እኤአ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የእሱን ያህል በተደራራቢ ክብር የተንቆጠቆጠ አትሌት ማግኘት ያዳግታል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክ ብቻ 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 7 ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የአትሌቲክስ ቤተሰቡን አጀብ አሰኝቷል። አስደማሚው የዚህ አትሌት ብቃት በተለይ በ10ሺ ሜትር ሲሆን፤ በ5ሺ ሜትር ካገኘው አንድ የብር ሜዳሊያ በቀር ሁሉም የተመዘገቡት በዚሁ ርቀት ነው፡፡ የዓለም አትሌቲክስም በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የ40 ዓመት ታሪክ ከ1993-2001 የኢትዮጵያዊውን ጀግና አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን ያህል በድል የደመቀ የለም ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት ትልቁ፣ የኦሊምፒክን ያህል በድምቀት የሚካሄደውና በስፖርት ቤተሰቡም ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የዓለም ቻምፒዮና መካሄድ ከጀመረ በተያዘው ዓመት አራት አስርት ዓመታትን ይደፍናል፡፡ የዓለም አትሌቲክስም ይህንን ክብረ በዓል ከአምስት ወራት በኋላ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ያከብራል፡፡ እአአ ከ1983 ጀምሮ ባለፉት ዓመታት በርካታ አስደናቂና አስገራሚ የአትሌቲክስ ሁነቶች ታይተዋል፡፡ በዓለም አቀፉ ተቋም የክብር መዝገብ በልዩ ሁኔታ ተመዝግበው ከሚገኙት መካከልም፤ በ1980ዎቹ የጦር ወርዋሪዋ አትሌት ቲና ሊላክ ትውስታ፣ በ1990ዎቹ የሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የ10ሺ ሜትር ርቀት ገድል እንዲሁም ከ2ሺ ወዲህ የዓለም ፈጣን ሰው የተባለው ዩሴን ቦልት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡
ከዚህ ውድድር እአአ እስከ 2022 ድረስ በተካሄዱ 18 የዓለም ቻምፒዮናዎችን የዓለም አትሌቲክስም ሆነ የስፖርቱ ቤተሰብ ስፖርቱ (የሩጫ፣ ውርወራ፣ ዝላይ እና እርምጃ ስፖርቶች) የደረሰበትን የእድገት ደረጃ በቀላሉና በግልጽ ሊመልከት ይችላል፡፡ በቡዳፕስቱ ቻምፒዮና ላም ከውድድር ባሻገር እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በጉልህ ለዕይታ የሚቀርቡ ሲሆን፤ ሌሎች መርሃ ግብሮችም እንደሚከናወኑ ማህበሩ ከወዲሁ አሳውቋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የስፖርት ቤተሰቡ ድምጽ በመስጠት የሚሳተፍበት የምርጥ 10 ሴት እና 10 ወንድ ምርጥ አትሌቶች ምርጫ አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ዓለም አቀፉ ማህበር ዘርፈ ብዙ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም በፕሬዚዳንቱ ሰባስቲያን ኮ በኩል አሳውቋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአንጻራዊነት ከሌሎች ቻምፒዮናዎች ያነሰ ዕድሜን ያስቆጠረ ውድድር ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆነው ኦሊምፒክ ላይ የሚካሄዱት የአትሌቲክስ ውድድሮች በማህበሩ በኩል ልክ እንደ ዓለም ቻምፒዮና የሚቆጠሩ ስለነበረ ነው፡፡ በዚህም መሰረት እአአ ከ1913 ጀምሮ ባሉት 50 ዓመታት በአራት ዓመት አንዴ የኦሊምፒክ መካሄድን ተከትሎ ታላቁ ውድድር ይካሄድ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የማህበሩ አባል የሆኑ ሀገራት የራሳቸውን ትንንሽ ቻምፒዮናዎች ያዘጋጁ ነበር፤ ይህ ሁኔታ እያደገና እየሰፋ በመጣ ጊዜም ማህበሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኦሊምፒክ ተለይቶ የሚካሄድ ውድድር መኖር እንዳለበት በማመኑ እአአ በ1970ዎቹ ጀምሮ ሃሳቡ መብላላት ጀመረ፡፡
የሃሳቡ ተግባራዊነት ላይ እምነት በመጣሉም እአአ በ1983 በፊንላንድ ሄልሲንኪ ላይ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ቻለ፡፡ በወቅቱም ከ153 ሀገራት የተወጣጡ 1ሺ333 አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን፤ በ41 የውድድር ዓይነቶችም ተካሂደዋል፡፡ እአአ እስከ 2022ቱ የዩጂን ዓለም ቻምፒዮና ድረስም ውድድር የሚካሄድባቸው የስፖርት ዓይነቶች እየተጨመሩ 49 የግል እና የቡድን ውድድሮች ሊደርስ ችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ ቻምፒዮናዎችም 35 የዓለም ክብረወሰኖች ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህ ውስጥም 18 የሚሆኑት በወንድ አትሌቶች፣ 15ቱ በሴት አትሌቶች እንዲሁም 2ቱ በድብልቅ ሪሌ ናቸው፡፡
በመጀመሪያው የሄልሲንኪው ቻምፒዮና አንድ ክብረ ወሰን በ400 ሜትር ሲመዘገብ፤ በጀርመኗ ስቱትጋርት በተደረገው 4ኛው የዓለም ቻምፒዮና ደግሞ 5 የዓለም ክብረወሰኖች ነበሩ የተሰባበሩት፡፡ እጅግ ፈጣኑ ጃማይካዊ አትሌት ዩሴን ቦልት ደግሞ በ100ሜትር፣ 200ሜትር እንዲሁም በ400ሜትር ተደራራቢ ክብረወሰኖችን በመሰባበር ወደር ያልተገኘለት አትሌት ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም