በጥናትና ምርምርም ሆነ በተምሮ ማስተማር፤በእለት ተእለት ሕይወትም ሆነ ከልደት እስከ ሞት “ቁልፍ ቃላት” ከሚባሉት መካከል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የሆኑት ሁለቱ፣ “ቅድመ–” እና “ድህረ–” ናቸው ፤ በሁለቱ መካከል ያለው ያው እሳቱ የነደደበት፤ ንፁሀን እንደ ቅጠል የረገፉበት፤ ንብረት ዶጋ’መድ የሆነበት፤ አገር የኋሊት የሸመጠጠችበት። እዬዬና ዋይታ የነገሠበት …(ተቆጥሮ አያልቅም) ነበርና ስለእሱ እዚህ አናወራም። ስለ እሱ፣ ስለ “መሀሉ” ብቻ አይደለም እዚህ የማናወራው፤ ውሾን ያነሳ ውሾ እንዲሉ፣ ስለ “ቅድመ–”ም አናነሳም። የምናነሳው አሁን ስላለንበት፣ ስለ “ድህረ–” ብቻ ነው።
ከሁለት አመት ደም መፋሰስ በኋላ ፕሪቶሪያ (ደቡብ አፍሪካ) ላይ ከትሞ በነበረው ውይይት አማካኝነት ደም መፋሰሱ ቆሞ፣ በምትኩ ጦርነት ለሰላም እጁን ሰጥቷል። እስካሁን ባለው መረጃ ፕሪቶሪያ ላይ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ ወራትን ያስቆጠረውና “አቻ የለሽ”፣ አስከፊ ጥፋት የተመዘገበበት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አብቅቶ ቀጣናው፣ እንደ አጠቃላይም አገሪቱ ድህረ ጦርነት (“አንፃራዊ ሰላም” ነው የሚሉት) ላይ ትገኛለች።
መንግሥት እና ሕወሓት» ለሁለት ዓመት ያደረጉት ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪቃ፣ ፕሪቶሪያ ላይ ከተካሄደና የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ፣ ይነስም ይብዛ ሰላም አግኝተናል። “. . . ሰላም አግኝተናል” ስንል ከራስ ካሳ እስከ ራስ ዱሜራ ከ . . . እስከ . . . እያልን እንዳልሆነ ግን ሊታወቅልን ይገባል።
“ድህረ–” ከአንድ አስደሳችም ሆነ አሳዛኝ ክስተት፣ ድርጊት፣ ሁነት . . . በኋላ ያለው ጊዜ ሲሆን፣ ይህም “በኋላ” ከሚለው ጋር በተለዋዋጭነት ሊታይ የሚችል ጽንሰ-ሀሳብ ነው።“ድህረ–” ከ“ቅድመ–”ም ሆነ ሌሎቹ የሚለይበት ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር “ነገሮች” ካለፉ በኋላ መሆኑና እነዛን “ነገሮች” እንዳልነበሩ ያህል ለማድረግ ይቻል ዘንድ በእቅድ፣ በአገራዊና ሕዝባዊ አላማ የሚሰራ ተግባር መሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው፣ ጦርነት አውዳሚ ነው። ጥሎት የሚያልፈው የስነልቦናም ሆነ መንፈሳዊ፤ አካላዊም ሆነ ህሊናዊ ጠባሳ እንዲህ በቀላሉ ከሰዎች አእምሮ ውስጥ ሊጠፋ የሚችል ጉዳይ አይደለም። በተለይ ችግርና ጉዳቱን ከገፈት ቀማሹ ወገን በኩል ሆኖ ለተመለከተው በቃላት መግለፅ ከሚቻለው በላይ ስለ መሆኑ መከራከር አይቻልም።
ስለ “ድህረ–” በሚነሳበት ሰአት አንድ የማይቀር ጥያቄ ቢኖር “ምን ቢደረግ ነው፤ ምን ምን ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሰብአዊ፣ ፖለተካዊ ወዘተርፈ ተግባራት ቢፈፀሙ ነው ያንን ማህበረሰብ፤ ያንን በማያገባው እንዲገባ ተደርጎ በእሳት የተለበለበን ሕዝብ፤ ያንን እምቦቀቅላ ልጆቹን የተነጠቀ ሕዝብ፤ ያንን ሀብት ንብረቱን ያጣን ሕዝብ . . . ከነበረበት ድብርት፣ ከነበረበት ስነልቦናዊ ቀውስ፣ ከነበረበት ኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ከነበረበት ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ፣ ከነበረበት ያለ ማመን ሁኔታ፣ ከነበረበት የመጠራጠር ስጋት፤ ከነበረበት የመገለል ስነልቦናዊ ጫና . . . አውጥተን፤ ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ የምንመልሰው?” የሚለው ነው። ከባዱ ጥያቄ ይሄው ነው።
ይህ ጥያቄ በአንድ ወገን የሚመለስ፣ ይመለስ ዘንድም የሚታሰብ አይደለም። ምናልባት የአንበሳውን ድርሻ “ከፍተኛ አመራር” የሚባለው ይወስድ ይሆናል እንጂ፣ በአንድ ክፍል፣ በአንድ ተቋም፣ በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት፤ በአንድ . . . የሚመለስ አይደለም። እንኳን ሊመለስ የሚታሰብም አይደለም። ጥያቄው በአግባቡ፣ ውጤታማ በሆነ መልኩ ይመለስ ዘንድ የሁሉንም ያልተገደበ ተሳትፎ ይፈልጋል፤ ይጠይቃልም።
እርግጥ ነው አንዳንድ ጅማሬዎች እንደሚያሳዩት በዚህ አግባብ እየሄዱ ያሉ ክፍሎች አሉ። ታሪካዊው የደሴ ሙዚየም በጦርነቱ ከደረሰበት የከፋ አደጋ መልሶ ያገግም ዘንድ ለማድረግ በራሱ፣ ተነሳሽነቱን ወስዶ የተቋቋመ አስተባባሪ ኮሚቴ እየሄደበት ያልው እርቀት፤ ለዚሁ ኮሚቴም የእንግሊዝ ኤምባሲ ያደረገው የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እየተነጋገርን ስላለነው “ድህረ–ጦርነት” አንድና ጥሩ ማሳያ ነው።
ይህንን አንድ እውነት እንግለፅ እንጂ ይህንን መሰል ተግባራት እየተካሄዱ አይደሉም እያልን አይደለም። ጥያቄና ስጋታችን “በተፈለገው ቦታና ጊዜ እየተካሄደ ነው ወይ?” የሚለው ሲሆን፤ በአብዛኛው እየታዩም ሆነ እየተሰሙ ያሉ ጉምጉምታዎች እነዚህን አይነት ጥያቄዎች በአዎንታ እየመለሱ አይደሉም።
በጦርነት ወቅት ለእንግልት፣ ስቃይና መከራ የተዳረገ ሕዝብ ተራ ጭፈራ ቤት ያደረ ዳንሰኛ አይደለም። ሲቆስል፣ ሲደማ፣ ሲሞት . . . የነበረ ሕዝብ ነው። በመሆኑም ከነበረበት ከዛ ሁኔታ፤ ከነበረበት ድብርት እንዲህ በቀላሉ ልውጣ ቢል፤ ላውጣህ ቢሉት፣ ነገሮችን በጥርጣሬ ከማየትና “ደሞ ሌላ ዙር . . .” ከማለት የሚመልሰው የለም። “ድህረ ጦርነት” ከ“ድህረ ጭፈራ ቤት” ይለያያል። ሀንጎቨሩ የውስኪና ሆት ዶግ ሳይሆን የደምና አጥንት ነውና ጉዳዩ የዋዛ አይደለም።
ከጦርነት በኋላ ያለ ህብረተሰብ ከልቡ የሚደግፈው ሰው ይፈልጋል፤ የሚታመን ወገን ይፈልጋል፤ አይዞህ የሚለው አካል ይሻል፤ የታመነ የመንግስትን ተደራሽነት በቅጡ ይጠብቃል፤ ቀን ከሌትም እጁን ዘርግቶ ”እጃችሁ ከምን?” ይላል። ይህ ደግሞ (እንኳን በማያገባው ይገባ ዘንድ ተገዶ ይቅርና) ድሮም ቢሆን መብቱ ነው።
አምጡ የማለት ሙሉ መብት አለው። መንግስት ፈጥኖ የመድረስ ግዴታ አለበት። የእርዳታ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ . . . ድርጅቶች፣ . . . ድርጅቶች፣ . . . ድርጅቶች፤ ምሁራን ሁሉ ይህን ማድረግ የተልእኮ ወይም የአላማ ወይም . . . እየተባለ በቃላት የሚሽሞነሞን ርእዮተ አለማዊ ጣጣ ሳይሆን የህሊናም፣ የሕግም ግዴታ ነውና ካልገቡ ፈጥነው ወደ’ዚህ ተግባር ሊገቡ ይገባል።
ይህ በጤናውም፣ በትምህርቱም፣ በፋይናንስ ተቋማትም፣ በግብርናውም፣ በመሰረተ ልማቱ . . . በሁሉም ሊሆን፣ ሊደረግ የሚገባው ነውና ችላ የሚባል ነገር አለመሆኑ ታውቆ ሁሉም ወደ’ዚሁ፣ ወደ ታመነና ተጎጂውን ወገን ወደ ነበረበት ጤናማ ሁኔታ የመመለስ ተግባር ሊያመራ ይገባል።
በተለይ አዲስ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተግባሩ ፊት መሪ ብቻ ሳይሆን አስተባባሪነቱንም ሊካነው ሁሉም ነገር የግድ ይለዋል። አገራትም ልክ ከላይ እንደጠቀስነው ኤምባሲ ሁሉ፣ በእንደራሴዎቻቸው አማካኝነት ከጎናችን ሊቆሙ ሰአቱ አሁን ነው። ከላይ ስለ “ቅድመ–” ያልነው እንዳለ ነውና ስለ ደረሰብን ደባ (የፖለቲካ ወጉ ሆኖ) እዚህ ባናነሳውም፣ ስለሚደረግልን ትብብር ግን ከወዲሁ እናመሰግናለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም