አስተውሎት ነገሮችን ሰከን ብሎ ለማሰብ፣ ለመገንዘብ እና ለመፍትሄው ለመሰለፍ የሚያስችልን ከፍ ያለ ሰብዓዊ ልዕልናን የማጎናጸፍ ኃይል አለው፡፡ በአስተውሎት ሲራመዱ በቀስታ ውስጥ ፈጥኖ ካሰቡበት መድረስ አለ፤ በአስተውሎት ሲናገሩ በትህትናና በጥበብ ሃሳብን የመግለጥና የማስረዳት አቅም አለ፤ በአስተውሎት ሲሰሩ ከዛሬ የተሻገረንና ለትውልድ የሚተርፍ አሻራን ለማኖር የሚያስችል ብርታት ያጎናጽፋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሃሳብ እስከ ተግባር የዘለቁ ሁነቶች ታዲያ በአስተውሎት ውስጥ የሚገለጡ የዛሬን ፈተና መሻገሪያ፤ የነገን ማንነት ለመስራት መሰረት ማኖሪያ ጡቦች ናቸው፡፡
ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚቀጥለው፤ ሃገርም እንደ ሃገር ጸንታ የምትቆየው ደግሞ በትውልዱ የማስተዋል ጉዞ ውስጥ ነው፡፡ አስተዋይ ትውልድ ከዛሬ የተሻገረን ሃሳብ ያመነጫል፤ አስተዋይ ሕዝብ በጊዜያዊ ግርግር ከሚገኝ ትርፍ ይልቅ ለችግሮች ዘላቂ እልባት በማግኛ መንገዶች ላይ ያተኩራል፡፡ በጥቅሉ ማስተዋልን ገንዘቡ ያደረገ ትውልድና ሕዝብ ትዕግስትን ተላብሶ፣ ጥበብን ደርቦ ይራመዳል፤ ሃገርና ሕዝብን አሻጋሪ መፍትሄዎችን በርጋታ ያጤናል፤ በይቅርታና ተግሳጽ አጥፊዎችን ያርማል፣ ወደ ትክክለኛ መንገድም ይመልሳል፡፡
ኢትዮጵያም ዛሬ እንዲህ አይነት ትውልድና ሕዝብ ትሻለች፡፡ ችግሮች ሲደራረቡባት አሻጋሪ መፍትሄ አፍላቂ ወጣት ትናፍቃለች፤ የጥፋት ሃሳቦች ከፍ ብለው ለመውጣት ሲታትሩ የሚገስጹና መክረው የሚመልሱ ሽማግሌዎችን ትፈልጋለች፡፡ ሃገር እንድትጸና፣ ሕዝቦችም አንድነታቸው እንዲዘልቅ በሚያስችሉ ሃሳቦች ላይ ማተኮርን፤ ለእነዚህ ሃሳቦች የመገዛት ሰብዕና መላበስን፤ የተሻለ ነገ እንዳይታይ የሚጋርዱ ክፉ አካላትንና ሃሳቦቻቸውን ገልጦ የማሳየት አቅምን ሃብቱ ያደረገ ትውልድ አብዝታ ትሻለች፡፡
አንድ ሆና ጠንክራ እንድትወጣ የጠነከረ አንድነትን፤ በጥንካሬዋ ውስጥ የሚያንጸባርቅ ውበቷ ከፍ ብሎ እንዲገለጥም ብዝሃነትን ጠብቆ በኅብር መቆምን፤ የራሷን ብልጽግና፣ የልጆቿን ልዕልና የማይሹ ኃይሎችን የተንኮልና የሴራ መንገድ እንቢኝ ማለትን ከልጆቿ አጥብቃ ትጠብቃለች፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ጸንታ የምትቆመው፤ ሕዝቦቿም በኅብር ሆነው በጸናችው ሃገር ውስጥ በክብር የሚኖሩትና የፍቅር፣ የሰላም፣ የመተሳሰብና የመፈቃቀር መንገዳቸውን የሚያጸኑት በአስተውሎት ነው፡፡
ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ “ከጊዜያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም!”፤ በሚል ማጠንጠኛ ሃሳብ ባስተላለፉት መልዕክት ያስገነዘቡትም ይሄንኑ ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገራዊ ጉዳይ ላይ በማተኮር ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሰፈሩት፤ ሀገራት አጣዳፊ የጸጥታና የደህንነት ሥጋቶች ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ፣ በማዕከላዊ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አማካኝነት የሚጋረጡባቸውን ሥጋቶች መመከት የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ እንደ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ያሉ፣ ለማቋቋም እምብዛም አዳጋች የማይሆኑ አነስተኛና መካከለኛ የጸጥታ ኃይሎችን አደራጅተው ለመንቀሳቀስ ይገደዳሉ።
እነዚህ ኃይሎች በጥድፊያ ውስጥ በጊዜያዊነት እንደመቋቋማቸው መጠን የሚሰጡትም ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ይታወቃል። በውትድርና ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም በጊዜያዊነት የሚቀመጡ መፍትሔዎችን ዘላቂ አድርጎ መውሰድ በራሱ አደጋ ሊጋርጥ እንደሚችል የታመነ ነው፡፡ ዛሬም በኢትዮጵያ በጸጥታው ዘርፍ ጊዜያዊውን መፍትሄ ወደ ዘላቂ መፍትሄ ለመለወጥ የሚያስችል ሂደት የተጀመረውም ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ ጊዜው ሲደርስ፣ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙ የመፍትሔ አማራጮች ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ማድረግ የተለመደ አካሄድ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ እርምጃ ነው።
ሊታወቅ የሚገባው ሃቅ፣ የየክልሉ ልዩ ኃይሎች ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ፈተና በገጠማት ጊዜ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። በየአካባቢው የተሰጣቸው ግዳጆችን በመወጣት ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ታግለዋል። አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የልዩ ኃይል አደረጃጀት አስፈላጊ አይደለም ማለት ግን የልዩ ኃይል አባላት አያስፈልጉም ማለት አይደለም። ለሀገራችን የሚችሉትን ሁሉ ያደረጉ፤ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአቅማቸው የተወጡ፤ ለወደፊትም በተሻለና ይበልጥ ኢትዮጵያን ማገልገል በሚያስችላቸው ቦታዎች ላይ እንደየፍላጎታቸው ተመድበው ያገለግላሉ። ይሄም ለረዥም ጊዜ የታሰበበትና የተመከረበት ነው፡፡
ጊዜያዊ የመፍትሔ አማራጭ በዘላቂነት መወሰድ ኢትዮጵያን ከአንዴም ሁለቴ ለችግር አጋልጧታል፡፡ በክልሎች መካከልም አላስፈላጊ ፉክክርን ፈጥሯል፡፡ ሕገወጥነትን እና ሽፍትነትን ወልዷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ ላይ ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅም ሲባል አስፈላጊውን የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው። ይህ ደግሞ በሁሉም ክልል አመራሮች በጋራ የተወሰነና በጋራ የሚተገበር ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃሳባቸው ማጠቃለያ ይህ ውሳኔ ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሕዝቡ ሰላም ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው ተቋማትና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ፣ የውሳኔውን ሃገራዊ ፋይዳና የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት በማስገባት ለተግባራዊነቱ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ውሳኔውን በአስተውሎት ተመልክቶና ውሳኔው ከዛሬ ያለፈ ዘላቂ ሃገራዊ መፍትሄ መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ ኃላፊነትን መወጣት ከሁሉም የሚጠበቅ ግዴታ እንደሆነም መገንዘብ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም