በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በእጅጉ ተጠባቂ የሆነው የበልግ ዝናብ ዘንድሮ መዘግየት ቢታይበትም ፤ ቀስ በቀስ በሚጠበቀው መልኩ እየጣለ ስለመሆኑ መረጃዎች አመላክተዋል። የዘርፉ ባለሙያዎችም በቂ ዝናብ ይዞ መምጣቱን እያስታወቁ ናቸው። የኢትዮጵያ ሚትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት ሰሞኑን እንዳስታወቀው፤ የበልጉ ዝናብ ከ45 ቀናት በላይ ጥሏል፡፡ ይህን ዝናብ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በአግባቡ ከተጠቀሙበት ለእርሻ ስራቸው ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።
በልግ ሁለተኛና ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነ አካባቢዎች እስከ 400 ሚሊ ሜትር ዝናብ መመዝገቡን የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመልክቷል፡፡ ይሄም በዘንድሮው በልግ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣሉን በሚገባ ያመላክታል፡፡ የበልጉ ዝናብ የውሃ አካላት አቅም አንዲጨምር በማድረግ ለእነዚህ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አካባቢዎችም መትረፍ የሚችል መልካም አጋጣሚ ይዞ የመጣ ነው፡፡
በተለይ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት እና ባለፉት አምስት የዝናብ ወቅቶች ዝቅተኛ ዝናብ ለነበራቸው እና ይህን ተከትሎ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ ለማግኘትና ለሰብል ሽፋን መጨመር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆነው የአገሪቱ አካባቢዎችም እንዲሁ ለግብርና ስራ መጀመር፣ ለእንስሳት ግጦሽ ሳር ማግኘት እንዲቻልና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡
ይህንን መልካም አጋጣሚ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በሚገባ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ የግብርና ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሙያዊና ሌሎች ድጋፎችን ለአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በማድረግ በዚህ የምርት ወቅት የሚጠበቀው ምርትና ምርታማነት እንዲገኝ አበክረው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
በተለይ እንደ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ያሉት ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ያላገኙ፤ በዚህ ምክንያትም ለከፋ የድርቅ አደጋ ተጋልጠው የቆዩ አካባቢዎች አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እየጣለ ያለውን ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም፤ ለተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይጋለጡ መስራት ይኖርባቸዋል።
ከዚህ አኳያ በቦረና አከባቢ ማሳዎቻችን በዘር ለመሸፈን፤ አነስተኛ ግድቦች ውሃ እንዲይዙ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሚበረታቱ ሲሆኑ በአካባቢው ደርሶ ከነበረው ችግርና ችግሩ ካስከፈለው ዋጋ አንፃር ሲታይ ግን አሁንም ብዙ አቅዶ ብዙ መስራት ይጠበቃል።
በዚህ በኩል የአካባቢው መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሰራርን በማስፈን አርብቶ አደሮች እና አርሶ አደሮች ከተረጂነት በፍጥነት እንዲላቀቁ፣ በነገዎቹ ላይ የተሻለ ተስፋ እንዲሰንቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርን ጨምሮ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ በወቅቱ እንዲደርሳቸው ማድረግ ላይ በትኩረት መስራት ይገባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የበልጉ ዝናብ በሌሎች አካባቢዎች አስቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ አንጻር፤ እንደ ዘንጋዳ፣ ማሽላና በቆሎ ያሉት ሰብሎች የሚዘሩት በዚህ ወቅት በመሆኑ ማሳን ለማለስለስ፣ በዘር ለመሸፈንና ለቡቃያው እድገት ዝናቡን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ የሚካሄደው የመኸር ወቅት የእርሻ ስራ የኋላውን በእጅጉ ስለሚያቃልለው፤ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች የበልጉ ዝናቡ ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ ለበልግም ለመኸርም ወቅት እርሻ ለመጠቀም መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህም ውጤታማ መሆን ከተቻለ አገሪቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለያዘችው አቅጣጫም ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡
አሁን ያለንበት ወቅቱ የበልግ ወቅት ብቻ ተብሎ የሚወሰድ ሳይሆን፤ ለመኸር እርሻ መልካም አጋጣሚ የሚፈጠርበት በመሆኑ አርሶ አደሩ ሙሉ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም ቀጣይ ስራውን በሚያቀልለት አግባብ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ስራዎችን በልዩ ትኩረት ሊያከናውናቸው፤ ባለድርሻዎችም በዛው ልክ ሊደግፉት ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም