ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጎበዝ ልጅ ሁሌ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርት ነው። እናንተም ጎበዝ ተማሪ ስለሆናችሁ ሳምንቱን ያሳለፋችሁት በትምህርት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ጎበዝ ተማሪ የጊዜን ጥቅም በሚገባ ያውቃል ስለዚህ ያለውን ጊዜ በአግባቡ በመከፋፈል ይጠቀማል፤ ማንበብ ባለበት ሰዓት ያነባል መጫወት ባለበት ሰዓት ይጫወታል መማር ባለበት ሰዓት ደግሞ ይማራል፡፡ እናንተም ሰዓታችሁን እንደዚህ በስርዓት ከፋፍላችሁ እንደምትጠቀሙበት አምናለሁ፡፡
ልጆች ስራ የአንድ ሰው ጠንካሬ መገለጫ መሆኑን ታውቃላችሁ? ስንፍናን ያሸነፈና ሁልጊዜ ሳይሰለች፤ በሚገጥሙት ችግሮች ተስፋ ሳይቆርጥ፤ በተስፋ ተሞልቶ እንደሚያልፈው እርግጠኛ በመሆን ስራውን በአግባቡና በታታሪነት የሚሰራ ሰው የጥንካሬ መገለጫ ምሳሌ ነው። ታዲያ ይህንን ለማዳበር ከልጅነት ጀምሮ የስራ ባህልን ማሳደግ በጣም አስፈላጊ እና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ልጆች ዛሬ የማስተዋውቃችሁ በታታሪነቷ እና በስራ ወዳድነቷ እውቅና ያገኘችውን ጠይሟን እና የተስፋ ጮራ ከፊቷ የሚንፀባረቀውን ታዳጊ ዘምዘም ከድርን ነው፡፡
ልጆች ዘምዘም በሻሸመኔ ከተማ የምትኖር ሸንኮራ በመሸጥ ቤተሰቧን የምትደግፍ የአስራ አራት አመት ታዳጊ እና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ልጆችዬ ዘምዘም የሸንኮራ መሸጥ ስራዋን የጀመረችበት አጋጣሚ ምን መሰላችሁ፤ ከዕለታት ባንዱ ቀን ዘምዘም እንደተለመደው ከሰፈር እኩዮቿ ጋር ከትምህርት ቤት ተመልሰው ሰፈር ውስጥ ሰብሰብ ብለው በመጫወት ላይ ሳሉ ሸንኮራ የሚሸጡ ሰዎች ወደ እነሱ ይመጣሉ፤ ዘምዘም ታዲያ ሸንኮራውን ገዝታ ከመብላት ይልቅ ቀልቧን የሳበው የሰዎቹ ሸንኮራ የመሸጥ ስራ ነው፡፡ ወዲያው እነሱ የሚሰሩትን ስራ ለምን አልሰራም የሚል ሃሳብ ወደ አዕምሮዋ መመላለስ ጀመረ፤ ሰዎቹ ርቀው ከመሄዳቸው በፊትም ከምትሸጡት ሸንኮራ ላይ በዱቤ ስጡኝና ሽጬ እከፍላችኋለሁ በማለት ትጠይቃቸዋለች። ነገር ግን ሰዎቹ ሰርታ መክፈል መቻሏን ባለማመናቸው ሸንኮራውን ሊሰጧት አልፈለጉም፡፡
ልጆችዬ ዘምዘም ግን ተስፋ አልቆረጠችም ወደ እናቷ በመሄድ የሸንኮራ መሸጥ ንግድ መጀመር እንደምትፈልግና ለመነሻ የሚሆናትን የሸንኮራ አገዳ ሰዎቹን አነጋግራ እንድትቀበልላት ትጠይቃታለች፡፡ የዘምዘም እናትም የልጃቸውን ፍላጎት ለማሟላት ወደ ሰዎቹ በመሄድ የሸንኮራ አገዳውን ሰጥተዋት ንግዱን እንድትጀምር ይጠይቁላታል፤ ሰዎቹም ዘምዘም በእናቷ በኩል ስለመጣችባቸው እውነትም የመስራት ፍላጎት ቢኖራት ነው በማለት የሸንኮራ አገዳውን በዱቤ ሰጧት፤ ዘምዘምም የሸንኮራ መሸጥ ስራዋን በዱቤ በተቀበለችው የሸንኮራ አገዳ ሀ ብላ ጀመረች፡፡ ሽጣ ከምታገኘው ላይ እዳዋን እየከፈለች የምታገኘውንም ትርፍ ማጠራቀሙን ተያያዘች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እዳዋን ከፍላ ጨርሳ ባተረፍችው ብር ሸንኮር እያመጡ የሚሰጧት ሰዎች ሸንኮራውን ከሚያመጡበት ቦታ ድረስ በመሄድ ሸንኮራ አምጥታ መሸጥና ከበፊቱ የተሻለ ትርፍ ማግኘት ጀመረች። ዘምዘም ታዲያ ሸንኮራ ሽጣ በምታገኘው ገንዘብ እራሷን ብቻ ሳይሆን ወላጅ እናቷንም ታግዛለች፡፡
ልጆች ዘምዘም ወደፊት ትልቅ ልጅ ስትሆን ምን መሆን እንደምትፈልግ ታውቃላችሁ? መሐንዲስ መሆን ነው የምትፈልገው፡፡ በምህንድስና ሙያ ተመርቃ በሻሸመኔ ከተማ ውስጥ በስሟ የሚጠራ ትልቅና ታዋቂ ሆቴል መክፈትና ለእናቷም ትልቅ የመኖሪያ ቤት መስራት ትፈልጋለች፡፡ ልጆች ዘምዘም ይህንን ስራ ለመጀመር ያነሳሳት ሃሳብ ምን መሰላችሁ፤ ለፍታና ጥራ ያሳደገቻትን እናቷን ከድህነት ኑሮ አላቃ ነገ ጥሩ ኑሮ እንድትኖር ለማድረግ ስለምትፈልግና ከሷ በፊት የተወለዱ ታላላቆቿ ወላጅ እናታቸውን ምንም ሲረዱ አይታ ስለማታውቅ እሷ ግን እንደነሱ ላለመሆንና የእናቷን ልፋት ላለመርሳት በመፈለግ ካሁኑ ከልጅነት ጊዜዋ ጀምራ እናቷን ስራ እየሰራች በምታገኘው ገቢ ለማገዝ በማሰብ ይህንን ስራ ጀመረች፡፡
ልጆች ዘምዘም በአጠቃላይ የሸንኮራ ሽያጭ ሥራውን የጀመረችው በብዙ ነገር ስትቸገር የምታያትን እናቷን ካሁኑ ከልጅነት ጊዜዋ ጀምራ ስራ እየሰራች በምታገኘው ገቢ ለማገዝ በማሰብ ጀመረች፡፡
ልጆችዬ ዘምዘም ሰርታ የምታመጣውን ገንዘብ ማባከን አትፈልግም፡፡ ስራ ሰርታ ለፍታ የምታመጣው ገንዘብ ያለአግባብ እንዲባክን ስለማትፈልግ ከቀን ገቢዋ ላይ በየቀኑ ሃምሳ ብር ትቆጥባለች፡፡ በምታገኘው ገቢ ለራሷ የሚያስፈልጓትን ነገሮች በማሟላት ባሻገር እናቷንም በቻለችው ሁሉ ትደግፋለች፡፡
ልጆችዬ ስራ እንደሚያስከብር እና ዝቅ ብሎ ስራ ሳያማርጥ ጠንክሮ የሰራ ሰው ሁልጊዜም ቢሆን የሚከበርና ለጥንካሬውን እውቅና የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ዘምዘምም ታዲያ ታታሪነቷ ከፍ አድርጎ በሰዎች ፊት ቀና ብላ በኩራት እንድትቆም አደረጋት እንጂ አላሳፈራትም፡፡ በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እጅ ታዳጊ ስራ ፈጣሪ በሚል የእውቅና የምስክር ወረቀት ወስዳለች፡፡ ልጆች በርትተን ቤተሰቦቻችንን በመርዳት እና ትምህርታችንን በመማር ትልቅ ደረጃ መድረስ ይኖርብናል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡
ልጆች ከዘምዘም ብዙ እንደተማራችሁና ወደፊትም እንደሷ ጠንካራና ጎበዝ ስራ ወዳድ እንደምትሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለዛሬ የዘምዘምን መልእክት ተግባራዊ እንድታደርጉ አደራ በማለት ፅሁፌን በዚሁ ላብቃ ሳምንት በሌላ አስተማሪ ፅሁፍ እስክንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም