ቪዚት ኢትዮጵያ ለቱሪዝም መነቃቃት

ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ከሀብትነት ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ይታወቃል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከተፈጥሮ ጋር ለተቆራኙ ሀገራት ደግሞ ሌሎችም ልዩ ትርጉም ያላቸው ጉዳዮች አሉት። ይህንን መሠረት በማድረግ በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ የመጣው መነቃቃት ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚገልፅ ነው። የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያም ይበል የሚያሰኝ ነው።

ጊዜው ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ተሳስረው እና ተደጋግፈው ያሉበት ወቅት ነው። አንዱን ያላንዱ ማሰብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በዚህም ቱሪዝምን ለቴክኖሎጂ ቴክኖሎጂን ለቱሪዝም የሚሉ እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ በስካይ ላይት ሆቴል የቴክኖሎጂ አንድ አካል የሆነ ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› ድጂታል ፕላት ፎርም በይፋ ተመርቋል። በዝግጅቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ የነበረውን ያለውን እና ወደፊት የሚኖረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ቃኝተው፤ አሁን ላይ ቱሪዝምን ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር አስተሳስሮ መሄድ ለመጪው ጊዜ ወሳኝ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ድንቃድንቅ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ጸጋዎችን በሚያስገርም መጠንና ስብጥር የታደለች ምድር ናት። ይሁንና ሀብቶችን ከማልማት፣ ተወዳዳሪ የቱሪዝም ምርቶችን እና መዳረሻዎችን ከመፍጠር እንደዚሁም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ከማረጋገጥ አኳያ አመርቂ ሥራዎች እንዳልተሠሩ አስታውሰው፤ እነዚህ ነባር ሂደቶች በዘመናዊ መልኩ ተቀይረው ሀገርና ሕዝብ የሚጠቀሙበት አቅጣጫ መቀየሱን ጠቁመዋል።

እንደሚኒስትሯ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ስር ነቀል የኢኮኖሚ ለውጥም ሆነ የሀገር ግንባታ መሠረት ይሆናሉ ብላ በአንክሮ እየሠራችባቸው ካሉ ዘርፎች መሀል ቱሪዝም አንዱ ነው። ለዚህም በቴክኖሎጂ የታገዙ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ሀገሪቱ ከታደለችው የተፈጥሮ ሀብት እና መልከአምድር በመነሳት የአፍሪካ የቱሪስት መዳረሻ ከፍ ሲልም ዓለም አቀፍ መዳረሻ እንድትሆን ሁሉንም አይነት እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፤ በተለይ በዲጅታላይዜሽን እሳቤ ላይ መሠረት አድርጎ እየተሠራ ያለው የቱሪዝም ገበያ መልካም ተስፋን የሰነቀ ነው።

አሁን ላይ በመንግሥት ይሁንታ አግኝተው እየተሠሩ ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች፤ ነባር የቱሪስት መስህቦችን ማደስ እና መጠበቅ፣ የመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ቴክኖሎጂ ተኮር ልማት፣ የቱሪዝም ሀብቶችን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የማስተዋወቅ ተልዕኮ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳዩ ናቸው።

የቱሪዝም ዘርፉን ከኋላ ቀርነት አውጥቶ ዘመኑን የዋጀ ከማድረግ አኳያ የቴክኖሎጂ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ አሁን ላይ ወደ ሥራ የገባውን ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ››ን ጨምሮ ሌሎች አቅም እና ሃይል የሚፈጥሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ቱሪዝሙን ማነቃቃት፣ የሀገሪቱን ሀብቶች መሸጥ፣ ጎብኚዎችን ለኢኮኖሚ ፍጆታ መጠቀም አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ በአፍሪካ በርካታ ቅርሶችን ያስመዘገበች ሲሆን፤ መሥራት ከተቻለ ከዚህም በላይ እድሎችን መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል። አክለውም በአሁኑ ጊዜ ሀገራት ቱሪዝምን ወሳኝ የኢኮኖሚ ማዕከል አድርገው እየሠሩ በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ እድሎች እንዲፈጠሩ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በማስተዋወቅ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይ ተግዳሮቶችን ቀርፎ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ብዙ የቤት ሥራዎች አሉ። ለዚህም ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር በመቆራኘት ለዘመናዊ አሠራር በር መክፈት ተገቢ ነው ሲሎ ተናግረዋል።

እንደሳቸው ገለፃ፤ ቴክኖሎጂዎች ከየትኛውም አማራጭ በተሻለ አንድን ተልዕኮ ለመፈጸም ምቹ በመሆናቸው፤ ለቱሪዝሙ ተመራጭ ናቸው። ሁሉንም አይነት የቱሪዝም ልማት በቴክኖሎጂ በማጠንከር፣ ከቱሪዝም ገበያ ወቅታዊ ለውጦችና ፍላጎቶች ጋር ማጣጣም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ይሁንና የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪነት ከሚገዳደሩ ነገሮች አንዱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም ዝቅተኛ መሆን ነው። ቴክኖሎጂ ሊሸሽ የማይቻል በሁሉም ሕይወት ውስጥ ያለ በመሆኑ አቅምን በማጎልበት ዘርፉን መጥቀም የግድ ነው።

አያይዘውም በቱሪዝም ዘርፍ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መፍጠር፣ ማልማት እና ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ዋና የፖሊሲ ጉዳይ ተደርጎ እየተሠራበት እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በሀገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሀል አንዱ ጎብኚዎች የቱሪዝም ቦታዎችን፣ መስህቦችን፣ ምርቶች እና አገልግሎቶችን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና የተሟላ መረጃዎችን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ አለመቻል መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በተጨማሪ በዘርፉ ላይ የተሠማሩ እንደአየር መንገድ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የቱሪስት ትራንስፖርት አቅራቢዎች ሌሎችም የሚተሳሠሩበት አንድ ዲጂታል ፕላት ፎርም አለመኖሩ በግብይት እና በማስተዋወቅ ተግባር ላይ እንከን ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

እንደሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የተመረቀው ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› ነባር ችግሮችን በመቅረፍ እንደዚሁም የቱሪዝም ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን ሀገሪቱ ምቹና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የበኩሉን የሚወጣ ሲሆን፤ ከአገልግሎት አኳያ ሰፋ ያለ ጠቀሜታ ያለው ነው። ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› ቱሪዝምን ለቴክኖሎጂ በሚል እሳቤ የተጀመረ የእንቅስቃሴ አካል ሲሆን፤ ሰፊውን እና ብርቅዬውን ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ለልማት፣ ለኢኮኖሚ፣ ለሀገር ግንባታ ለማዋል ዓለም አቀፋዊነትን በተላበሰ መርህ ወደ ሥራ የገባ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው።

ከፋይዳ አንጻር ሲታይ በአንድ ጊዜ ብዙ እድሎች ብዙ ጊዜ አይገኙም። ይሁንና ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› ለዚህ ዓላማ ታስቦ በባለሙያ የለማ የዲጂታል ፕላት ፎርም በመሆኑ በአንድ ጊዜ ብዙ እድሎችን የሚሰጥ ነው። የቱሪዝም ጸጋዎችን፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን፣ የቱሪዝም ምርትና አገልግሎቶችን እንዲሁም የሀገሪቱን ልዩ የቱሪዝም መገለጫዎችን በአንድ ስፍራ ለማስተዋወቅ ይረዳል ሲሉም ተናግረዋል።

በቱሪዝም ሰንሰለት ውስጥ የተሰማሩ አካላትን በአንድ ስፍራ በማገናኘት፣ አገልግሎታቸውን እና ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚሸጡበት እንደዚሁም ከጎብኚዎች ጋር የሚገናኙበት በመሆን ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪ ጎብኚዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች፣ አገልግሎቶች፣ ምርቶች እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን የተመለከቱ መረጃዎች በቅልጥፍና እንዲገኙ ያደርጋል። የጉዞና ጉብኝት ፕሮግራሞችን መርጠው ለመግዛት ወይም የራሳቸውን የጉዞና ጉብኝት ዝግጅቶች ለማሰናዳትም እንደሚያግዝ ጠቁመዋል። እንደዚሁም ፈጣን እና ቀልጣፋ የቡኪንግ ሥርዓትን በመፍጠር፣ ሁሉንም አገልግሎት ሰጪዎች በአንድ ቦታ በማሰባሰብ የጎብኚዎችን አማራጭ ለማስፋት ጥሩ መሆኑም ተጠቁሟል።

እንደእሳቸው ገለፃ፤ ሕጋዊ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከሕገወጦች እና በሕግ ማሕቀፍ ውስጥ ካልተካተቱት ለመለየት እንደዚሁም ለመጠበቅ ግልጽ እና ጤነኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ለባለድርሻ አካላት ደግሞ አስተማማኝ የቅድመ መረጃ ምንጭ በመሆን ያገለግላል። ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ ስለነበራቸው ቆይታ እና ርካታ ግብረ መልስ የሚሰጡበት አሠራር በመፍጠሩ እንደዚሁም ትስስር እና ቅንጅትን በመፍጠር ቱሪዝምን ለቴክኖሎጂ ቴክኖሎጂውን ለቱሪዝም በማዋል ረገድ የማይተካ ሚና ያለው ነው።

እንደአጠቃላይ ‹‹ቪዝት ኢትዮጵያ›› ቱሪዝሙን ከመጪው ዘመን ጋር አቀናጅቶ በማስተሳሰር ለአዲስ እና ለዘመናዊነት መንገድ የሚከፍት የድጅታል ሥርዓት ነው። እንደሀገር ለተጀመረው የቱሪዝም ልማት እንቅስቃሴ ሃይል በመሆን እድሎችን ለመጠቀም የሚያስችል ነው።

ቪዚት ኢትዮጵያ በቀላል እና በተሻለ መንገድ ኢትዮጵያን እና ሀብቶቿን ለዓለም ማስተዋወቅ የሚቻልበት፣ ከነባር አካሄድ ወደተሻለ እና ዘመኑን ወደሚመስል የቴክኖሎጂ ዓለም የተገባበት፣ ሁሉንም ሥርዓቶች በአንድ ቦታ ለተጠቃሚ ያቀረበ የዲጂታል ገበያ በመሆኑ ምቹነቱ አጠያያቂ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል።

ይሄን ዓላማ ከማስፈጸም አኳያ ሁሉም ተሳታፊ መሆን እንዳለበት የገለጹ ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ትልቅ እንደሆነ አንስተዋል። ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤት እንደመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር ቀዳሚ እና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ እንዲሁም የግብይት ማእከል እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የቱሪዝም ሚኒስቴር የተለያዩ ቬንዶርስ እንዲመዘገቡ ተደርጎ ስልጠና በመስጠት በቀጣይ ሁሉም የቱሪዝም እሴት ተዋንያን በዚሁ ፕላትፎርም ውስጥ እንዲገቡ እንደሚያደርግ ታውቋል። በሂደት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የቱሪዝም ዘርፉ በቴክኖሎጂ እገዛ ከነሙሉ አገልግሎቱ ወደ አንድ ስፍራ አገልግሎት ሰጪ ሆኖ የሚመጣ ይሆናል ።

ሀገሪቱ የጀመረችውን የዲጂታል ዓለም የተቀላቀለው የቱሪዝሙ ዘርፍ ከነባር አሠራር ወጥቶ ዘመናዊ አማራጮችን መጠቀሙ ከላይ የተገለጹትን ጥቅሞች ጨምሮ ሌሎች በርካታ እድሎችንም የሚያመጣ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ በዘልማድ እና የፖሊሲ ማሕቀፍ ባልተበጀለት አሠራር አማካኝነት ሀብቶች ምርት እና አገልግሎት ሳይሰጡ የመቆየታቸው እውነታ ቁርጠኝነት ከማነስ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ክፍተት መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም።

አሁን ላይ በተወሰዱ እና እየተወሰዱ ባሉ ቁርጠኛ ሥራዎች ቱሪዝሙ ከነበረበት ነቅቶ በተሻለ እና ተስፋ ሰጪ በሆነ ንቃት ላይ ይገኛል። መንግሥትም ሆነ ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ሚናቸውን በማሳየት ቱሪዝምን ለሀገር ብልፅግና መጠቀም እንደሚቻል የተረጋገጠበት እውነታ አለ። ይህ ንቃት አብቦና አሽትቶ ሀገራችንን የቱሪስት መናኸሪያ የማድረግ ንቅናቄ በተግባር ተገልጾ እንዲታይ ሂደቱ ላይ መሳተፍ የሁላችንም ድርሻና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ሕዝቡ በተፈጥሮ የተሰጠውን ጸጋ እና ሀብት ከማንም በፊት ተጠቃሚ መሆን ይገባው ነበር። ሆኖም ለዘርፉ በተሰጠ አነስተኛ ትኩረት ተጠቃሚነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ኖሯል። አሁን ላይ በመንግሥት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ቱሪዝምን ለሀገር፣ ሀገርን ለቱሪዝም የሚል እሳቤን በመያዙ የሕዝቡ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ እንደሚችል ነው።

ቱሪዝም በባህሪው ቁርጠኝነትን ይፈልጋል። ትግል የሚደረገው ከተፈጥሮ ጋር በመሆኑ ተፈጥሮን መረዳት እና መጠበቅ ወሳኝ ነው። ስለሀገር ሲነሳ ዐሻራዎች አስፈላጊ ናቸው። ሀገራዊ እድገት ግለሰባዊ ዐሻራን ብቻ የሚያሳይ ሆኖ አያውቅም። የጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ለጋራ ከመትጋት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው።

የቱሪዝም ሀብቶች ከለሙና ከተጠበቁ የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆን የሚችሉ ናቸው። ከሌላው የተፈጥሮ ሀብት በተለየ ጥቅም በመስጠት በቀዳሚነትም ይጠቀሳሉ። በተለይ ከቴክኖሎጂ ጋር ተሳስረው በአንድ ቦታ ለተጠቃሚዎች መቅረባቸው የበለጠ አትራፊ ለመሆን እድል ይሰጣል።

ቴክኖሎጂ በባህሪው ድካምን ከመቀነስ፣ ሕይወትን ከማቅለል፣ ምቹ፣ ቀላል እና አስተማማኝ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አኳያ አሁን ላይ ተመራጭ የሚባል ነው። ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ለየትኛውም ዘርፍ ጥሩ ቢሆንም በተለይ ደግሞ በአንድ አካባቢ ያለን የተፈጥሮ ሀብት፣ ሁሉም አካባቢ ላሉ ጎብኚዎች ከማስተዋወቅ አንጻር ለቱሪዝሙ ዘርፍ የበለጠ ቅርብ ሆኖ እንዲገኝ ያግዛል እንላለን።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You