ትምህርት የአንድን አገር ምንነትና ማንነት ሊቀይር የሚችል ግዙፍ ዘርፍ ነው። የትምህርት አስፈላጊነት በሁሉም የሕይወት ዘርፎች በተለይም በአገር ዕድገት ይንጸባረቃል። መንግስታት ለአገር ምን ሰሩ የሚለውን ጉዳይም በግልፅ የሚያሳይም ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የብልጽግና ጉዞ በትምህርቱ ዘርፍ ብዙ ፈተናዎችን እድሎች ገጥመውታል። በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ የነበራት ጉዞ ምን ይመስላል? የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ መልስ አላቸው።
የትምህርት ጥራት ከለውጡ ወዲህ
የትምህርት ጥራት ችግር አለ የሚለው ጉዳይ እንደ አጠቃላይ በሁሉም አገር የሚነሳ ጥያቄ ነው። በእኛም አገር እንደዚሁ የትምህርት ጥራት ችግር ውስጥ እየገባ ነው የሚሉ ሃሳቦች በየጊዜው ይነሳሉ። ከዚህ አንፃር ባለፉት አምስት ዓመታት ችግሩን ለመፍታት ብዙ ተግባራት ተከውነዋል። መጀመሪያ የተደረገው ችግሩ የመለየት ስራ ነው። በዚህም ችግሩ የፖሊሲ ችግር ነው ወይስ የትግበራ ችግር የሚለው በጥናት ተለየ። የፖሊሲ ችግር ያለባቸውን ለማስተካከል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት፤ የትግበራ ጉዳዮችን ደግሞ የመፈተሽና የማረም ስራ መስራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ።
በዚሁ መሰረት ባለፉት አምስት ዓመታት የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተወያይተውበት በየደረጃው ሲሻሻል ቆይቶ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል። ይህም በትምህርትና ስልጠና ሴክተሩ ትልቁ መነሻ ነው። በዚህ ፖሊሲ ብዙ ጉዳዮች ሕጋዊ ስርዐት ይበጅላቸዋል፤ የመንግስት ቁርጠኝነት የሚያሳያም ነው። ከሌሎች የአገሪቱ ፖሊሲዎች ጋር በደንብ እንዲጣጣም እንዲዛመድ ተደርጓል። ፖሊሲውን በተቀመጠው መሰረት ተግባራዊ ካደረግን የአገራችንን የትምህርት ጥራት አንድ እርምጃ ወደፊት ማሻገር ይቻላል የሚል እምነት አለን።
ዋናው ትኩረታችን ካለን ሀብት አንፃር የቱ ጋር ብናተኩር የተሻለ ነው የሚለውን መለየት ነው። በመደበኛ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን መስራት ሲባል ብዙ ወጪ ይፈልጋል። በዚህም በዓምስት ዓመቱ የለውጥ ስራ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ መዋጮ ሲደረግ ነበር። መፅሀፋቸውን አሳትመው ካስገኙት ገቢ ላይ ትምህርት ቤቶችን አሰርተዋል፤ ባለቤታቸውም እንዲሁ በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በኩል በርካታ ትምህርት ቤቶችን መስራት ችለዋል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ከዚህ ቀደም ያልነበር ሲሆን፤ አሁን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበት ማድረግ በአምስት ዓመቱ ውስጥ በስፋት የተሰራበት ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ በመገንባት ላይ ናቸው። ይህም የሆነው ባለሃብት፣ መንግስትና የትምህርት ሴክተሩ ተቀናጅተው ነው።
ትምህርትን ወደኋላ ከሚጎትቱ ነገሮች መካከል በኢኮኖሚ ምክንያት ትምህርት ቤት መጥተው ትኩረት አድርገው የማይማሩ ተማሪዎች መኖራቸው፤ በመሰረታዊነት ቁርስና ምሳቸውን የማያገኙ ተማሪዎች መፈጠራቸው በዋናነት ይጠቀሳል። እናም ይህንን ለመቀየር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የልማት አጋሮችን አስተባብሮ የክልል መንግስታትም ትኩረት ሰጥተውት በገጠርም በከተማም በተለያየ አማራጭ በሚሊየን የሚቆጠር ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመግቡ ማድረግ ተችሏል። ይህ ነገር በእኛ አገር ስለተሰራ ትኩረት አንሰጠውም እንጂ ለአንዳንድ አገራት በቀን ሁለት ጊዜ ሙሉ ህዝብ እንደመመገብ ማለት ነው።
ቁርስ ሳይበላ የሚመጣ ተማሪ ትምህርቱ ላይ ትኩረት አያደርግም፣ ቤተሰብም የሚመግበው ስለማይኖረው ልጆች ትንሽ ከፍ ሲሉ ራሳቸውን እንዲደግፉ በማሰብ ስራ መስራት በማይገባቸው እድሜ የተለያዩ ስራዎችን ያሰሯቸዋል። ይህ ደግሞ ከትምህርት የመቅረት እድላቸውን ከፍተኛ ያደርገዋል። ስለዚህም የምገባው መጀመር የትምህርት ጥራትንና ፍትሃዊነትን ይጨምራል፤ የትምህርት ብክለትንም ይቀንሳል። እናም ይህ በአምስት ውስጥ የተሰራ ትልቅ ትርጉም ያለው ስራ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ይህ የሆነው ግን በመደበኛው ዘመን አይደለም፤ ይህ የሆነው በአገራችን በርካታ ችግሮች ወረፋ ይዘው አንድ ላይ በመጡበት ዘመን ላይ ነው። በለውጡ መጀመሪያ አካባቢ ችግሮች ነበሩ። አሁንም የሚስተዋሉ አሉ፤ ለውጡን ተከትሎ ወዲያው ድርቅና ጎርፍን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ተከስተው ነበረ። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ተማሪዎችም ቤት ውለዋል።
እንደአገር ተማሪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው እንዲማሩ ለማድረግ አገራችን ካላት የቴክኖሎጂ አንፃር ለሁሉም ተማሪ ታብሌትና ላፕቶፕ ማዳረስ የማይቻል ነበር። በቴሌቪዥን እና በሬዲዮም ቢሆን በበቂ መልኩ ማዳረስ አልተቻለም። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ኮቪድን የተቋቋምንበት ሁኔታ የትምህርት ስርዓቱ እንዳይጎዳ፤ በጎርፍና በመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት የምርት መቀነስ በመከሰቱ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ትኩረት ተሰጥቶ በመንግስት የተሰራበት ነው።
ቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ ላይ መስራት ዛሬ ላይ ጥቅሙን ላንረዳ እንችላለን። ከጊዜያት በኋላ ግን ኢትዮጵያን የሚረከባት ዜጋ በዚህ የትምህርት ስርዓት ከተገነባ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት ያስችላል። ስለዚህ የትላንት ስህተቶችን መርገምና መውቀስ አቁመን መጪው ትውልድ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ዓለም ከቴክኖሎጂ ጋር የምትራመድ በመሆኑ ቴክኖሎጂውን በአግባቡ የሚጠቀም ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነ በኢትዮጵያዊ እሴቶች የተገነባ የአገሪቱን ነባር እውቀቶች የሚያዳብር ትውልድ መፍጠር ይገባል።
ተደራሽነትና የዘመናዊ አደረጃጀቶች ትግበራ
ዜጎች ትምህርትን በስፋትና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማግኘት ካልቻሉ ተጎጂው ሁሉም ዜጋ ነው። አንድ ተማሪ ሁኔታዎች ሳይመቸው ቀርቶ ትምህርት ቢያቋርጥ በውስጡ ያለውን እምቅ ሀይል እናጣለን፤ ያ እምቅ ሀይል አገርን አለፍ ሲል ደግሞ ዓለምን የሚለውጥ ሊሆን ይችላል። የዜጎች ትምህርትን የማግኘት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ በፍትሃዊነት ላይ ያልተገነባ አገር ዘላቂነቱ ችግር ላይ ይወድቃል። ስለሆነም የትምህርት ፍትሃዊነትን ከአገር ጋር ማስተሳሰር አለብን።
ትምህርት ማስፋፋት ፖለቲካዊ ጉዳይ ሳይሆን የዜጎች መብትን ማስጠበቅ ነው። ከዚያም አለፍ ሲልም የዜጎች የልማትና የተወዳዳሪነት ጥያቄን መመለስ ነው። አገሪቱን የሚመስሉ ተቋማትን ለመገንባትና ከሌሎች አገራት ጋር የሚመጣጠን የልማት ደረጃ ላይ ለማድረስ የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት ለሁሉም ዜጎች ማዳረስ ግድ ያስፈልጋል።
ይህ ግን የአጭር ጊዜ ፕሮጀክት ሊሆን አይችልም፤ ከመቶ ዓመታት በላይ ዘመናዊ የአስኳላ ትምህርት ተግባራዊ ስናደርግ ቆይተናል አሁንም ግን ትምህርት ቤት የሌለባቸው አካባቢዎች በርካታ ናቸው። በመሆኑም እነሱን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መስራት ይገባል። ተደራሽነቱ ግን በጥራት ሚዛን ላይ መቀመጥ አለበት። ጥራትና ተደራሽነት እኩል ለእኩል መሄድ ይኖርባቸዋል።
የትምህርት ጥራት ላይ ብቻ በማተኮር ጥቂቶች ብቻ የሚማሩበት ስርዓት መገንባት አንችልም፤ ተደራሽነትን ማስፋት አለብንም ብለን በየደሳሳ ጎጆው ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ አይቻልም። ስለዚህም የመማሪያ ክፍልንና የተማሪ ጥምርታን ሚዛናዊ ለማድረግ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ስንገነባ አለያም አዲስ ስንሰራ ተደራሽነትና ጥራትን በሚያሟላ መልኩ መሆን ይገባዋል። ይህም እየተደረገ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት የክልል የትምህርት ቢሮዎች ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን እየገነቡ ነው፤ የትምህርት ተደራሽነትም እያሰፋን የተሻለ ትምህርት የመቀበል አቅም ያላቸው ተማሪዎችን ደግሞ በእነዚህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የማሰባሰብ ስራ እየሰራን ነው። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትንም በየዘርፉ በመከፋፈል ተማሪዎች በአቅማቸውና በፍላጎታቸው እንዲማሩ እያደርግን ነው። ዩኒቨርሲቲዎችም ተለይተው በተሰጣቸው መስክ ተማሪዎችን እንዲያበቁ እድሉ መመቻቸቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተከናወነ ነው።
የኮቪድ ወረርሽኝና ጦርነቱ ያስከተላቸው ችግሮች
ባለፉት አምስት ዓመታት አገር የነበረችበት ሁኔታ እጅግ የተለየ ነው። ብዙ ችግሮች በአንድ ጊዜ የተከሰቱበት ዓመት ነበረም። ሆኖም ችግሮቹ ላይ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶ ሌሎች ሥራዎች ለነገ ሳይባሉ ፕሮጀክቶች ሳይቋረጡ ትምህርት በተቻለ መጠን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ሁሉንም አንድ ላይ ማስኬድ ተችሏል። የአገር ሉአላዊነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በመከላከል ጎን ለጎን የዜጎች የወደፊት ተስፋ የሆነው ትምህርትን በማስቀጠል በኩል ትልቅ ስራ ተሰርቷል።
ኢትዮጵያ በኮቪድ ወቅት ሁሉንም ችግር ያለፈችው በራሷ ጥበብ ነው። ኮቪድ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትርጉም ነበረው። ከዚያም በላይ በኢኮኖሚው ጉዳይ የንግድ እንቅስቃሴዎች መቆማቸው በራሱ የፈጠረው የዋጋ ንረት አለ፤ አገሪቱ የትምህርት መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን ከውጭ ተጉዛለች። የንግድ እንቅስቃሴው ሲቀንስ ገቢ ይቀንሳል። ገቢ ሲቀንስ የተቋማት በጀት ይቀንሳል።
የነበረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ላይ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ተጨምሮ ሁኔታዎችን ከባድ አድርጓቸው ነበርም። በተለይ ጦርነቱ አውዳሚ ነበር። በዚህም ጦርነት መከሰቱ ትምህርት ቤቶችን አውድሟል፤ ዜጎችን አፈናቅሏል፤ ትምህርት ቤቶች ለተፈናቃዮች ማረፊያ እንዲሆኑ ተደርጓል። በዚህ ምክንያት ትምህርት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።
ቢሆንም ትምህርት ማስቀጠል እንደዋና ስትራቴጂ ተወስዶ ተግባራዊ ማድረግ፤ ከገፅ ለገፅ ውጭ ሌሎች የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ችግሮችን ማለፍ፤ ድንኳንን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የተቋረጡ ትምህርቶች እንዲቀጥሉ ማድረግ፤ ድህረ ኮቪድ በራሳችን ኢትዮጵያዊ ጥበብ መምራት፤ ዩኒቨርሲቲዎችን ስራ ማስጀመር፤ የፈረቃ ትምህርት በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን እንዲያስተናግዱ እድል መስጠት የሚሉትና መሰል ተግባራት በእቅድና በጥበብ የተተገበሩ ናቸው። ባለፉት አምስት ዓመታት እነዚህ ችግሮች ባይኖሩ ኑሮ ኢትዮጵያ ከትምህርት ዘርፉም ባሻገር በሌሎች ዘርፎችም አሁን ካለችበት የተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኝ ነበር።
የአዲስ ነገሮች ስኬታማነት
በትምህርት ዘርፍ ስኬታማ የሆኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። እየተገበርናቸው ያሉ ሥራዎችን ውጤታቸውን ለማየት ትውልድ የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- የፈተና ስርዓታችን ተቀይሯል። ከዚህ በፊት ወደነበረው መመለስ አይቻልም፤ ይህ በትምህርት ዘርፉ ትልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ትልቅ ትጋትን ይጠይቃል። የፈተና ስርዓትና አጠቃላይ የትምህርት ስርዓትን ስብራትን ካላረምን ይህችን አገር ወደ ብልፅግና መውሰድ አንችልም። በመሆኑም የዲፕሎማሲ ጫና፣ የብድሮች መቆም፣ የእርዳታ መቋረጥ፣ በኮቪድ ምክንያት የመንግስት ገቢ መቀዛቀዝ ባለበት መንግስት ብዙ ተግባራትን ፈጽሟል። ለፈተናው የወጣውን ከፍተኛ ሀብት ጭምር ተቋቁሞ ውጤታማ ለማድረግ ተግቷል። ይህ ደግሞ ትልቅ እርምጃ ነው።
ዩቨርሲቲዎችን በተልኮና በተግባር መለየትም አንዱ ትልቅ ለውጥ ነው። የዩኒቨርሲቲ ቆይታን ከሶስት ዓመት ወደ አራት ዓመት ከፍ እንዲል ተደርጓል ይህ ማለት ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት ተጨማሪ የአስር ወር በጀት ለእያንዳንዱ ተማሪ መጨመር ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርትን የሚመራው መንግስት ነው፤ በየእለቱ ወደ 600 ሺህ ተማሪዎችን እየመገበ እንዲማሩ ያደርጋል። ትንሹ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ አራት ዓመት ማድረግ ማለት ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተማሪ በግቢ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ በጀትን ይጠይቃል።
የመጀመሪያ ዓመት ትምህርት ለመስጠትና አጠቃላይ አዲስ ስርዓተ ትምህርት ለመተግበር ተጨማሪ መምህራንን መቅጠር ይፈልጋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የመፅሃፍት ህትመቶችም ያስፈልጋሉ። ስለዚህም እነዚህ ነገሮች በድፍረት ተገብቶበት በስኬት የተሰሩ ሥራዎች ናቸው። በእነዚህ ስራዎች ውስጥ ጉድለት የለም ብሎ መናገር ግን አይቻልም። ጉድለቶቹን እያረሙ መሄድ ግን አስፈላጊ ነው።
እየተተገበሩ ያሉ የስርዓተ ትምህርት ትግበራዎች ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረግ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የትምህርት ቤቶችን አቅም የማሻሻል ስራ፤ የተማሪዎችን አቅም የመገንባትና የመምህራንን ህይወት ማሻሻል ጊዜ የሚጠይቁ የመንግስት ድጋፍን የሚሹ ስራዎች ናቸው።
ወደ 48 ሺህ ከሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 98 በመቶው ከደረጃ በታች ሲሆኑ፤ እነዚህን በመንግስት አቅም ብቻ እናሻሽላለን ቢባል 100 ዓመት ሊያስጠብቀን ይችላል። 100 ዓመት መጠበቅ አንችልም። ስለዚህ ማህበረሰቡም መንቀሳቀስ አለበት፤ በአቅሙ ልክ የሚጠበቅበትን ማዋጣት አለበት፤ በአካባቢው ያሉ ባለሃብቶች እና ተቋማትም በሚጠበቅባቸው ማህበራዊ ኃላፊነት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የመምህራንን ሕይወት የመቀየር ስራ መስራት ይኖርባቸዋል። መንግስት የራሱን ድርሻ ይወስዳል። ትምህርት ቤቶችና ማህበረሰቡም የራሱን ድርሻ በመውሰድ በርካታ ነገሮችን ማሻሻል አለበት።
የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና
የመውጫ ፈተናን ከ2015 ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ከተቋማት ጋር በመነጋገር እየሰራን ነው። አስፈላጊ የሆኑ የህግ ስርአቶችን ዘርግተናል። አንድ ተማሪ በሁሉም የትምህርት ክፍሎች በመጀመሪያ ዲግሪ ሲመረቅ ሊያውቃቸው ስለሚገቡ የብቃት መመዘኛ ወጥቷል።
ፈተናው ብቻውን ግን ጥራት አያመጣም። ለትምህርት ሂደቱ የመደብነው የሰው ኃይል፤ ለትምህርቱ ያቀረብነው ግብአት፤ የመምህራኖች ፍላጎት እና አቅም፤ ሙያውን የማክበር ሁኔታ ተደምሮ ነው ትምህርት ጥራትን የሚያመጣው። ፈተና የሚናገረው ስርአቱ በምን ያክል እየተጠናከረ እና እየተዳከመ እንዳለ ይነግረናል። የፈተና ውጤቱ የቱጋ ጉድለት እንዳለብን የማሳያ ግብረ መልስ ነው።
ተማሪዎች በተከታታይ ምዘናዎች ውስጥ አልፈው ወደ ኢንዱስትሪው ሲቀላቀሉ ተመራቂዎች ብቃት የላቸውም የሚለውን አመለካከት ይቀይራል። ተመርቄ ስራ አጣሁ የሚለውንም ወቀሳ ይቀንሳል። በቀጣይ ደግሞ ችግሮቹን ስንፈታ የተስተካከለ የትምህርት ስርአት ይኖረናል። ለትምህርት መሻሻል ስርአቱም እንደ አንድ ግብአት ይሆነናል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም