አንድ ሀገር ታላቅ እና ሉዓላዊ ከሚያስብሏት አቅሞች መካከል አንዱ እና ቀዳሚው የመከላከያ እና ደህንነት ኃይሏ ተቋማዊ አቅም ነው:: በዚህ ረገድ የበለጸጉትም ሆኑ ያደጉ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴያቸው በውስጥም ሆነ በውጪ የሚመጡ ትንኮሳዎችና ወረራዎችን ተቋቁሞና አሸንፎ እንዲቀጥል ማድረጊያ ዋና መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙትና ሲጠቀሙ የሚስተዋለው ይሄንኑ የመከላከያ እና ደህንነት ኃይላቸውን ነው:: ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ትልቅ ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም፤በተለይ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ግን እጅጉን የሚያበረታቱና ተጨባጭ ውጤቶችን ያሳዩም ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀጥታ ኃይል የሪፎርም ሥራ መነሻ ያደረገው ደግሞ የሃገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሰላምና ደህንነት ባስተማማኝ መሠረት ላይ ማጽናት መቻል ነው:: ይሄን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የሪፎርም ሥራው በሦስት መሠረታዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ሲያደርግ ነው:: ከእነዚህ አንዱ ብሔራዊ የፀጥታ ኃይሉ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብን የተላበሰ እና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተገነባ ሆኖ ለሁሉም ሕዝብ እኩል አለኝታና መከታ የሆነ ኃይል ማድረግ ሲቻል ነው:: ሁለተኛው፣ የግዛት አንድነትን የሚያስጠብቅ አቅምና ችሎታን መፍጠር ነው:: ሦስተኛው፣ የተሟላ ትጥቅ እንዲኖረው እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ፤ እንዲሁም ዘመናዊ አሠራርና አካሄድን መከተል ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ከችሎታ፣ ችሎታን ከትጥቅ አቅም እና ከቴክኖሎጂ ጋር ያዳመረ እና በዘመናዊ አሠራርና አካሄድ የሚመራ ብሔራዊ የጸጥታ ኃይል መፍጠር ማለት ደግሞ፤ ከውስጥ የሚነሱ ችግሮችን መግራት፣ ከውጭ የሚቃጡ ጥቃቶችንም መከላከል የሚያስችል ሃገራዊ አቅም መፍጠር ማለት ነው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአንድ በኩል አካባቢያዊ ስጋት አለባት፤ በሌላ በኩል መልኩን እየቀያየረ የሚከሰተው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የሚያሳድርባት ተጽዕኖ አለ:: በመሆኑም እነዚህን በልካቸው ተገንዝቦ ለመመከት የሚችል የፀጥታ ተቋም መገንባት ጊዜ የማይሰጠው ሥራ እንደመሆኑ ላለፉት አራት ዓመታት ይሄው ሲከናወን ቆይቷል፡፡
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ከትናንት በስቲያ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ያስረዱትም ይሄንኑ ሐቅ ነው:: ጄኔራሉ በማብራሪያቸው እንዳስቀመጡት፤ የሪፎርም ሥራው ሲጀመር ታሳቢ ያደረገው አንደኛው ጉዳይ የሕዝቦችን ሰላም ማረጋገጥ እና የተጀመረው ሃገራዊ የልማት ጉዞ በሰላም እንዲራመድ ማስቻል ነው:: ለዚህ ደግሞ በሕዝቦች ሰላምም ሆነ በልማት ጉዞው የተጋረጡ ፈተናዎችን ከመለየት አንስቶ ሥራውን ከውስጥ መጀመር ተገቢነት ነበረው:: ይሄ ሥራ ደግሞ ዝም ብሎ የሚከናወን አይደለም፤ ይልቁንም ሕገ መንግሥቱን መነሻ በማድረግ እንጂ:: በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የደህንነት እና የፖሊስ ተቋማትን የማደራጀት ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: በአንጻሩ ክልሎች የክልል መደበኛ ፖሊስ የማደራጀትና የክልሉን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ክልሎች ከመደበኛ ፖሊስ በዘለለ ልዩ ፖሊስ ማቋቋማቸው የታወቀ ነው:: ይሄ ምንም እንኳን ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ውጪ ቢሆንም፤ እነዚህ የክልል ልዩ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት ሃገር ችግር ላይ በሆነች ወቅት ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ሆነው ተዋድቀዋል፤ የሃገርንም ሉዓላዊነትና ክብር አስጠብቀዋል:: ይሄ ደግሞ ለእነዚህ ኃይሎች የፈጠረላቸው አቅምና ችሎታ መኖሩ እሙን ነው:: ይሄ አቅም ደግሞ መባከን ስለሌለበትና እነዚህ ኃይሎች የብሔራዊ የጸጥታ ኃይሉ የሪፎርም አካል እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢነት ያለው በመሆኑ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ወደማደራጀት ተግባር ተገብቷል፡፡
ይሁን እንጂ ይሄ ሃገራዊ አቅም የመፍጠር እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትም ሆነ የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ መሰረት ላይ የማጽናት ጉዞ ያልተዋጠላቸውና ሆን ብሎ ለማወናበድ የሚፈልጉ አካላት፤ ስለሂደቱ የተዛባ መረጃ በመልቀቅ ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ ይታያል:: ይህ ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑም ሕዝብ ድበቅ ዓላማቸውን ሊረዳና እንዲታቀቡ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ምክንያቱም የሪፎርሙ መሠረታዊ መነሻ የሀገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅን፤ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ተረጋግጦ ሕዝቦች ያለ ስጋት ወጥተው የሚገቡባትን ሃገር እውን ማድረግ ነው:: ይሄ ደግሞ ታስቦ የሚቀር ሳይሆን የሚፈጸም ነው:: በምንም ዓይነት እንቅፋትም ወደኋላ የማይመለስ ተግባር ነው:: ዘርን ተገን ያደረገ አካሄድ፣ የፀጥታ መዋቅር፣ የሃይማኖት እሳቤ፣ ሌብነትና ሌሎችም ለተጀመረው የግዛት አንድነት፣ ሰላምና ይሄን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ከኪሳራ ውጪ ለድል ስለማይበቃቸው አደብ ሊገዙ ይገባል:: መላው ሕዝብ፣ የጸጥታ ኃይሉ እና ፖለቲከኞችም ይሄንኑ ተገንዝበው በሪፎርሙ አንድ ጠንካራ ብሔራዊ የጸጥታ ኃይል የመፍጠሩን ሂደት ማፋጠንና ለውጤታማነቱም የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም