ፖለቲካ በጥበብ የመምራት ችሎታን ይጠይቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝብና ሀገርን ማስቀደም፤ልዩነትን ማቻቻል፤ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መቆምን ይሻል፡፡ ከራስ ፍላጎትና ምቾት ይልቅ ለህዝብና ለሀገር ፍቅርና ተቆርቋሪነትንም ያስቀድማል፡፡ እንደ ስልጡን ማህበረሰብ መመካከርና መወያየትም አብዝቶ ይፈልጋል፡፡
የሀገራችንን የትናንትም ሆነ የዛሬ የፖለቲካ ታሪክ ስንመለከተው ደግሞ፣ እውነታዎች የተገላቢጦሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች ከመወያየትና ከመመካከር ይልቅ መዝለፍ የሚቀናቸው፤ ከዘላቂ የሀገር ሰላምና ዕድገት ይልቅ ጊዜያዊ ጥቅም የሚበረታባቸው፤ ስልጣንን በምርጫ አሸንፎ ከመረከብ ይልቅ የተለያዩ አጀንዳዎችን እና ውዥንብሮችን በመፍጠር በአቋራጭ ለመቆናጠጥ የሚሞክሩ፤ ለዚህም ሌት ተቀን የሚተጉ ናቸው።
ሰበብ እየፈጠሩ የህዝብን ስሜት መቆስቆስና ሰላም እንዲደፈርስ ማድረግን እንደ አንድ የፖለቲካ ግብ አድርገው የሚወስዱ፤ ለዚህም የተሳሳቱ መረጃዎችን በስፋት ወደ ሕዝብ ጆሮ ከመልቀቅ ጀምሮ የጥፋት ትርክቶችን በመፍጠር ሕዝብን ከመንግስት ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት ያዘወትራሉ፤ ከሚፈጠረው ግጭትም አትራፊ ለመሆን ያለመታከት የሚሰሩ ናቸው።
እነዚህ የፖለቲካ ሀይሎች / ተዋናዮች ከያዙት የፖለቲካ ስትራቴጂ አንጻር ያልተረዷቸው ሁለት መሰረታዊ ነገሮች አሉ ፡፡ አንደኛው ስልጣን ላይ ወጥቶ ሀገር መምራት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ እንደሆነ፤ ሁለተኛው ደግሞ ለስልጣን መሻታቸው ብለው የሚጠምቁት ጥፋት ለነሱም የሚተርፍ የከፋ መንገድ መሆኑን ነው።
ሰላም በሌለበት እንኳንስ ሀገር መምራት በህይወት የመቆየት ዋስትናን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሸክሟ በከበደ ሀገር ላይ በፖለቲካ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች እሩቅ አሳቢ ካልሆኑ በቀር ፤ የስልጣን መሻታቸውን ብቻ እየተከተሉ በጭፍን የሚሄዱበት መንገድ ሀገርና ህዝብን ሊያስከፍል የሚችለው ያልተገባ ዋጋ የከፋ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዘመንና ትውልዶችን የተሻገሩ በርካታ ችግሮች የተጋረጡባት ሀገር ነች፡፡ ለሀገሪቱና ለህዝቦቿ እናስባለን የሚሉ ፖለቲከኞች የችግሮቹን ስፋትና ጥልቀት በሚገባ ተረድተው በብዙ ማስተዋል መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ የሚሆንም የፖለቲካ ስብእና ሊገነቡ ያስፈልጋል።
የቀደሙት ችግሮቻችን ትተን አሁነኞቹን እንኳን ብናስብ፤ ለሁለት አመታት ያህል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት የፈጠረብን ሀገራዊ ቁስል ገና አላገገመም፡፡ ድርቅ ዛሬም እየተፈታተነን ነው፤ መልከ ብዙ የኑሮ ውድነት የህዝባችን ዋነኛ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ስራ አጥነት ገና ያልተፈታ ችግር ነው፤ የዕዳ ጫና እና የውጭ ሀገራት ፖለቲካዊ ተጽዕኖም ገና ፈር ያልያዘ ጉዳይ ነው፡፡
እነዚህና መሰል ችግሮች ባልተፈቱበት ሀገራዊ አውድ ሌሎች ተጨማሪ ችግሮችን እየቀመሩ የፖለቲካ ገበያውን የግጭትና የሁከት ገበያ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት በግልጽ ከሀገርና ህዝብ ጥቅም በተቃራኒ ከመቆም የተለየ አይደለም፤ የህዝባችንንም የዴሞክራሲ ስርአት ተገንብቶ የማየት መሻት በአደባባይ የመጻረር እኩይ ተልእኮ አካል ነው።
በአሁኑ ሰአት መርህ አልባ በሆነ መንገድ፤ ሀገርና ህዝብን አደጋ ውስጥ በሚከት የጥፋት ተልእኮ ውስጥ የምትገኙ የፖለቲካ ሀይሎች / ተዋናዮች ከዚህ ተግባራችሁ ልትታቀቡ ይገባል፡፡ ይህ ተግባራችሁ ነገ ከነገ በስቲያ የሞራልም፣ የህግም ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው።
መንግስት ለጀመረው የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ስኬት የፈጠረውን ሆደ ሰፊነት ፤ በአግባቡ ተገንዝቦ መመላለስ፤ ለሀገርና ለህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሰከን ማለት ከእናንተ ይጠበቃል፡፡ በተለይ በዚህ ጊዜ በሰከነ መንገድ መነጋገርና መደማመጥ ወሳኝ ነው፡፡ ሰሞኑን ልዩ ኃይሎችን መልሶ ከማደራጀት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ጉዳይም በዚሁ ልክ መገንዘብም፣ ማየትም ያስፈልጋል፡፡
ተደጋግሞ እንደተገለጸው እና በህገ መንግስቱም ላይ በማያሻማ መልኩ እንደተመለከተው፤ ሀገርን እና ህዝብን ከየትኛውም ጥቃት እና ጠላት የሚከላከል ሀገራዊ ሀይል የመገንባት ኃላፊነት እና ስልጣን የፌዴራል መንግስቱ ብቻ ነው፡፡ የክልል መንግስታትም የክልላቸውን ሰላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅ ክልላዊ ፖሊስ አደራጅተው እንደሚመሩ በህገ መንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ስለዚህም ይህንን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ውይይትና ምክክርን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ መሬት ማውረድ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያም በበርካታ ችግሮች ትከሻዋ የዛለ ሀገር እንደመሆኗ፤ ተጨማሪ ችግሮችን እንድታስተናግድ መንገድ ማበጀት አይገባም፡፡ ከዚህ የተነሳ በፖለቲካው ውስጥ ካሉ ተዋናዮች ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ በአግባቡ መረዳት እና በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ፤ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ይልቅ ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግና ሰላም ማስፈን ላይ ማተኮር ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም