በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን አሁን ላይ ትኩረት እያገኙ መጥተዋል። በተለይም ዕድሜ እንቅስቃሴያቸውን የገደበባቸው ዜጎች በተለየ ሁኔታ ድጋፍና እንክብካቤ ሲደረግላቸው ይስተዋላል። ይህ እንደ ሀገርም ሆነ አካባቢ እጅጉን የሚያስደስትና ለሌሎች ምሳሌ መሆን ያለበት ሰናይ ተግባር ነው።
በዚህ የተቀደሰ ዓላማ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በአቧሬ አካባቢ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት የ70 ዓመቷ አዛውንት እማማ አበበች ዘውዴ ናቸው። እኚህ እናት የአንድ እግር ጉዳተኛ ሲሆኑ፤ በእርጅና ምክንያት እቤት ውለዋል። ቤት ሳይውሉ ግን የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን በዱላ እየታገዙ ይንቀሳቀሱ ነበር። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አረጋውያንን ካሉበት የከፋ አኗኗር ለማውጣት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በተካሄደ መርሐ-ግብር ባለፉት ሁለት ዓመታት ቤታቸው የመታደስ ዕድል አግኝቷል። በዚህ እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ሲገልፁም ‹‹እሰየው በላዬ ላይ ሊፈርስ የነበረው ቤቴ ታድሷል። እንደውም በአካል ጉዳተኛነቴ ምክንያት ከሌሎች አረጋውያን በተለየ ሁኔታ ’ቅድሚያ ይሰጣት’ ተብሎ ነው የታደሰልኝ። የምበላውም አግኝቻለሁ›› ይላሉ።
በፊት ቤታቸው በማፍሰሱ ብቻም ሳይሆን ከታችም የክረምት የጎርፍ መተላለፊያ የነበረ በመሆኑ ሲቸገሩ ኖረዋል። ዕድሜ ተጭኗቸው እግርና እጃቸው እንደልብ አልንቀሳቀስ ስላላቸው ጾም ውለው ያድሩ ነበርም። ቤታቸው በሴቶችና ማህበራው ጉዳይ የቁሳቁስ ድጋፍና በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ታድሶላቸው በጥሩ ሁኔታ መኖር ሲጀምሩ ግን ሁሉ ነገር ተቀየረ። ቤታቸው በደስታ ተጎበኘም። ቤታቸው ከታደሰ ጀምሮ “የደሀ ደሀ” በሚል በቀበሌ ተመልምለው የአንድ ሺህ ብር ድጋፍ ያገኛሉ። እናም ይህንን ሁኔታ ሲያስረዱ ‹‹አሁን በቀሪ ዕድሜዬ ፈጣሪዬን እያመሰገንኩ የምገፋበት ሁኔታ ላይ ነኝ›› በማለት ነው።
‹‹ሁለት እግሬ ጉዳተኛ ነው። በሁለት ክራንች ነው የምሄደው›› የሚሉት አባት አረጋው ቶማስ ቶላም የዚህ እድል ተጠቃሚ ናቸው። ዕድሜ ተጭኗቸው መንቀሳቀስ ባቃታቸው ወቅት የመንግስት ሠራተኛ የሆኑ ጓደኛቸው ይደግፏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁንና ይህ እስከመጨረሻው የቀጠለ አልነበረም። ጓደኛቸው በ60 ዓመታቸው ጡረታ በመውጣታቸው እጅ አጠራቸውና እሳቸውን መደጎም ቀርቶ በጡረታ የሚያገኝዋት ጥቂት ብር የራሳቸውንም ወጪ አልሸፍን ስላለቻቸው ድጋፋቸውን አቆሙ። በዚሁ ምክንያትም ወደ ልመና ወጡ። መቄዶኒያ ለመግባትም ጥረት አድርገው “ቤተሰብ አለህ” በሚል ምክንያት አልተሳካላቸውም።
“ሰው ሲሸመግል አስታዋሽ ያጣል። ብዙ ጊዜም ጡረታ ከወጣ በኋላ የሚጠቅም ፍጡር ተደርጎ አይታሰብም” የሚሉት ባለታሪካችን፤ ጓደኛቸው በጊዜው እኔ ነኝ ካለ ጎረምሳ የበለጠ የጉልበትም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሥራ የመሥራት አቅም ስለነበራቸው በአንድ ቀበሌ ፈቃደኝነት በኮንትራት ጥበቃ ሥራ በመቀጠራቸው የአቅማቸውን ያግዟቸው ነበር። በዚህም ልመና እንዳቆሙ ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደጋፊ ጓደኛቸው በሞት ተለዩዋቸው። ስለዚህም ምርጫ ስላልነበራቸው ተመልሰው ወደ ልመና ወጡ። ይህም ፈታኝ ነበር። ምክንያቱም ደግፎ ወደ ውጪ የሚያወጣቸውን ይሻሉ። ይህንን ያዩ የአካባቢው ወጣቶች ደረሱላቸውና ታደጓቸው። እራሳቸውን ችለው ባይሄዱም መሥራት ይችሉ ነበርና ወጣቶቹ “አንዲ ማማ” ከተባለ የግል ድርጅት ጋር በመነጋገር የተለያየ ሥራ እንዲሰሩ አደረጓቸው። በሥራው ጉልበታቸው መጠንከሩንም ያወሳሉ። ይሄ ድርጅት በወር 1ሺህ 500 ብር ደሞዝ ይከፍላቸዋል። አሁንም መሥራት ተሰኗቸውም ቢሆን ድርጅቱ የዕለት ጉርሳቸውን አልነፈጋቸውም።
በሴቶችና ሠራተኛና ማህበራው ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች የአድቮካሲና መብት ጥበቃ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጥላሁን እንደሚናገሩት፤ የአካል ጉዳት ዕድሜ በገፋ ጊዜ ተደራራቢ ችግር ይሆናል። በመሆኑም የአካል ጉዳት ያለባቸው አረጋውያንን ለመደገፍ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። አቅም ያላቸው እንደ ‹‹አንዲ ማማ›› ባሉም ሆነ በሌሎች የግል ድርጅቶች ባሉበት ሆነው እንዲሰሩ ይደገፋሉ። ተግባሩ የሚከወነው ደግሞ ከእነዚህ ዓይነት ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት ነው።
እንደ ተቋም የአካል ጉዳት ከሌለባቸው አረጋውያን በተለየ ሁኔታ አካል ጉዳት ያለባቸው አረጋውያን ቅድሚያ አግኝተው የሚደገፉበት ሁኔታ በተቋማቸው አማካኝነት ተመቻችቷል። ለምሳሌ በእርጅና ምክንያት ቤት ከፈረሰባቸው እናቶች የቤቱ መፍረስ አካል ጉዳተኛ አረጋውያን እናቶችን የበለጠ ስለሚያስቸግር በቅድሚያ የእነርሱ ቤት እንዲሰራና እንዲታደስ ይደረጋል። ከላይ ከሚኒስቴር መሥርያ ቤት ጀምሮ በየደረጃው ባለው አረጋውያን የ‹‹ደኃ ደኃ›› በሚል ተመልምለው መሥራት ባይችሉም እንኳን የዕለት ጉርሳቸውን እንዲሸፍኑ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ለአካል ጉዳተኛ አረጋውያን ቅድሚያ እንዲሰጥም በአሰራር ተደግፏል።
“በአረጋውያን አያያዝና እንክብካቤ የበለፀጉት ሀገሮች አይታሙም። ከጎለበተ ኢኮኖሚያቸው አንፃር የተሻለ ልምድ አላቸው” የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ በእነዚህ ሀገሮች አረጋውያን በልዩ ሁኔታ እንደሚታዩ ያነሳሉ። የሚሰጧቸው ስያሜ በራሱ ‹‹የዕድሜ ባለፀጎች›› የሚል ክብርና ሞገስ የተሞላበት ነው። ለቀሪ ዘመናቸው ጉልበት የሚቸር ተስፋ ሰጪ ስምም እንደሆነ ይናገራሉ። የበለፀጉት ሀገሮች ምግብና መጠጡን እንዲሁም የመጠለያውን ጉዳይ ተሻግረው የእነሱ አረጋውያኖች የዲጂታላይዜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው የሚያምኑ ናቸው።
እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ካለንበት ኢኮኖሚያውና ማህበራው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የእኛ ሀገር አረጋውያን የዲጂታላይዜሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም ጉዳይ አይደለም። እንኳን አረጋውያኑ ወጣቱም ያለበት በዚህ ልክ ነው ማለት አያስችልም። የእኛ ሀገር የአረጋውያን አንገብጋቢ ጉዳይ የማህበራው ጥበቃ አገልግሎት ስርዓት ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ሴቶችና ማህበራው ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ሁሉም በቅንጅት መሥራት አለበት።
የአረጋውያንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ብሄራው ማህበራው ጥበቃ ፖሊሲ ላይ የተቀመጡ አምስት የትኩረት መስኮች አሉ። መስኮቹ አካል ጉዳተኞቹን ወይም ሴት አረጋውያንን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አረጋውያንን የሚመለከቱ ናቸው። እነሱም የመሥራት አቅም ላላቸው አረጋውያን የሴፍትኔት መርሐ ግብር፣ የሥራ ስምሪትና የተሻሻለ የኑሮ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። የጤንነት ሁኔታቸው ካሉበት የዕድሜ ደረጃ አንፃር የተለየ እንክብካቤ የሚፈልግ ነውና የሚያስፈልጋቸውን ማህበራው መድህን መስጠት ግድ ነው። ትራንስፖርት፣ መጠለያ፣ ቤትና ሌሎች መሰረታው አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችላቸው እንዲሁም በብዙ ተጋላጭ የሆኑበትን ጥቃትና በደልን መከላከል ተገቢ እንደሆነ ያስቀምጣል። ስለዚህም ይህንን ተግባራው ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ያስረዳሉ። እኛም ማህበራው ጥበቃ ፖሊሲው ተግባራው ይደረግና አካል ጉዳተኛ አረጋውያን መፍትሄ ይሰጣቸው በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2015