ኢትዮጵያ በአርኪዮሎጂና በታሪክ ቅርስነት መዝግባ ካሰፈረቻቸው የመስህብ ሃብቶቿ መካከል ጥቂት የማይባሉት ሃብቶች ተዘርፈው በልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በጦርነት፣ በህገወጥ ንግድ እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከአገር የወጡ እነዚሀ ሃብቶች እስካሁንም ድረስ በባእዳን እጅ ተቀምጠው የሙዚየሞቻቸው ማድመቂያ ሆነዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ጨረታዎች በሚያወጧቸው ድረገፆች ላይ በግለሰቦች በግላጭ እየተቸበቸቡም ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እና ዘርፉን የሚመሩት ተቋማት ሃብቶቹን በተደራጀና በሚመጥን ሙዚየም አደራጅተው ከመጠበቅ ባሻገር ተዘርፈው ከአገር የወጡ ቅርሶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስመለስ ጥረቶች እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ በዚህና በመሳሰሉት መንገዶች ተዘርፈው የወጡ ቅርሶች የተመለሱበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየምም በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር ወጥተው የቆዩና ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመለሱ ቅርሶችን በቅርቡ በጊዜያዊ አውደ ርእይ ለተከታታይ 10 ቀናት ካስጎበኘበት ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም የኢትዮጵያ ቅርሶች አስተዳደር፣ የሙዚየም ስርዓትና ቅርሶች አያያዝ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ከአገር የወጡ ሃብቶችን ለማስመለስ ስለሚደረግ ጥረት እና ሙዚየምን የመጎብኘት ባህልን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የብሔራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር አቶ ደምረው ዳኜ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ብሔራዊ ሙዚየሙ ከውጪ የተመለሱ ቅርሶችን በቅርቡ በጊዜያዊ አውደ ርዕይ ለእይታ አቅርቧል፡፡ የእዚህ አውደ ርዕይ ዋና ዓላማ ምን ነበር?
አቶ ደምረው፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በዋናነት ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል አውደ ርዕይ ማዘጋጀት ቀዳሚው ነው፡፡ ይህንን ስንል የተለያዩ አይነት አውደ ርዕዮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል ቋሚ የምንለው አንደኛው ሲሆን፣ በዚህም በብሔራዊ ሙዚየም በዋናው ህንፃ ውስጥ ከአምስትና አስር ዓመት በላይ ቆይታ የሚያደርጉ አውደ ርዕዮች አሉ፡፡ ይህም የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አርኪዮሎጂ፣ ስነጥበብና፣ ፓሎንቶሎጂን ያካትታል፡፡ ሌላኛው ተንቀሳቃሽ ኤግዚቢሽን ሲሆን በአንድ በተመረጠ ርእሰ ጉዳይ ላይ ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሰ የሚታይ ነው፡፡
እኛም ይህንን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ያዘጋጀነው የአውደ ርዕይ አይነት ጊዜያዊ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ ከአገር የወጡ ልዩ ልዩ ቅርሶችን ይዞ ለእይታ የቀረበ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ይደረግ የነበረው ቅርሶቹ በተመለሱበት ቀን ደማቅ ዝግጅት በማካሄድ ይፋ ማድረግ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ቅርሶች በጊዜያዊ አውደ ርዕይ ቀርበው አያውቁም ነበር። የመጀመሪያ በሆነው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ይህንን ለመስበር ተሞክሯል፡፡
አዲስ ዘመን፦ በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት ቅርሶች ይዘት ምን ይመስላል? የት አገሮች ነበር የቆዩት?
አቶ ደምረው፦ በዋናነት ከአራት አገራት የተመለሱ ናቸው፡፡ የተወሰኑት በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ናቸው፡፡ በህገወጥ መንገድ ሲባል ወይ በጦርነት ምክንያት የወጡ ቅርሶች ናቸው፡፡ ከመቅደላ በ1860 ዓ.ም የተወሰዱ ቅርሶች ይገኙበታል /ይህም ከ150 ዓመት በፊት የሆነ ነው/፡፡ በዚያን ጊዜ እንደሚታወቀው ከአፄ ቴዎድሮስ መውደቅ በኋላ በናፒር የተመራው የእንግሊዝ ጦር መቅደላን በሙሉ ዘርፏል፡፡ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑ ቅርሶች ባለፈው ዓመት /በ2014 ዓ.ም/ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ እነዚህ ቅርሶች የተመለሱት በእንግሊዝ አገር በግለሰቦች ለጨረታ ሊቀርቡ ሲሉ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲና አገር ወዳድ ግለሰቦች ጨረታው እንዲቆም አድርገው ባደረጉት ውይይት ነው፡፡ ሌሎችም ከኔዘርላንድ፣ ከዴንማርክና ከአሜሪካ የተመለሱ ይገኙበታል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተለይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል በሚሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አካላት ጥረት ነው፡፡
ለእይታ ከቀረቡት ውስጥም ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ መስቀሎች፣ ጎራዴዎች፣ ጠልሰም ፅሁፍና ስዕል፣ የብራና መፃህፍት እና ሌሎችም ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ በአጠቃላይ ለመጀመሪያ ጊዜ 20 የሚደርሱ ቅርሶች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ በዚህም የተመለሱ ቅርሶች በአግባቡ እንደሚያዙና እንደሚጠበቁ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡
አዲስ ዘመን፦ በስፍራው ተገኝተን እንደተመለከትነው ተዘርፈው ከሀገር ከወጡት ሃብቶች አንፃር ተመልሶ ለእይታ የቀረበው ውስን መሆኑን ነው፡፡ ይህ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን አያመላክትምን?
አቶ ደምረው፦ ቅርስን ማስመለስ እጅግ ፈታኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዋናነት የሚገጥመው ችግር አገራት የሚያወጡት ህግ ነው፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝ አንዴ ቅርሶች ወደ ሀገሪቱ ከገቡ ሃብት ሆነው እንዲመዘገቡ የሚደነግግ ህግ አላት፡፡ ይህን በመሰሉ ምክንያቶች አንድ ጊዜ በሙዚየም ውስጥ ያሉትን ሃብቶች እንዳይመለሱ ፈተና ይሆናሉ፡፡
ዩኔስኮም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ቅርስን ለማስመለስ ያወጡት ህግ ቢኖርም አብዛኛውን ጊዜ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚደረግ ጥረትን የሚያበረታቱ እንጂ አስገዳጅ ሁኔታን የሚያስቀምጡ አይደሉም፡፡ ይህ ምክንያት ነው ለእይታ የቀረቡት ቅርሶች ውስን እንዲሆኑ ያስገደደው፡፡ ይሁን እንጂ የተመለሱትም ቢሆኑ ትልቅ መልእክት ይኖራቸዋል። እነዚህ መመለሳቸው ለምሳሌ በፈረንሳይ በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ እነርሱ / ፈረንሳዮች/ ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀው፣ ነገር ግን ቅርሶቹ በተሻለ ሁኔታ ላይያዙ ይችላሉ የሚል ነገር ያነሳሉ፡፡ ይህን ለመሰለው አግባብነት የጎደለው አስተያየት ምላሽ ለመስጠት መሰል የማሳያ ስፍራዎችና ተጠብቀው የሚቆዩበት አግባብ እንዳለ ለማሳየት ይረዳናል፡፡
በሀገር ቤት የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ አለ፡፡ በውጪ ደግሞ ኤምባሲዎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ በእነዚህ አካላት ልዩ ልዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝ አገር በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተዘረፉ ሃብቶችን የያዘው ሙዚየም ቅርሶቹ እንዲመልሱ ለሚቀርበው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ “በጊዜያዊነት ወይም በውሰት ወስዳችሁ ለእይታ አቅርቡና መልሱ” የሚል ነው፡፡ ይሄ የራሱ አሉታዊ ትርጉም አለው። ይህ አባባል ለአገር ክብር የማይመጥንና ትርጉሙም አሉታዊ ነው፡፡ በቋሚነት ቅርሶቹን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ አገር ውስጥ ያሉ ቅርሶችን በተመሳሳይ ላለማጣት የቅድመ መከላከል ስራም እንሰራለን፡፡ ከውጪ የሚገኙትን ደግሞ በዲፕሎማሲም በህግ አግባብም እንዲመለሱ ይሰራል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረና የኢትዮጵያን ዋና ዋና ቅርሶች የያዘ ነው፡፡ ይህን ለማስፋፋት፣ ለመጠበቅ፣ የበለጠ ለማደራጀት እንዲሁም ለማልማት ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ደምረው፦ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከ200 ሺህ በላይ የቅርስ ስብስቦች አሉት። በተለይ ከሰው ዘር መገኛ ጋር የሚያያዙ እጅግ በርካታ መረጃዎችና ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ አንፃር በቅርቡ የተጀመረና በእቅድ ላይ ያለ “የሰው ዘር መገኛ ሙዚየም” ለመገንባት ሃሳቡ አለ፡፡ ሃሳቡን ወደ መሬት ለማውረድ ዛሬ ሳይሆን ከረጅም ጊዜ በፊት በቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የአስተዳደር ወቅት ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ ቦታ ብሔራዊ ሙዚየም ፊት ለፊት ተፈቅዶ ነበር፤ እስካሁን ድረስ ግን የቦታው ርክክብ አልተፈፀመም፡፡ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ለሚነሱ የግል መኖሪያ ቤቶች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ለካሳ ክፍያ በ2011 ዓ.ም ቢከፍልም እስካሁን ግን በልዩ ልዩ ቢሮክራሲዎች ቦታውን ማስረከብ አልቻለም፡፡
እንደምታየው ብሔራዊ ሙዚየም ካሉት ሃብቶች አንፃር አነስተኛ ነው፡፡ ከተሰራም ረጅም ጊዜን አስቆጥሯል፡፡ የተቋቋመውም በ1930ዎቹ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እስካሁን ሊያድግና ሊደራጅ የሚገባውን ያህል ማደግ አልቻለም፡፡ ይህ የሰው ዘር መገኛ ሙዚየም ቢቋቋም ብዙውን የቅርስ ስብስብ መውሰድና በተደራጀ መንገድ ለእይታ ምቹ ማድረግ ይቻል ነበር፤ ለከተማውም ሆነ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በምርምር ዘርፍ ላይ የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ወደዚህ ለማምጣት ምቹ አጋጣሚም ይፈጥራል፡፡ ይህ ባለመሆኑ የተሻለ ነገር እንዳንሰራ አግዶናል፡፡
ከዚህ ውጭ ባሳለፍነው ዓመት ትልቅና ራሱን የቻለ ብሔራዊ ሙዚየም ይገነባል የሚል በእቅድ ላይ አለ። ይሄ በአገሪቱ ጥቅል እቅድ ላይ የተቀመጠ ነው። ይህ በቻ ሳይሆን በክልሎች የመስራት እቅድ አለ። ለምሳሌ በአፋር ክልል አካባቢ ከ2016 እስከ 2018 ለመስራት ለፕላን ኮሚሽን የተላከ እቅድ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ በሂደት ላይ ያሉ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ብሔራዊ ሙዚየሙ የተፈቀደለትን መሬት ለመረከብ እንዲችል ወደ ሌሎች ውሳኔ ሰጪ አካላት አልሄደም?
አቶ ደምረው፦ እውነት ለመናገር እንደ ተቋም ይህን አላደረግንም፡፡ ነገር ግን በቀድሞው የባህልና ቱሪዝም አደረጃጀት የተለያዩ ደብዳቤዎችን አጠናክረን ሰጥተን እስከ ከንቲባው ፅህፈት ቤት ለማድረስና ውሳኔ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፤ ይሁን እንጂ በግሌ ይሄም በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አሁንም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማሳወቅ ነገር ቢኖርም፣ ጥያቄው ግን አሁንም ድረስ እንደተንጠለጠለ ይገኛል። በዚህ ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ሄደናል አልልም። በበላይ አካላት የጎንዮሽ ስራ መሰራት ነበረበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ቦታው ቢፈቀድ ሙዚየሙን ለመስራት የሚያስችል በጀት አለ?
አቶ ደምረው፦ እንደተባለው በአንድ ዓመት ውስጥ የሚገኝ ሳይሆን በመንግስት የሚመጣ ነው። የሰው ዘር መገኛ ሙዚየሙ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የውጭ አካላትም የሚሳተፉበት ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የፈረንሳይ መንግስትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌላው ድጋፍ ማሰባሰብ የሚችል በክብርት ፕሬዚዳንቷ የሚመራ ቦርድም አለ። ስለዚህ በጀቱ ከዚህ አካባቢ የሚመጣ ነው፡፡ ከ2016 እስከ 2018 በሶስት ዓመት እቅድ እስከ 3 ቢሊዮን ብር በጀት ተጠይቆበታል፡፡ ስለዚህ ስራው ቢጀመር በጀት ከውጪም ከውስጥም ሊገኝ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፦ አሁን ያለው ብሔራዊ ሙዚየም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ጎብኚዎች ተደራሽ እንዲሆን ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ደምረው፦ በአገር ውስጥ የጉብኝት ባህል ደካማ ነው፡፡ ይሄ አገራዊ ችግር ነው፡፡ የክበባትና አገርህን እወቅ እንቅስቃሴዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ተቀዛቅዟል፡፡ በተለይ ከዚህ አንፃር ብሔራዊ ሙዚየም ላይ ብዙ የሰራነው ስራ የለም፤ የሚዋሽ ነገር የለውም፡፡
በቀጣይ ግን በሙዚየሙ በር ላይ አንድ ራሱን የቻለ ትልቅ ስክሪን የማቆም ሃሳብ አለን፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተግባራዊ የሚሆኑ ሁለት አዳዲስ አሰራሮችንም እየተከተልን ነው፡፡ የመጀመሪያው የብሔራዊ ሙዚየም የገበያና ፕሮሞሽን የስራ ክፍል አለ፡፡ በዚህ መንገድ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ በቅንጅት ለመስራት እያሰብን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ አሁን ተቀርፆ ተግባር ላይ የሚውለው የትምህርት ስርዓት “የተግባር ትምህርትን” የሚያበረታታ ስለሆነ ጎብኚዎች ወደ ብሔራዊ ሙዚየም በስፋት እንዲመጡ የሚያበረታታ እንደሆነ እናምናለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር በእጅጉ እናመሰግናለን!
አቶ ደምረው፦ እኔም አመሰግናለሁ!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም