የዓለም አትሌቲክስ ከጥቂት ወራት በኋላ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በሚያካሂደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 40ኛ ዓመቱን ያከብራል። ይህንን ክብረ በዓል ተከትሎም የዓለም አትሌቲክስ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ከወዲሁ ማዘጋጀት ጀምሯል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ባለፉት 18 ቻምፒዮናዎች የታዩ ምርጥ ክስተቶችንና የአስደናቂ ታሪኮች ባለቤት የሆኑ አትሌቶችን ማስመረጥ ነው።
ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው ይህ ምርጫ በኢንተርኔት ተደግፎ በደጋፊዎች ድምፅ የሚሰጥበት ሲሆን፤ 40 የሚሆኑ አትሌቶችና አስደናቂ ገድሎቻቸው በሁለቱም ጾታ ተዘርዝረዋል። ከእነዚህ መካከልም አንድ መራጭ በሁለቱም ጾታ ለአስር አስር አትሌቶች ድምጽ የሚሰጥ ይሆናል። አሸናፊዎቹም በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት በሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ይፋ ይሆናሉ። ከመራጮች መካከል ሁለት የሚሆኑት ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ በቻምፒዮናው የመታደም ዕድል ያገኛሉ።
የዓለም አትሌቲክስ እስካሁን በተካሄዱ የዓለም ቻምፒዮናዎች አስደናቂ ክስተቶች ናቸው ብሎ በዝርዝር ካቀረባቸው መካከልም ኢትዮጵያውያን ድንቅ አትሌቶች ተካተዋል። በዝርዝሩ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ ተካተዋል። ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በተለየ መልኩ እ.አ.አ በ2003ቱ የፓሪስ እና በ2009 የበርሊን ቻምፒዮናዎች ላይ ባሳየው አቋም ሁለቴ ሊመረጥ ችሏል። ኢትዮጵያ በዚህ ቻምፒዮና ተሳትፎዋን ከመነሻው (እ.አ.አ በ1983 ፊንላንድ) ስታደርግ፤ ማራቶንን ሁለተኛ ሆኖ በገባው አትሌት ከበደ ባልቻ የመጀመሪያውን ሜዳሊያም አሳክታለች። ባለፉት 18 ቻምፒዮናዎችም 33 የወርቅ፣ 34 የብር እና 28 የነሐስ በጥቅሉ 95 ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል።
አትሌቶቹ ሜዳሊያዎችን ከማስመዝገብ ባለፈ ያሳዩት ብቃት ደማቅና የማይረሳ ታሪክ ሆኖ ሊመረጡ ችለዋል። እ.አ.አ በ1999 በስፔኗ ሴቪሌ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ስታስመዘግብ አንደኛው የተገኘው በምንጊዜም ምርጡ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ነበር። እ.አ.አ ከ1993 የስቱትጋርት ቻምፒዮና አንስቶ በዚህ ውድድር ተካፋይ የነበረው ኃይሌ በተከታታይ በ10ሺ ሜትር ሊደፈር የማይችል አትሌት መሆኑን አስመስክሯል። አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀበትን ውድድርም ዓለም አቀፉ ተቋም ታሪካዊ ከሆኑ ክስተቶች መካከል አካቷል።
ቀጣዩ ቻምፒዮና እ.አ.አ በ2001 ካናዳ ኤድመንተን ላይ ነበር የተካሄደው። በዚህ ቻምፒዮናም አሁን ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በመምራት ላይ የሚገኙት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገዛኸኝ አበራ ነበሩ የወርቅ ሜዳሊያዎች ያሳኩት። በሴቶች 10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ ደራርቱ ቱሉ በቻምፒዮናው አሸናፊ የሆነችው ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ሲሆን፤ ከወሊድ መልስ በአስደናቂ አቋም በኦሊምፒክና የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ላይም አስደማሚ ብቃት ነበር ያሳየችው። አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚም ተከትለዋት በመግባት ሜዳሊያዎቹን ጠራርገው የወሰዱበት አስደሳች ውድድር በመሆኑም በበርካቶች ዘንድ ይታወሳል።
ከረጅም ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ዳግም በኦሊምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያሳካችው ሲድኒ ላይ ነበር። የሜዳሊያው ባለቤት ገዛኸኝ አበራ የሰራው ገድል ሳይቀዘቅዝ በዓመቱ ኤድመንተን ላይ ዳግም ቻምፒዮን በመሆንም በርካቶችን አስደንቋል። እጅግ ፈታኝ በነበረው ውድድር ገዛኸኝ ኬንያዊውን አትሌት በአንድ ሰከንድ ቀድሞ በመግባትም ነበር አሸናፊነቱን የተቀዳጀው። ከፍተኛ ጽናትና አቅም በሚጠይቀው ማራቶን በተከታታይ ዓመት በሁለት ትልልቅ ውድድሮች አሸናፊ መሆን ደግሞ የተለየ ብቃት የሚጠይቅና የምንጊዜም ጀግና የሚያሰኝ በመሆኑ ለምርጫ ቀርቧል።
ፈር ቀዳጇ ሄልሲንኪ ቻምፒዮናውን ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀችበት 2005 በሴቶች 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ተዓምር ነበር የታየው። በሁለቱም ርቀት ኢትዮጵያውያኑ ከወርቅ እስከ መዳብ ያሉ ሜዳሊያዎችን ጠራርገው ሲወስዱ፤ የጥንካሬ ተምሳሌቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በሁለቱም ርቀት ወርቅ ያጠለቀች የመጀመሪያዋ አትሌት በመሆን አስደናቂውን ገድሏን አጽፋለች። አይረሴ በሆነው በዚህ የአትሌቷና የዓለም ቻምፒዮና ታሪክ ታላቅ እህቷ እጅጋየሁ ዲባባ ደግሞ ተከትላት በመግባት ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቋ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የሚታወስ ነው።
ጀግናው የረጅም ርቀትና የማራቶን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኦሊምፒክ፣ በዓለም ቻምፒዮና እና በአገር አቋራጭ ቻምፒዮናዎች የሠራቸው ጀብዱዎች ተዘርዝረው አያልቁም። በዚህ የውድድር መድረክ 6 ሜዳሊያዎችን ያስቆጠረው አትሌቱ፤ መነሻው እ.አ.አ የ2003ቱ የፓሪስ ቻምፒዮና ነበር። የታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ተተኪ መሆኑን ባስመሰከረበት በዚህ ውድድር የ10ሺ ሜትር አሸናፊ ሲሆን በ5ሺ ሜትር ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ነበር ያገኘው። ከሄልሲንኪ እና ኦሳካ በመቀጠልም በ2009 በርሊን ላይ ዳግም በሁለቱም ርቀት አሸናፊ በመሆን ሌላ ክብር ደርቧል። ቀኒሳ ከድሉ ባሻገር በ10ሺ ሜትር የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻልም ቻምፒዮናው ከማይረሱት መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጓል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2015