በ14 የዓለም ከተሞች የሚካሄደው ዓመታዊው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከሳምንታት በኋላ በኳታሯ ዶሃ ይጀመራል። ውድድሩን ተከትሎም በስፖርት ቤተሰቡ ትኩረቱን በ3ሺ ሜትር ርቀት ላይ አድርጓል። አምስቱ የወቅቱ ድንቅ ብቃት ባለቤት የሆኑ አትሌቶች በዚህ ውድድር ላይ እንደሚካፈሉ ማረጋገጣቸው ደግሞ ይበልጥ ፉክክሩን አጓጊ አድርጎታል። በተለያዩ ውድድሮች ባስመሰከሩት ጥንካሬ ለአሸናፊነት ከፊት ረድፍ ከተቀመጡትና በውድድሩም ለአሸናፊነት ተጠባቂ ከሆኑት አትሌቶች መካከል ሶስት የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በዶሃ ከሚካሄዱ ፉክክሮች መካከል በተለይ በ3ሺ ሜትር የሚካሄደው ፍልሚያ ከፍተኛ ትኩረት ከወዲሁ ያገኘውም የርቀቱን ባለ ክብረወሰን አትሌት ከሌሎች በርቀቱ ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች ጋር ስለሚያገናኝ ነው። በተለይም ወጣቱ ድንቅ አትሌት በርቀቱ ከፍተኛ ልምድ ካካበተው ሞሮኳዊ አትሌት የሚኖራቸው ፉክክር ተጠባቂ ሲሆን፤ በርቀቱ የተሻለው አትሌት የሚለይበትም ይሆናል። ከሁለት ወር በፊት በሌቪን የ3ሺ ሜትር ርቀት የዓለም ክብረወሰንን በመስበር የግሉ ያደረገው ወጣቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ ከተጠባቂዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። ከአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና አንስቶ በአጭር ጊዜ እስከ ትልልቅ የውድድር መድረኮች ስኬታማ መሆን የቻለው ለሜቻ የቅርብ ጊዜ ድሉን ይደግማል የሚል ከፍተኛ ግምት አግኝቷል።
የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም የቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ለሜቻ፤ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናም የብር ሜዳሊያ ማጥለቁ የሚታወስ ነው። በተያዘው የውድድር ዓመት ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ተሳትፎው ሌቪን ላይ 3ሺ ሜትር ርቀትን 7:23.81 በሆነ ሰዓት የዓለም የክብረወሰን ባለቤት መሆን ችሏል። ይህም የ22 ዓመቱን አትሌት በርቀቱ ቅድሚያ ተጠባቂ ሲያደርገው ዶሃ ላይም እንደተለመደው ብቃቱን በማስመስከር አሸናፊ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ይሁንና ፈታኝ ፉክክር እንደሚገጥመው ግልጽ ነው።
ምክንያቱም ተፎካካሪው ለረጅም ዓመታት 3ሺ ሜትር መሰናክልን የሮጠውና በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በዩጂኑ የዓለም ሻምፒዮና ለሜቻን የረታው ሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ በመሆኑ ነው። አትሌቱ በተለይ የሚታወቀው በመሰናክል ይሁን እንጂ በዚህ ውድድር ዋዛ ሊሆን እንደማይችል ይገመታል። ውድድሩን ተከትሎ በሰጠው አስተያየትም ‹‹ይህ ትልቅ ዓመት ነው፤ በቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊነቴን ለማስጠበቅ ይህ ውድድር ይረዳኛል። የእስካሁኑ ዝግጅቴ ምን ይመስላል የሚለውንም በዶሃ በሚኖረኝ ተሳትፎ መረዳት እችላለሁ›› ማለቱ ለአሸናፊነት መዘጋጀቱን ያመላክታል።
በዚህ ርቀት ከለሜቻ ባሻገር ሁለት ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶችም ተሳታፊነታቸውን ያሳወቁ ሲሆን፤ ከወቅታዊ አቋማቸው በመነሳት ለአሸናፊነት የሚወዳደሩ መሆኑን መገመት አያዳግትም። ለውድድሩ ፈተና እንደሚሆኑ የሚጠበቁት እነዚህ አትሌቶችም በቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮናው ሰለሞን ባረጋ እና በርቀቱ ስኬታማው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ናቸው። አትሌት ሰለሞን ባረጋ በተለይ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ታዋቂ ይሁን እንጂ በ3ሺ ሜትርም አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻለ አትሌት ነው። በወጣቶች ቻምፒዮና ላይ ውጤታማ የሆነው ሰለሞን እአአ 2018 ላይ በበርሚንግሃም እንዲሁም ያለፈው ዓመት የቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የብር እና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ነው።
እአአ በ2018 በ5ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ የሆነው ሰለሞን በ3ሺ ሜትር ርቀት ያለው ፈጣን ሰዓትም ከክብረወሰኑ በ3 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነው። ይህም አትሌቱ በዚህ ውድድርም የተለየ ቅድመ ግምት ካገኙት አትሌቶች ጋር ፉክክር በማድረግ አሸናፊነቱን የሚያሳካበት እድል መኖሩን የሚያሳይ ነው። ሌላኛው ወጣት አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻም በተመሳሳይ ከ5 እና 10ሺ ሜትር በተጓዳኝ በ3ሺ ሜትር ርቀትም ስኬትን ማጣጣም የቻለ አትሌት መሆኑ ለአሸናፊነት ተጠባቂ አድርጎታል። እአአ በ2016 በፖርትላንድ በተዘጋጀው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ባለ ድል ሲሆን፤ በ2018ም በርሚንግሃም ላይ አሸናፊነቱን በድጋሚ ተቀዳጅቷል። ይህም አትሌቱን ሌላኛው የዳይመንድ ሊግ ተፋላሚ ሊያደርገው ይችላል።
ለኢትዮጵያውያኑ እንዲሁም ለሞሮኳዊው አትሌት ፈተና ሊሆን እንደሚችል የተገመተውና የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱን ካገኙት መካከል አንዱ ኬንያዊው አትሌት ቲሞታይ ቹሪዮት ነው። እአአ ከ2017 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ዓመታት በ1ሺ500 ሜትር የዳመንድ ሊግ አሸናፊ የሆነው አትሌት ዘንድሮ ደግሞ የሚወዳደርበትን ርቀት በመቀየር ዶሃ ላይ የ3ሺ ሜትር ርቀት ተፎካካሪ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2015