ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የመጡ ስምንት የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች አንድ ወቅት ላይ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ ተገናኝተው እንዲመክሩ ተደረገ። እንዲህ በአንድ ላይ መሰብሰባቸው ትልቅ አላማን ያነገበም ነበር። አሰልጣኞቹ የተገናኙበትን አላማ ከግብ ለማድረስ መክረውና ዘክረው፤ አውጥተውና አውርደው በአንድ ሃሳብ ይስማማሉ። ይህም ከየመጡበት አካባቢ አሉ ያሏቸውን የአርሶ አደሩን ችግሮች ነቀሰው በማውጣት ዋንኛ በሚሉት ላይ ትኩረት አድርገው በመምከር መፍትሔ ማስቀመጥ ነው።
ችግር ናቸው ብለው ካሰቧቸው መካከል ዋንኛው አርሶ አደሩ በእጅጉ የደከመበት የእህል አዝመራ በምርት መሰብሰብ ሂደት የሚያጋጥመው የምርት ብክነት አንዱ ሆነ። አሰልጣኞቹ ለእዚህም መፍትሔ ይሆናል ያሉት የእህል መውቂያ ማሽን መሥራት ሆኖ አገኙት፤ ይህን ሃሳባቸውን መሬት ለማውረድም እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን አንድ ላይ ማድረጉን ተያያዙት፤ እንዳሰቡትም ምርትን ከብክለት የሚታደግ የእህል መውቂያ ማሽን መሥራት ቻሉ።
አሰልጣኝ ቃልኪዳን ሶዴ እና ሰባቱ የሙያ አጋሮቿ ናቸው ለእዚህ አላማ እንዲሰባሰቡ የተደረጉት። እነዚህ አሰልጣኞች በዚህ ታላቅ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ እነሱን በማሰባሰብ ምቹ ሁኔታ የፈጠረው ደግሞ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው። አሰልጣኞቹ ለእዚህ አላማ እንዲሰባሰቡ ከመደረጋቸው በፊት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሆነው የየራሳቸውን የፈጠራ ሥራ የሰሩ ናቸው። የፈጠራ ሥራቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው ብሩህ ተስፋ ውድድር ላይ ያቀረቡም ናቸው።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እነዚህ በተለያዩ ቦታዎች የተጀመሩት የፈጠራ ሥራዎች በጋራ ቢሰሩ ድምር ውጤታቸው የተሻለ መሥራት ያስችላል በሚል ስለታመነበት አሰልጣኞቹ በክረምት መርሃ ግብር በአንድነት መሰብሰባቸውን አሰልጣኝ ቃልኪዳን ትናገራለች። አሰልጣኞቹ የአርሶ አደሩን ችግር በቅርበት እንደሚያወቁ ታምኖበትም፣ ዋንኛ ችግር ነው ብለው ያሰቡትን የእህል መውቂያ ማሽን እንዲሰሩ መደረጉን ትገልጻለች።
አርሶ አደሩ እስካሁን እየተቸገረበት ያለው ጉዳይ ዋንኛው ምክንያት ጉልበቱን ሳይቆጥብ ለፍቶና ደክሞ፣ በበሬ አርሶ ያለማውን ሰብል ለመውቃት የሚጠቀመው ኋላቀር መንገድ መሆኑ ነው። ይህም ምርቱን በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ሲያደርገው ኖሯል፤ ለብክነት የሚዳረግበትን ሁኔታም ይፈጥራል። ችግሩ ቢፈታ ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንዲሁም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። እነሱም ለእዚህ ችግር የመፍትሔ ሃሳብ በማፍለቅ የእህል መውቂያ ማሽን መሥራታቸውን አሰልጣኟ አስታውቃለች።
ቃልኪዳን እንዳለችው፤ የእህል መውቂያ ማሽን ሃሳቡ ከመምጣቱ በፊት አሰልጣኞቹ በየግላቸው የበቆሎ፣ የጤፍና የሌሎች እህሎች መውቂያ ማሽኖችን ሰርተዋል። በእዚህ መነሻነትም ነው ሁሉንም የእህል ዓይነቶች መውቃት የሚችል ማሽን ለምን አንሰራም በሚል መነሻ ሃሳብ ወደ ሥራ የገቡት።
‹‹ሁላችንም በየአካባቢያችን ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በማሰብ የበቆሎ መፈልፈያ፣ የጤፍ መውቂያ እያለን የተለያዩ የእህል የመውቂያ ማሽኖችን ሰርተናል። እኔ በበኩሌ ሁሉንም የእህል ዓይነቶች የሚወቃ ማሽን ሰርቼ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የፈጠራ ሥራ አንድ ላይ ቢመጣ እንደ ሀገር ጥሩ ሥራ በመሥራት አንድ ማሽን ማውጣት እንደሚቻል ስለታመነበት በአንድነት ማሽኑን መሥራት ተችሏል›› ስትል አብራርታለች።
አሰልጣኝ ቃልኪዳን እንደምትለው፤ አሁን ሁሉንም የእህል ዓይነቶች መውቃት የሚችል ማሽን ሰርቷል። ማሽኑ ጤፍ፣ ባቄላ፣ በቆሎ የመሳሰሉትን ማንኛውንም የእህል ዓይነቶች መውቃት ይችላል። ማሽኑ ብረት በማቅለጥ፣ በመበየድና የመሳሰሉትን በመሥራት ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ጥራታቸውን ከጠበቁ ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ብረታ ብረቶች የተሰራ ሲሆን፣ እንደ ቺንጋና ዲናሞ ያሉ እቃዎች ብቻ ከውጭ የመጡ ናቸው።
በተመሳሳይ የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን የሚወቃ ማሽን ከውጭ ሀገር ይመጣል፤ ይህ ማሽን በሀገር ውስጥ ከተመረተው ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት አለው። ከውጭ የሚገባው ማሽን እንደ በቆሎና ባቄላ ያሉ ጥራጥሬዎችን ለመውቃት ይቸግራል። ምክንያቱ በውስጡ ያለው መውቂያ ጤፍ፣ ስንዴ ፣ ሩዝ ፣ ገብስ እና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን ለመውቃት ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ ነው። በሀገር ውስጥ የተሰራው አዲሱ ማሽን ግን ሁሉንም የእህል ዓይነቶች ያለምንም ችግር መውቃት እንዲችል ተደርጎ የተሰራ ነው።
ማሽኑ የተለያዩ የእህል ዓይነቶች እንዲወቃ ካስፈለገ እንደየእህሉ ዓይነት ሊያገለግሉ የሚችሉ የተለያዩ መቀያየሪያዎች መሳሪያዎች ተዘጋጅተውለታል። መሳሪያዎቹ በቀላሉ እየተፈቱ ሊቀየሩ የሚችሉ ናቸው። መሳሪያዎቹን መቀየር የሚያስፈልገው የአገዳ እህል የሚባሉት በቆሎና ባቄላን ለመውቃት ሲፈለግ ብቻ ነው። ሌሎች 14 ዓይነቶች መሳሪያዎችን ግን ምንም ዓይነት መቀየር ሳያስፈልግ እንዳለ መጠቀም ይቻላል።
ማሽኑ እህሉን ወቅቶ፣ አነፍሶና አበጥሮ ምርቱን ወደ ተገጠመለት ታንከር እንዲገባ ያደርጋል፤ ምርቱ 50 ኪሎ ግራም ሲሞላ ንጽህ የሆነው ምርት ወደ ማዳበሪያ ይገለበጣል። ገለባውና ሌሎች ተረፈ ምርቶችን ደግሞ ለከብቶች መኖ በሚሆን መልኩ አዘጋጅቶና አስተካክሎ ያወጣል።
አሰልጣኝ ቃልኪዳን፤ ማሽኑ አሁን ላይ በሰዓት 18 ኩንታል እህል መውቃት ያስችላል ስትል ጠቁማ፣ ማሽኑን ከዚህ ባነሰ መጠን የሚፈልጉ አርሶ አደሮች ካሉ እንደየአርሶ አደሩ ፍላጎት በሰዓት እስከ 10 ኩንታል እህል እንዲወቃ አድርጎ መሥራት ይቻላል ብላለች።
እሷ እንዳለችው፤ ይህን ማሽን በ250 ሺ ብር ለመሸጥ ታሰቧል። ከውጭ የሚመጣው ግን በጣም ውድ እና በግማሽ ያህል ልዩነት ያለው ነው። ማሽኑ የሚጠቀመው የኃይል ዓይነትም እንደ ደንበኛው ፍላጎት የሚወሰን ይሆናል። የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በሆነበት አካባቢ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ባለሆነባቸው አካባቢዎች ደግሞ በነዳጅና በሶላር እንዲሰራ አድርጎ መሥራት ይችላል።
ማሽኑ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ አሁን ያለውን መልክ የያዘ ሳይሆን፣ በየጊዜው በተሰጡት አስተያየቶች መሰረት ክፍተቶችን በመሙላት ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ ነው ብላለች። የማሽኑ የጥራት ደረጃም በኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ኤጀንሲ የተረጋገጠ መሆኑን ገልጻለች።
በአሁኑ ወቅት ኬር ይሁን ፋርሚንግ ቴክኖሎጂ የተሰኘ ድርጅት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወርክሾፕ በመክፈት ማሽኑን ለማምረት በሂደት ላይ እንደሆነም ጠቁማለች። ለዚህም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመሥሪያ ቦታና እና የተለያዩ ማሽነሪዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጻለች።
ይህ ማሽን ባለፈው ዓመት በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው የፈጠራ ውድድር ላይ ቀርቦ ሁለተኛ ወጥቷል የምትለው ቃልኪዳን፤ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ ለማግኘት በሂደት እንደሚገኝም ታስረዳለች። ቀደም ሲል በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚደገፉ የፈጠራ ሥራዎች በአውደ ርዕይ ቀርበው በቀረቡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህን የፈጠራ ሥራ እንደጎበኙትና ማበረታቻም እንደሰጧቸው አስታውቃለች። በወቅቱም ማሽኑ ከተመረጡ የፈጠራ ሥራዎች አንዱ ሆኖ መጠቀሱን አስታውሳ፣ በመንግሥት በኩል ማሽኑን እንደሀገር ለሁሉም ክልሎች ለማዳረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መቆየቱንም ገልጻለች።
በዚህም ቅድሚያ የተሰጠው ለኦሮሚያ ክልል መሆኑን ጠቅሳ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አማካኝነት 100 ያህል ማሽኖች እንዲመረቱ ጥያቄ መቅረቡን ትጠቁማለች። ማሽኑን ለማምረት በቅድሚያ የንግድ ፈቃድ ማውጣት እንደሚያስፈልግና እሱም ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሳ፣ የንግድ ፈቃድ ጋር ተያይዞ ያለው ሂደት ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እስከዚያው ድረስ ከሌላ የቴክኖሎጂ ድርጅት ጋር በመሆን በፍጥነት ወደ ማምረት ሥራው ለመግባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብላለች።
እሷ እንዳለችው፤ ማሽኑ ከተመረተ በኋላ ክልሉ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚያደርገው ይሆናል። ሥራው የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የኦሮሚያ ክልል ማሽኑ እንዲሰራ ያዘዘ ቢሆንም፣ ሌሎች ክልሎችም እንዲሁ ማሽኑ እንዲመረትላቸው የሚፈልጉ ከሆነ ድርጅቱን በመጠየቅ እንደ ቅደመ ተከተላቸው የሚሰተናገዱ መሆኑን አስታውቃለች። ‹‹ማሽኑ ኤግዚቢሽን ላይ በቀረበበት ወቅት ያዩ እንዲሰራላቸው የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ከእኛ ጋር እየተነጋገሩ ነው ›› ትላለች።
እንደ አሰልጣኟ ማብራሪያ፤ ማሽኑን የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም እንዲተዋወቅ እየተደረገ ነው። የማምረቱ ሥራ በደንብ ሲጀመር የማስተዋወቁ ሥራም እንዲሁ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በዚህም አርሶ አደሩ ስለማሽኑ አውቆ እንዲገዛና እንዲጠቀምበት ይደረጋል።
