የዋጋ ግሽበት ለብዙዎች ፈተና እየሆነ ነው። በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ድረጃ ላይ የሚገኘውንና የመንግስት ሰራተኛውን ኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው። የዋጋ ግሽበቱ ደግሞ መሰረታዊ በሆኑት ጤፍን በመሳሰሉ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካላቸው አገራት ተርታ ትገኛለች። በአፍሪካ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት የተመዘገበባት አገር ዚምባብዌ ስትሆን ይህም 285 በመቶ ነው። በተከታይነት ደግሞ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን በ125 በመቶ የሸቀጦች የዋጋ ሁለተኛ ናት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት ሀገራዊም አለም አቀፋዊም ነው ይላሉ ባለሙያዎች። በዋነኝነትም የግብርናው በሚፈለገው ደረጃ አለመዘመን፤ ለሁለት አመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነትና ይህንኑ ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ብድርና ዕርዳታ ማሽቆልቆል፤በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታና አለመረጋጋት ችግሮች፤ኮቪድና ይዟቸው የመጣው ቀውሶችና በአለም አቀፍ ደረጃ የዩክሬንና የራሺያ ጦርነት የፈጸረው ተጽዕኖ ተጠቃሾች ናቸው።
የኢትዮጵያ የኑሮ ወድነቱ ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት በየጊዜው ማሻቀቡና ተባብሶ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎችና በማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የኑሮ ጫና ያመላክታል። የዋጋ ግሽበቱ የእድገት መጠኑ ይለያይ እንጂ ከምግብ እስከ ቁሳቁስ፣ ከአልባሳት እስከ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ሆኖ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮው እየፈተነ ነው። በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት አሁን ላይ ዝቅተኛ ገቢ ካለው የማኅበረሰብ ክፍል አልፎ መካከለኛ ገቢ እስካለው የማኅበረሰብ ክፍል ድረስ የዜጎችን ኑሮ እየፈተነ ይገኛል።
የየካቲት ወር 2015 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 32.0 ከመቶ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል። ኤጀንሲው ይፋ እንዳደረገውም የየካቲት ወር 2015 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር 32.0 ከመቶ ሆኗል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ካለፈው ዓመት የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር 29.6 ከመቶ ሲሆን በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ካለፈው ዓመት የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀርም የ35.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በአንዳንድ እህሎች (ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ) ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ የታየ ሲሆን ምግብ-ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ልብስና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫትና የአሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ጭማሪ ተይቷል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና በሀሮማያ ዩኒቪርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ሞለ አለማየሁ እንደሚናገሩት፣ የዋጋ ግሽበት ማለት የዜጎች ገቢ አቅም እና የዕቃዎች ዋጋ አለመጣጣም ነው። አጠቃላይ ዋጋ የአንድ ወይም የሁለት ዕቃ ዋጋ ሳይሆን የአጠቃለይ ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የሚሄድበት ሁኔታ ማለት ነው።
በሌላ በኩል የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ማለት ነው። ባለሙያው ለአብነት እንደጠቀሱትም በፊት በአንድ መቶ ብር የሚገዛን ቁስ አሁን በሁለት መቶ ወይም በሶስት መቶ ሲገዛ እና የዕቃዎች አማካይ ዋጋ በአጠቃላይ ከሚገባው በላይ በፍጥነት ሲጨምር የዋጋ ግሽበት ተከሰተ እንላለን ይላሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት የሚያደርጉ ሶስት ነገሮች ናቸው የሚሉት ዶክተር ሞላ፤አንዱ የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም ነው። ፍለጎት ሲጨምር አቅርቦቱ ሲያንስ ነው፤ሌለው ደግሞ አቅራቢዎች አላስፈላጊ ትርፍ ለማጋበስ ብለው የትርፉን ደረጃ ሲጨምሩ ነው። ሶስተኛው በተለይ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ በስፈት የሚታያው የምርት አቅርቦት እጥረት መዋቅሩ ውጤታማ አለመሆን የሚያስከትለው ችግር ነው።
በአብዘኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተየው በሁለቱ ነው። የአቅርቦት እጥረት እና የአምረቾች የትርፍ ህዳግ ከመጠን በላይ መጨመር ለግሽበቱ ዋናው መንስኤ ነው። ከአቀርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ጋር በተያያዘ እንደምሳሌ የሚጠቀሰው ከግብርና ምርቶች ጋር የተያያዘው ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ሞላ፤ የግብርና ምርቶች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ይጠቁማሉ።ሆኖም እያደገ የመጣውን የግብርና ምርቶች ፍላጎት ለመስተናገድ የሚችል አቅርቦት አለመፈጠሩ የምርቶች ዋጋ እንዲንር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ያስረዳሉ።
የኑሮ ወድነት ተከሰተ የሚባለው የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም ወይም ገቢ ማነስ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው ጫና ነው። በኢትዮጵያ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እያሻቀበ ቢሆንም፣ የአብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ግን ከዋጋ ግሽበቱ እኩል ማደግ አለመቻሉን የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስት የምጠኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶዘካርያስ ሚኖታ ናቸው፤
እንደ እሳቸው ማብራሪያ የሰዎች ገቢ ባልጨመረበት የዋጋ ግሽበቱ እየናረ ሄደ ማለት ሰው መግዛት አይችልም ወይ ደግሞ የቆጠበውን እያወጣ ጥሪቱን እያሟጠጠ ይጠቀማል አልያም ብድር ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ባስ ሲልም ገዝቶ መጠቀም አይችልም ዜጎች በዋጋ ግሽበት ምክንያት በሀገራቸው ላይ ያላቸው ተስፋ እንዲሟጠጥ ያደርጋል ይላሉ ምሁሩ።
በተጨማሪም የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር ካልተቻለ የውጭ ኢንቨስትመንት ይቀንሳል ፤ይህ መሆኑ ደግሞ የስራ ዕድል የሚፈጠርባቸው ዘርፎች እንዲጠቡና ዜጎችም የስራ ዕድል ተተቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ይፈጥራል።
አቶ ዘካርያስ የእኛ ሀገር ዋጋ ግሽበት መሰረታዊ ችግር የአቅርቦት ችግር መሆኑን ያስረዳሉ። በቂ አቅርቦት የለም። ከምርታማነት አለመጨር ጋር ተያይዞ እጥረት አለ። ግብርናውም ሆነ ኢንዱስትሪው በቂ አቅርቦት የላቸውም። እንደሀገር እጥረት አለ። ይህ ደግሞ ጥቂት ምርቶችን ብዙሃኑ ሲፈልጋቸው የዋጋ መናር ይከሰታል::
ከ80 በመቶ በላይ አርሶ አደር በሆነበት ሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶች ማነስና ዋጋቸውም መሻቀብ የግብርናውን ምርታማነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ነው። ከዓለም እኛን ልዩ የሚያደርገን በምግብ ነክ በሆኑ ነገሮች ላይ ያለው የዋጋ ንረት ነው። ሌሎች ሀገሮች ላይ መሰረታዊ በሆኑ የምግብ ግብዓቶች ላይ ዋጋ አይጨምርም። እኛ ጋር ግን በዋናነት በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ የሚጨምረው፤ የዚህ ምክንያት በዋናነት እርሻው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ፤በጥቃቅን ማሳ ላይ የሚታረስ መሆኑ ችግር ፈጥሯል። ስለዚህም አሁን የተጀመረው የኩታ ገጠም እርሻ አስተራረስ ዘዴ ማጠናከርና ሰፋፊ እርሻዎችን ማስፋፋት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚረዳ በመፍትሄነት ይጠጠቁማሉ።
እንደግብርናው ሁሉ ኢንዱስትሪውም የአቀርቦት ችግር የሚታይበትና ለዋጋ ግሽበቱም የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኑን አቶ ዘካርያስ ያስረዳሉ። ኢንዱስትሪው በተለያዩ የግብዓት እና የቴክኖሎጂ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣የደህንነት ችግሮች ተተብትቦ ዘርፉ በጣም የተዳከማበት ጊዜ ነው። ጦርነቱ እና ኮቪድም የራሳቸውን ጥቁር አሻራ አሳርፈውበታል።በዚህም ኢንቨስትመንት ተዳክሟል ሆቴልና ቱሪዝም የመሳሰሉት የአገልግሎት ዘርፎች የእነዚሁ ችግሮች ፈት ቀማሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡:
ሰው ሰራሽ ምክንያቶችም ለዋጋ ግሽበት መንስኤ እንደሚሆኑ ምሁሩ ያብራራሉ። ለምሳሌ በሀገራችን የጤፍ ምርት በሚመረትባቸው ጥቅምት፣ህዳር፣ታህሳስ ወራት አካባቢ የጤፍ ዋጋ መውረድ ሲገባው በሰው ሰራሽ ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ይህን እንግዲህ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሊያስተካክለው የሚገባ ነው።
አቶ ዘካርያስ አክለውም የምርቶች የወደብ ላይ ቆይታ በተቻለ መጠን ያጠረ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ አስምረውበታል። ምርቶች ወደብ ላይ በቆዩ ቁጥር ለኪራይ ወጪ ሰለሚዳረጉ ያንን ለማካካስ ዋጋ ጭማሪ ይመጣል።ስለሆነም በተቻለ መጠን ቀልጣፋ የሎጅስቲክ አሰራር በመዘርጋት ምርቶች ቶሎቶሎ ከወደብ የሚነሱበትን ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ መክረዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የዋጋ ግሽበትን መከላከያው አንዱ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል። ምርቶች በሀገር ውስጥ ሲመረቱ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረታቸው በላይ ለመጓጓዣ የሚሆነውን መዋዕለ ንዋይ ማዳን ስለሚቻል በተመጣጣን ዋጋ ሀገር ውስጥ እንዲሸጡ በር ይከፍታል።
ኢንዱስትሪና በግብርና ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ማበረታታትና ድጋፍ ማድረግ በቂ ምርት እንዲመረትና ወደ ገበያ እንዲወጣ በር ስለሚከፍት ዋጋ ግሽበቱን ለማርገብ መፍትሄ እንደሚሆን ባለሙያው ይጠቁማሉ።
በሌላም በኩል የግብር ሁኔታ በጣም መሰረታዊ ስለሆነ መንግስት አንዳንድ የግብር ፖሊሲ ጉዳዮችን እንደገና መለየት እንዳለበት የጠቆሙት ፤ኢኮኖሚያችን አምራች ሳይሆን ሸማች ኢኮኖሚ ስለሆነ ከፍተኛ ግብር የተጣለባቸውን ሸቀጦች በማጥናት ቅናሽ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል። የኢኮኖሚ ፖሊሲው መሰረታዊ በሆኑ እቃዎች ላይ ከመጨመር ይልቅ መቀነሱ መንግስትንም ህዝብንም ተጠቃሚ ያደርገዋል ይላሉ። በመንግስት የተጀመረው የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ለሌለ ህገ ወጥነት የኑሮ ውድነት የራሱን ድርሻ እያበረከተ በር እየከፈተ ስለሆነ ድጋሚ መታየት አለበት ብለዋል።
ዶክተር ሞላ በበኩላቸው፤ መፍትሔ ነው የሚሉትን ሲያብራሩ፤ መጀመሪያ ምክንያቱ ምንድነው ተብሎ በደንብ መጠናት አለበት ይላሉ። ወደ መፍትሔው መኬድ ያለበትም በሽታው በአግባቡ ከተጠና በኋላ መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው። ‹‹በሽታውን ያልተናገረ ከመድሀኒት ጋር አይገናኝም እንደሚባለው›› መንግስት እንዲሁ ዝም ብሎ እሳት ማጥፋት አይነት መፍትሔ ሳይሆን በጥናት ተመርኩዞ መንስኤው ምንድነው የሚለውን በመለየት ስትራቴጂክ እቅድ ቀርጾ በአጭር ጊዜ በረጅም ጊዜ ምን ማድረግ አለብን የሚለው በደንብ ተጠንቶ ነው ውሳኔ መሰጠት ያለበት ይላሉ።
ዶክተር ሞላ የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል ህዝቡም የራሱ ድርሻ አለው ይላሉ። ህዝቡ አልገዛም ማለት መቻል አለበት። ለምሳሌ ስድስት መቶ የነበረን ነገር አንድ ሺህ ብር ሲበል አይሆንም ማለት አለበት:: ከልክ በላይ ዋጋ በሚጨምር ምርት ላይ አልገዛም የማለት ባህል ማዳበር አለበት።
የሀገሪቱ የንግድ ህግ የሚለው አንድ ሰው አስር ከመቶ ነው በአማካይ ማትረፍ ያለበት። መሬት ላይ የሚስተዋለው ግን ከ400 እስከ 500 ከፍ ሲልም 1000 በመቶ ትርፍ ነው። ስለዚህም መንግሥት ሕጉን ማስከበር አለበት። ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል። ሻጩም ስግብግብነቱን ተወት ማድረግ አለበት። ምንም እሴት ሳይጨምርበት ድንች ከአርሶ አደሩ በአስር ብር ገዝቶ 50 እና 60 ብር የሚሸጥበት ምክንያት የለም፡: እንደ ሀገር እንደ ዜጋ ምክንያታዊ መሆን መቻል አለበት፤ በደሀው ላይ እየበረታ ያለው የኑሮ ጫና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ስለሚያናጋ ነጋዴው ስነምግባር ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
አቶ ዘካርያስ በበኩላቸው፤ ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ መንግስት የሀገሪቱን ሰላም እና መረጋጋት ማስጠበቅ አለበት። በመላው ሀገሪቱ የምርቶች ሆነ የሰው ሰላማዊ ዝውውር ሊኖር ይገባል፤ሌላው አቅርቦት እንዲጨምር ግብርናን ዘመናዊ ማድረግ የግድ ነው። የግብርና ምርትን በዓይነት እና በጥራት የማቅረብ ስራ በሰፊው መሰራት አለበት።
የግብርና፣ የእንዱስትሪ፣ የአገልግሎት እና ሌሎች ዘርፎች ፖሊሲዎች፤ ስትራቴጂዎች እና ዕቅዶች የአየር ለውጥን ተጽእኖ ታሳቢ እንዲያደርጉ ሆነው መዘጋጀት አለባቸው። ለዚሁ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ በሚሰጥ መልኩ መቀረጽ እና መተግበር ይኖርበታል። ማንኛውም ጥሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ አዎንታዊ ፋይዳ የሚኖረው አግባብነት እና ተጠያቂነት ያለው ተቋም፤ አደረጃጀት፤ ሀብት (በጀት)፤ የሰው ኃይል፤ መሠረተልማት፤ ብቁ አመራር ሲኖረው ብቻ ነው። በመሆኑም የዋጋ ግሽበት እንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ለብሄራዊ ባንክ በመሆኑ በብቃት ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችል ገለልተኛ መሆን አለበት። ተጠሪነቱ ለአስፈጻሚው ከሚሆን ለህግ አውጭው ሆኖ እንዲሰራ ማድረግ አግባብ እንደሆነ ገልፀዋል። አለአግባብ ወደ ገበያው እየገባ ያለው የገንዘብ ስርጭት ገደብ ሊበጅልት እንደሚገበ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ባንኮች በውጭ ምንዛሪ በአንድ ዶላር ላይ እስከ ሰባ ብር ጨምረው እስከ 130 ብር እየሰጡ እየተቀበሉ ነው። እሄ አይን ያወጣ ወንጀል ነው። ለዋጋ ግሽበቱ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ይሄንን ለመቆጣጠር በህግ ኃላፊነት የተጣለበት ብሄራዊ ባንክ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም። ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዲችል የአስተዳደራዊ እና የፖሊሲ ነጻነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምሁራኑ እንደተናገሩት፤በዋናነት ግሽበቱን በዘላቂነት ለመቆጣጠር አቅርቦት መጨመር በቅድሚያ መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህም ግብርናን ማዘመን እና የግብይት ስርዓቱን ህገ ወጦች የሚፈነጩበት እንዳይሆን ማድረግ ለነገ የማይባል የመንግስት ኃላፊነት እንደሆነ ገልፀዋል።
በዚሁ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡት የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመግታት ሰፋፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትር ደኤታው እንዳሉት፤ በአንድ በኩል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ምንም እንኳ ክፍተቶች ቢኖሩትም አሁን ያለው ምርት በፍትሐዊነት ለሸማቹ ሕብረተሰብ እንዲደርስ በማድረግ ጊዜያዊ መፍትሄ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በዘላቂነት ግን ሀገር በቀል ኢኮኖሚውን በተጠናከረ መልኩ በመተግበር እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት የመግታት ስራ ይሰራል ብለዋል።
ኑሮ ውድነቱ አሁን በድንገት የተከሰተ ጉዳይ ሳይሆን የአለም አቀፋዊና የአገራዊ ምክንያቶች ውጤት መሆኑ መታወቅ አለበት ያሉት ዶክተር ነመራ፤ በአገር የሰሜን ጦርነት፣በአለም የሩሲያና ዩክሬን እንዲሁም የኮረና ወረርሽኝ አሁን በተፈጠረዉው የኑሮ ውድነት ትልቁ ግብዓት እንደሆኑ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአለም ገበያ ተጽእኖ ውጭ ባይሆንም በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ጥረት ከማድረግ በተጓዳኝ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ስለተሰጠ፣ ችግሩ በዘላቂነት እንደማይቀጥልም ጠቁመዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2015