እንቁጣጣሽ፣ ገና ወይም ጥምቀት ወይም ፋሲካ በዓል መቼ እንደሆነ ዘንግተዋል እንበል።የከፈቱት ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን በግድ ያስታውስዎታል።በቤትዎ ውስጥም ይሁን በታክሲ እየሄዱ የተለቀቀ ማስታወቂያ ‹‹እንዴ በዓል ደረሰ እንዴ?›› እንዲሉም ያደርግዎታል።ሬዲዮ እያዳመጡ የበዓል ዘፈን ሲለቀቅ የበዓሉን መድረስ እያበሰረዎት ነው።የበዓል ዘፈኖች የሚለቀቁት የበዓል ሰሞን ብቻ ስለሆነ የድባቡን መጣሁ መጣሁ ያስታውሳሉ። የበዓሉን ዕለት እንመልከት። በበዓል ቀን የበዓል አድማቂዎች መገናኛ ብዙኃን ናቸው።ቤተሰብ ሰብሰብ ብሎ በጋራ ይከታተላል። ይሄ ማለት በዓሉን የሚያከብሩት በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ያለውን የበዓል ሁኔታም ነው።በበዓል ቀን በየቤቱ ልብ ብላችሁ ከሆነ ከሌላው ቀን በተለየ ነው ቴሌቪዥን የሚከፈተው።
ሌላ ጊዜ የዜና ሰዓት ወይም የሚፈልጉት ፕሮግራም ላይ ሊሆን ይችላል፤ የበዓል ቀን ግን ራሱን ችሎ ማድመቂያ ነውና ሙሉቀን ላይዘጋ ይችላል። በተለይም በትምህርት፣ በሥራ፣ በተለያየ አጋጣሚ ከቤተሰብ ርቀው ላሉ ሰዎች ደግሞ የተለየ ቦታ አለው።ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የበዓልን ትዝታ የሚያዩት፣ የሚዝናኑት ቴሌቪዥን በማየት ነው። አሁን ባለን ተጨባጭ ሁኔታ መገናኛ ብዙኃን ለበዓል ምን ያህል አስፈላጊና ማድመቂያ እንደሆኑ ግልጽ ነው።አሁን ዋናው ጥያቄ መገናኛ ብዙኃንና በዓላት ምን እያስተላለፉልን፣ ምን እያስተማሩን ነው? የሚለው ነው።
ባስ ሲልም በሚያስተላልፉት ፕሮግራሞች አሰልችና ፋይዳ ቢስነት የተነሳ ‹‹በበዓል ቀን ቴሌቪዥን ላልከፍት ቃል ገብቻለሁ›› የሚሉ ሰዎችን እየሰማን ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበዓል ቀን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን አስተውላችሁ ከሆነ ከዝንጀሮ ቆንጆ ማንን ይመራርጡ አይነት ናቸው። አብዛኞቹ በተሰለቹ ፊቶች የሚቀርቡ የተኮረጁ ፕሮግራሞች ናቸው። አንድ ሰዓት ወይም ሁለት ሰዓት ሙሉ እዚህ ግባ የማይባል አሰልች ፕሮግራም ያልቃል።ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የኪነ ጥበብ ሰዎች መሆናቸው ይበልጥ ያሳዝናል።እንዲሁም ይህን የሚያደርጉት ትልቅ አገራዊ ኃላፊነትን የተሸከሙት የመንግስትና የግል የመገናኛ ብዙኃን ናቸው።
ይህን የሚያደርጉት በህዝብ ገንዘብ ሀብታም የሆኑት አጋር(ስፖንሰር) አድራጊ ድርጅቶች ናቸው።ካልጣመዎ ያለዎት አማራጭ ቴሌቪዥኑን መዝጋት ብቻ ነው።ቻናል እንዳይቀይሩ በየቀየሩበት ቻናልም ያው አቅራቢዎቹ ይቀየሩ ይሆናል እንጂ ያው ተመሳሳይ ይዘት ነው የሚሆነው። ለዚህ ሃሳብ ማጠናከሪያ የሆነኝ ከአንድ ወዳጄ ጋር በአጋጣሚ ያደረግነው ጭውውት ነበር። ወዳጄ ባለፉት ሶስት በዓላት ጥሩ የሆነ ሀገራዊ ለዛ ያለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቀርፆ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና አጋር ድርጅቶችን ፍለጋ ተንከራቷል። በተለይም ትልልቆቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቀድመው ፋይዳ ቢስ በሆኑ ፕሮግራሞች ስለሚያዙ ትልቅና አዳዲስ ሃሳቦችን እንደማያስተናግዱ ታዝቧል።
በተለይም አሁን ሀገራዊ ጉዳዮቻችን የሆኑ የላሊበላ፣ የጣና፣ የፓርኮቻችንን ጉዳት የሚታደጉና እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትንና ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአቶቻችን ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ማቅረብ እንደማይፈልጉም ተረድቷል። በተለይም ባለቤቶቹና ገምጋሚ ተብለው የሚቀመጡ ሰዎች የሚቀርቡትን ፕሮጀክቶችን በብቃት ከመመዘን ይልቅ በመተዋወቅና የተሻለ ማስታወቂያ ያስገኛሉ የሚሏቸውን እንደሚመርጡ አስተውሏል። ስፖንሰር የሚያደርጉት ድርጅቶች የገበያ ባለሙያዎችም ገንዘብ የሚያስለቅቁት በፐርሰንት ተደራድረውና በትውውቅ እንደሚሰሩ ነበር ያጫወተኝ። ጋዜጠኛ ይርጋ አበበ በእንዲህ አይነት ፕሮግራሞች ላይ በእንግድነት ተጋብዞ ያውቃል።ፕሮግራሙ አንዱ አንዱን እያባረረ መያዝ አይነት የሕጻናት ጨዋታ ነበር የሆነበት።
ጋዜጠኛ ይርጋ እንደሚለው ብዙ ችግር ባለባት አገር ውስጥ እንዲህ አይነት ፕሮግራሞችን መሥራት ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መጥፋቱን ያሳያል።የበዓል ቀን ማለት ሰዎች በሥራ ቀን እንኳን የማያዩትን ነገር ሳይወዱ ተገደው የሚያዩበት ነው።ዘመድና ጓደኛ ተሰባስቦ ሃሳብ የሚለዋወጥበትም አጋጣሚ ነው።በዚህ አጋጣሚ ጠቃሚ ነገር መተላለፍ ሲገባው ውሃ ሲራጩ፣ እርስ በርስ ሲጓተቱ፣ ሲሯሯጡ ማየት ማንንም ሊያዝናናም ሆነ ሊያስተምር አይችልም።ይህን የሚያስተላልፍ የሚዲያ ኃላፊ ኃላፊነት የማይሰማው እንደሆነም ያስባል።
እርግጥ ነው የበዓል ቀን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መተንተን የበዓል ድባብ ሊያበላሽ ይችላል፤ ይሁን እንጂ እየቀረበ ያለው ነገር እያዝናና ቁምነገር የሚያስተላልፍ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው።‹‹ ለእኔ አንድ ጨርቄን ጥዬ የማደንቀው አርቲስት ውሃ ሲራጭና ጭቃ ሲቃባ ማየት ምኑም አያዝናናኝም›› ይላል ጋዜጠኛ ይርጋ ትዝብቱን ሲገልፅ።መዝናኛ ሲባል መሳቅ ብቻ አይደለም፤ ማስተማርም ጭምር ነው፡፡
የሚያሳዩን ነገር የሚያሳቅቅ እንጂ የሚያስቅ ነገር አልሆነም።ፕሮግራሙ ታይቶና ተገምግሞ ነው የሚያልፈው? ለሕዝቡ ይመጥናል? ብሎ የሚጠይቅ የሚዲያ ኃላፊ ያለመኖሩን ነው መገንዘብ የሚቻለው። በሌላ በኩል ደግሞ አጋሮች(ስፖንሰር) ምን ፕሮግራም ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል።በትራፊክ አደጋ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ በሆነች አገር ላይ እየኖሩ እርባና የሌለውን ፕሮግራም ስፖንሰር የሚያደርጉት የቢራ ፋብሪካዎች ናቸው።ባንኮችም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፤ ቁጠባንና ብልጽግናን ማበረታታት ሲገባቸው ትውልድ አደንዛዥ የሆኑ ፕሮግራሞችን መደገፋቸው ያስተዛዝባል። ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሥዩም ሌላው አስተያየት ሰጪ ነው።በበዓል ቀን የሚቀርቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ምንም አይነት የበዓል ይዘት የላቸውም ይላል።
«ብዙዎቹ የበዓል ፕሮግራሞች አሰራራቸው ከፈረንጅ የተኮረጁ ናቸው።ከፈረንጅ መኮረጁ አይደለም ችግሩ፤ ጨዋታዎቹ ፈረንጆች ለበዓል ብለው ያዘጋጇቸው አይደሉም፤ በማንኛውም ቀን የሚያቀርቧቸው ናቸው፡፡በምንም መስፈርት ጭቃ ላይ መንከባለል የበዓል መገለጫ ሊሆን አይችልም፤ ገመድ መጓተትና ውሃ መራጨት ለበዓል የሚደረግ ባህላዊ ክዋኔ አይደለም።ለበዓል የሚደረጉ ባህላዊ ሥርዓተ ክዋኔዎች አሉ፤ ችግሩ ግን እነዚያን ማን ሄዶ ያጠናል? በመጀመሪያ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ይጀምረዋል፡፡አንዱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲጀምረው ምናልባትም የመጀመሪያ ነውና የተወሰነ ሰውም ቢሆን ሊያስቅና ሊያዝናና ይችል ይሆናል።
ችግሩ ግን ከዚያ በኋላ የሁሉም ቴሌቪዥን የጋራ ፕሮግራም ይሆናል።የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማለት ከአርቲስቶች ጋር ዕቃ መወራወር ብቻ የሚመስላቸው ብዙዎች አሉ» በማለት እስከዛሬ ያስተዋላቸውና የታዘባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ያስታውሳል። ጋዜጠኛ ሄኖክ ለችግሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሎ ያሰበውንና መፍተሄውንም ይናገራል። «እስካሁን ሰዎችን ወዲህ የከተታቸው የቢራ ገበያው ነበር።አሁን እሱ ሲቀር የተሻለ ነገር ይመጣ ይሆናል።እስካሁን ምንም ሃሳብ የሌለው ሰው ከቢራ ባለቤቶች ጋር ባለው ቀረቤታ የፈለገውን ነገር ያቀርባል።በበዓል ቀን ሊያዝናኑ የሚችሉ ብዙ ባህላዊ ነገሮች አሉን።
በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የበዓል አከባበር የተለያየ መልክ አለው።የአንዱ አካባቢ ለሌላው ያስተምራል፣ ያዝናናል፤ ያንን ማሳየት ግን እውቀት ይጠይቃል።ማጥናትና ማንበብ ይጠይቃል።አጋር ስለተገኘ ብቻ ምንም ሳያስቡና ሳያፈላልጉ ቁጭ ብሎ የጉርሻ ውድድር፣ የእቃ መወራወር፣ የወሃ መራጨት አያዝናናም አያስተምርም። ይሄ አካሄድ ሊያበቃ ይገባዋል» ‹‹ድሮ በዓል ሲመጣ በጣም ያጓጓ ነበር›› የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ ያኔ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሥራዎቻቸው የሚቀርቡበት፣ ቤተሰባዊ ጉዳዮች የሚወሩበት፣ ጥበባዊ ሥራዎች የሚቀርቡበት ስለሆነ ነው።
አሁን የኪነ ጥበብ ሰዎችን ሰብስቦ የሕጻናት ጨዋታ ማጫወት በህዝብ ላይ መቀለድ ነው።እንዲያውም አሁን አሁን ሰው ቴሌቪዥን የሚከፍተው መሃል መሃል ላይ ለሚለቀቁ ሙዚቃዎች እንጂ ፕሮግራሙ አስተማሪና አዝናኝ ሆኖ አይደለም። የሙስሊም በዓላት ሲከበሩ የሚቀርቡ ዝግጅቶች እንደ ጥሩ ምሳሌ ይጠቅሳል።የበዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘት ብቻ ሳይሆን ጥበባዊ ነገሮች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሳይንሳዊ ግኝቶቹና ምርምሮቹ ይቀርቡበታል።በውስጡ ያሉ ጥበባዊ ፍልስፍናዎች ይተዋወቁበታል።ቤተሰባዊ ጉዳዮች ይቀርቡበታል።
በአገራችን ያሉ በዓላት ሁሉ ሰፊ የሆነ ሃይማኖታዊ፣ ሳይንሳዊና ጥበባዊ ታሪክ ያላቸው ናቸው።እነዚያን ግን የሚያጠና የለም።የሚሰራው እዚሁ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ ነው፤ ምናልባት ርቀው ሄዱ ከተባለ እንጦጦ ወይም ሱሉልታ ከደረሱ ነው፤ ለዚያውም ሜዳ ለሜዳ እየተሯሯጡ ለመቅረጽ እንዲያመቻቸው ነው። በጋዜጠኛ ሄኖክ አስተያየት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ገንዘብ የላቸውም።ገንዘብ የሚያገኙት እነዚያው ሃሳብ የሌላቸው ሰዎች ናቸው።አስተማሪ የሆነ ሃሳብ ያላቸው ፕሮግራሞች ስፖንሰርም ለበዓል ቴሌቪዥናችንን እንዝጋ ወይስ…? ላያገኙ ይችላሉ።
የሚዲያ ባለቤቶች ኃላፊነት ማጣትም የጋዜጠኛ ሄኖክ ትዝብት ነው።አንድ ሆቴል ምግብ ሲያዘጋጅ ትልቅ ጥንቃቄ አድርጎ ነው።የደንበኞቹን ፍላጎት አስልቶ ነው።ማዘጋጀት ያለበትንና የሌለበትን ነገር ህግ አውጥቶ ያንን ጠብቆ ነው።ሰላጣ ማዘጋጀት የለብኝም ካለ አያዘጋጅም፤ ማዘጋጀት አለብኝ ካለ ሳያጓድል ያዘጋጃል።የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች ግን ከንግድ ተቋም አንሰዋል።በመላ አገሪቱ የሚታይ ፕሮግራም ትልቅ ኃላፊነት ሊወሰድበት እንደሚገባም ያሳስባል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎች ውስጥ ‹‹የፈጠራ ሃሳብ ማጣት›› የሚለውን እናስምርበት።እነዚህ ቴሌቪዥን የሚያስዘጉ ፕሮግራሞች እንግዲህ በአርቲስቶች የቀረቡ መሆናቸው ነው አሳዛኙ ጉዳይ።በዚህ ሊያፍሩ ይገባል።አርቲስት ማለት የፈጠራ ሰው ነው።
በምናብ ፈጥሮ የሌለን ነገር ያለ አስመስሎ ማስተማር ሲገባው አገሪቱ ውስጥ በገሃድ ያለውን ነገር እንኳን ማሳየት አልቻለም። አርቲስቶች ተጋባዥ ብቻ አይደሉም፤ ራሳቸው የፕሮግራሙ አዘጋጆችም እነርሱው አርቲስቶቹ ናቸው።የአገርን ባህልና ወግ እንዲያስተዋውቁልን እና እንዲያስከብሩልን የምንጠብቃቸው አርቲስቶች ናቸው ከፈረንጅ ኮርጀው ውሃ ሲራጩ የሚውሉት።ባልሰለጠኑበት ሙያ ጋዜጠኛ የሚሆኑት። ከምንም ነገር በላይ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።በነገራችን ላይ አስተማሪና የአገሪቱን ባህል የሚያስተዋውቁ አገርኛ ፕሮግራሞች የሚያቀርቡት በራሳቸው ዝግጅት ክፍሎች ነው።
ይህን ያደረገ ጣቢያ ግን ገንዘብ ስላስገኘለት ብቻ የተኮረጀና የተሰለቸውን የበአል ፕሮግራም ደግሞ ይፈቅዳል።መጀመሪያ ከማወዳደሪያ መስፈርቱ ጀምሮ ለተመልካች በሚመጥን መንገድ መሆን እንደነበረበት ጠፍቷቸው እንዳልሆነ ለማናችንም የተደበቀ አይሆንም፡፡ገንዘብ ስላስገኘ ብቻ በተመልካች ጊዜ መቀለድ ግን ተገቢ አይደለም። የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች፣ አርቲስቶችም ሆኑ አጋር አካላት ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።አዳዲስ ነገሮች ይፍጠሩ፤ የሀገራችንን ባህል፣ ትውፊትና ሌሎች መልካም ነገሮቻችንን በጥበብ ከሽኖ በማጉላት ይስሩ። አለበለዚያ ለበዓል ቴሌቪዥን ዘግተን መቀመጣችን አይቀሬ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011
ዋለልኝ አየለ