ኢትዮጵያውያን በመረዳዳትና በመደጋገፍ ይታወቃሉ፤ ባሕላቸውም ነው። መረዳዳትና መደጋገፉ ሰው ባጣ በነጣ ጊዜ ካላቸው በማካፈል፣ ይህ ቀን ያልፋል፤ አይዞህ በማለት የሞራል ስንቅ በመስጠት ሲያረጋግጡት ኖረዋል።
መደጋገፍና መረዳዳቱ ያጣንና የተቸገረን በመደገፍ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም፤ ከዚህም ይሻገራል። ተረዳድቶ ሰውን ሰው ማድረግ ሌላው እሳቤ ነው። ሰዎች ተረባርበው ሰውን ሰው ያደርጋሉ፤ ልጆች ያስተምራሉ፤ ሥራ ያስጀምራሉ፤ የደከመ ካለ ቀና እንዲል ያደ ርጋሉ፤ ሥራ ያጣን ሥራ ያስጀምራሉ። ይህ የኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊ ባሕሪ ነው።
ይህ የመደጋገፍ፣ የመስጠትና የመረዳዳት ባህል በክፉ ቀን ሲሆን ደግሞ ከዚህም ይልቃል፤ ይህ በጎ ተግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ በበዓል ወቅቶች እየጎለበተ መጥቷል። በጠቅላይ ሚኒስትሩና በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ሳይቆራረጥ እየተፈጸመ ያለው በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ማዕድ የማጋራት ተግባር እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባዋል። ከሃገራዊ ለውጡ አንስቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ይህ የኢትዮጵያውያን የመስጠት፣ የመረዳዳትና መደጋገፍ ባሕል ይበልጥ ለማጠናከር የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው።
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ግጭቶች ሳቢያ ከቤትና ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ኢትዮጵያውያን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ሁሌም ይታወሳል። በዚህ ተግባር በሃገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆኑ በውጭ የሚኖሩትም በመሳተፍ ከወገኖቻቸው፣ ከመንግሥታቸውና ከሃገራቸው ጎን ቆመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ባለሀብቶችን፣ ድርጅቶችን፣ ወዘተ በማስተባበር በተለይ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር በችግር ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ማዕድ በማጋራት የፈጸሙት ሰብዓዊ ተግባር ትርጉሙ ብዙ ነው። ይህ አርአያነት ያለው ድጋፍ ክልል ከተሞች ድረስ እየዘለቀም ይገኛል። የክልል መሪዎች፣ ከንቲባዎችና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ሕዝቡን፣ ባለሀብቶችን። ድርጅቶችን እያስተባበሩ ችግረኞች ዓመት በዓልን ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ እያደረጉ ናቸው።
በዚህ በጎ ተግባር እነዚህ ዜጎች ዓመት በዓልን ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ ማድረግ ተችሏል፤ በበዓል ወቅት ምግብ ከመቋደስም ባለፈ ኑሮን ለመደጎም ያስቻለም ነው፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ በሁሉም ዋና ዋና የሃይማኖት በዓላት ወቅት ይህ ድጋፍ ተደርጓል፤ ድጋፉም እየሰፋ መጥቷል። ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በክፉ ቀን የሚደርሱላቸው ወንድሞች እህቶች እናቶችና አባቶች ልጆች እንዳሏቸው እንዲረዱ አድርጓል።
ድጋፉ ከተደረገላቸው ዜጎች በስተጀርባ ያሉ ሕጻናት ፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ወዘተ. ሲታሰቡ ደግሞ ድጋፉ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን አንደሚችል መገመት አይከብድም። ከሁሉም ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳትና መደጋገፍ ባሕል በሚገባ ማስጠበቅ ያስቻለ ብቻ ሳይሆን የመስጠትን፣ የመደገፍንና የመርዳትን አስፈላጊነትና ታላቅ ተግባርም ያስተማረም ነው።
በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኪስ ውስጥ ለእነዚህ በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ሊሆን የሚችል ሀብት ስለመኖሩ ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና የመስጠትን፣ የመርዳትና የመደገፍን ጽንሰ ሀሳብ ባለመረዳት፣ ምናልባትም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ካለመስጠት የተነሳ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ይህን ታላቅ እሴት ያላጤኑበት ሁኔታ ይስተዋላል። ሁሉም ዜጎች በዚህ ጉዳይ ላይ ግንዛቤው እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ በመሥራት ለእነዚህ በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ ማስገኘት ይቻላል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚገነዘበው ኢትዮጵያውያን ይረዳዳሉ፤ ይደጋገፋሉ፤ ይሰጣሉ። መረዳዳቱ፣ መደጋገፉና መተጋገዙ ግን ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት ከአቅራቢያ ብዙም የተሻገረ ነው ብሎ ማለት አይቻልም፤ ይህን በጎ ተግባር ማሻገር ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ችግሩ ደጅ እስከሚመጣ፣ መንገድ ላይ እስከሚታይ መጠበቅም አይገባም፤ እንደ ታዳጊ ሃገር ባለው የምጣኔ ሀብት ውስንነት በከፋ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በርካታ ናቸው። እነዚህ ዜጎች የመንግሥትን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን የቅርብ ድጋፍ ይፈልጋሉ። ይህን ማስገነዝብ ላይ መሥራት ለነገ ሊባል የሚገባው ተግባር አይደለም።
የእያንዳንዱ ዜጋ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ድጋፉ የተደራጀ እንዲሆን ማድረግ ላይ መሥራትም ይገባል፤ ሜቄዶኒያና ሌሎች ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ተቋማት ለእዚህ ትልቅ ትምህርት ቤት ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ ተቋማት በማቋቋም ዜጎችን አሰባስቦ በኅብረት መርዳትም ይቻላል።
አንዳንድ ባለሀብቶች አንደሚያደርጉት ሌሎች ባለሀብቶችም በዓመት ከሚያገኙት ትርፍ የተወሰነውን ለዚህ ታላቅ ተግባር እንዲያውሉ ቀርቦ ማስረዳት፣ ድጋፍ ያደረጉ ባለሀብቶችን በጎ ተግባር እንዲመለከቱት ማድረግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
ሁሉም ዜጎች የሌሎች ዜጎች ሕመም እንዲሰማቸው ማድረግ ላይ ከትምህርት ቤት ጀምሮ መለማመድም ሌላው ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ለእዚህ ደግሞ በማዕድ ማጋራት፣ በኢትዮጵያውያን በተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንዲደርሷቸው ማድረግ በትምህርት ቤታቸው ለእዚህ ተግባር የሚሠሩ ክበባትን በማቋቋም ላይ ተማሪዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል። ይህ ሁሉ ሲሆን የኢትዮጵያውያን የመደጋገፍ፣ የመረዳዳትና የመስጠት እሴት ይበልጥ እየጎለበተ ይሄዳል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ.ም