የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻልና እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። አገሪቱ ያላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ የገበያ እድል፣ ያስመዘገበቻቸው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገቶች፣ በተለይ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባሮች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዘርፉ ማበረታቻዎች፣ አገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ አገራት መካከል አንዷ እንድትሆን ማስቻላቸው ሲጠቀስ ቆይቷል። ይህ ሁሉ ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ማደግ ዓይነተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገትም ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ በአገሪቱ ላይ የተደረጉ ጫናዎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታዩ የምጣኔ ሀብት ቀውስና ጦርነቶች ጋር ተዳምረው በአገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። በተለይም ባለፈው ዓመት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸው በተደጋጋሚ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ባለፈው ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ጦርነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከአጎዋ (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልፆ ነበር።
ከጦርነት በኋላ በሚኖር የኢንቨስትመንት አስተዳደርና አመራር ብቻም ሳይሆን በሰላም ጊዜም ቢሆን የኢንቨስትመንት አቅሞችንና አማራጮችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን መሳብና ዘርፉን ማሳደግ ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን የሚያገናኙ፣ የኢንቨስትመንት አቅሞችንና አማራጮችን የሚያስተዋውቁ መድረኮች ከፍተኛ ሚና አላቸው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም ለባለሀብቶች ማስተዋወቅን ዓላማቸው ያደረጉ ልዩ ልዩ መድረኮች እንደተካሄዱ ይታወሳል። በመድረኮቹ ቀላል የማይባሉ ውጤቶችም ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በሕግ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አቅሞችና በዘርፉ ያሉ መልካም እድሎችን ለማስተዋወቅ ያለመ፣ ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› (Invest Ethiopia) የተሰኘ የኢንቨስትመንት ፎረም ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ፎረሙ ከሚያዝያ 18 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ፣ ስካይላይት ሆቴል እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ከ600 በላይ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተዋንያን እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን እንደሚሉት፣ እንደ አገር ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ዘላቂ የሆነና የተሻለ ጥቅም ለማግኘት በራስ ተነሳሽነት የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ሥራዎችን መሥራት ተገቢ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት አቅም ማስተዋወቂያ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ይህን አሠራር ባለፉት ዓመታት በሚፈለገው ደረጃ መተግበር አልተቻለም። ባለፉት ሦስት ዓመታት የኮቪድ ወረርሽኝ የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓትን ሲያናጋ ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም፣ በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት ተሸጋግራለች ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ስጋትነቱ መቀነሱንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አገራትም ያሏቸውን አማራጮች በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለመጨመር እየሠሩ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት። ይህን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሌሎች አጋር የመንግሥት አካላት ጋር፣ በተለይም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በውጭ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ሚሽኖች ጋር፣ በመተባበር ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ትልቅ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም እንዳዘጋጀ ገልፀዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ እንደሚሉት፣ የፎረሙ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያሏትን ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማስተዋወቅ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኮቪድ ወረርሽኝ እና በግጭቶች ምክንያት ያልተዋወቁ አዳዲስ ለውጦች አሉ። ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና መወዳደሪያ መስፈርቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል ወደ ሥራ የገቡት አዳዲሶቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የኢንቨስትመንት አዋጅ (1180/2012) ተጠቃሽ ናቸው። አዋጁ ለግሉ ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን የሚከፍት ነው። በቅርቡ ይፋ የተደረገው የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ፖሊሲም ተጨማሪ ማሳያ ነው።
ባለፉት ዓመታት ከ80 በላይ ለቢዝነስና ኢንቨስትመንት ሥራ ማነቆ የነበሩ ሕግጋት ተሻሽለዋል ያሉት አቶ ተመስገን፣ አዲሶቹ ሕግጋት ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ የሚፈጥሩ ቢሆኑም ለግል ባለሀብቶች በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ አልተቻለም ይላሉ። ‹‹ፎረሙ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ የተደረጉ ለውጦችን እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የተተገበሩት የኢንቨስትመንት ከባቢ ማስተካከያ ሥራዎች ያመጧቸውን መሠረታዊ የሕግና የአሠራር ለውጦችን የሚያስተዋውቅ መድረክ ይሆናል›› ሲሉ ይገልጻሉ።
አቶ ተመስገን እንደሚሉት፣ ፎረሙ በማክሮ- ኢኮኖሚ ደረጃ የተደረጉ ማሻሻያዎች (በተለይም በቴሌኮምና በፋይናንስ ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎችን)፣ በዘርፍ ደረጃ የምጣኔ ሀብት እድገት ምሰሶ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ ዘርፎች (ግብርናና የግብርና ማቀነባበሪያ፣ የማምረቻ፣ የማዕድን፣ የቱሪዝም እና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ) እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳለጥ የተጀመሩ የዲጂታል አሠራሮች የሚተዋወቁበት የኢንቨስትመንት አቅም ማሳያ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የቆዩ ባለሀብቶች ሥራቸውን በማስፋት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲመለከቱ ፎረሙ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ባለሀብቶቹ ከፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላት ጋር በሚኖሯቸው ግንኙነቶች ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች በቅርበት ለመወያየትም እድል ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪም ፎረሙ ክልሎች ያሏቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለባለሀብቶች የሚያስተዋውቁበት መድረክም ይሆናል። የቢዝነስ ተቋማት እርስ በእርሳቸውና ከመንግሥት አካላት ጋር የሚገናኙባቸው መድረኮችንም ያካትታል።
በፎረሙ ላይ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ከ600 በላይ አዳዲስና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን ድረስ 500 ባለሀብቶች ተመዝግበዋል። ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚገኙበት የሚካሄዱ ከፍተኛ የፓናል ውይይቶችን (High Level Panel Discussions) ጨምሮ፣ የኢንቨስትመንት አማራጭ ማስተዋወቂያ እና የልምድ ልውውጥ መድረኮች፣ የልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉብኝቶች፣ ኤግዚቢሽኖችና ተዛማጅ መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ። ከወሳኝ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከዚህ ቀደም ከኮሚሽኑ ጋር ግንኙነት ከነበራቸው አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ይፈረማሉ። ይህን ለማሳካትም ልዩ የኢንቨስትመንት ምንጭ ይሆናሉ ተብለው በሚታሰቡ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ምልመላዎችን እያካሄዱ ናቸው።
በፎረሙ ላይ ከ50 በላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ይገኛሉ። የሥራ ኃላፊዎቹ በየዘርፎቻቸው ያሉ እድሎችን በማስተዋወቅ እንዲሁም ለባለሀብቶች ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ በመስጠት ይሳተፋሉ። ከዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኤጀንሲዎች ማኅበር የሚመጡ ተወካዮች ደግሞ ስለዓለም አቀፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት አቅጣጫዎች ገለፃ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር የሆኑ የቢዝነስ ተቋማት ሥራ አስፈፃሚዎችም ልምዳቸውን ያካፍላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የየራሳቸውን ቦታ ወስደው ያሏቸውን አማራጮች በሰፊው የሚያሳዩበት እድል ይኖራቸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፎረሙ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የመነሻ መድረክ ይሆናል ብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም ቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት እስከሚገባ ድረስ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
አቶ ተመስገን ባለፉት ዓመታት በተሠሩት የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራዎች ከተመዘገቡ ስኬቶች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ያሏትን ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች በማየት በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ አገሪቱ መጥተው በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› ፎረም በቀጣይ ዓመታት እያደገ እንዲሄድና በአፍሪካ ደረጃ ተጠቃሽ የሆነ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረም እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
መሰል የኢንቨስትመንት አቅም ማስተዋወቂያ መድረኮች ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚሳዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ያስረዳሉ። በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ ‹‹በምጣኔ ሀብታቸው ያደጉ አገራት ጭምር እንዲህ ዓይነት የኢንቨስትመንት አቅም ማስተዋወቂያ መድረኮችን የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን ለማሻሻል ይጠቀሙባቸዋል።›› ሲሉ ይገልጻሉ። ‹‹ብዙ አገራት የኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸውን መድረኮች በተደጋጋሚ ሲያዘጋጁ ማየት የተለመደ ነው። መድረኮቹ አገራት ያላቸውን አቅም በትክክል ለማሳየት ይጠቅማሉ። ስለሆነም ፎረሙ ለአገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ የሚኖረው ሚና የሚያጠያይቅ አይደለም›› ይላሉ።
እንደሳቸው ማብራሪያ፣ የውጭ ባለሀብቶች በተለይም ስለአፍሪካ ያላቸው ግንዛቤ በቂ ስለማይሆን መሰል የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው። እነዚህ መድረኮች ግንዛቤ በመፍጠር ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ያመቻቻሉ። ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› ፎረምን በታቀደለት ዓላማ መሠረት በመምራት የኢንቨስትመንት ዘርፍ አቅምን ማሳደግና ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ ይገባል።
ዶክተር ሞላ ፎረሙ ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመው፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በዘላቂነት ለማሳደግ ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን እንደሚገባም ገልፀዋል። እንደ ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› ያሉ ፎረሞችን ከማዘጋጀት ባሻገር ሰላምና ፀጥታን በዘላቂነት በማስፈን፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት መጠን እና የተሳትፎ መስክ በማስፋት የዕውቀት፣ የክህሎት፣ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ስርጸትን ማፋጠን ተገቢ ይሆናል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ በውጭ እና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች መካከል ትስስርን በማስፋት፣ የኢንቨስትመንት ክልላዊ ስርጭትን በማሻሻል፣ እንዲሁም የውጭ ካፒታል በመጠቀም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ፤ ኢንቨስትመንቶች በአገራዊ የኢንቨስትመንት ዓላማዎች የተመለከቱ ግቦችን ማሳካታቸውን ይገባል። እንዲሁም በሕግ አግባብ መከናወናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት፣ ኢንቨስትመንት የሚመራበትን ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ፣ ተገማች እና ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠንና የእድገቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2015