በብዙዎች ዘንድ ‹‹ዝምተኛው ስፖርት›› በሚል ቅጽል ይጠራል፤ መስማት የተሳናቸው ስፖርት። መስማት በተሳነው ፈረንሳዊ ሰው ሩቤንስ አሊሼስ የተመሰረተው ይህ ስፖርት፤ መነሻ የሆነው በወቅቱ በሀገሩ ያሉ እሱን መሰል በርካታ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ነው:: አንቶኔ ድሬስ በተባለው ቤልጂየማዊ አጋሩ እገዛም እአአ በ1924 የመጀመሪያው መስማት የተሳናቸው የስፖርት ውድድር ሲካሄድ፤ ተሳታፊ የነበሩት ጥቂት አውሮፓውያን ብቻ ነበሩ::
በሂደትም ስፖርቱ አድጎ በብሄራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፌዴሬሽን የተቋቋመለት ሲሆን፤ በተለያዩ ስፖርቶችም ውድድሮች ይካሄዳሉ:: በጥቂቶች የተጀመረው ስፖርቱም በዚህ ወቅት በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ስር ያሉ አባላት ቁጥሩን ወደ 108 አሳድጓል። ይህ መስማት የተሳናቸው ስፖርት በኢትዮጵያም በማደግ ላይ ካሉ ስፖርቶች መካከል ይገኛል:: ከሰሞኑም ለ3ኛ ጊዜ መስማት የተሳናቸው አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል:: በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከመጋቢት 27-30/2015 ዓ.ም የተካሄደው ውድድሩ፤ በፉክክሮች ታጅቦ በደመቀ ሁኔታ ፍጻሜውን አግኝቷል::
ለአራት ተከታታይ ቀናት በሜዳና የመም ተግባራት ፉክክሮች ሲካሄድ የቆየው ውድድር፤ ዓላማውም መስማት የተሳናቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊና አቋማቸውን መፈተሻ እንደሆነ ሀገር አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን አስታውቋል:: በተጨማሪም በውድድሩ የተሻሉ አትሌቶችን በመለየት
ለአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊ ለማድረግ መሆኑም ተጠቁሟል:: እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሌላው በተለየ መልኩ ድጋፍና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ሥራ ያስፈልጋቸዋል:: በዚህም በስፖርቱ ዘርፍ እነሱን የሚያሳትፉ ውድድሮችን ማዘጋጀት እና ተፎካካሪነታቸውን ማሳየት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ልዩ ፍላጎት ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ስፖርታዊ ውድድሮችን በስፋት ማዘጋጀት አልተለመደም::
ነገር ግን ሀገርን በመወከል የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ስለሚችሉ ትኩረት ሰጥቶ መሰል የውድድር እድሎችን ማስፋትና መስማት የተሳናቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቋሚ ነው:: በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቃልቤሳ ኤባ፤ መስማት ለተሳናቸው የህብረተስብ ክፍሎች ውድድሮችን ከማዘገጀት አንጻር ያለው እንቅስቃሴ በቂ እንዳልሆነና በስፋት መስራት እንደሚኖርበት ይገልጻሉ::
በአሁኑ ወቅትም ሀገር አቀፍ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን በአትሌቲክስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና በክብደት ማንሳት ስፖርቶች ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአትሌቲክስ ውድድር መካሄዱን ተከትሎ በቀጣይ ደግሞ በጠረጴዛ ቴኒስና ክብደት ማንሳት ስፖርቶች ውድድሮችን ለማዘጋጀት መታቀዱንም ያብራራሉ:: በእግር ኳስ ስፖርትም ከአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር ለመስራት በእቅድ ተይዟል:: ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነውም በአንድ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፎ ማድረጉን ነው:: በቀጣይም ስፖርተኞቹ ባላቸው ውጤት ተመርጠው በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳተፊ እንደሚሆኑም ተነግሯል::
በስፖርት እንቅስቃሴ መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰጣቸው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቀልቤሳ፤ ጅማሮ እንዳለና ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅም አክለዋል:: ማህብረሰቡ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች ያለውን አመለካከት እንዲቀይርና ተሳታፊነታቸውንም ማረጋገጥ እንደሚገባም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል::
በቻምፒዮናው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፤ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች እድል ከተሰጣቸው ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያሳዩበት መድረክ ሆኖ መጠናቀቁም ተነግሯል:: በውድድሩ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችሏል:: በ8 የወርቅ፣ በ5 የብርና በ8 የነሃስ በአጠቃላይ 21 ሜዳሊያዎችን ይዞ በቀዳሚነት አጠናቋል:: አማራ ክልል በ7 የወርቅ፣ በ12 የብርና በ8 የነሃስ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን ይዞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሷል። ኦሮሚያ ክልል ደግሞ በ3 ወርቅ፣ በ6 ብርና በ4 ነሃስ በአጠቃላይ በ13 ሜዳሊያዎች በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2015