በአንድ አገር ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻለው ጠንካራ የመከላከያና የፀጥታ ተቋሞችን በአስተማማኝ ሁኔታ መገንባት ሲቻል ብቻ ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን አገራት በአካባቢያዊ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተደማጭነት ለማሳደግ በእነዚህ ተቋማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለነዋዮችን እየመደቡ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ አቅማቸውን ሲገነቡ ይስተዋላል።
በተለይም ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ብሩህ ሆኖ የሚታያቸው፣ ለዚህም ብዙ ተስፋ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ያሉ አገሮች፤ ዘላቂ ሰላምን ዋነኛ አጀንዳቸው በማድረግ ለመከላከያና ለፀጥታ ተቋሞቻቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። በሚያስመዘገቡት ስኬት ልክም ሰላማቸውን በማስጠበቅ የሕዝባቸውን የመልማት ፍላጎት እውን ማድረግ እየቻሉ ነው።
በእኛም አገር ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን የሕዝባችንን የመልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አገራዊ የፖለቲካ ባህሉን (የሴራ ፖለቲካ) ከመቀየር ጀምሮ፤ ለውጡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጓዝ በመንግሥት በኩል ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ሰላምን እንደ አንድ ዋነኛ የፖለቲካ እሴት ከመስበክ ጀምሮ ስለ ሰላምም ብዙ ዋጋ ከፍሏል።
ከዚህም ጎን ለጎን መንግሥት አገራዊ የለውጥ አስተሳሰቡን መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በስፋት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህም ውስጥ በዋነኝነት በመከላከያና በፀጥታ ተቋሞቻችን ላይ የጀመራቸው የሪፎርም ሥራዎችና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው።
እንደ አገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው እልህ አስጨራሽ ትግል አቅም እንደሚሆን የሚታመነው ይህ በመከላከያና በፀጥታ ተቋሞቻችን ላይ የጀመርነው የሪፎርም ሥራ፤ ዕለት ተዕለት አቅሙን እያገዘፈ አገርን ከየትኛውም የህልውና ስጋት መታደግ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ፤ የተቋማቱ አመራሮች በብዙ መተማመን የሚናገሩት እውነት ከሆነ ውሎ አድሯል።
ተቋማቱን በተልእኮ በአዲስ መልክ በመግራት ሕዝባዊነታቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ ማነጽን፤ የሰው ኃይልና የትጥቅ አቅማቸውን በማዘመን ወቅቱን የሚመጥን ማድረግን ያካተተው የሪፎርም ሥራው፤ ተቋማቱ በርግጥም ትናንት ከነበሩበት አገርን የማይመጥን ቁመና ወጥተው እንደአገር ትልቁን ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ እያስቻላቸው ነው።
የክልል ልዩ ኃይሎችን በአዲስ መልክ የማደራጀቱ ውሳኔና የማስፈጸም ሂደት የዚህ ሪፎርሙ አካል የነበረና በተለያዩ ውስጣዊ ምክንያቶች የዘገየ ነው። ዋንኛ ዓላማውም ይህንን ኃይል የተሻለ ቁመና በማላበስ አገራዊ አቅም ሆኖ እንዲወጣ ማስቻል ነው።
የክልል ልዩ ኃይል አገር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በነበረችባቸው ወቅቶች ለሕይወቱ ሳይሳሳ ስለአገሩ የሞተ እና የቆሰለ በዚህም ደማቅ ታሪክ መጻፍ የቻለ ነው። አገሩን በታማኝነት ለማገልገል በእሳት የተፈተነ ማንነት የገነባ፣ ይህ ማንነቱ በየትኛውም ሁኔታ እና አሉባል,ታ የማይፈታ፤ በቀጣይም እየተፈተነ የሚጠራ ነው።
ይህንን ኃይል በተራ አሉባልታ በማደናገር በሞት የተፈተነውንና ጠርቶ የወጣውን የአገር ፍቅሩን ማራከስ የሚቻል አይሆንም። ይህ ኃይል መቼም ቢሆን በጽንፈኞችና ሁከት ጠማቂዎች አጀንዳ ተጠልፎ በሕይወቱ ተወራርዶ በታደጋት አገሩ ላይ የሚነሳ አይሆንም። ለዚህ የሚሆን ማንነት የለውም፤ መቼም ቢሆን ሊኖረው አይችልም።
ከዚህ ይልቅ አሁን እያደረገ እንዳለው የጽንፈኞችንና የሁከት ጠማቂዎች አጀንዳ ረግጦ ራሱን ለላቀ አገራዊ ግዳጅ የሚያበቃበትን የተሻለ ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅበታል። ከዚህ ጎን ለጎንም በጉዳዩ ዙሪያ በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ብዥታ በማጥራት ሂደት ውስጥም ራሱን ግንባር ቀደም አድርጎ ሊንቀሳቀስና የአገር አለኝታነቱን በድጋሚ ሊያረጋግጥ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም