሞና የሚያሳልፍበት፤ ከራሱ የሚያልፍ ሰላም ለሕዝብና ለወገኑ ለመስጠት የሚተጋበት ነው።ከዚህ አኳያ ቤተክርስቲያናችን ባለፉት ሁለት ወራት ዋነኛ ተልዕኮዋ የሆነውን ስለሰላም መስበክና ማስተማር ለአገር ሰላም ምዕመኑን ወደ መልካም አቅጣጫ የመመለስ ሚናዋን ስትወጣ ቆይታለች።
ቤተክርስቲያኒቱ ለሰላም ቅድሚያ የምትሰጥበት ዋነኛ ምክንያትም የእምነታችን መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለሰዎች ልጆች ደህንነትና ሰላምን ለመስጠት በመሆኑ ነው።እንደሚታወቀውም አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከድንግል ማርያም ሲወለድና ትንሳኤውን ሲያበስር የመጀመሪያ ሥራው ሰላምን መስበክ ነበር።ከዚህ ባሻገር መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን በሞቱ አዝነው ተቀምጠው ለነበሩ ሐዋርያት ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ብሎ ከሙታን መነሳቱን አብስሯቸዋል፤ መፅናናትም ሆኖላቸዋል።ለዚህም ነው ቤተክርስቲያናችን ከሁሉ በላይ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥታ በፆም ወቅት ስታስተምርና ምዕመኑን ለአገር ሰላም ስታስተባብር የቆየችው።
በመሠረቱ ዛሬ በዚህች ዓለምም ሆነ ለሰው ልጆች ሁሉ ከምንም በላይ የሚያስፈልገው ሰላም ነው፤ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው የምድር ፍጥረት ሁሉ ተረጋግቶ መኖር እና መሥራት የሚችለው።ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ።ለምዕመናን ህብረት ፤ ለዚህች አገር አንድነት ሰላም ወሳኝ ሚና ነው ያለው።ኢትዮጵያ አገራችን ዛሬ በብርቱ እየተፈተነች ያለችው በሰላም እጦት ነው።በየአካባቢው ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ የሰው ልጆች ቀያቸውን ለቀው ለስደት ተዳርገዋል፤ ተርበዋል፤ ተንከራተዋል።አገሪቱም የምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ተስተጓጉለውባታል።ድህነቱም በርትቶባታል።በመሆኑም የመጀመሪያ ሥራችን መሆን ያለበት ሰላም ለቤተክርስቲያን፤ ለምድራችን እንዲሆን መፀለይና ለሰላም መሥራት ነው።ዜጎችም የመጀመሪያ ምርጫቸው መሆን የሚገባው ሰላም ነው።
ከሰላም ባሻገር ግን በእነዚህ ሁለት ወራት መላው የእምነቱ ተከታዮች የተቸገሩትን በመርዳትና የሌላውን ሸክም በመሸከም ክርስቲያናዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው የቆዩት።መተባበር ያስፈልጋል።በተለይ ደግሞ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ጎዳና የወጡን በመርዳትና የተለያዩ በጎ ምግባራትን ሲያከናውኑ ነው የቆዩት።ምክንያቱም ፈጣሪ እንደሚያዘው አንዱ ጠግቦ ሌላው ተርቦ ማደር የለበትም።በመሠረቱ የተቸገሩትን ባለን አቅም መደገፍና መርዳት ካልቻልን ጾምና ጸሎት ብቻውን በቂ አይደለም፤ በፈጣሪም ዘንድ ቅቡልነት አይኖረውም።ልክ እንደፆሙ ወቅት ሁሉ የትንሳኤውንም በዓል ስናከብር በብዙ ጭንቅ ውስጥ ያሉ በርካታ ወገኖቻችን በማሰብና ያለንን በማካፈል ፍቅራችንን ልናሳያቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከምዕመኑ ምን ምን ሥራዎች ይጠበቃሉ?
መልአከ ምህረት አማረ፡- በአገር ሰላም የሚፈጠረው በመጀመሪያ በግለሰብ ደረጃ ሰላም ሲኖር ነው።ይህም ማለት ማንኛው ግለሰብ የሰላም ሰው መሆንና ከወገኖቹ ጋር በሰላም ለመኖር ፍቃደኛ ሆኖ ሲገኝ ነው።ሌሎችን ‹‹እንዲህ እና እንዲህ አድርጉ›› ከማለት ይልቅ ‹‹እኔ አጠገቤ ላሉ ሰዎች፤ ለቤተክርስቲያኔ፤ ለአገሬ ሰላም ምን ሠራሁ?›› ብሎ ራስን መጠየቅ እና ራሳችንን ማየት ያስፈልጋል ማለት ነው።አንዱ አካል ብቻ በሚሠራው ሥራ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም።ስለዚህ ሰላም የሁሉም ነው፤ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለም።አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ደግሞ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ተግባሯም ሆነ ተልዕኮዋ ሰላም ነው።‹‹ጸሎቷን ስትጀምር ሰላም ለሁሉም›› ብላ ነው የምትጀምረው።ስትጨርስም ‹‹እትሁ ለሰላም›› ብላ ነው የምትጨርሰው።ይሄ ለሰላም የምትሰጠውን ዋጋ እና ታላቅነት የሚያሳይ ነው።
በነገራችን ላይ ሰላም ለአንድ አካል ብቻ የሚተው የቤት ሥራ አይደለም ሲባል ከመንግሥት፤ ከሕዝቡ፤ ከቤተ-እምነቶች ጋር በቅንጅት የሚሠራ በመሆኑ ነው።ልክ አንድ እጅ ብቻውን እንደማያጨበጭበው፤ አንድ እንጨት እንደማይነደው ሁሉ በዚህች አገር ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ሁሉም አካል ተባባሪ መሆንና የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ፍቃደኛ ሊሆን ይገባል።ምክንያቱም የሰላም ዋጋውም በዚያው ልክ ነው።ደግሞም ሰላም ሲጠፋ ባለስልጣን ነው፤ ድሃ ወይም ሃብታም ነው ብሎ አይመርጥም።ሁሉንም ነው የሚያጠፋው።በተቃራኒው ሰላም ሲመጣ ደግሞ ለተቸገረውም፤ ለተራበውም ሰላም እስካለ ድረስ ልንደርስለት እንችላለን።በአጠቃላይ ዘላቂ ሰላም የሁላችንም አስተዋፅኦ የሚሻ ተግባር ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸው መልካም እሴቶች አሁን ላይ እየተመናመኑ ስለመምጣታቸው ይነገራል፤ እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
መልአከ ምህረት አማረ፡- እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር የተመረጠችና የፈጣሪን ትዕዛዝ ተቀብለው የሚተግብሩ ፅኑ አማኞች ያሏት አገር ናት።ይህች አገር ብዝሃ-ቋንቋ፤ ሃይማኖትና ማንነት ያሉባት ብትሆንም የፈጣሪ ትዕዛዝ የሆኑትን የመከባበር፤ የመቻቻል፤ የመረዳዳት ትዕዛዞችን በማስጠበቅ በዓለም ላይ ስሟ ገኖ ነው የሚገኘው።ያ እሴት ባይኖረን ኖሮ እንደሕዝብም ሆነ እንደአንድ አገር መቀጠል ባልቻልን ነበር።ሁላችንም ብንሆን ተከባብረን እና ተቻችለን አገራችንን የማስቀጠል ግዴታ ስላለብን ይነስም፤ ይብዛ ይህንን እሴት ይዘን ነው የቆየነው።ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ በብዙ ችግርና ጫና ውስጥ ነው የቆየችው።ይሁንና ያንን ክፉ ጊዜ ማለፍ የቻልነው ግን የውስጣችንን ችግር በውስጣችን በመያዝ፤ ተቻችለንና ተከባብረን ስለኖርን ነው።አሁንም መቀጠል ያለበት እሱ ነው ባይ ነኝ።
የቀደሙት አባቶቻችን በትልልቅ እሴት ይታወቃሉ፤ ለአብነት ያህል አገርን በማስከበር፤ በማስቀጠል፤ እርስ በርስ በመደጋገፍ አብሮ በመብላትና በመጠጣት እንዳቆዩልን መጥቀስ ይቻላል።አሁን ላይ የእምነት ተቋማትንም ሆነ አገርን ለምንመራ አካላት እነዚህን ትልልቅ እሴቶች ከአባቶቻችን በመውረሳችን እና ኃላፊነቱን ስለተቀበልን ነው አገርን ለማስቀጠል እየተጋን
ያለነው።አንቺ እንዳነሳሽው አንዳንድ ሰዎች አሁን ላይ እነዚህ የቀደሙት መልካም እሴቶቻችን ጠፍተዋል ብለው እንደሚያምኑ እረዳለሁ፤ ነገር ግን እይታቸው ሊለያይ ይችላል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ጠፍተዋል ብዬ አላምንም።አሁንም በአገራችን መደማመጥ፤ መከባበርና መቻቻሉ አለ።ይህንን ስል ግን ከዚያ ተቃራኒ የሆነ እና ፅንፍ የወጣ ነገር ፈፅሞ የለም እያልኩኝ እንዳልሆነ እንድትረጂልኝ እሻለሁ።እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ የሚሉ ከኢትዮጵያዊነት ሥነምግባር ያፈነገጡ፤ ሕዝባዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ ተግባራት ይታያሉ።ያ ግን ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።
በመሆኑም እነዚህ እሴቶቻችን መቀጠል እንዲችሉ ከተፈለገ ሁላችንም ማለትም የሃይማኖት አባቶች፤ የፖለቲካ ተዋናዮች፤ እያንዳንዱ ዜጋ የመከባበርም፤ የመደማመጥም ባህል የግድ ማዳበር ይገባናል።በመካከላችን አለመግባባት እና ልዩነቶች ማጥበብ የሚቻለው፤ ዝም ብሎ በመመልከት አልያም በማባባስ ሳይሆን በመከባበርና በመደማመጥ መነጋገር ሲቻል ነው።ለዚያ ደግሞ ፅንፍ የወጡና የማያግባቡንን ልዩነቶቻችን ማስወገድ ይገባናል ብዬ አምናለሁ።እርግጥ ነው አሁን ላይ እንደምናየው የሚያስማሙን ልዩነቶች ሰፍተዋል።ይህ የመነጨው ምንአልባት የፖለቲካው ይዘትም የፈጠረው ሊሆን ይችላል።ነገር ግን አንዱ ሌላውን የሚያይበት እይታ እንደአገር ስናየው ዋጋ እያስከፈለን ነው ያለው።
ያም ቢሆን ይህንን ችግር ማስተካከል የሚቻልበት እድል አሁንም አለ።ይህ ችግር በሁሉም ቦታ የሚታይ ባለመሆኑ የቀደሙት የመቻቻል፤ የመከባበር እሴቶቻችን የሚስፋፉበት ሁኔታ መፍጠር መቻል አለብን።እኛም እንደእምነት አባት ሆንን ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በየሥራ ድርሻቸው ሚናውን በመወጣት የቀደሙትን እሴቶቻችንን ማስቀጠል ይገባናል።ይህንን ማድረግ ካልቻልን በታሪክም፤ ባለንበት የሥራ መስክም ተወቃሽ ነው የምንሆነው።ቀድሞ እንደገለፅኩት የአንድ አካል የሥራ ድርሻ ብቻ ሊሆን አይገባም፤ ሁላችንም የየራሳችንን ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።በተለይ ትናንት አባቶች ያስረከቡን የታፈረችና የተከበረች አገር ዛሬም ባለው ትውልድ እንድትቀጥል የላቀ ትጋት ይጠበቅብናል።ለዚህ ደግሞ ወጣቱን ትውልድ ሁላችንም ሳንሰለች ማስተማር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ በተለይ ወጣቱ ላይ ለሚታየው ኢ-ስነምግባራዊ እና ከኢትዮጵያዊነት ሞራል የወጣ ተግባር በዋናነት የእምነት ተቋማት ኃላፊነታቸውን በሚገባ ባለመወጣታቸው እንደሆነ ይነሳል።ይህስ ምንያህል ተጨባጭ ነው?
መልአከ ምህረት አማረ፡- እውነት ነው! አሁን ያለው ትውልድ ድጋፍ ይፈልጋል።አንቺ እንዳነሳሽው የእምነት አባቶች በተወሰነ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብዬ አላምንም።የእምነት አባቶች ትውልዱን በሚገባ የመቅረፅ ትልቅ ኃላፊነታቸው ብቻ ሳይሆን ዋነኛ ሥራቸውም ይኸው ነው።ይሁንና ችግሩ በእነሱ ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ የሚመለከተው ሁሉ በሚገባ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብዬ አላምንም።ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ሁሉም የቤት ሥራውን በሚገባው ልክ አልሠራም።በተለይም በሉላዊነት ሰበብ እየመጣ ያለው ከባህላችንና ከወጋችን እንዲሁም ከእምነታችን ያፈነገጠ ስልጣኔ በእያንዳንዱ ቤት፤ በእያንዳንዱ ተቋም ላይ ብዙ ጫና አሳድሯል።እርግጥ ነው፤ ሉላዊነት የራሱ ጥሩ ጎን አለው፤ ልንማራቸውና እንደተሞክሮ የምንወስዳቸው ነገሮች አሉ።ግን ደግሞ የማይጠቅመንና ባህላችንን የሚበርዝብንን ነገር ልናስወግደው ነው የሚገባው።
ይህንን አጓጉል የሆነና በስልጣኔ ሰበብ የገባብንን ጎጂ አስተሳሰብ በመከላከልና በማስወገድ ረገድ ቤተ- እምነቶች ኃፊነታችንን ስለመወጣችን በየራሳችን ቤት መፈተሽ ይገባናል።በእኔ እምነት ግን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።ወጣቱ ልዩና ትኩስ ኃይል ነው፤ የነገርነውን ለማዳመጥም ሆነ ለመተግበር ዝግጁ ነው።በያዘው ንፁህ አዕምሮ ላይ ንፁህ ነገር እንዲይዝ ማድረግ ከሃይማኖት አባቶች ትልቅ የቤት ሥራ አለብን።በጥቅሉ ቤተእምነቶቹ እስካሁን የተወጡት አለ፤ ነገር ግን ብዙ ነገር ይቀራል።መሥራት ይጠበቅብናል።ብንሠራ ውጤቱን እናየዋለን።አሁን የምናየው ክፍተት ባልሠራንበት አቅጣጫ ነው።በመሆኑም ሁላችንም ወደየራሳችን ቤት ተመልሰን ትውልዱን እየቀረፅንበት ያለበትን መንገድ በአግባቡ መቃኘት ይገባናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ የሚታዩት ሙሰኝነት፤ ዘረኝነትና ፅንፈኛ ፖለቲከኝነት ችግር በእምነት ተቋማትም በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ?
መልአከ ምህረት አማረ፡- ያነሳሻቸው ጉዳዮች በሙሉ ከአስተዳደራዊ ችግር የመነጨ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ።ግን ደግሞ ይህ አስተዳደራዊ ችግር ከእምነቶች ብቻ የመነጨ ነው ብዬ እኔ አልወስደውም።ይህ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ችግር ነው።በተለይ በአገራችን የምናየው ችግር የተፈጠረው ከአገሪቱ የፖለቲካ ስሪት አኳያ ይመስለኛል።በእርግጥ ይህ ችግር በእምነት ተቋማቱ አለ፤ የለም የሚለውን ጉዳይ ለመተንተን አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ እይታችንን ይለያያል፤ ግን ደግሞ በጅምላ መፈረጁም ይከብዳል።በዚያ ውስጥ ወገባቸውን ታጥቀው ስለአገርም፤ ስለቤተክርስቲያንም የቆሙ አባቶች አሉና ነው።በደምሳሳው ችግር የለም አይባልም፤ በአስተዳደር ውስጥ ሰው ነው የሚሠራው፤ ልዩ ፍጡር ወይም መልዓክ አይደለም።እንደሰውኛ ስህተቶች አሉ።ጫፍ የወጡ ነገሮችም ይታያሉ።
ነገር ግን ሁሉም ነው ወይ ያንን የሚያደርገው? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ በዚያ ውስጥ ከኃላፊነታቸውና ከተሰጣቸው ተልዕኮ በላይ የሚሠሩ አባቶች አሉ።ሕይወታቸውን፤ ጊዜያቸውን ሰውተው የሚሠሩ አባቶች አሉ።በተቃራኒው የሰው ኃይል አስተዳደራችንን ስንመለከት በርካታ ችግሮች አሉበት።በዚያ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች በፍጥነት ካላስወገድናቸው አገርንም ሆነ የእምነት ተቋማቱን ለትውልድ ማስተላለፍ አይደለም አሁን ላሉት ማቆየት ከፍተኛ ስጋት ነው የሚፈጥረው።ያንን ግን በጅምላ ፈርጀን ሊሆን አይገባም።እንደምናውቀው በቤተክርስቲያናችን በኩል የሚታዩ ጠንካራ ጎኖች አሉ፤ በአገር ደረጃ የሠራቻቸው ትልልቅ ሥራዎች አሉ፤ በአስተዳደር ዙሪያ ደግሞ ስናይ ጉድለቶች አሉባት።በመሠረቱ ሁሉነገር የተዋጣለት አስተዳደር በዓለም ላይም ቢሆን አይኖርም።የእኛን ልዩ የሚያደርገው በመንረፈሳዊ ዓለም የምንተዳደር እንደመሆኑ ቤተክርስቲያን ከዚያ አኳያ የሚጠበቅባትን ያህል መሥራት ይጠበቅባታል።
አዲስ ዘመን፡- በተጨባጭ ሊሠሩ ይገባቸዋል ከሚሉት ሥራዎች መካከል ቢጠቅሱልን?
መልአከ ምህረት አማረ፡- በዋናነት ሊሠራ ይገባል የምለው በሰው ሀብት አስተዳደር ላይ ነው።እዚያ አካባቢ የሚታየውን ችግር መሠረቱን መንቀል ያስፈልጋል።የሰው ሀብት አስተዳደራችን ችግሮች አሉበት ሲባል ከአገልጋዮች ባሻገር ምዕመኑንም ጭምር የምንመራበትና የምናስተዳደርበት መንገድ ማለት ነው።ተቸግሮ የመጣ ሰውን ለሌላ ችግር ከመዳረግ ይልቅ ችግሩን ማስወገድ ነው የሚያስፈልገው።ታሞ የመጣ ሰው የሚያስፈልገው መድኃኒት ነው።ምክንያቱም ህመምተኞች ናቸው መድኃኒት የሚሹት።በዚህ ረገድ ሰፊ ክፍተት የሚታየው በሰው ሀብት አስተዳደራችን ዙሪያ ነው።በእምነቱም ሆነ በመንፈሳዊ አገልግሎት ረገድ ጎልቶ የሚታይ ችግር የለብንም።በአስተዳደር ዙሪያ ግን በደንብ ሊሠሩ የሚገባቸው ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ ሥራዎች የሰው ኃይል አስተዳደራችን በመሆኑ መፈተሽ ይጠይቃል።የሚታዩትን ጉድለቶች በተቋም፣ በግልም፣ ቡድንም ሆኖ እንዲስተካከል መስራት ይገባል።ይህንን ክፍተታችንን ካላስወገድነው በስተቀር ሌላ ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል ስጋት ስላለኝ በአፋጣኝ ማረም ይገባናል የሚል እሳቤ ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ ሙስና ወይም ሌብነትን በሚመለከት የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አስተምህሯችሁ ምን ይመስላሉ፤ ከዚያ አኳያስ የሚታየው ክፍተት ምንድን ነው?
መልአከ ምህረት አማረ፡- ሙስና የሚለው ቃል በመንፈሳዊ አስተምህሮ ከባድ የሆነ ትርጓሜ ነው የተሰጠው።ሙስና ወይም ሌብነት የሃጥያት ስር እንደሆነ ነው መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚያስተምረው።ያልተገባ ዓለማዊ ጥቅምን ለማጋበስ የሚደረገውን ጉዞ መጨረሻው ጥፋት እንደሚያመጣብን በግልፅ ይነግረናል።ይህ ጥፋት ደግሞ አንድን አካል ወይም ተቋምን ብቻ ነክቶ አይቆምም።እንግዲህ እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ቃሉ ‹‹ጉቦ የዓይናማዎችን ዓይን ያሳውራል›› ይላል።ይህም ማለት መማለጃ አንድ ሰው ከተቀበለ የእይታ ሳይሆን የልቦና እውር ይሆናል ማለት ነው።ስለዚህ ጉቦ የሰውን ሕይወት ያጠፋል።ተቋምንም ያፈርሳል።እውቀት አላቸው የሚባሉ ሰዎች ልቦናቸው በሌብነት አስተሳሰብ ከተማረከ እውቀታቸው ይጠፋል እንደማለት ነው።በመሠረቱ በሙስና ውስጥ ሦስት የሃጥያት መሠረቶች አሉ፤ አንደኛውና ዋነኛው አፍቅሮ ንዋይ ነው።በአስተዳደራዊ ሥርዓት ውስጥ የሚያገለግል ማንኛውም አካል የገንዘብ ፍቅር ካለበት ከሰው መስመር ወጥቶ ይወድቃል፤ ተቋሙንም ይዞ ይወድቃል።
በመሠረቱ ይህ ጉዳይ አይደለም ሰው በዲያቢሎስ አማካኝነት ክርስቶስ እንኳን ተፈትኖበታል።በተለይ የሰው ልጆች የአምላካቸውን ትክክለኛ ትዕዛዝና መርሆ ማየትና በየለቱ መተግበር ካልቻሉ ለዚህ የዲያቢሎስ አሳሳች መንገድ መውደቃቸው ወይም መፈተናቸው አይቀርም።በሌላ በኩል ሙስና የጉቦ ሰንሰለቱ ረጅም ነው።ሂደቱም ስውር ነው።ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል እንደእግዚአብሔር ቃል ፍፁም የተወገዘና የሃጥያት ምንጭ ተደርጎ ነው የተገለፀው።እንደአማኝ መማለጃ መቀበልም ሆነ ገንዘብ መውደድ ትልቅ ሃጥያት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ የተቀመጠ በመሆኑ ምንአልባት በዚህ ስህተት ውስጥ የወደቁ ካሉ በአፋጣኝ መመለስ ይገባቸዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።በተለይ አገልጋዮች ለሌሎች መልካም ምሳሌ በመሆን መገለጥና በንፅህና መመላለስ ይጠበቅባቸዋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ ማንነት ላይ ያተኮረ አድሏዊ አስተሳሰብም በእምነት ተቋማት ስር መስደዱ ይጠቀሳል፤ ይህስ ያመጣው ችግር ምንድን ነው ይላሉ?
መልአከ ምህረት አማረ፡- ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለን ሁላችንም በክርስቶስ ደም የተዋጀን አንድ ሕዝብ ነን።በጎሳ ወይም በቋንቋ ምክንያት የሚፈጠር ልዩነት ሊኖር አይገባም፤ አገራዊ አንድነታችንንም ልንተው አይገባም።በመሠረቱ ዓለም የታመሰበት አንዱ ችግር ቋንቋ ለሰው ልጆች መግባቢያ ከመሆን ባሻገር ለፖለቲካ ግብዓት እንዲውል መደረጉ ነው።ወደ ክርስርስትናውም ብንመጣ ልንግባባበት የተሰጠን ሀብት ሆኖ ሳለ የልዩነት ምንጭ ሊሆን ባልተገባ ነበር።ያም ቢሆን ቋንቋ መግባቢያ እንጂ የምንፀድቅበት መንገድ አይደለም።በመጽሐፍ ቅዱሳችንም አንድም ቦታ የፅድቅ መገለጫ ተደርጎ አልተገለፀም።ፈጣሪ ቋንቋ ለሓዋርያት የተሰጣቸው ሥራ እንዲሠሩበት፤ ያላመኑትን እንዲያሳምኑ፤ ያልተጠመቀውን እንዲያጠምቁ ፤ በሕዝቡ ባህልና በአካባቢው ሁኔታ ገብተው አስተምረው ዓለምን አንድ እንዲያደርጉ ነው።
እንዳልኩሽ ቋንቋ የተሰጠን ለመግባቢያና ለመገልገያ ቢሆንም አሁን የምናየው ሰዎች በቋንቋ ምክንያት የሚገደሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።ይሄ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው።እንደአገር ትልቅ ፈተና ነው።አሁን በአገራችን የምንመለከተው ነገር በቋንቋ በጎሳ ባሻገር ወደ ጎጥ ድረስ ወርዶ መንፈሳዊ ተልዕኳችንን እንድንስት አድርጎናል።ይሄ ለአገርም ሆነ ለቤተክርስቲያን አደጋ ነው እየፈጠረ ያለው።ፅንፈኛ ብሔርተኝነት አገር ያፈርሳል።ይሔ በሽታ ደግሞ ማንም አይመርጥም፤ ገዳይ ስለሆነ፤ ትውልድ የሚያጠፋ፤ አገር የሚያፈርስ ስለሆነ ከወዲሁ ይህንን የልዩነት አስተሳሰብ ልናስወግደው ይገባል።በዚህ ረገድ እንደቤተክርስቲያን ሁልጊዜም ቢሆን አዘውትራ የምትሰብከውና የምታስተምረው ልዩነት በክርስቶስ አለመኖሩን ነው።ደሃ ሆነ ሃብታም፤ ሐጥዕ ሆነ ፃድቅ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ማህበር ሆነዋል።ከዚህ የወጣው ግን የክርስቶስም ሊሆን አይችልም።በመሆኑም ቤክርስቲያንም ሆነ መንግሥት በቁርጠኝነት ትውልዱን ካልመከርን ካላስተማርን አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው።እንደእምነት ተቋም ይህ ዓይነቱ ነገር መምጣት አይገባውም ነበር፤ ግን ደግሞ ቤተክርስቲያን ከዚህ ፈተና የተሰወረች አለመሆኗን መገንዘብ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?
መልዓከ ምህረት አማረ፡- እንደሚታወቀው መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ክርስቶስ 40 መዓልት 40 ሌሊት ከምግብም፤ ከመጠጥም ተከልክሎ በፅድቅ አሳልፉ አርአያ ሆኖ እንዳስተማረ ሁሉ እኛም በፆም በጸሎት አሳልፈናል።ከዚሁ ጎን ለጎን በምግባሩም ከክፉ ነገሮች ተጠብቀን ቆይተናል።አሁንም በዓሉን ስናከብር በጭንቅ ውስጥ ያሉትን እያሰብንና እየደገፍን ሊሆን ይገባል።ምክንያቱም ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ከመልካም ስብዕና ጋር ካልተያያዘ ፆም ብቻውን አያድንም።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ፆም ብቻውን ፍሬ ሊሰጠንም ሆነ ሊያድነን አይችልም።ለተራቡትና ለተቸገሩት መድረስ ያስፈልጋል።እናም በዚህ ሃይማኖታዊ መርሆ መሠረት ነው ቤተክርስቲያናችንም ምዕመኖቿን ስታስተምርና ስትመራ የቆየችው፤ ምዕመኑም ይህንኑ ሲተገብር ነው ላለፉት ሁለት ወራት የቆየው።
ከዚሁ ጎን ለጎን በተለይ በሰሞነ ህመማት ሃይማኖቱ በሚያዘው መሠረት ክርስቲያኖች ከፆምና ከጸሎቱ ባሻገር አባቶች የታናናሾችን እግር በማጠብና በስግደትም ክርስቶስ ስለኛ የከፈለውን ዋጋ አስታውሰዋል።ደቀመዛሙርቱ በተጨነቁበት ጊዜ ክርስቶስ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ብሎ እንዳበሰራቸው ሁሉ ዛሬም ብዙ ወገኖቻችን በጭንቅ፤ በችግር ውስጥ በመኖራቸው የተቸገሩበትን ነገር በማገዝ ሰላማቸው እንዲመለስ መሥራት አለብን።የታመሙትን ልንጠይቅና ልንረዳቸው ይገባናል።በመጨረሻም በግሌም ሆነ እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፤ የበረከት እንዲሆንላችሁ ምኞቴን መግለፅ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
መልአከ ምህረት አማረ፡- እኔ በዚህ የትንሳኤ በዓል መልዕክቴን እንዳስተላልፍ ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም