አገራችን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደረገው ጥረት እንዲሳካ የማድረጉ ሥራ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ማስፋትን ይጠይቃል፡፡ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት ቀላል የሚያደርጉ ቀልጣፋ፣ ጊዜንና ወጪን የሚቆጠቡ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የማድረጉም ሥራ የሚፈልግውም ይህንኑ ነው፡፡
የአገሪቱ ተቋማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ሕይወት ቀላል ለማድረግ የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ፈጣንና ቀልጣፋ እያደረጉ፣ እንግልትን እያስቀሩ እንዲሁም ወጪንም በመቀነስ፣ የክፍያ ሂደቱንም እያሳለጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች የሚያበለጽጉ አካላትም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ የእነዚህ በግለሰቦችም ሆነ በተቋማት ደረጃ እንዲበለጽጉ የሚደረጉ መተግበሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡
አለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበት በዚህ በረቀቀ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ ይህን የሚመጥኑ አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ወደ ሥራ በማስገባት አገልግሎትን የተቀላጠፈ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ፈጣን ማድረግ ይገባል፡፡ መተግበሪያዎቹ በቴክኖሎጂ ታግዘው የሚሰሩ እንደመሆናቸው ሰዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በፍጥነት አገልግሎቶችን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላሉ፡፡
ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች ባለችው ኢትዮጵያም እነዚህን አይነት መተግበሪያዎች በማበልጸግ ወደ ሥራ በማስገባት በኩል ብዙ ለውጦች እየታዩ ናቸው። የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ መተግበሪያ ወደ መስጠት እየተገባም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት አቅዳ እየሰራች ላለች አገር ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም ሥራ ላይ ያዋለው መተግበሪያም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› የተሰኘና ‹‹እልፍ ጉዳይ በአንድ መተግበሪያ›› መፈፀም እንደሚያስችል የተነገረለት መተግበሪያ ሥራ ላይ አውሏል፡፡ ይህ መተግበሪያ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ የያዘ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት መተግበሪያው ይፋ በተደረገበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
ወይዘሪት ፍሬሕይወት እንደሚሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ የአገራችንን እድገት ለማሳለጥ የመሪውን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ይህ ኢትዮ ቴሌኮም ያበለጸገው አዲሱ ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› (telebirr Super App) የተሰኘ መተግበሪያም እንደ አገር ለሚገነባው ዲጂታል ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
ዲጂታል አካታችነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ሰፊውን ማኅበረሰብ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለውን ማኅብረሰብ ማገልግል ሲቻል ነው ያሉት ወይዘሪት ፍሬሕይወት፤ ብዙዎችን ያላካተተ እድል ቀጣይነት ሊኖረው አይችልምና ቀጣይነት ያለው እድገት ለመፍጠር ቴክኖሎጂን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ቴክኖሎጂ ስንል ደግሞ በአገራችን 99 በመቶ የሕዝብ ተደራሽነት ያለውን የሞባይል ቴክኖሎጂ የሚመለከት ነው፡፡ የሞባይል ቴክኖሎጂዎች አጭር መልዕክትን ከመላላክ፣ የድምፅ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ነው የሚገልጹት፡፡
ሀሳብ የሚያመነጩ፣ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ባለሙያዎች ሀሳባቸው ወደ ገበያ የሚመጣበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ስናደርግ የምናፋጥነው የዲጅታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ነው ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የሚመጣ በመሆኑ ያለንን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል ቴክኖሎጂ መጠቀም አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው ብለዋል።
‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› (telebirr Super App) የተሰኘው መተግበሪያ በዕለት ተዕለት ኑሯቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞችንና አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ ታግዘው ለደንበኞች ለማድረስ የሚሰሩ ቢዝነሶችን ለማገዝና ለማሳለጥ ታስቦ የበለጸገ መተግበሪያ ነው፡፡
በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን እንኳ ብናይ በጣም ጥቂት መተግበሪያዎች ብቻ ነበሩ የሚታወቁት፡ አሁን በኢትዮጵያ ብቻ ከ100 በላይ መተግበሪያዎች አሉ፡ ተጠቃሚዎችም ከእነዚህ ውስጥ የሚፈልጉትን አይነት መተግበሪያ እያወረዱ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡
ዲጂታል ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ወደፊት በርካታ መተግበሪያዎች እየበለጸጉ የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚሉት ወይዘሪት ፍሬሕይወት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ሥራ ያስገባው ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› የተሰኘ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በአንድ ላይ ሰብሰብ አድርጎ የሚይዝ ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ቀላልና ምቹ የሚሰጠውም አገልግሎት ፈጣንና አስተማማኝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ይህ መተግበሪያ ከዚህ ቀደም ገንዘብ ለመላክ ለመቀበል ክፍያ ለመፈጸም ስንጠቀምባቸው የነበሩ እንዲሁም ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን የሚያስፈልጉ ሁሉንም መተግበሪያዎች ወደ አንድ መተግበሪያ አምጥቶ የያዘ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከአንድ በላይ የሆነ መተግበሪያ ለመጠቀም የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን መተግበሪያ ከተጠቀሙ በኋላ ያንን አጥፍተው ነው ሌላ መተግበሪያ መጠቀም ይችሉ የነበረው። ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› ሲጠቀሙ ግን የመጀመሪያውን ማጥፋት ሳያስፈልጋቸው የሚፈልጓቸውን መተግበሪያዎች መጠቀም ይችላሉ፡፡
እያንዳንዱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መሠረታዊ ከሚባሉ የቴሌኮም አገልግሎቶች ለመግዛት፣ የመብራት ቢል ለመክፈል፣ ትራንስፖርት ለማግኘት፣ ትኬቶችን ለመግዛትና የመሳሳሉትን ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት ለመፈጸም ሲፈልግ የትም መሄድ ሳያስፈልግ ‹‹የቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› በመጠቀም የሚፈልገውን መተግበሪያ በመጠቀም ክፍያውን በቴሌብር መክፈል ይቻላል፡፡ በዚህ መተግበሪያ ተጠቃሚው ያሻውን በመከወን ጊዜ ይቆጥባል፤ አላስፈላጊ ወጪንም ያስቀራል፡፡
ተጠቃሚው በርካታ ዌብ ሳይቶችን ማስታወስ ሳይጠበቅበት ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› ላይ በመግባት መገልገል ይቻላል ፤መተግበሪያው ከ20 በላይ መተግበሪያዎችን በአንድ ላይ የያዘ ነው የሚሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣ እነዚህን መተግበሪያዎች ለመጠቀም የትም መውጣትና መውረድ ሳይስፈልግ ‹‹ቴሌብርሱፐር አፕ›› ላይ በመግባት እያንዳንዱን መተግበሪያ መጠቀም ይችላል ብለዋል፡፡
ለአብነት ብንመለከት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች በየወሩ አገልግሎት ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ ሳይከፈሉ ሲቀር የሚሰጣቸው አገልግሎት ይቋረጣል፡፡ ይህ ደግሞ በተቋሙና በደንበኞች መካከል ያለውን ግንኙነት ያሻክራል፡፡ ስለዚህ ደንበኞችን ማርካት እንዲያስችል በቴክኖሎጂ በመታገዝ ‹እስኬጁል ፔይመንት› መጠቀም ይቻላል፡፡ ‹እስኬጁል ፔይመንት› በየሳምንቱ፣ በየወሩ እንዲሁም በየዕለቱ ለሚከፈሉ የተለያዩ ክፍያዎች ደንበኛው ማስታወስ ሳይጠበቅበት አንድ ጊዜ ከተሞላ በየወሩ ከተሞላለት ሂሳብ ላይ እየቆረጠ ወደሚመለከተው አካል ይልካል፡፡
መተግበሪያው ለቢዝነስ ተቋማት የሚሰጠውን ፋይዳ ሲያስረዱ የቢዝነስ ተቋማትን ከማበረታታትና በርካታ የሥራእድል ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በተለይ ከደንበኞቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የተሻለ በማድረግም ረገድ ሰፊ እድልን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያየ የስራ መስክ ላይ ለተሰማሩ 30 ሚሊዮን ለሚሆኑት የቴሌብር ተጠቃሚዎች በአንድ ጊዜ ለመድረስ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ለመንግሥት ተቋማት ቅልጥፍናን ይጨምራል፤ወጪን ይቆጥባል፤ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያደርጋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፣ ሁለትና ሦስት መተግበሪያዎች ያላቸው ተቋማት ደንበኞቻቸው ሁለት ወይም ሦስት ቦታ መሄድ ሳይጠበቅባቸው በአንድ መተግበሪያ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የላቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የደንበኞች አገልግሎት የላቀ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ወይዘሪት ፍሬሕይወት፤ ተደራሽነትን በማስፋት፣ ጥራትን በማሻሻል ደንበኞችን ለማርካት እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማቅለል ተቋሙ ለቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁንም ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
‹‹ቴሌብር ሱፐር አፕ›› መተግበሪያ ሁለት ምዕራፍ እንዳለው የጠቆሙት ወይዘሪት ፍሬሕይወት፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ መምጣቱን አመልክተዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የሚካተቱት እነዚህን የቢዝነስ ተቋማት በቀላሉ ከደንበኞቻቸው ጋር ለማገናኘት እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ደንበኞች ጥያቄ ሲኖራቸው እዚያ ላይ ሆነው ለተቋማቱ የሚያደርሱበት እና ተቋማትም ምርትና አገልግሎታቸውን ለእነርሱ ማስታወቅ ሲፈልጉ ባሉበት ሆነው የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል፡፡ ለተቋማቱም ትልቅ አቅም፣ ለደንበኞችም ይፈጥራል፡፡ እነዚህንና መሰል አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ይመጣል በማለት ያስረዳሉ፡፡
የግሎባል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ አበበ በቀለ በበኩላቸው አሁን ያለንበት ዘመን የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘመን ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ የቴክኖሎጂውንና የዲጂታሉን ዘርፍ አጠቃሎ የሚይዝ ስለሆነ ውስን ከሆነው የኢንተርኔት ኢኮኖሚ ዘመን ተመራጭ ነው ይላሉ፡፡
መተግበሪያዎች በጣም ብዙ ጠቀሜታ ስላላቸው ለዲጂታል ኢኮኖሚው በጣም ወሳኝ ናቸው የሚሉት አቶ አበበ፤ ለአብነት ኢትዮ ቴሌኮም ያበለጸገው መተግበሪያ ልክ ባንኮች ባንድ መስኮት የተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ሁሉ ይህ መተግበሪያም እንደዚያው አይነት አገልግሎት ይሰጣል ይላሉ፡፡ ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› እንደ ኢ-ኮሜርስ፣ የምግብ ትዕዛዝ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኢንተርቴመንት፣ የተለያዩ ክፍያዎች እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በአንድ መተግበሪያ ተጠቅመን ሁሉንም በአንድ ላይ ማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በዋናነት የሚጠቀመበትን ‹‹ቴሌብር›› የተሰኘውን መተግበሪያውን ወደ ‹‹ቴሌ ብር ሱፐር አፕ›› እንዲያሳደግ አድርጎታል፡፡ ይህም አንድ የነበረውን መተግበሪያ በማሻሻል ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ እንዲያዝ የሚያደርግ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
አንድ ሰው የራይድ አገልግሎት የሚሰጡ ትራንስፖርቶችን ለማግኘት፣ የመብራት አገልግሎት ክፍያ ለመክፈል፣ የአየር መንገድ ቲኬት ለመቁረጥ ቢፈልግ እያንዳንዱን አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ መተግበሪያዎችን መጠቀም አለበት የሚሉት አቶ አበበ፤ ሁሉንም በአንድ አጠቃሎ የሚይዝ መተግበሪያ ቢኖር ጊዜና አላስፈላጊ ወጪን በመቆጠብ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ መተግበሪያ ማግኘት ይቻላል ይላሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ወይም ሦስት መተግበሪያዎች ከመጫን ይልቅ በአንድ መተግበሪያ ሁሉንም አገልግሎት ማግኘት የሚቻል ከሆነ እጅግ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡
በሌላ በኩል የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ አስር መተግበሪያዎችን ሚስጥራዊ ለማድረግ ብዙ ነገሮች እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ አስሩንም አገልግሎቶች በአንድ ላይ አድርጎ የያዘ አንድ መተግበሪያ ሚስጥራዊነቱን ለማድረግ በጣም ቀላል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
መተግበሪያዎች ብዙ ጠቀሜታ አላቸው የሚሉት አቶ አበበ፤ መተግበሪያን ተጠቅሞ ኢንተርኔትን ከሁሉም ጋር በማገናኘት ከፍሪጅ ( ከማቀዘቀዣ)፣ ከቴሌቪዝን፣ ከዘመናዊ ስልኮች (ከስማርት ፎን) እና ከመሳሳሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር በማገናኘት ሁሉንም ነገሮች በቀላሉ ለማወቅ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ይህም አንድ ሰው ሞባይሉን ተጠቅሞ መተግበሪያውን በመጫን የትም ቦታ ሆኖ የሚፈልገውን ሁሉ ማድረግ እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡
ለአብነት ብንመለከት አንድ ሰው እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን አንድ አዛውንት የቤተሰቡን አባል በመተግበሪያ አማካይነት እቤት ባሉበት ሆነው የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ በማድረግ መከታተል ይቻላል፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ጊዜ በማቀዝቀዣ ውስጥ ያለው ዳቦ(ወተት) አልቆ ሊሆን ይችላል፡፡ መተግበሪያውን በመጠቀም ማለቁን ማወቅም ሆነ ሌላ ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘትና ማወቅ የሚችልበት ቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ነን ያለነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር መተግበሪያን በመጠቀም አንድ የትራፊክ መብራት ጥሶ የሚሄድን ተሽከርካሪን ቦታው ላይ መሄድ ሳይጠበቅ፣ ባለንበት ሆነን መከታተልና መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡
በመተግበሪያዎች አማካይነት ሞባይል ባንኪንግ ስንጠቀም እቤት ሆነን ብር መላላክ ፣ክፍያ መክፍል እና የመሳሰሉት ማድረግ ይቻላል፡፡ መተግበሪያዎችን በመጠቀም እዚህ ሆኖ አሜሪካ ህክምና ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ሲሆን ቴክኖሎጂ ስንጠቀም አንደኛ ጊዜ ይቆጥባል፤ ሁለተኛ ደግሞ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚወጡት ወጪዎች ይቀንሳል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
መተግበሪያዎች ሁለት አይነት ናቸው፡፡ አንደኛው በክፍያ የሚገኝ ሲሆን ፤ሁለተኛው ደግሞ በነጻ የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ እንደኛ ባሉ ሀገራት ዲጅታል ቴክኖሎጂን ከማስፋት አንጻር መተግበሪያዎች ያላቸው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ይህንንም የኢንተርኔት ተደራሽነቱ እየሰፋ በመጣ ቁጥር ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
መተግበሪያዎችን ስናሰብ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ሁሉ ጎን ለጎን መታሰብ ያለበት የመጀመሪያ ጉዳይ የሴኩሪቲ (የደህንነቱ) ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ አበበ፤ መተግበሪያዎች አስተማማኝ፣ በቀላሉ ተደራሽ የሆኑና የተጣመረ አገልግሎት የያዙ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ መተግበሪያዎች ሁልጊዜ በቀላሉ የሚገኙ መሆን አለባቸው፡፡ ካልሆኑ ግን ተጠቃሚው መተግበሪያውን በቀላሉ የማያገኘውና ብዙ ጊዜ የሚወስድበት ከሆነ ደግሞ አይጠቀመውም ብለዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ መተግበሪያዎች ዲጅታል ኢኮኖሚን ለማፋጠን እንደሚጠቀሙ ሲታሰብ የመጀመሪያው ሁልጊዜ ከሴኩሪቲ (የደህንነቱ ጉዳይ) ጋር አብሮ ማያያዝ ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ መንግሥትም፣ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች እነዚህን ሥራዎች በማበረታታት ላይ ሰፊ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኢንተርኔት በተፈለገ መጠን ተደራሽ እንዲሆን መሥራት አለበት የሚሉት አቶ አበበ፤ ከሁሉም ደግሞ መተግበሪያዎቹን የሚያበለጸጉት አካላትም ሆኑ ተጠቃሚዎች እኩል ግንዛቤው ኖሯቸው ለዲጅታል ኢኮኖሚው ቅድሚያ በመስጠት መሥራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡ መተግበሪያዎችን ዕለት በዕለት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው፣ ሁሉንም በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን የሚያካትት መድረክ በመፍጠር የዲጅታል አኮኖሚን ለመገንባት እየተከናወነ ያለው ተግባር ስኬታ እንዲሆን መሥራት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2015