በቀጣይም በህብረተሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮችን በደንብ በመመልከት ለእነዚህ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎች እንደሚሰሩም ጠቁማለች። በዚህም መሠረት በእቅድ የተያዙ ሥራዎች እንዳሉም ገልጻ፣ ከእነዚያም ውስጥ አንድ በበሬ ማረስ ሊያስቆም የሚችል በራሱ የሚያርስ፣ የሚያጨድ እና ምርቱን የሚሰበሰብ እንደ ሞተር ባይስክል ተንቀሳቃሽ የሆነ ማረሻ ለመሥራት መታቀዱንም ጠቁማለች።
የመውቂያ ማሽኑ ከውጭ ከሚገባው ማሽን ጥራት ያለው መሆኑን አመልከታ፣ ማሽኑን ወደፊት በሰፊው በማምረት ከውጭ የሚመጣውን በማስቀረት እና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ብቻ ሳይወሰን ማሽኑን ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ መታቀዱንም ተናግራለች።
ድርጅቱ ወደ ማምረት ሥራው ሲገባ ከመጀመሪያ ገና ለ15 ያህል ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል የምትለው ቃልኪዳን፤ ምርቱ እየጨመረና እየሰፋ ሲሄድ ትልቅ ድርጅት እንደሚሆንና ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ተናግራለች። በአምስት ዓመታት ውስጥ ከሁለት ሺ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችል ታስረዳለች።
እንደ አሰልጣኟ ማብራሪያ፤ ማሽኑን እውን ያደረጉት ስምንቱ አሰልጣኞች በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁ ሲሆን፣ ማሽኑን ለመሥራት ሁሉም ያለውን እውቀት አውጥቷል። ድርጅቱ ማሽኑን የሚበይድ፣ ዲዛይን የሚያወጣ፣ ኤሌክትሪክ ሲሰተሙን የሚሰራ፣ በሁሉም ሙያ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች የተካተቱበት ነው።
‹‹ይህ እድል መፈጠሩ በራሱ ትልቅ ሥራ እንድንሰራ አድርጎናል። ይህንን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት በአንድ መሰብሰባችን ውጤታማ የሆነ ሥራ እንድንሰራ አስችሎናል። ›› ያለችው አሰልጣኝ ቃል ኪዳን፣ ‹‹አንዱ ያለው እውቀት ሌላው ሊኖረው ስለማይችል ሁሉም ያለውን እውቀት እንዲህ አንድ ላይ አምጥቶ በጋራ መሥራቱ ማሽኑን ለመሥራት የሚያስችሉ ክህሎቶችን እንድናገኝ አድርጎናል። የእውቀት ሽግግር እንዲኖር፣ የሥራ መንፈሳችን እንዲታደስና ለቀጣይ ሥራ ተነሳሽነት እንዲኖረን አድርጓል›› ስትል አብራርታለች።
በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ብዙ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች እንዳሉም ጠቁማ፣ እነዚህ ሃሳቦች በአንድ ቢጣመሩ ሀገሪቱ ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሚቻል የማሽኑ እውን መሆን እንደሚያሳይ ትገልጻለች።
ከውጭ የሚመጣውን የሚተካ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም የበለጠ የተሻለ ሥራን መሥራት እንደሚቻልም ገልጻ፣ ‹ለዚህም እኛ በአንድነት ሆነን ይህንን ማሽን መሥራት መቻላችን ጥሩ ማሳያ ነው ብላለች። ‹‹እኛ ከውጭ የሚመጣውን የሚተካ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ማሽን ነው የሰራነው። ምክንያቱም እኛ የሰራነው ምርቱን ወቅቶ፣ አነፍሶ፣ አበጥሮ እህሉን ብቻ የሚሰጥ ማሽን ነው›› በማለትም ነው ያብራራችው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም