የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ለቀድሞ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ የመታሰቢያ ውድድር ለማዘጋጀት ማቀዱን አስታወቀ። የመታሰቢያ ውድድሩ ከክለቦች ቻምፒዮና ጎን ለጎን በመጪው ወር የመጀመሪያ ሳምንት እንደሚካሄድ ታውቋል።
ብስክሌት በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ካላቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ ደግሞ ከፈር ቀዳጆቹ ጋላቢዎች መካከል አንዱ ናቸው። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካፈለችበት የሜልቦርን ኦሊምፒክ (እ.አ.አ 1956) ሀገራቸውን ወክለው ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን አስደናቂ ታሪክ የሰሩ ስፖርተኛ ናቸው። በተወዳዳሪነት ዘመናቸው በግል ባደረጓቸው ውድድሮች በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ለሀገራቸው ብስክሌተኞች አርዓያ መሆን ችለዋል።
በጎዳና ላይ በተደረገ የዓለም የብስክሌት ግልቢያ ውድድር 24ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ሲሆን ያስመዘገበው ደረጃ ከአፍሪካ እና ከእስያ ተፎካካሪዎቹ ቀዳሚ አድርጎታል። በጊዜው ኢትዮጵያ በብስክሌት በቡድን አራተኛ እንድትወጣም አስችለዋል። 17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በጣሊያን ሮም እ.ኤ.አ በ1960 ሲካሄድ ገረመው የተካፈሉ ሲሆን አሰልጣኝነት እ.ኤ.አ በ1968 ጃፓን ባዘጋጀችው 19ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካፈለውን ቡድን በአሰልጣኝነት መርተዋል።
ከተወዳዳሪነት ባለፈ የኢትዮጵያ ብስክሌት ብሄራዊ ቡድንን ለበርካታ ዓመታት ማሰልጠን የቻሉትን አንጋፋውን የሀገር ባለውለታ ለመዘከርም ከመታሰቢያ የብስክሌት ውድድሩ በተጨማሪ ሻማ የማብራት መርሀ ግብር እንደሚያዘጋጅም የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የመታሰቢያ ውድድሩ በመጪው ግንቦት 6/2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህም የቀድሞውን ታሪካዊ ብስክሌተኛ በመዘከርና የሰራቸውን ጀብዶች ለትውልድ አርዓያ እንዲሆን የማድረግ አላማ ያለው ነው።
የብስክሌት ስፖርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀዛቀዝ ቢታይበትም መሰል ውድድሮችን በማዘጋጀት ለማነቃቃት እየተሞከረም ነው። ከዚህ መታሰቢያ ውድድር በተጨማሪ የአዲስ አበባ ክለቦች ቻምፒዮናም ይካሄዳል። በእነዚህ ውድድሮች በሚደረገው ፉክክር ሀገርን የሚወክሉ ብስክሌተኞችን በማስመረጥ በዓለምና አህጉር አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉም ይደረጋል።
ሀገር ውስጥ ከሚደረጉት የብስክሌት ውድድሮች መካከል የክለቦች ብስክሌት ቻምፒዮና አንዱ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የ2015 ዓም የክለቦች ቻምፒዮና ካለፈው መጋቢት 17/2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ መነሻውንና መድረሻውን ቴዎድሮስ አደባባይ በማድረግ መጀመሩም ይታወሳል።
ውድድሩ በተለያዩ ደረጃዎች በርካታ ፉክክሮችን እያስተናገደ ባለፉት ሶስት እሁዶች ተካሂዷል። ውድድሩ በሳምንቱ መጨረሻ በእረፍት ቀናት የሚደረግና ለበርካታ ሳምንታት የሚቀጥል በመሆኑም ለስፖርተኛውና ለስፖርት ቤተሰቡ ጥሩ አጋጣሚን እንደሚፈጥር ይጠበቃል። የቻምፒዮናው ሁለተኛ ሳምንት ውድድሮች ሚያዝያ 1 ቀን/2015 ዓ.ም ከወሎ ሰፈር ወደ ኡራኤል በሚወስደው ጎዳና ሲካሄድ በክለቦች፣ በግል ተወዳዳሪዎችና ታዳጊዎች መካከል ተስፋ ሰጪና ጥሩ ፉክክር ታይቶ አሸናፊዎች ተለይተዋል።
ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ይህ የክለቦች ቻምፒዮና ክለቦች፣ ታዳጊዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎችና የቀድሞ ብስክሌተኞች የሚሳተፉበት ውድድር ነው። ቻምፒዮናው ከተወሰኑ ሳምንታት እረፍት በኋላ ሚያዚያ 22/2015 ዓ.ም ቀጥሎ የሚካሄድም ይሆናል። የቀሩትን አምስት ዙሮች ጨምሮ እስከ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም ድረስም የተለያዩ ፉክክሮችን በማስተናገድ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል።
በተለያዩ ዙሮች በሚካሄደው በዚህ ቻምፒዮና የመብራት ኃይል፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጋራድ ተሳታፊ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል። የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ፤ ስለውድድሩ ዝርዝር ጉዳዮች ወደ ፊት እንደሚገለፅ ጠቁመው፤ እነዚህ ውድድሮች ከዚህ ቀደም ይካሄዱ የነበሩ ረጃጅም የብስክሌት ውድድሮች በጸጥታ ጉዳይ በመቅረታቸው የከተማ ውስጥ የዙር ውድድሮችን ማድረግ እንደ መፍትሔ መወሰዱን አክለዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2015